የአገር ፍቅር ስሜት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ የጥበብ ስራ ነው። የጥበብ ስራዎች ሀይላቸው ትልቅ ከመሆኑ ጋርም ተያይዞ በርካታ መልዕክቶችን በአንድ ጊዜ በማስተላለፍ እንዲሁም በሰዎች ልቦና ውስጥ ቶሎ ብሎ በመስረጽ በአይረሴነታቸው የሚታወቁም ናቸው።
አገራችን ላይ ደስ የሚሉ ተግባራት ሲኖሩ እንደ ህዝብ ውስጣዊ ስሜታችንን የምንገልጸው መደሰታችንን አደባባይ አውጥተን ለተቀረው ዓለም የምናሳየው በጥበብ ስራዎቻችን ነው። በተቃራኒውም አገር ላይ ደስ የማይሉ ነገሮች ሲፈጠሩ ሀዘን ሲመጣ እንዲሁ ስሜታችንን ለመግለጽ የጥበብ ስራን በተለይም ደግሞ ሙዚቃን እንጠቀማለን። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን አገር እንደ ጦርነት ያሉ ነገሮች ሲገጥሟት ወታደሩን በማበረታታት ህዝቡን በማነሳሳት በኩል ሚናው ላቅ ያለ በመሆኑ እንጠቀምበታለን።
አሁን እንደ የገጠመን አይነት አገርን የማዳን የህልውና ጦርነት ውስጥ ስንገባ ደግሞ ህዝብን አንድ አድርጎ ለማስተባበር የወታደሩን የአገር ፍቅር ስሜት ከፍ ለማድረግ ሙዚቃን አብዝተን እንጠቀማለን፣ እየተጠቀምንም ነው።
በቅርቡም ሃገርን ለማፍረስ በተለያዩ ግንባር ጦርነት የከፈተውን አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስና ሃገራችንን ለመታደግ እየተካሄደ ባለው ጦርነት “ህይወታችንን ሰውተን ደማችንን አፍሰን የአገራችንን አንድነት እንጠብቃለን፤ ዳር ድንበሯንም ለውስጥ ባንዳም ይሁን ለውጭ ጠላት አሳልፈን አንሰጥም” በማለት ከተለያዩ ክልሎች ተውጣጥተው በአዋሽና በጦላይ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚሰለጥኑ ምልምል ወታደሮች የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አቅምን የሚጨምሩ፣ የአገር ፍቅርን የሚያሰርጹ ብሎም አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን ለማለት የሚያስችሉ የጥበብ ስራዎችን አቅርበው ተመልሰዋል።
በርግጥ ኪነ-ጥበብ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን በተለይም የኢትዮጵያን አንድነት ጠብቆ ለማቆየት በሚከናወን ጦርነት ላይ ሁሉ ሁሌም ከፍ ብላ የራሷን አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች። ከዚህ የተነሳ ሁሌም ቢሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ ላይ የኪነ-ጥበብ ስራና ባለሙያዎቹ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ እንዲህ በቀላሉ የሚጠቀስ አይሆንም ።
በጣሊያን ወረራ ዘመንም የህዝብን ሞራላዊ አንድነት በማነሳሳት ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በማድረግ በአንድነት እንዲሰለፉ ለማድረግ ጥበብ የነበራት ሚና ከፍተኛ ነበር። ይህ አንድነት ደግሞ ለዛሬው ማንነታችን መሰረት የሆነ ብሎም ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነን ድል በፋሺስት ኢጣልያ ሰራዊት ላይ እንድንቀዳጅ አድርጓል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል የህዝብን አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር ለማስቀጠል የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ደግሞ ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው።
በዚህ ረገድ ለሃገራቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ከሚገኙ አርቲስቶች መካከል የዛሬዋ እንግዳችን አንዷ ናት። እንግዳችን አርቲስት ሰናይት ሀይለማርያም ትባላለች። አባቷ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባል ነበሩ። እርሷ ደግሞ አሁን ላይ ሙዚቃን በተለያዩ የምሽት ክበባት ውስጥ ስትሰራ ቆይታ አሁን ላይ ግን በብሔራዊ ቲአትር ቤት በመቀጠር 17 የሚደርሱ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦችን ዘፈን አጥንታ ለአድማጭ ተመልካቿ ታቀርባለች። በቅርቡም በአዋሽና ጦላይ ላይ ያሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት ምልምል ወታደሮችን ለማበረታታት በተሄደበት ፕሮግራም ላይ ግንባር ቀደም ሆና ተሰልፋለች። እኛም እንግዳችን አድርገን ጋብዘናታል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁናዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ እንዴት ታይዋለሽ ?
