ቅድመ-ታሪክ
የልጅነት ዕድሜውን በገጠሩ መስክ ሲቦርቅ አሳልፏል። ቤተሰቦቹ ለሱ ያላቸው ፍቅርና እንክብካቤ የተለየ ነበር።ዕድሜው ከፍ እንዳለ ትምህርት ቤት ላኩት ። በልጃቸው ተስፋ ያደረባቸው እናት አባት ስለነገው መልካሙን አሰቡ። ዛሬን በርትተው ልጅ ቢያሳድጉ፣ ቢያስተምሩ ነገን እንደሚያትርፉ ገባቸው ።
ችግረኞቹ የመሀመድ ቤተሰቦች መተዳደሪያቸው ግብርና ነው። ጠዋት ማታ በሚተጉበት ህይወት መሀመድን ጨምሮ ሌሎችን ያስተዳድራሉ። ትንሹ መሀመድ ትምህርት ቤት መግባቱ እያስደሰተው ነው። ከእኩዮቹ ጋር ቀለም ቆጥሮ ሲመለስ ፊቱ በፈገግታ ይፈካል።
የመሀመድ ትምህርት ቀጥሏል። ከቀዬው መሀል ያለው ትምህርት ቤት እሱንና ባልንጀሮችን በዕውቀት መመገቡ ብዙዎችን ጠቅሟል። ከትምህርት መልስ ወላጆቹን በሥራ የሚያግዘው ታዳጊ ስለነገው አርቆ ያስባል። በትምህርቱ ቢገፋ፣በእውቀት ቢበረታ የሚያገኘውን እያሰበ ብዙ ያልማል።
መሀመድ አንድ ሁለት እያለ ስድስተኛ ክፍል ደረሰ። ከዚህ በኋላ ያለው የትምህርት ደረጃ መልካም እንደሚሆን ያውቃል። በዕድሜ መብሰሉ የትምህርትን ጥቅም አሳውቆታል።ቀጣዮቹን ክፍሎች በድል ቢሻገር እንደሌሎች ታላቅ ቦታ እንደሚደርስ እርግጠኛ ሆኗል።
የስድስተኛ ክፍል ትምህርት እንዳለቀ ፤ ታዳጊው መሀመድ ሀሳብ ገባው። ከዚህ በኋላ ድሀ ወላጆቹ እሱን ማስተማር አይችሉም። የቤታቸው አቅም፣የእጃቸው ላይ ሀብት፣ ለወደፊት ህልሙ አይተርፍም። መሀመድ ይህን ሁሉ ያውቃል። ‹‹ይሁንብኝ›› ብሎ ቢቀጥል ከመንገዱ፣ ከሀሳቡ እንደማይደርስ አረጋግጧል።
አሁን መሀመድ ቆም ብሎ ማሰብ ጀምሯል። ከቀዬውና ከእርሻው ቢውል ህይወቱን አይለውጥም።ለወላጆቹ አስቦ ከጎናቸው ቢቀር ነገ ሚስት አግብቶ ልጅ ከመውለድ የዘለለ ምርጫ አይጠብቅም። ለቀናት ከራሱ መከረ፤ትርፉን ከኪሳራው ፣ጥቅሙን ከጉዳቱ ለየ። የውስጡ ሚዛን ከቀዬው በመራቅ ውሳኔው አጋደለ ።
አዲስ አበባ
መሀመድ ያደገበትን የደቡብ ክልል ተሰናብቶ አዲስ አበባ ገባ። በዚህ ስፍራ በርካታ የአገሩ ልጆች ይኖራሉ ። የሚያውቃቸው ሁሉ ለፍቶ አዳሪዎች ናቸው። ሸቅጠው የሚያድሩ ፣ተሸክመው የሚበሉ፣ ጫማ ጠርገው የሚገቡ፣ ጀብሎ አዙረው የሚውሉ ጥቂት አይደሉም።
አገሩን እስኪለምድ ከተማውን እስኪለይ ጥቂት አማተረ። ውሎ አድሮ በእንግድነት ያረፈባቸውን ጠያየቀ። ያማከራቸው ሁሉ ለእሱ የሚበጀውን መከሩት። ይጠቅመኛል ባለው ሥራ ጊዜ ወስዶ አሰበበት ። ከዚህ በኋላ በእንግድነት ሰው ማስቸገር የለም። በሚያገኘው ገቢ ራሱን መጥቀምና መርዳት ግድ ይለዋል።
መሀመድ ከቀናት በኋላ ማንነቱን ሥራ መሀል አገኘው። ጫማ ለመጥረግ ሊስትሮ ይዞ ከአስፓልት ሲወጣ በደንበኞች ተከበበ። ውሎ ሲያድር ሥራውን ሙያዬ ብሎ በረታበት። ከጠዋት እስከማታ በሚውልበት እንጀራው ገቢውን ጨምሮ መልካም ሰዎችን አበዛ።
