ወርሃ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም። በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቀነስ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተወሰነ። በአጭር ጊዜ የመማር ማስተማሩ ሂደቱ እንደሚመለስ ቢነገርም፤ የቫይረሱ አስጊነት የእውቀት በሮች ዳግም ለመክፈት የሚያስደፍር አልነበረም። ይህም ከ25 ሚሊዮን በላይ እውቀትን ፍለጋ የሚማስኑ ተማሪዎች ከነእውቀት ረሀባቸው ከቤት ለመዋል ተገደዱ። 600 ሺህ የሚሆኑ እውቀትን መጋቢ መምህራንም እጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ ሆነ።
የአለም ህዝብ ስጋት ለሆነው ወረርሽኝ መፍትሄ በመጥፋቱ የሰው ልጅ የህይወት ኡደት ወደ መደበኛ መስመር መመለስ ዳገት እንደሆነ ቀጠለ። ይህም በመላ ኢትዮጵያ የተዘጉት የእውቀት በሮች ሳይከፈቱ ቀናት እንዲነጉዱ አደረገ። ወራት ቢፈራረቁም፤ ትምህርት ቤቶችን መክፈት የማይሞከር ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ የሚጠፋ ሳይሆን ከሰው ልጆች ጋር አብሮ የሚኖር ነው ሲል ማስታወቁን ተከትሎ የፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጉ ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ ሲልም አዘዘ። ይሕንኑ ተከትሎ ኢትዮጵያ ለወራት የተዘጉ የእውቀት በሮችን ወደ መክፈቱ ተሸጋገረች። አዲስ አበባ ህዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም መደበኛ የመማር ማስተማሩን ሂደት ጀመረች። ሌሎቹ መዲናዋን በመከተል ለወራት የተዘጉ የእውቀት ደጆቻቸውን ከፈቱ።
በኢትዮጵያ ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲጀመር ሲደረግ ግን፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ ቅድመ ዝግጅቶች በማድረግ ነበር። የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን በዚህ መልኩ ተጀምሮ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከሉ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማስቀጠል ረገድ ሁለት አይነት መልክ እንደነበረው ብዙዎች ይናገራሉ። ያሳለፍነው የትምህርት ዘመን ሁለቱን መልኮች በተለያዩ ደረጃዎች በመመልከት በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን መደረግ ስለሚኖርባቸው ክንዋኔዎች በዚህ ጽሁፍ ጠቁመን እንለፍ።
የ2013 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን እየተከላከሉ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማስኬድ ረገድ ከነበሩት ሁለቱ መልኮች ከመጀመሪያው ስንጀምር፤ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ተቋማት ኮቪድን እየተከላከሉ የመማር ማስተማሩን ሂደት በተጠናከረ መልኩ በማስኬድ ረገድ ጥሩ ጅማሮ ነበር። በዚህ ረገድ በርካታ ባለሙያዎች ተመሳሳይ ሃሳቦች ያላቸው ሲሆን በአዲስ አበባ የአራዳ ክፍለ ከተማ ምግብ መድሃኒት ቁጥጥር ባለሙያው አቶ አለማየሁ መስፍን አንዱ ናቸው።
ጠንካራው ጅማሮ
አቶ አለማየሁ በሃገራችን የመማር ማስተማሩ ሂደት ወደ መደበኛው ሂደቱ በተመለሰበት ሰሞን የነበረውን ሁነት በማስታወስ ሲያብራራ፤ ከጅምሩ መንግስትም ከፍተኛ ጥንቃቄና የመከላከል ወይም ቅድመ ጥንቃቄን መሰረት ያደረጉ ህጎችን አውጥቶ ስለነበር የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲጀመር በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚባል ደረጃ የኮቪድ ጥንቃቄ ባደረገ መልኩ ነበር። ከዚህ ውስጥም በእግር ተረግጦ የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ፣ የኮቪድ መከላከያ ስቲከሮች፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ በየትምህርት ቤቱ ሁለት ነርስ እና ሰልፍ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጥ ነበር።
በተጨማሪም ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ሁሉም ትምህርት ቤቶች የኬሚካል ርጭት መደረጉ፤የተማሪዎችን ጥግግት ለመቀነስ የተወሰዱ አማራጮች መኖራቸው፤ የመማር ማስተማር ስርአቱን በፈረቃ እንዲሆን በማድረግ ጥግግቱን ለመቀነስ የተሰራው ስራ በጥሩ መልኩ የሚነሳ ነው። አቶ አለማየሁ አክሎም የትምህርት አመቱ በዚህ መልኩ አመቱን ሙሉ የዘለቀ ሳይሆን ከአንድና ሁለት ወራት በላይ ያለመዝለቁን ይናገራል። በትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የሆነ መዘናጋት የታየ መሆኑን ይገልጻል። “እጅን አለመታጠብ፣ መምህራን እና ተማሪዎች አልፎ አልፎ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ አለማድረግ በተለይ ተማሪዎች በእረፍት ሰዓት ሁሉንም የጥንቃቄ አይነቶች የመዘንጋቱ ነገር በስፋት ይታይ ነበር “ሲልም ጉድለቶቹን ይነቅሳል።
