እንጨትን ለማገዶነት ከመጠቀም ጀምሮ ለቤት መስሪያነትና በቤት ውስጥ ለምንጠቀምባቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች ስንገለገል ኖረናል።እየኖርንም እንገኛለን። በቤት ውስጥ በተለይም ሀገር በቀል የሆኑ ዛፎችን በመጠቀም የሚመረቱ የተለያዩ ቁሳቁሶች ዕድሜ ጠገብ ሆነው ለትውልድ ሲተላለፉም ይስተዋላል፡፡
የቤት ውስጥ ቁሳቁስ በዘመናዊ መንገድ በፋብሪካ ደረጃ መመረት ከመጀመሩ አስቀድሞ በሀገሪቱ በርካታ ቁሳቁሶች በሰው እጅ በባህላዊ መሳሪያዎች ይሰሩ ነበር።በዚህ መንገድ ከተሰሩ ቁሳቁሶች መካከልም በአሁን ወቅት በቅርስነት ተመዝግበው መቀመጣቸው ይታወቃል፡፡
ከባህላዊ በተጨማሪ በአሁን ወቅት ዘመናዊ በሆነ መንገድ የእንጨት ሥራ ወይም የፈርኒቸር ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ መምጣቱም ይታወቃል።በመሆኑም በየዕለቱ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የፈርኒቸር መሸጫ ቤቶችንና ቁሶቹን እዚህም እዚያም መመልከት የተለመደ ሆኗል።
በዛሬው የሥኬት አምዳችንም ይህንኑ ጉዳይ የምናስቃኝ ሲሆን ላለፉት 40 ዓመታት በእንጨት ሥራ ላይ ተሰማርቶ በርካታ ምርቶችን እያመረተ ለገበያ በማቅረብ የሚታወቀው ፋሲሎ የእንጨት ሥራ ፋብሪካን የሥራ እንቅስቃሴን ይሆናል፡፡
በሀገሪቱ የፈርኒቸር ኢንዱስትሪ በቀዳሚዎቹ ተርታ የሚገኘው ፋሲሎ የእንጨት ሥራ ላለፉት 40 ዓመታት በሥራው ላይ ተሰማርቶ የበርካቶችን ቤት ቁሳቁስ ሲያሟላ ቆይቷል።መካኒሳ አካባቢ የሚገኘው ፋሲሎ የእንጨት ሥራ ፋብሪካ ገና ከደጃፉ ለተመለከተው ማምረቻ ኢንዱስትሪ አይመስልም።ነገር ግን ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ሰራተኞች ይዞ የተለያዩ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን በርና መስኮትን፣ ቁምሳጥን፣ ኪችን ካቢኔትና ሌሎችንም የሚያመርት ሰፊ ፋብሪካ ነው፡፡
በፋሲሎ የእንጨት ሥራ ፋብሪካ ጀነራል ማናጀር አቶ አብዱራህማን ሰኢድ እንደሚገልፁትም፣ ፋብሪካው ሲቋቋም መሰረት ያደረገው የተለያዩ የእንጨት ሥራዎችን ለማምረት ነው።አጠቃላይ ፈርኒቸሮች ማለትም በሮች፣ መስኮቶች፣ ቁምሳጥኖች፣ ኪችን ካቢኔቶች፣ ፐርኬዎችን ና ደረጃዎችን ያመርታል።ፋብሪካው በ1973 ዓ.ም ሲቋቋም ጀምሮ በወቅቱ በነበሩ የጀርመን፣ የጣልያን እና የራሺያ ሥሪት የሆኑና ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም ጠንካራና ጥራት ያላቸውን ምርቶች በማምረት ይታወቃል።
በወቅቱ በፋብሪካው ይሰሩ የነበሩት ጣልያኖች ሲሆኑ፤ ከጣልያኖች ወደ ሀገር ውስጥ ባለሃብት ተዘዋውሮ በወቅቱ የነበሩትን ዘመናዊና ትላልቅ ማሽኖች በመጠቀም ፈርኒቸሮችን እያመረተ ዛሬ ላይ ደርሷል።በአሁን ወቅትም ዘመኑ ያመጣቸውን እና የአዲሱ ትውልድ በሆኑ ማሽኖች ፈርኒቸሮችን ማምረት ቀጥሏል፡፡
በፋብሪካው ይመረቱ የነበሩ ምርቶች በተለይም ቁምሳጥኖችና በሮች ለ30 ዓመትና ከዛም በላይ ምንም ሳይሆኑ የሚቆዩ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አብዱራህማን፤ ለዚህም ምክንያቱ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ይመረቱ የነበሩት ምርቶች በጠቅላላ ሀገር በቀል የሆኑ ዛፎችን በመጠቀማቸው እንደሆነ ያነሳሉ።