መሀመድን ያሉ የእጁን ሙያ መርጠው፣ ከሌሎች ለይተው ከሊስትሮው ይገኛሉ። በሥራው ሲደሰቱ የጠረገበትን ሰጥተው፣ ከጉርሻው አክለው በምስጋና ይለዩታል። በሥራው የበረታው መሀመድ በደንበኞቹ ምክርና ሞራል እየታገዘ አቅሙን አዳበረ። ቤት ተከራይቶ፣ወጪውን ችሎ ገንዘብ ቋጠረ።
አዲስ አበባና መሀመድ በትውውቅ ዓመታትን ቆጠሩ።የከተማውን መውጫ መግቢያ አሳምሮ ያወቀው ወጣት ውሎ ሲያድር ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ሌሎች ዕቅዶችን አሰበ። በየቀኑ ሊስትሮ እየጠረገ ከመኖር የተሻለ ሥራ ቢያገኝ አይከፋም። ትምህርቱን መቀጠል፣ ራሱን መለወጥ ባይችልም በገቢው በልጦና ተሽሎ መገኘት እንዳለበት ተረድቷል።
መሀመድ አቀረቅሮ በሚውልበት የጫማ መጥረግ ሥራ ብዙ ነገሮችን ይሰማል። ደንበኞቹ እንደወዳጅ ዘመድ ቀርበው ያወጉታል። ከሚፈልጉት ቦታ ያሻቸውን እንዲያደርስ ይልኩታል። የተባለውን እየፈጸመ፣ከታዘዘው እየሮጠ ገቢውን ያሰመረው መሀመድ፤ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ መልካም ሆነለት።
ሥራ ለመቀየር ገቢውን ለማሳደግ ህልም ያለው ወጣት ዓላማውን ግብ የማድረሻ ጊዜው መቃረቡን አወቀ ። በሥራ መለወጥ፣ ምኞቱ ነውና በዕድሉ ሊጠቀም፣በአማራጩ ሊገኝ ከሌሎች መከረ ። ምክሩን የሰሙ ሀሳቡን ደገፉለት። ከሚኖርበት አካባቢ ተደራጅተው ለመስራት ያሰቡ ወገኖች ያቀረቡት ጥያቄ ጸደቀላቸው ።
በማህበር የተደራጁ፣ በጋራ ሰርተው ማግኘት ያሰቡ ዓላማቸው አንድ ሆነ። በጉልበታቸው ሰርተው በላብ ጠብታቸው ከሚያገኙት በረከት ሊካፈሉ ጠዋት ማታ ባተሉ ። በርካቶች የአንድነት ጥምረታቸው ፍሬ አሳየ። መደራጀታቸው፣ መተባበራቸው እንጀራቸውን አሰፋ። ሞሶባቸውን ሞላ።
መሀመድና ባልንጀሮቹ የተደራጁበት ዘርፍ የቆሻሻ ማንሳት ሥራ ነው ።በዚህ ሙያ በርካቶች ደህና የሚባል ገቢ ያገኛሉ ። የበረቱ፣ ሥራውን ያልናቁ ጠዋት ማታ ከቆሻሻ ጋር ናቸው። መሀመድ የሊስትሮ ሥራውን እርግፍ አድርጎ ተወው። የገባበት ሥራ ከነበረበት የጫማ ማሳመር ውሎ በእጅጉ ይለያል። ገቢውም ቢሆን ከሊስትሮነት አይገናኝም።
መሀመድ እሱን ከመሰሉ ባልንጀሮቹ ጋር ተባብሮ በየቦታው የቆሻሻ ክምር ያነሳል። ሁሌም ሥራውን ለመከወን ማልዶ መነሳት ግድ ይለዋል።ቱታውን ለብሶ፣የእጅ ጓንት አጥልቆ፣ፊቱን በኮፍያና በአፍ መከለያ ሸፍኖ ከሚፈለገው ስፍራ ይደርሳል።
እሱና ጓደኞቹ በየቦታው እየዞሩ ቆሻሻ ይሰበስባሉ።በማዳበሪያና በሰፋፊ ላስቲኮች የሚሞሏቸውን ክምሮች ተሸክመውም ከጋሪዎች ይጭናሉ።ጋሪዎቹ እርጥብና ደረቅ ቆሻሻ ሲሞሉ ጥንቃቄን ይሻሉ። የሚገፏቸውን ሰዎች ኃይል እያጋዳሉ ቁልቁል መፈትለክ ልማዳቸው ነው።