አርቲስት ሰናይት፦እኔ በሙያዬ በርካታ አገራትን የማየት እድሉ ነበረኝ ። በዚህ ደግሞ ለአገሬ የአምባሳደርነትን ሚና ተወጥቻለሁ። አንዳንድ አገራት እንደውም ከየት ነሽ ብለው ከጠየቁኝ በኋላ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ስነግራቸው እጅግ በመደመም በመደነቅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አገራቸውን ያስጠሩ፣ ሰንደቃቸውን ከፍ ያደረጉ ጀግኖቻችንን በመጥራት ይደመማሉ። እድለኛ መሆኔንም ይነግሩኛል።
ሌላውን ነገር ሁሉ ትተን ልብሳችንን እንኳን ብናይ ዓለም የሚጓጓበት፣ ባገኙት አጋጣሚም የሚዋቡበት ነው። ነገር ግን እንደዚህ ዓለም የሚቀናብን ሆነን ሳለን ለሆዳቸው ያደሩ ጥቅማቸውን ብቻ የሚያስቡ አካላት በሸረቡት ሴራና በፈጸሙት አገራዊ ክህደት አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን፣ የሚያበሳጭም ሆኗል። ኢትዮጵያ ቀድሞም ቢሆን በተለያዩ ነገሮቿ የአለምን ትኩረት የምትሰብ የምስራቅ አፍሪካ ኩራት፣ የቀጣናው ሰላም ዋስትናም የነበረች አገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የብዙዎች አይን እኛ ላይ ነበረ። ይህንን ክፍተት ተጠቅውም አገራችንን እንደሚፈልጉት ሊያፈራርሷት ያሰፈሰፉ አካላት በርካታ ናቸው። ለእነዚህ አካላት ደግሞ የውስጥ ባንዳዎች በተለይም እያደረጉ ያሉት ነገር እየሰሩ ያሉት ደባ እጅግ የሚያስቆጭ ከመሆኑም በላይ አሁን ላይ አገራችን ዓለም እንደሚቀናባት ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ የሁላችንም የተባበረ ክንድ እንደሚያስፈልጋት ደግሞ ጥርጥር የለውም ።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ እንዲህ አለም ቢቀናብንም በተለይም አሸባሪው ህወሓት የራሱን ጥቅም በማስቀደም አገርን ለማፍረስ እየሰራ ነውና እንደው ይህንንስ እንዴት ታይዋለሽ?
አርቲስት ሰናይት ፦ ይህ እንዲሆን ያደረገው ሌላ አካል አለ ብዬ ነው የማስበው። ለምን እንዲህ አልሽ ብትይኝ ደግሞ እኔ እንኳን በሙያዬ በዞርኩባቸው አገራት ላይ ያሉ ህዝቦች ኢትዮጵያ ሲባል ከብዙ ነገሮች ጋር አስተሳስረው የሚያዩበት ሁኔታ አለ፤ ይህ ደግሞ በመጥፎም በጥሩም አይናቸው ነው። እናም እኔ ዘንድሮ የመጣብን ነገር ሳስበው እነዚህ ባእዳን አገራት እውነትም የኢትዮጵያን ቀና ማለት አይወዱም ማለት ነው፤ ሁሌም ስንዴ ለማኝ እንድንሆናቸው ነው ለካ የሚያስቡት እላለሁ። ምክንያቱ አሁን ላይ ጥሩ መሪ አገኘን፣ ህዳሴው ግድባችን አንድ ደረጃ ላይ ደረሰ፣ እያልን በምንደሰትበት እኛም ነገ አልፎልን እንደነሱ ህዝባችንን ከስደት እናድናለን ብለን ስናስብ ውስጣችን በበቀሉ ለዛውም 27 ዓመት ባስተዳደሩን መሪዎቻችን ይህ መሰሉ ሸፍጥ ሲፈጸም ሳይ የሚቀኑብንና በጎአችንን የማይመኙ አገራትማ እጅ አለበት ለማለት እነሳሳለሁ።
ኢትዮጵያውያን እኮ ከሚያኮሩ ባህሎቻችን አንዱና ግንባር ቀደሙ ሽምግልናችን ነው። ምን ብንበደል እንዴትም ሆኖ ቢከፋን ሽማግሌ ላለማስቀየም ብለን ይቅር የምንል ህዝቦች እኮ ነን፤ አሁን ግን በባህላችን በእኛነታችን መሰረት ብዙ ነገር ተሞከረና ሳይሳካ ቀርቶ ወደማያስፈልገን እስከ ዛሬ ድረስም ባደረግነው ብዙ ዋጋ ወደከፈልንበት ጦርነት ውስጥ ገባን።