እንደ አቶ አብዱራህማን ገለፃ፣ ባለፉት አስርና አስራ አምስት ዓመት ወዲህ ኤም ዲ ኤፍ የሚባል ቴክኖሎጂ በመምጣቱ አብዛኛው ምርት በዚሁ ዘመን ባመጣው ግብአት አማካኝነት ተተክቷል።ቀደም ሲል እንጨት በእንጨት ሆኖ የሚሰሩ ቁምሳጥን፣ በሮች፣ ኪችን ካቢኔትና ሌሎችም በኤም ዲ ኤፍ በሚባለው ምርት ተተክተዋል፡፡
ሀገሪቷም ከፍተኛ መጠን ያለውን የውጭ ምንዛሪ እያወጣች ኦስትሪያ የሚባል እንጨት ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባለች።ኦስትሪያ የሚባለው እንጨትም በማሸጊያነት የሚያገለግሉ ናቸው።እያንዳንዱ ምርት የሚመረተው ኤም ዲ ኤፍና የኦስትሪያ እንጨትን በመጠቀም ነው።ከዚህም ባለፈ የተለያዩ ፈርኒቸሮች ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ።ይህም በርካታ የውጭ ምንዛሪን ይጠይቀል።ዘርፉ የሚጠይቀውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ብዙ ሥራ ይቀራል።በዘርፈ በርካታ ለነገ የማይባሉ ቀሪ ሥራዎች አሉ።በዚህ ረገድ በርካታ ተግባራት ማከናወን ይጠይቃል፡፡
በተለይም የተለያዩ ፈርኒቸሮችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ከመሸጥ ባለፈ አምራች የሆኑ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ ሊበረክቱ ይገባል።ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ ሲበራከቱ ይዘውት የሚመጡት ትርፍ ብዙ ነው።የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ላይም የጎላ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።ነገር ግን ፋብሪካ ከፍቶ መስራት አድካሚ በመሆኑ አብዛኛው ሰው ከውጭ አምጥቶ መሸጥና መለወጥን ይመርጣል።ይህ ደግሞ የፈርኒቸር ኢንዱስትሪውን እድገት ላይ የራሱን ማነቆ የሚፈጥር ነው፡፡
‹የፈርኒቸር ኢንዱስትሪውን የማዘመን እና የማሳደግ ሥራ ደካማ ነው።በተለይም በአሁን ወቅት በሀገሪቱ ደረጃቸውን የጠበቁ ትላልቅ ሆቴሎችን ጨምሮ በከፍተኛ መጠን እየተገነቡ ናቸው።እነዚህ ቤቶች ደግሞ ፈርኒቸር ይፈልጋሉ።በመሆኑም ፈርኒቸሮችን ከውጭ ሀገር ከማስገባት ይልቅ አምራች ፋብሪካዎች ማበርከት የግድ ይላል።
‹‹በሀገር ውስጥ ካሉት ጥቂት የፈርኒቸር አምራች ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነው ፋሲሎ የእንጨት ሥራ ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም ከጊዜው ጋር እየተራመደ ይገኛል።ነገር ግን በዕድሜው ልክ ተራምዷል ማለት አይቻልም››የሚሉት አቶ አብዱራህማን፤ ለዚህም ከጥሬ ዕቃ አቅርቦት ጀምሮ በርካታ ውጫዊ የሆኑ ምክንያቶች መኖራቸውን ችግሮች መኖራቸው ያነሳሉ።
