በመላው ዓለም ለሰዎች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን እያስገኘ የሚገኘው በይነ – መረብ (ኢንተርኔት) ሰዎች የኑሮ ሁኔታቸውን እንዲያሻሽሉ ከፍተኛ ሚና እየተጨወተ ይገኛል። ሰዎች ከዘመነ በይነ መረብ በፊት ነገሮችን አስቀድመው እንዲያገኙም ዕድል እየፈጠረላቸው ይገኛል፡፡ የሰዎች አኗኗር የተቃና እንዲሆን በማድረግ ረገድም ይኸው በይነ መረብ አስተዋፅኦው እየጎላ መጥቷል፡፡
በይነ-መረብ ከምንም በላይ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ የመገናኛ መሣሪያዎች አንዱ ሆኖ ብቅ ካለ የሰነባበተ ሲሆን፤ በጣም ፈጣን እና ወጪ ቆጣቢ የመገናኛ እና የመረጃ መጋሪያ ዘዴዎች እውን እንዲሆኑም አስችሏል። ፈጣን እና በጣም ምቹ የሆነ የግንኙነት መስመሮችን ለመፍጠር፣ ሰፋ ያለ መረጃ ለመለዋወጥ፣ እንዲሁም በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘትም አስችሏል፡፡
ሆኖም የበይነ – መረብ ተደራሽነት እና የተጠቃሚዎች ቁጥር ከሀገር ሀገር ብሎም ከአህጉር አህጉር ይለያያል፡፡ አውሮፓና አሜሪካ አህጉራት የተሻለ የኢንተርኔት ተደራሽነት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ሲመደቡ አፍሪካ እጅግ ዝቅተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ከኢንተርኔት ጋር የተገናኘባት አህጉር ናት፡፡
በአፍሪካ ውስጥ ከሚኖር አንድ ነጥብ 3 ቢሊዮን ገደማ ህዝብ ውስጥ ከበይነ- መረብ (ኢንተርኔት) ጋር የተገናኘው ሩቡ ወይም 325 ሚሊየን ገደማው ህዝብ ብቻ መሆኑን ፌስ ቡክ ከታላላቅ የቴሌኮም ኩባኒያዎች ጋር በመሆን እ.አ.አ በ2020 ያስጠናው ጥናት ያመላክታል፡፡ ከዚህ አሃዛዊ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው አፍሪካ እንደ አህጉር ዝቅተኛ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ ከበይነ- መረብ ጋር ግንኙነት የፈጠረባት አህጉር መሆኗን ነው፡፡
በዚህም ምክንያት የአህጉሪቱ ህዝብ ከኢንተርኔት ማግኘት ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞችን ለማግኘት ሳይታደሉ ኖረዋል፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በአህጉሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የኢንተርኔት ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ዛሬም የአህጉሪቱ የኢንተርኔት ሁኔታ ከሌሎች ዓለማት አንጻር ሲታይ የሰማይይና የምድርን ያህል የተራራቀ ነው፡፡
ይህን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀልበስ አፍሪካን ከአውሮፓ የሚያገናኘው የባሕር ውስጥ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር ዝርጋታ አፍሪካን በባሕር ውስጥ በሚዘረጋ የፋይበር ኦፕቲክ ገመድ ከአውሮፓ ጋር የማገናኘት እቅድ ያለው ‹‹ቱ አፍሪካ›› በሚል ስያሜ በፌስቡክ እና በዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች ጥምረት ለአፍሪካ የኢንተርኔት ተደራሽነት የተሻለ አማራጭ ያቀርባል የተባለለት ፕሮጀክት አምና ነበር የተጀመረው፡፡
ይህ ፕሮጀክት በወርሐ ግንቦት እ.ኤ.አ በ2020 ነው የተጀመረ ሲሆን፤ እጅግ በጣም ሰፊ እና አካታች የሆነውን የባህር ዳርቻ ገመድ ለመገንባት ፌስ ቡክ ከአፍሪካ እና ከዓለም አቀፍ የቴሌ ኦፕሬተሮች ጋር በመተባበር ሥራው ተጀምሯል። ‹‹ቱ አፍሪካ›› የተሰኘው ፕሮጀክት በዓለም ላይ ካሉት ግዙፍ የከርሰ ምድር ኬብል ፕሮጄክቶች አንዱ ሲሆን፤ በአፍሪካ ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአውሮፓ ሃያ ሦስት አገሮችን ያገናኛል።