በሃምሌ 19 አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆነው አቶ ስንታየሁ ግርማ በተመሳሳይ፤ በየትምህርት ቤቱ ይደረጉ የነበሩት ጥንቃቄዎች በጊዜ ሂደት እየላሉ፣ እየላሉ መሄዳቸውን ይናገራል። ቫይረሱ ስለመኖሩ እስከ መዘንጋት መደረሱን እንደታዘበ ያጫወተን መምህር ስንታየሁ፤ በተማሪዎች በኩል በተለየ መልኩ ይህ አይነቱ እንዝላልነት ጎልቶ የሚታይ ስለመሆኑ ይናገራል። ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ቤት ሲገቡ በር ላይ ሙቀት የመለካቱ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው እንዲገቡ ማድረግ እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚደረግ መሆኑን ይናገራሉ። እርሱ የሚያስተምርበትን ትምህርት ጨምሮ በመዲናዋ በሚገኙ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች መሰል ጥንቃቄዎች ቢደረጉም፤ በእረፍት ሰዓት፣ በመውጫ ሰዓት እንዲሁም ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ከወጡ በኃላ ጥንቃቄ እንደማይታይ ይናገራል።
በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የኮቪድ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ደረጃው ቢለያይም ችግር እንደነበረ ያመኑት፤ የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል መርሃ-ግብር ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ወጋሶ ናቸው። በትምህርት ዘመኑ የኮቪድ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች አፈጻጸም ለመፈተሽ 150 የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶችን ያካተተ ጥናት መደረጉን ያመላከቱት አቶ ዮሃንስ፤ ጥናቱ በትምህርት ተቋማት ላይ የአካላዊ ርቀት አጠባበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የመጸዳጃ ቤት አገልግሎቶች ምን ይመስላሉ በሚሉ ነጥቦች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
“በትምህርት ቤት ማስክ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በከተሞች የተሻለ አፈጻጸም ታይቷል። በገጠር አካባቢዎች ከግንዛቤ ጋር በተያያዘ አጠቃቀሙ አነስተኛ መሆኑን በጥናቱ ተለይቷል። በአንድ ክፍል ውስጥ መማር ያለባቸውን የተማሪዎች ቁጥር በሚመለከት የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ውስንነት መኖሩንም እንዲሁ፡፡ ህብረተሰቡ እና የትምህርቱ ማህበረሰብ በትምህርት ቤቶች የውሃ እጥረት እንዳይከሰት የተሻለ ስራ ተከናውኗል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
በጎውን ነገን ለመፍጠር ትናንትን እንደ መስታወት
መምህር ስንታየሁ በመጪው የትምህርት ዘመን ተመሳሳይ ስህተቶች መደገም እንደሌለባቸው ይናገራል። “በአሁን ወቅት በሃገራችን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ከመጨመሩ ባሻገር መልኩን በመቀየር ብዙዎችን እየገደለ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል። ስለዚህ በ2014 ዓ.ም ቀደም ሲል የነበሩትን ችግሮች መሰረት ያደረገ መፍትሄ ከመፈልግ ጀምሮ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን ማከናወን ይጠበቃል” ሲልም ምክረ ሃሳቡን ለግሷል።
አቶ አለማየሁ ደግሞ በሃገራችን የገጽ ለገጽ ትምህርቱ በተጀመረ ሰሞን በትምህርት ቤቶች ይደረጉ የነበሩ ጥንቃቄዎች ዘላቂ እንዳልነበሩ በማስታወስ፤ “በዚህ ደረጃ ለተፈጠረው ክፍተት ደግሞ ለተማሪዎች ከወላጅ ጀምሮ ሁሉም ኃላፊነቱን ካለመወጣቱ ጋር ይያያዛል። በየትምህርት ቤቱ የሚገኙ ኃላፊዎች ደግሞ በሰልፍ ወቅት ይደረጉ የነበሩ ግንዛቤ መስጫ ትምህርቶች እንዲቀጥሉ አለማድረጋቸው፤ መምህራን ደግሞ የኮቪድ-19 ጥንቃቄ እና ቅድመ ጥንቃቄ ህጎችን በመጣስ ለተማሪዎች መጥፎ አርዓያ መሆናቸው ችግሩ ስር እንዲሰድ በር ከፍቷል “ሲል ያመላክታል። ስለዚህ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመንግስትም ሆነ በግል ትምህርት ቤቶች ተገቢውን ጥንቃቄ ባደረገ መልኩ የመማር ማስተማር ሂደቱን መከወን የሚገባቸው መሆኑን ያመላከተው አቶ አለማየሁ፤ በተለይ ወላጆች የትምህርቱ ማህበረሰብ የጤና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በተገቢው ደረጃ ሊወጡ እንደሚገባ ምክረሃሳቡን ለግሷል።
የሃሳቡ ተጋሪ የሆኑት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ፤ በሀገሪቱ የትምህርት አሰጣጥ ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ የሆነ የጊዜ ብክነት ማስከተሉን በማስታወስ፤ ትምህርት ቤቶች ለ2014 የትምህርት ዘመን ከወዲሁ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ያገናዘበ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013