ፋሲሎ የእንጨት ሥራ የዘርፉን ፈታኝ ሁኔታዎች ተቋቁሞ ለ40 ዓመታት ፈርኒቸሮችን እያመረተ ዘልቋል።በዚህ ጊዜ ውስጥም ፋብሪካው በሚፈልገው ፍጥነት ማምረትእና አሁን ካለበት ወደ ላቀ ደረጃ በፍጥነት መጓዝ እንዳይችል በርካታ ማነቆዎች ቢገጥሙትም አሁን ድረስ እጁን የሚይዘው በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የግንባታ እስታንዳርድ አለመኖሩ ነው።
የእንጨት ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸው ምርቶች በጠቅላላ አገልግሎት የሚሰጡት በሚገነቡ ህንጻዎች ውስጥ ነው።ህንጻዎቹ ደግሞ ስታንዳርድ የሌላቸው በመሆኑ ዘርፉን ፈታኝ ያደርገዋል።ለአብነትም ለአንዱ ህንጻ የተመረተው በር ለሌላው አይሆንም።ሌላውም ሌላ መጠን ወይም ስፋትና ቁመቱ ይፈልጋል።ይህ በመሆኑ ምክንያትም ፋሲሎ የእንጨት ሥራ ፋብሪካ በስፋት ወደ ማምረት መግባት አልቻለም።በሁሉም ሰው ቤት በመሄድ የተለያየ መጠን ያላቸውን በሮች፣ ኪችን ካቢኔቶችና ሌሎች ምርቶችንም ያመርታል።ነገር ግን ይህ በራሱ የፋብሪካውን ዕድገት ጎትቷል።
ምንም እንኳን በሀገሪቱ የሚሰሩ ህንጻዎች ስታንዳርድ የሌላቸው በመሆኑና ፋብሪካው በስፋት ወደ ማምረት መግባት ባይችልም በአማካኝ ከ500 እከ 600 በሮችን የማምረት አቅም አለው።የበሮቹ አይነትም የተለያየ ሲሆኑ እንደ ሰዎቹ ፍላጎት ዘጠኝ አይነት በሮች በፋሲሎ የእንጨት ሥራ ፋብሪካ ውስጥ ይመረታሉ።
እንደ አብዱራህማን ገለፃ፣ በውጭው ዓለም ሁሉም ነገር የሚሰራው በስታንዳርድ ነው።አንድ ሰው ከስታንዳርድ ውጭ የሆነ ነገር ማሰራት ቢፈልግ ተጨማሪ ክፍያ ይጠይቃል።ምክንያቱም ተጨማሪ የዲዛይን ሥራን ይጠይቃልና ነው። በሀገሪቱም እንዲህ አይነት ስልጣኔን ማምጣት ለዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ማለማመድ ያስፈልጋል።ምክንያቱም የያንዳንዱን ግለሰብ ቤት በመስራትና ለብዙሃኑ አንድ ጊዜ በስፋት በማምረት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ።ይህ ልዩነትም የኢንዱስትሪን ዕድገትን ወደ ኋላ ያስቀራል።
‹‹የስልጣኔ መገለጫ አንዱ ስታንዳርድ ነው›› የሚሉት አቶ አብዱራህማን፤ እያንዳንዱን ነገር በስታንዳርድ ማምረት ከተቻለ ሥራም ሆነ ህይወት እየቀለለ እንደሚሄድ ያስገነዝባሉ።በአሁን ፋብሪካው 150 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን ከግማሽ የሚልቅ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ሴት ሰራተኞች ናቸው።
ሰራተኞች በፋብሪካ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ ተከፋይ ከመሆናቸው ከጥበቃም ይሁን ከሌሎች የሥራ ዘርፎች ወደ ሙያው መምጣት ለሚፈልጉ ሁሉ ፋብሪካው ዕድሉን በመስጠት ባሉት ማሽኖች ተጠቅመው ሙያ እንዲቀስሙ ያደርጋል።በዚህም በርካቶች ተጠቃሚ ሆነዋል።
ወጣቶች እንዲህ ባሉ ፋብሪካዎች ውስጥ ገብተው በመዋላቸው በርካታ ዕውቀት ይቀስማሉ።ሀገር የሚቀየረውም በዕውቀትና በሥራ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ፋብሪካዎች ተበራክተው ወጣቱን ሊጠባበቁ እንደሚገባ አቶ አብዱራህማን ይናገራሉ።