አሁንም ግን በተለይም ይህንን ጁንታ ቡድን በአገር ውስጥም በውጪም ካሉ ግብራበሮቹ ጭምር ቅጣቱን ሰጥተን የምንመኛትን አገር በእጃቸን ማስገባት እንዳለብን አስባለሁ። ይህንን አላስፈለጊ ጦርነት ለመመከት በየማሰልጠኛ ጣቢያው የገባው ወጣት እኮ በጥባጭ ባይኖር አገሩን ድንቅ አድርጎ የሚገነባ ነበር ።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ ጦርነት የከፈተብን አሸባሪ ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት አገርን ያስተዳደረና የመራ ነበር፤ እንደው መለስ ብለሽ እነዛን ጊዜያት ስታስቢያቸው ይህ ቀን ይመጣ ይሆናል ብለሽ ታውቂያለሽ?
አርቲስት ሰናይት ፦ እነሱ አገር ሲመሩ እኔ የመንግስትም የግል ስራም እየሰራሁ አብሬያቸው ነበርኩ። ግን ደግሞ መጥፎ የነበሩ ነገሮች ቢኖራቸውም በዚህን ያህል ደረጃ የእናት ጡት ነካሽ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ግን አላሰብኩም። እንደ ወጉ ቢሆን በመጥፎም ይሁን በደግ ጎን ለዚህች አገር ያበረከቱት ነገር ነበር፤ አሁን ላይ ደግሞ ስልጣኑም በቅቷቸው አረፍ ብለው በሰሩት ስራ እየተወደሱም እየተወቀሱም እነሱም ወደኋላ ዞር ብለው ስለስራቸው እያሰቡ እንደ ዜጋ ተከብረው መኖር ሲገባቸው 27 ዓመት ሙሉ ቁጭ ያሉበት ስልጣን በቂ አይደለም ብለው አገርን ወደሌላ ቀውስ ማስገባታቸው የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋቸዋል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ በተለይም በሁለቱ ክልሎች በአፋርና አማራ ክልል ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሁሉ እየተፈጸሙ ነውና አንቺ ይህ ሁኔታ ምን ይፈጥርብሻል?
አርቲስት ሰናይት፦ ኢትዮጵያውያን ውበታችን አንድነታችን፤ ሀይላችንም መደጋገፋችን እንጂ እርስ በእርስ መጠፋፋታችን አይደለም፤ ኢትዮጵያውያን የእከሌ ዘር ጠፍቶ የእከሌ ዘር ነው መቀጠል ያለበት የምንባባል አይደለንም፤ አንድ ሆነን ስንቆም ቀለማችን ባህላችን ቅርሶቻችን ብቻ በጠቅላላው እኛን ለመግለጽ አቅም የሚኖራቸው ሁላችንም ስንኖር ነው እንጂ ባልተጨበጡ አፈታሪኮች እየተመራን አማራ የእከሌ ጠላት ነው፤ እከሌ እከሌን ለማጥፋት ተነስ ማለት ከእኛ የማይጠበቅ ነው። ዛሬ ላይ በትንንሽ ስህተቶች የጀመርነው ህዝብን ከህዝብ የማባላት፤ ዘርን ደም የማቃባት ስራ ለማንም የማይጠቅም ውጤቱም እንደ ሶሪያና የመን እንዲሁም እንደ ሌሎች ሰከን ብለው ማሰብ አቅቷቸው አገራቸውን እንደበተኑ ዜጎች ነው የሚያደርገው።
አሸባሪው ህወሓት በአፋርና በአማራ ላይ እያደረሰ ያለው ዘር የማጥፋት ስራም እጅግ አስነዋሪ ከመሆኑም በላይ ለማንም የማይበጅ አገር እንዳትቀጥል እንቅፋት የሚሆን ነው። በመሆኑም ሁሉም የሚፋለመው አገርን ለመምራት ህዝብን ለማስተዳደር ከሆነ እንዲህ ያለውን ጭፍጨፋ ካደረጉ በኋላ ማንን እንደሚያስተዳድሩ ራሳቸው ናቸው የሚያውቁት።