‹‹ቴክ ክራንች›› በዘገባው እንዳስነበበው፤ ቱ አፍሪካ ኮንሶርቲየም ፕሮጀከት የቻይና ሞባይል ኢንተርናሽናል ፣ ፌስቡክ ፣ ኤም ቲ ኤን ግሎባል ኮኔክት ፣ ኦሬንጅ ፣ ስ ቲሲ ፣ ቴሌኮም ኢጂፕት ፣ ቮዳፎን እና ዊ ዮ ሲሲሲን ያካትታል፡፡ እነዚህ የቴሌኮም ኩባኒያዎች እና ፌስ ቡክ በጋራ በመሆን ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ በመሥራት ላይም ይገኛሉ፡፡
ሲጠናቀቅ የዓለማችን ረዥሙ የፋይበር ገመድ ዝርጋታ እንደሚሆን የሚጠበቀው ሁለት አፍሪካ ፕሮጀክት ሥራ ሲጀምር 180 ቴራ ባይት በሰከንድ የሚደርስ አቅም እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ ፕሮጀክቱ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅን ጨምሮ በ26 ሀገራት 35 መዳረሻዎች ይኖሩታል፡፡
ይህ ፕሮጀክት፤ ከርዝመቱ ባሻገር በርካታ አስደናቂ ነገሮችን አካቶ ይዟል፡፡ ዛሬ ላይ አፍሪካን የሚያገለግሉ የሁሉም ንዑስ ባህር ኬብሎች አጠቃላይ የኔትወርክ አቅም ሦስት እጥፍ ያህል ይሰጣል። ይህ አዲስ መስመር ሲጠናቀቅ በጣም የሚያስፈልገውን በይ -ነመረብ በተሻለ አቅም እና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለመላው አፍሪካ ያቀርባል። በመካከለኛው ምሥራቅ በፍጥነት እየጨመረ የሚሄደውን የኢንተርኔት ፍላጎት ማሟላት ፣ እና በመቶ ሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የተሻለ የ4ጂ ፣ 5ጂ እና የብሮድባንድ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቴክ ክራንች ዘግቧል።
አዲስ የሚስፋፋው የኢንተርኔት አቅም ለሰዎችም ሆነ ለንግድ ሥራዎች በጣም የተሻሻለ ተደራሽነትን በማስፋት ጤናማ የበይነ-መረብ ሥነ ምህዳርን እንደሚያመቻች ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፤ ለንግድ ድርጅቶች በሰፊው ተደራሽ የሆነ በይነ-መረብ ሲኖር ኢኮኖሚዎች እንደሚያድጉ እሙን ነው። የአፍሪካ እያደገ የመጣ የዲጂታል ኢኮኖሚ አካል እንደመሆኑ መጠን ‹‹ቱ አፍሪካ›› እጅግ በጣም ትልቅ የበይነ-መረብ መስፋፋትን የሚደግፍ እንደ አስፈላጊ ምሰሶ የሚታይ ነው።
በዓለም ላይ ትልቁ የከርሰ ምድር ኬብል ፕሮጀክት የሆነው ቱ አፍሪካ ፣ በሚያርፍበት አካባቢ ለሚገኙ ለእያንዳንዱ ሀገራት ፈጣን እና የበለጠ አስተማማኝ በይነመረብ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በበይነ-መረብ ላይ የተመሰረተ ሥራ የሚሠሩ የማህበረሰብ ክፍሎችም ከትምህርት እስከ ጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች እና ንግድ በፊት ከነበረው የተሻለ የኢንተርኔት ትስስር እንዲያገኙ የሚረዳ ሲሆን፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞችንም እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።
የ ‹‹ቱ አፍሪካ ፕሮጀክት›› ከተጀመረበት ከግንቦት 2020 ጀምሮ ኬብልን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የኢንተርኔት ኬብል ማስተላለፊያ መስመር በማቀድ እና በማዘጋጀት ረገድ አመርቂ ሥራዎች መሠራታቸውን ፌስቡክ በቅርቡ ባወጠው መግለጫው ያብራረ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በ2023 ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የመጀመሪያ ዙር የኬብል ዝርጋታ በ2022 ለማከናወንም የኬብል እና የሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች የማምረት ሥራው በፍጥነት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ኬብሉ ከሚያልፍባቸው ቁልፍ ቦታዎች አንዱ የግብፅ አዋሳኝ በሆኑት ሜዲትራኒያን እና ቀይ ባህር ዳርቻ ሲሆን፤ ግብፅን ከቀይ ባህር እና ከሜዲትራኒያን ጋር የሚያገናኘው ክፍል ላይ የሚሠራው ሥራ ከእቅዱ አስቀድሞ ተጠናቋል፡፡ ከሜዲትራኒያን እስከ ቀይ ባህር ያለው ሥራም በተመሳሳይ ተጠናቋል፡፡ በቀጣይም ከቀይ ባህር ቀጥሎ ያለው ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የኬብል ዝርጋታውን በማከናወን ላይ ያሉ የቴክኖሎጂ ኩባኒያዎች እንደሚሉት፤ ‹‹ቱ አፍሪካ ፕሮጀክት›› የአህጉሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ አካል ወደ ሆነ ክፍት እና ሁሉን አቀፍ የበይነ-መረብ ሥነ ምህዳር ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ የ ቱ አፍሪካ ኬብል በሚያርፍባቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች በአነስተኛ ዋጋ፣እና ፍትሐዊ ዋጋ አገልግሎቱን ያገኛሉ፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ከሚዘረጉ ኬብሎች አንዱ ምሥራቅ እና ምዕራብ አፍሪካን ያለምንም እንከን የሚያገናኝ ይሆናል፡፡ ይህ የመጀመሪያው የከርሰ ምድር ገመድ ስርዓት ከባህር ዳርቻ እስከ ባህር ዳርቻ ድረስ አዲስ የመገናኛ መንገዶች እውን እንዲሆኑ ያስችላል። በተጨማሪም፣ ቀይ ባሕርን እና ከሜዲትራኒያን ባሕር የሚያገናኘው አዲስ መስመርም በቀጣናው የመጀመሪያው ነው፡፡
ቱ አፍሪካ እንደሌሎች ኢንቨስትመንቶች ኢንቨስትመንቶችን በቀጣናዎች ከፍሎ የሚያካሂድ ሲሆን፤ በአፍሪካ ውስጥ በአራት ቀጣናዎች በመክፈል ነው ሥራውን እየሠራ የሚገኘው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ቀጣና በደቡብ አፍሪካ ፣ የምሥራቅ አፍሪካ በኡጋንዳ ፣ የምዕራብ አፍሪካ በናይጄሪያ እና የማዕከላዊ አፍሪካና በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ አድርጎ ሥራውን እየሠራ ይገኛል፡፡
ቀጣይነት ባለው የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ዙሪያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራቸውን ለመሥራት ፣ ትምህርት ቤት በመከታተል እና ከሚያስቡላቸው ጋር ለመገናኘት ኢንተርኔት የተጫወተው ሚና የኢንተርኔትን አስፈላጊነት የጎላ መሆኑን ለዓለም ይፋ መሆኑን ያብራረው የብሉም በርግ ዘገባ፤ ቱ አፍሪካ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የግንኙነት መሠረተ ልማት ለማስፋፋት አስፈላጊ አካል ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ ማገገም ወሳኝ በሆነ ጊዜ የመጣ ትልቅ ኢንቨስትመንትም መሆኑን ገልጿል፡፡
ከፍተኛ የኢንተርኔት ኮኔክሽን ለማረጋገጥ እና ኬብሎቹ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ፤ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የዝርጋታ ሥራው እየተከናወነ የሚገኘው የቱ አፍሪካ ፕሮጀክት፤ ዓለም አቀፍ የአውታረ መረብ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፤ በመዳረሻ ፣ በአቅም እና በተለዋዋጭነት ኢንዱስትሪውን የሚመሩ በርካታ የከርሰ ምድር ፋይበር ኦፕቲክ ኬብሎችን በመገንባት ረገድ በዓለም ዙሪያ ልምድ ያላቸው አጋሮች ተባብረው እየሠሩት ያለ ሥራ ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡
ፕሮጀክቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረው በተጨማሪ ሰሞኑን አራት አዳዲስ ቅርንጫፎች እንዲካተቱ ያደረገ ሲሆን፤ አዲስ የተካተቱት ሀገራት ሲሼልስ፣ ኮሞሮስ፣ አንጎላ እና የካናሪ ደሴቶች መሆናቸውን ቴክ ክረንች ዘግቧል፡፡ አልካቴል ባሕር ሰርጓጅ አውታር (ኤ ኤስ ኤ ን) አዲሶቹን ቅርንጫፎች ወደ ሥራ ለማስገባት የተመረጠ ሲሆን፤ ይህም በ 26 አገሮች ውስጥ የቱ አፍሪካ ማረፊያዎችን ቁጥር ወደ 35 ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ ይህም በአፍሪካ እና በአካባቢው ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያሻሽላል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013