ፋብሪካ ማለት ብዙ ነገሮችን የሚሸከም እንደመሆኑ ፋሲሎ የእንጨት ሥራ ፋብሪካም በርካታ ፈታኝ የሆኑ ነገሮችን ተቋቁሞ አራት አስርት አመታትን አስቆጥሯል። የሚያመርታቸው ምርቶችም ፋብሪካው በዘላቂነት መቀጠል እንዲችል የሚያደርጉ በመሆናቸው በቀጣይ የተለያዩ ማሽነሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት የማምረቻ ፋብሪካውን የማስፋት ዕቅድ አለው።
ፋሲሎ የእንጨት ሥራን ከሌሎች ፋብሪካዎች ለየት የሚያደርገው ማምረቻ ፋብሪካው ለደንበኞች ክፍት ነው።በመሆኑም ደንበኞች በፋብሪካው ገብተው የሚፈልጉትን ምርት ያዛሉ።ሲመረትም መመልከት ይችላሉ።ይህም ደንበኛው የፈለገው እቃ እንዴትና በምን አይነት ግብአት እንደሚመረት ማወቅ ከማስቻሉም ባለፈ እምነት እንዲኖራቸውም ያደርጋል።
ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ለተለያዩ ተቋማት በስፋት በሮችን የሚያመርት ቢሆንም በብዛት የሚሰራው ግን ዘመናዊ የሆኑ የግለሰብ ቤቶችን ፈርኒቸር ማሟላት ነው። የሚሰሩ ሥራዎችም ጥራታቸውን የጠበቁ በመሆናቸውና እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት መዘግየት ይኖራል። ነገር ግን ደንበኞች ስለፈለጉ ብቻ በፍጥነት አይወስዱም።ጠንካራና ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ይሰራል።የፈርኒቸር ሥራ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ፋሲሎ የእንጨት ሥራ በዘመናዊ ማሽን ጥራት ያላቸውን ምርቶች በማምረት የሚታወቅና የረጅም ጊዜ ደንበኞች ያሉት ነው።
ሀገሪቱ በዕድገት ጎዳና ላይ እንደመሆኗ የፈርኒቸር ኢንዱስትሪው በተለይም አምራች የሆኑ ፋብሪካዎች መስፋፋት ያለባቸው መሆኑን የሚያስገነዝቡት አቶ አብዱራህማን፤ ፋብሪካዎች ሲስፋፉ ሰፊ ቁጥር ላለው የሰው ሐይል የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል።በመሆኑም ፋሲሎ የእንጨት ሥራ የማስፋፋያ ቦታ ከመንግስት እንዲሰጠው ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ጥያቄው ምላሽ ሲያገኝም ተጨማሪ የሥራ እድል በመፍጠር ምርቶቹን በስፋት የማምረት ዕቅድ አለው፡፡
መንግስት መሸጥ መለወጥ ላይ ተሰማርተው ከሚሰሩት ይበልጥ በተለየ ሁኔታ አምራች የሆኑ ፋብሪካዎችን በመደገፍ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እዲችሉ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል።ከዚህም ባለፈ እያንዳንዱ ሰው የሚሰራው የማንኛውም ሥራ ውጤት ተደማምሮ ውጤቱ የሚታየው ሀገር ላይ ነው።ስለዚህ ጠንካራ የሥራ ባህልን ባህላችን በማድረግ ሀገርን መቀየር እንደሚገባና የግድ እንደሆነ ያነሱት አቶ አብዱራህማን የአንድ ሰው የስኬት ጉዞ ለብዙዎች እየተረፈ መሄድ እንዳለበትና የብዙዎች ስኬት ድምር ደግሞ ሀገርን ማሳደግ እንደሚችል ያላቸውን እምነት በመግለጽ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።እኛም የእርሳቸውን ሀሳብ በመዋስ እያንዳንዳችን በተሰማራንበት የሥራ መስክ ለውጤት በመስራት ሀገርን እንቀይር በማለት አበቃን።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013