አሸባሪው ህወሓት ይህንን መሰሉን ጭካኔ የተሞላበት አገርን የካደ ተግባር እየፈጸመ ያለው ተነጠኩ ብሎ የሚያስበውን ስልጣን ለማስመለስ ነው። ግን እንዲህ ክልልን ከክልል ዘርን ከዘር ደም አቃብቶ ኢትዮጵያን የምታክል አገር እንድትፈርስ የሚችለውን ሁሉ ከተባባሪዎቹ ጋር አድርጎ የትኛውን ህዝብና አገር ነው የሚመራው? በመሆኑም ለሁሉም ነገር ሰከን ረጋ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።
ይህ ሁሉ ህዝብ አልቆ ወደወንበሩ ቢመጣ እንኳን አንተ እኮ ያደረከኝ መባባል ይመጣል፤ በመሆኑም ህዝብን ለመምራት ከሆነ ፍላጎቱ ሌላ አላማ ከሌለው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ወደቦታው መምጣት እየተቻለ ነፍጥ ማንሳት ለማንም አይጠቅምም።
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው ህወሓት ሰብዓዊ ድጋፎች እንኳን በአግባቡ እንዳይደርሱ መንገድ እየዘጋ የተለያዩ ችግሮችን እየፈጠረ አሸባሪነቱን በግልጽ እያሳየ ነውና እንደው ይህ ቡድን እውነት ለትግራይ ህዝብ የቆመ ነው ማለትስ ይቻላል ?
አርቲስት ሰናይት ፦ አባቴ የትግራይ ተወላጅ ነው፤ እኔም የተወለድኩት እንዳእየሱስ የሚባል አካባቢ ነው። ምንም እንኳን እድገቴ አዲስ አበባ ቢሆንም በስራም በሌላም ጉዳይ ወደክልሉ በተጓዝኩበት ጊዜ ግን ህዝቡ ሳየው እጅግ የሚያሳዝን ነው ። ዘላለም አለሙን ለጦርነት ልጁን አገሩን የተፈጥሮ ሀብቱን የገበረና አሁን ላይ ባዶ እጁን የቀረ ከመሆኑ አንጻር በተለይም በዚህ ዘመን በዚህ ህዝብ ላይ እንኳን ጦር ሊነሳበት እኔንጃ ብቻ በጣም ከባድ ነው።
የትግራይ እናት እኮ ለብዙ ጊዜያት አብራት የኖረች አንዲት ዶሮ ብትኖራት እንግዳ መጣ ብላ የምታርድ የምታበላ እናት ናት፤ ዛሬ በብዙ ችግርና ፈተና ውስጥ ወልዳ ያሳደገችውን ወጣት ልጇን በጦርነት እየተነጠቀች ያለችው፤ ይህ ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ከመሆኑም በላይ በተለይም የትግራይን ህዝብ ነጻ እናወጣለን ብሎ ከድሮ ጀምሮ ነፍጥ አንግቦ ጫካ ገብቶ በኋላም በስልጣን ላይ ቆይቶ ሁሉን ያየ ቡድን ዛሬ ላይ ለዚህ ምስኪን ህዝብ ምንም አለመጥቀም ሊቆጨው ሲገባ ወደዳግም እልቂት እናትን ወደማሳዘን ምድሪቷን ምድረ በዳ ወደማድረግ ነው የገባው።
እውነት ቃልና ተግባር አንድ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ የትግራይ ክልል በእድገት በህዝቡ ተጠቃሚነት የት በደረሰ ነበር፤ ነገር ግን ቀድሞውንም ቢሆን በስሙ ሲነገድ ነው የቆየው አሁንም እንደዛው ነው። እግዚአብሔር በቃ ካላለ ወደፊትም የሚቀጥለው ይኸው ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ሰሞኑን ደግሞ አንቺና የስራ ባልደረቦችሽ በተለይም በጦላይና አዋሽ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ላይ ወታደራዊ ስልጠናን ከሚያደርጉ ምልምል ወታደሮች ጋር ከርማችኋል እስቲ ሁኔታውን እንዴት ትገልጪዋለሽ?