እነ መሀመድ የድፍን ብረት ጋሪዎቹን ዙሪያ ከበው ከጎንና ከኋላ እየተከተሉ ይሮጣሉ።ብዙ ጊዜ የጋሪዎቹ ኃይል ገፊዎቹን አሸንፎ ወደፊት ይፈጥናል። ከመኪኖች እኩል እያሯሯጠም ሰራተኞችን ይፈትናል፣ ያታግላል።በሥራው ጥንቃቄ ካልታከለበት ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል።
መሀመድ የቆሻሻ ማንሳት ሥራው ተመችቶታል። ቆሻሻ ለእሱ የዕለት እንጀራው ከሆነ ወዲህ እንደ ቀድሞው ሽታውን አይጠላውም። በፊት በቆሻሻ ክፉ ሽታ የሚፈተነው ወጣት አሁን ለአፍንጫው ትርጉም ሰጥቶት አያውቅም። ጎንበስ ቀና ብሎ ያሻውን ሲሰበስብ ሥራውን ያከብራል፣እንጀራው ህይወቱ መሆኑን ያስባል።
አንዳንዴ ቆሻሻ ሲሰበስብ ችግር ይገጥመዋል።አንዳንድ ሰዎች በላስቲክና በማዳበሪያ ጠቅልለው የሚጥሉት ጠርሙስና ስለት በእጆቹ ላይ ጉዳት ያደርሳል።ይህ አይነቱ አጋጣሚ በተለይ የእጅ ጓንት በሌላቸው ሰራተኞች ላይ የከፋ ነው።
አንዳንዴ ደግሞ የሥራ ባህርይው ያልታሰበ ሲሳይ ያመጣል። ከሚወገዱ የቆሻሻ ክምሮች መሀል ደህና ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች ይገኛሉ። ዕቃዎቹ እይታን የሚስቡና የማይገመቱ ሊሆኑ ይችላሉ።እንዲህ በሆነ ጊዜ ቆሻሻ ሰብሳቢዎቹ ተጠቃሚዎች ናቸው።ሲሻቸው ለራሳቸው፣አልያም ለሽያጭ አውለው ጥሩ ገንዘብ ያገኛሉ።
መሀመድ የየዕለት ሥራውን እየከወነ መኖሪያውን ቦሌ አካባቢ ከሚገኝ የጨረቃ ሰፈር አድርጓል።በዚህ ሰፈር መልከ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ።ሰርተው የሚገቡ፣ ሰርቀው የሚደበቁ፣ ተኝተው የሚውሉ ፣ ቁማር የሚጫወቱና ሌሎችም። መሀመድ ከእንዲህ አይነቶቹ መሀል እየኖረ ህይወትን ይገፋል።እሱ በእያንዳንዱ ቤት የሚሆነውን እውነት አያጣውም። ከሁሉም ግን በአካባቢው ተሰባስበው ቁማር የሚጫወቱ ወጣቶች ድርጊት ከልብ ያበሽቀዋል። ተሰባስበው ባያቸው ቁጥር ከስፍራው እንዲርቁ ፣ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቅቃል።
ወጣቶቹ የቆሻሻውን ገንዳ ከበው ቁማር የመጫወት ልምዳቸው የከረመ ነው። ከሚመጣው ቆሻሻ የሚፈለግ ዕቃ እየፈለሱ ውሏቸውን ያጋምሳሉ።ይህ ድርጊት የማይመቸው መሀመድ በስፍራው እንዲቆዩ አይፈልግም፡፤ በየአጋጣሚው እየተናገረ ይጋጫቸዋል።
መሀመድ ስለሚለው ሁሉ ወጣቶቹ ደንታ የላቸውም። የቆሻሻ ገንዳውን ተከልለው ፣ ከቆሻሻው የሚመጣውን፣ሲሳይ ያተራምሳሉ። አረፍ ሲሉም ወደቁማራቸው ይመለሳሉ። መሀመድ በእነሱ ይናደዳል ። እነሱ ለእሱ አይጨነቁም። የጀመሩትን ይቀጥላሉ።ካርታ ቁማሩን ይጫወታሉ፤ ይህ ሂደት ለቀናት በዚህ መልኩ ተጉዟል።
የካቲት 5 ቀን 2006 ዓም