አርቲስት ሰናይት ፦ ሁኔታው እንኳንም ኢትዮጵያዊ ሆንኩ የሚያስብል ነው፤ በማሰልጠኛ ጣቢያው ላይ የተገኙ ወጣቶችም በተለይም የአሻባሪው ህወሓት አገርን የመካድ ተግባር አስቆጥቷቸው ከዳር እስከ ዳር ነቅለው የመጡ እንደመሆናቸው ኢትዮጵያዊ ቀለምና ውበት በእጅጉ ይታይባቸዋል። ከዛ በላይ ግን አገርን ለማዳን የሚታይባቸው ቁርጠኝነት እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም።
ምናልባት ያለምንም ማጋነን እኛ ለእነሱ ሞራል ለመሆን ደጀንነታችንን ለማረጋገጥ አይዟችሁ አብረናችሁ ነን ብለን ሞራል ለመስጠት ሄድን እንጂ ሞራል አግኝተን እምዬ ኢትዮጵያ አገራችን ከማንምና ከምንም በላይ መሆኗን በሚገባ ተረድተን የመጣነው እኛ ነን።
አሸባሪው ህወሓት ይህንን መሰሉን አገር የካደ ተግባር ባይፈጽምና በእነዚህ ምልምል ወታደሮች ዘንድ የሚታየው ኢትዮጵያዊነት እንዲሁም አቅምና ወኔ ለሌላ የልማት ስራ አውለነው ቢሆን ኖሮ የት ልንደርስ እንደምንችል መገመት ቀላል ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እናንተ አርቲስቶች አገር በተለይም እንደዚህ አይነት ጊዜ ላይ ስትሆን ለወታደሩ ደጀን በመሆን በኩል የነበራችሁ ሚና ቀላል አልነበረም፤ ወደፊት ምን ዓይነት እቅዶች ናቸው ያሏችሁ ?
አርቲስት ሰናይት ፦ እኔ በተለይም እንደምሰራበት ብሔራዊ ቲአትር ብናገር ተቋሙ አገርን ለማያውቃት ሁሉ በማሳወቅ በኩል ከፍተኛ የሆነ ስራን እየሰራ ነው። ይህ መሰሉ የከሀዲዎች ሴራ በአገር ላይ ሲከሰት ደግሞ ሀላፊነቱ እጥፍ ድርብ ይሆናል።
ይህ አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ በተለይም በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ሲፈተፍቱ የነበሩ ምዕራባውያንና ተቋሞቻቸው ሲጠብቁት የነበረ ጊዜ ነው፤ በመሆኑም እኛ ያንንም እያየን አገራችን ያለችበትን ሁኔታም ከግምት እያስገባን በሁለት ጎራ የሚታየውን ችግር ለመመከት በቁርጠኝነት ቆመናል።
በቀጣይም አገር እኛን በምትፈልገን ሁኔታ ሁሉ ቀድመን በመገኘት መነቃቃት በሚያስፈልግበት ቦታ እየሄደን ጀግኖቻችንን አይዟችሁ እንላለን ፤ የሚጠበቅብንን በማድረግ በኩል ሙሉ ዝግጁነትና ፍቃደኝነት ነው ያለን።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ካለንበት ችግር ወጥተን አገራችንን ወደሰላሟ ህዝቡም ወደልማቱ ተመልሶ የጀመርነው የእድገት ጉዞ ይቀጥል ዘንድ ከማን ምን ይጠበቃል ትያለሽ?