በዚህ ቀን መሀመድ የተለመደውን ሥራ ሲከውን ውሏል።ምሽቱን ባረፈበት የጨረቃ ሰፈር ከጎረቤቶቹ አምሽቷል። በጊዜ ቁማር ከሚጫወቱት ወጣቶች አንደኛውን አግኝቶ ሲጨቃጨቁ ቆይተዋል። ጭቅጭቃቸው መካረር ወልዶ እጅ ለእጅ ተያያዙ። ጠባቸውን የተለመደው አይነት የመሰላቸው ሌሎች ለጉዳዩ ነገሬ ሳይሉት ቆዩ።
ጥቂት ቆይቶ ደረጀ የተባለው ወጣት መሀመድን አጠቃው። መሀመድ ለጥቃቱ በቴስታና በጥፊ ምላሹን ሰጠ። ገላጋዮች ከመሀል ገቡ።ሁለቱም ጠበኞች እልህ ያዛቸው። አንዳቸው ሌላውን ለማጥቃት አጋጣሚን ፈለጉ። ግርግሩ ለጊዜው ጋብ እንዳለ መሀመድ ወደመኝታው አመራ። ይህኔ ደረጀ ወደ መሀመድ ፈጠነ። በእጆቹ ድንጋይ ይዟል። እያደባ ወደፊት አለፈ። ጠበኛውን እንደቀረበው ድንጋዩን አስተካክሎ ወረወረ፡፡
መሀመድ በደረጀ የተወረወረበት ድንጋይ ግንባሩን አገ ኘው። ፊቱ በደም ተሞላ። ሁኔታውን ያዩ ገላጋዮች አሁንም ከመሀል ገቡ። መሀመድን እንደተኛ ያጠቃው ወጣት ከእጃቸው አምልጦ ከስፍራው ተሰወረ። መሀመድ በእልህ ጥርሱን እየነከሰ በብስጭት ተከነ። ቁማርተኛው ወጣት ሳያስበው ስላጠቃው ተበሳጭቷል። እሱን እያሰበ ዓይኖቹን በጨለማው ያማትራል። የተመታ፣ የተፈነከተ ግንባሩን እያሻሸ፣ ደም የለበሰ ፊቱን እየጠረገ እጆቹን ደጋግሞ ያጋ ጫል።
ምሽት ሁለት ሰዓት ማለት ሲጀምር ከስፍራው ነዋሪዎች ጥቂቶቹ የእንግሊዝን እግርኳስ ጨዋታ ለማየት ከየቤታቸው ወጡ። የጨረቃ ሰፈርን የኋሊት ጥለውም ወደ አስፓልቱ ዘለቁ። ደረጀ መሄድ ፈልጎ ከእነሱ ተቀላቀለ። መሀመድ ህመም እየተሰማው ወደማደሪያው ሄደ።
ምሽት 4 ፡ ሰአት ከ 30
እግር ኳስ ጨዋታውን ሲመለከቱ ያመሹት የጨረቃ ሰፈር ነዋሪዎች በቆይታቸው ተዝናንተዋል። ጨዋታው ለእረፍት መቋረጡን ተከትሎ ወደመኖሪያቸው መመለስ እያሰቡ ነው። ሰብሰብ ብለው ወደማደሪያቸው ሲዘልቁ ስለነበረው የጨዋታ ስልት ፣ ስለተጫዋቾቹ ጥበብና እውቅና እያወሩ ነበር። ነዋሪዎቹ ወደመንደራቸው ሲዘልቁ የጨረቃ ሰፈር ከነዝምታው ተቀበላቸው። ደረጀን ጨምሮ የተወሰኑት እሳት አንድደው ለመሞቅ ተስማሙ። ሌሎቹ ምሽቱን በእንቅልፍ ለመቀበል ወደ ደሳሳ ጎጆዎቻቸው አመሩ።
መሀመድ ከጠቡ በኋላ ቤት እንደገባ እንቅልፍ ይሉት በዓይኑ አልዞረም። በጊዜ ደረጀ ያደረሰበትን ጥቃት እያሰበ ሲብከነከን አምሽቷል። ሳያስበው በደረሰበት ጉዳት እፍረትና ንዴት ይፈራረቁበት ይዘዋል። ቤቱ እንደተኛ ከውጭ በኩል የሰዎች ድምጽ ሰማ። በጊዜ ኳስ ለማየት የሄዱ ጎረቤቶቹ መሆናቸው አልጠፋውም።
ቀስ ብሎ ከድምጾች ድምጽ መረጠ። ከሰዎቹ መሀል የደረጀን ቅላጼ መለየት አላቃተውም። ተጠንቅቆ ወደውጭ አጮለቀ። ደረጀ ከአንድ ጎረቤቱ ጎን ተቀምጦ እሳት እየሞቀ ነው ። ኮቴውን አጥፍቶ ከቤቱ ወጣ። የቆመበት ጨለማ ወደ እሳቱ የብርሀን አቅጣጫ አመላከተው። ኮሽታ ሳያሰማ በጀርባቸው አልፎ ቆመ።
ድንገቴው ዱላ
ደረጀና ጎረቤቱ የእሳት ዳር ጨዋታቸው ቀጥሏል። መሀመድ በእጁ የጨበጠውን ወፍራም ዱላ እንደያዘ አጠገባቸው ደርሷል።ድንገት በደረጀ አናት ላይ ያረፈው ከባድ ምት ሁኔታውን ሁሉ ቀየረ ። ድንገት ደረጀ በተቀመጠበት የኋሊት ወደቀ። መሀመድ ጨከነ። የእጁን ዱላ አልጣለውም። በጭንቅላቱ፣ በእግሩ ደጋግሞ አሳረፈበት። ደረጀ በደመነፍስ የደብዳቢውን እግር ለመያዝ ሞከረ። አልቻለም።ጉዳቱ ከነበረበት አላስነሳ፣ አላላውስ አለው።
በሆነው ሁሉ ክፉኛ የደነገጠው ጎረቤት መሀመድ ደረጀን ከወደቀበት በዱላ ሲደጋግመው ከድርጊቱ እንዲያቆም ተማጸነ ። ሰሚ ጆሮ አላገኘም ። ግርግሩን ያዳመጠ ሌላው ጎረቤት ከእንቅልፉ ተነስቶ ከመሀል ገባ ። ፈጥኖም የደብዳቢውን ዱላ ለመንጠቅ ሞከረ። መሀመድ ለእሱም አልተበገረም። በያዘው ዱላ አንድ ጊዜ አሳረፈበት።
የቀደመው ጎረቤት የሰዎችን መሰባሰብ እንዳየ የደረጀን የቅርብ ዘመዶች አድራሻ ለማፈላለግ ከቦታው ራቀ። ደረጀ ክፉኛ ተጉድቷል። ከጭንቅላቱ ደም ይፈሳል፣ መናገር፣ መንቀሳቀስ ተስኖታል። በስፍራው የደረሱ ተሯሩጠው ሆስፒታል አደረሱት። የከፋ ጉዳት ያገኘው ወጣት ከሁለት ቀናት በኋላ ህይወቱ እንዳለፈ ተሰማ ።
የፖሊስ ምርመራ
የወንጀሉ መፈጸም ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ በስፍራው ተገኝቶ ስድስት ተጠርጣሪዎችን ያዘ። በዕለቱ የሆነውን ሁሉ ከእማኞች አረጋግጦም የድርጊቱ ፈጻሚ መሀመድ እንደሆነ ደረሰበት ። ፖሊስ መሀመድን በቁጥጥር ስር አውሎ ተገቢውን ጥያቄ አቀረበ ። መሀመድ የሆነውን ፣ ያደረገውን አልደበቀም ። ድርጊቱን የፈጸመው በቂም በቀል መነሻ መሆኑን አረጋግጦ ቃሉን ሰጠ።
መርማሪ ረዳት ኢንስፔክተር ታምሩ ቀነኒ ተጠርጣሪው የሰጠውን ሙሉ ቃል በወንጀል መዝገብ ቁጥር 626/06 ላይ አስፈረ ። ተገቢውን ምርመራና ማስረጃዎች አጠናክሮም ዶሴውን ወደ ዓቃቤ ህግ የክስ መዝገብ አሳለፈ ።
ውሳኔ
ሀምሌ 11 ቀን 2007 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ መሀመድ ሀምዛ ላይ የተከፈተውን የክስ መዝገብ ለመቋጨት በቀጠሮው ተገኝቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በቀረበበት ከባድ የሰው መግደል ክስ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡በዕለቱ በሰጠው የመጨረሻ ብይንም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ቀን አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስድስት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013