አርቲስት ሰናይት ፦ እኛ እኮ ጦርነት ብርቃችንም አዲሳችንም አይደለም ። ከጥንት ጀምሮ ሊወሩን ከመጡ የውጭ ጠላቶቻችን ጋርም ስንፋለም ነው የኖርነው። ግን ደግሞ ከጀግንነት ታሪኮቻችን በዘለለ ምንም ለህዝቡ ጠብ ያለ ነገር አለ ብለን ብናስብ መልሱ ምንም ነው የሚሆነው። ለዘመናት አልፈንበት ምንም ላልፈየደልን ጦርነት ዛሬ በሰለጠነው ዘመን ተነጋግሮ መግባባት ብሎም መልስ ማግኘት በሚቻልበት ጊዜ ወደጦርነት መግባት እጅግ የሚያሳዝን ነው።
ለእኛ እሚበጀን አንተ ትብስ አንተ ተባብለን መቀጠል ነው የሚያስፈልገው። አሁን ላይ የእኛ የኢትዮጵያውያንን መፈራረስ የሚመኙ ሁሉ ይህንን ጊዜ በጉጉት እየጠበቁ ነው፤ ይህ እንዳይሆን ግን ችግሮች እንኳን ቢኖሩ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ ቁጭ ብሎ በመነጋገር አገርን ከብተና ህዝብንም ከሞትና እንግልት ማዳን ያስፈልጋል።
ምንም ጊዜም እንኳን አገርን በመምራት ደረጃ ላይ ያሉ አካላት አይደሉም ቤተሰብ በአንድ አይነት ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋምን ይይዛል፤ ላይስማማም ይችላል። ነገር ግን በአንድ ጉዳይ ላይ አልተስማማንም ብለው ቤታቸውን አይበትኑም፤ እንደ ቤተሰብም አንቀጥልም አይሉም፤ በሚያስማሟቸው ነገሮች ላይ እየተስማሙ ባላስማሟቸው ነገሮች ላይ ደግሞ እየተወያዩ ይቀጥላሉ። ምናልባትም በጊዜ ሂደት የሀሳብ መቀራረብ ሊያመጡም ይችላሉ። እንደ እኔ አገርም እንዲህ ነው መሆን ያለበት፤ መሪዎች ሁሌም ይስማማሉ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን በልዩነት መስማማት የሚባለውን ነገር ለራሳቸው በመንገር መቀጠሉ ጥሩ አማራጭ ነው። ምናልባት ጦርነቱን ከፈጠሩት አካላት በላይ እውቀት ላይኖረኝ ይችላል። ነገር ግን ለእኔ የሚታየኝ አማራጭ ይህ ነው።
የትግራይ ህዝብ ምን ባጠፋ ነው ዘመኑን በሙሉ በጦርነት ውስጥ የሚያልፈው። ሁሌ ጦርነት ረሃብ ብቻ በአጠቃለይ የመጣው ሁሉ ክልሉን የስቃይ ምድር ሲያደርገው በጣም ያሳዝናል። እነዚህ አሸባሪ ቡድኖችም ቢያንስ ቢያንስ ላለፉት 30 ዓመታት አገርንም ክልሉንም አስተዳደርዋል። ሁሉንም ያውቃሉ፤ ምንም እንዳልጠቀሙትም ያውቃሉ፤ አሁን እንኳን በመጨረሻ ጊዜያቸው ህዝቡን ለዚህ መከራ እናት ልጄ ደረሰልኝ ብላ አውርታ ሳትጨረስ ከጉያዋ ባይነጥሉት መልካም ነው። እውነት ህዝቡን ነጻ ለማውጣት ቆመናል ካሉ ማድረግ የሚገባቸው ይህንን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ጦርነት ከባድ ጉዳት ከሚያደርስባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉና እንደው የትግራይ እናቶች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ስታይው ምን ይሰማሻል ?
አርቲስት ሰናይት ፦ የትግራይ እናቶችማ ዘመናቸውን ሁሉ በጦርነት ያለፉ እጅግ በጣም የሚያሳዝኑ መሰረታዊ የሚባሉት ፍላጎቶቻቸው እንኳን ሳይሟሉ እንዲሁ ለሰዎች የስልጣን ጥማት ልጆቻቸውን በመገበር ላይ ያሉ ናቸው።
የሚገርምሽ እኮ የዛኔ በትጥቅ ትግሉ ወቅት እናቶች ነጻ እንወጣ ይሆናል፤ እንደ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች እኛም መሰረታዊ ፍላጎቶቻችን ተሟልተው ልጆቻችን ተምረው ክልላችን ለምቶ ለመኖር ምቹ ይሆንልናል ብለው ልጆቻቸውን መርቀው ወደጦር ሜዳ ከመላክ ጀምሮ እነሱም በሚችሉት ሁሉ ጦርነቱ ላይ በመሳተፍ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው ነበር። ነገር ግን ሁሉም ነገር ከተጠናቀቀ ነጻ እናወጣችኋለን ያሏቸውም ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ያደረጉላቸው ነገር ምንም ነው። በመሰረታዊነት የሚጠቀሙበትን ውሃ እንኳን በአካባቢያቸው እንዲያገኙ አልሆነም። ይባስ ብለው ሀብታቸውን ለግላቸው እየተጠቀሙ እነሱን በእርዳታ እህል አኖሯቸው፤ አሁን ደግሞ ይባስ ብለው ጦርነት ከፈቱባቸው። ሁኔታው እጅግ የሚያሳዝን እድሜ ዘመናቸውን በሙሉ የስልጣን ጥመኞች መጠቀሚያ መሆናቸውም ከምንም በላይ የሚቆጭ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የትግራይ እናቶችስ ምን ይጠበቅባቸዋል?
አርቲስት ሰናይት ፦ ውይ የሚጠበቅባቸውማ ብዙ ነው፤ እንደውም በጣም ፈተና ውስጥ ናቸው። የትግራይ እናትን ፈተና ያበዛው ወይም ያባባሰው ልጆቿ ያለፉትን 30 ዓመታት ለማለት ይቻላል ወደ አእምሯቸው አማራጭ ሀሳብ እንዳይገባ ለካ ይህም አለ እንዴ ብለው እንዳያገናዝቡ ሆነው በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር መውደቃቸው ነው።
ትግራይ ላይ ያለ ህወሓት ህይወት ያለ ውሃ ማደር እማይቻል እስኪመስል ድረስ ወጣቱ በዚህ መሰሉ ሀሳብ ተተብትቧል። ምንም አይነት አማራጭም ማየት አይፈልግም ፤ አሁንም አሸባሪ ቡድኖች ለራሳቸው የስልጣን ፍላጎት የለኮሱትን እሳት ከሩቅ ሆነው እየሞቁ የሚማግዱት ግን ያንን 30 ዓመት አእምሮው ላይ የተጫወቱበትን ወጣት ነው ፤ ይህ ደግሞ ለእናት ምን ያህል ሞት ከሞትም ሞት እንደሆነ መቼም ሁሉም ይገነዘበዋል።
ግን ስንት ዓመት ነው ልጅ ወልዳ እያሳደገች ወደበርሃ የምትልከው? በነገራችን ላይ እርሷም እኮ በረሃ ነበረች። ከበረሃ መጥታ ወለደች፤ አሳድጋ ደግሞ ለበረሃ እየሰጠች ነው። ይህ እንደው ምን ዓይነት ቅጣት ምን አይነት ፍርድ እንደሆነ እኔ አላውቅም፤ 27 ዓመታትም ምን እየተባሉ እንዳደጉ ፈጣሪ ይወቀው ፤ አሁንም ከትግራይ እናት የሚጠበቀው ነገሩ ሁሉ የማይጠቅም የጥቂቶች ፍላጎት መሆኑን ለወጣት ልጆቻቸው ቢመክሩ፤ በቃን እኛም እንደ ሌሎች ክልሎች በሰላም መኖር ሰርተን መለወጥ ወልደን በሰላም ማሳደግ አለብን በማለት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መምከር ነው የሚጠበቅባቸው። በግላቸውም በቃን ጦርነት ልጆቻችንንም አንሰጥም ማለት መቻል አለባቸው።
የትግራይ እናት ብትሰማኝ ልላት የምፈልገው ነገር ልጅሽን ሌሊት ከእንቅልፉ እየቀሰቀስሽ ጦርነት አይጠቅምም፤ ለእኔም ላንተም አይበጅም፤ ወጥተህ አትሙትብኝ፤ ነገ ነገሮች ሁሉ ያበቁና ሁሉም ነገር ይጠናቀቃል ፤ኢትዮጵያም ዳግም ትሰራለች፤ ኢትዮጵያንም ትኖርባታለህ ብላ እንድትመክር እፈልግለሁ። እነግራታለሁም።
አዲስ ዘመን ፦ በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልጊው መልዕክት ካለ?
አርቲስት ሰናይት ፦ እኔ ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር አገር ማለት ትልቅ ነገር ከመሆኑም በላይ ሰው እንደ እብድ እንኳን ጨርቁን ከላዩ ላይ አውልቆ ለመሄድ ሰላም የሚታይባት አገር ያስፈልጋል፤ ለምኖ ለመብላትም እንደዛው አገር ያስፈልጋል። አገራችን እንድትኖር ደግሞ ሁላችንም መክፈል ያለብንን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል ይገባናል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አርቲስት ሰናይት ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013