አንድ ሰው የቱንም ያህል ሀብት ቢያፈራ፣ ምንም ዓይነት ጥሩ ባህርይ ወይም ደግሞ የቱንም ያህል ስኬታማ ቢሆን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የቅናት ስሜት ሊያድርበት ይችላል። የተፈጠረው የቅናት ስሜት የሚስተናገድበት መንገድ ግን ከሰው ወደ ሰው የተለያየ ነው። አንዳንዱ የተፈጠረበትን የቅናት ስሜት ለለውጥ ለመሻሻል የሚጠቀምበት ሲሆን፤ አንዳንዱ ሌሎችን ለመጉዳት ያውለዋል ለመሆኑ ቅናት ምንድን ነው እንዴትስ መቆጣጠርና ለበጎ አለማ መጠቀም እንችላለን ስንል የዘወትር ተባባሪያችን የሆኑትን የማህበራዊ ሳይንስ አመራርና ባለሙያ አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ቅናት ስንል ክፉ ምኞት ወይም መመቅኘት ወዘተ እንደማለት አቻ ትርጉም አለው። የራስን ትንሽ በሌሎች ብዙ ውስጥ በማዬት ለምን ተበለጥኩ ወይም ተቀደምኩ ከሚል የበታችነት የሚመነጭ ነው። እኛ የሌለንን ወይም ያጣነውን ሌሎች ስላላቸው የሚፈጠርብን መብከንከንም እንደማለት ይሆናል። በሌላ በኩል ራስን ከመለወጥና ከማሳደግ አንጻር በሌሎች መቅናት ሊፈጠር ይችላል፤ ይህ ግን ስንቆጣጠረውና አቅጣጫውን ወደ በጎና መልካም የግል እድገት መጠቀም ስንችል ብቻ ነው።
የቅናት መነሻ ምክንያት
ቅናት ሰው ማሰብ ገና ሳይጀምር በደመነፍስ ከነበረበት ከሕፃንነቱ ጊዜ ጀምሮ አብሮት የሚጀምርና ምንጩ አካላችን፣ ስጋችን ወይም ሰውነታችን አልያም በአጠቃለይ ህዋሳዊ አካሎቻችን የሚፈጥሩብን ስሜት ነው። ይህም አብሮን ከአካላችን ጋር በማደግ ህይወታችንን ሙሉ እስክንሞት ድረስ አይነጠለንም። እነዚህ የስጋ ምኞት የሚባሉት ደግሞ ምንዝርና፣ መስገብገብና መሳሳት፣ ውድድር፣ እንቅልፍ፣ ልምድ፣ መጋጨትና መገፋፋት፣ ራስ ወዳድነት ወዘተ ናቸው። እነዚህንም ከእኛ ቁጥጥር ውጪ እኛ ብንፈቅድም ባንፈቅድም አካላዊነታችን በራሱ ያመነጫቸዋል። ልክ የከዋክብት አካል ብርሃን እንደሚያመነጨው ሁሉ ስጋችንም እነዚህን ባህሪት፣ መሻት ወይም ፍላጎት ያመነጫል።
በተጨማሪም ሰው ሲቀድም፣ ሲበለጥ ወይም ዝቅ ሲልና ወደ ኋላ ቀርቻለሁ ሲል ሊፈጠርበት የሚችል ባህሪም ነው። ለእኔም ሆነ ለእነሱ አይገባም ነበር የሚል ስሜታዊ ሃሳብ ነው። መስጋት፣ መጠራጠርና መገመት ደግሞ መቅናታችንን የሚያባብሱ ማዳበሪዎች ናቸው።
ራስ እንዲሁምን በስሜት ብቻ መመዘን ቅናትን ይወልዳል። ምክንያቱም መስፈርታችን የስሜታዊ አካሎቻችን መረጃና ያለንበት የዛሬ ብቻ ስለሚሆን የተገደበ ትንሽ ይሆናልና ነው። ይህም የማነስ ሚዛን በሌሎች መበለጥን ስለሚያጎላ “ለእኔ” የሚልን ቅናት ይወልዳል። ወይም በተሳሳተ መልኩ ራሳችንን ከሌሎች አንጻር ስናነጻጽር የተበለጥንና ያነስን እንደሆንን ከተሰማን መቅናታችን አይቀርም። ያለኝ ይበቃኛል ተመስገን በማለት ማመን እስካልጀመረ እና የማይታየውን ረቂቅ የሃሳብ ዓለም በአስተሳሰቡ መረዳት እስካልቻለ ድረስ ሰው መቅናት ማቆም ይከብደዋል።
የመቅናት ጉዳቶች
• ለዘርፈ ብዙ የጤናና ስነልቦናዊ ችግር ይዳርጋል። በተለይ የሚቀና ሰው ለደም ግፊት፣ ለልብ በሽታ፣ በሽታ የመከላከል አቅምን ያሳንሳል፣ ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ከፍተኛ ለሆነ የእንቅልፍ እጦት ያጋልጣል።
• የምንወድ የምናፈቅረውን ያሳጣል። በተለይ ትዳርን ያፈርሳል፣ ጓደኝነትና ቤተሰባዊነትን ይንጣል።
• ሰዎችን ለመበደልና ለወንጀል እንዲሁም ለተንኮልና ሸር ያነሳሳል። ይህም ቅናት ቂምን፣ ቁጣን፣ ጥላቻን፣ በደልን፣ ግፍን ወይም ማግለልን ስለሚያመጣ አንዳንድ ጊዜ እስከ ሞትና መገዳደል ሊያደርስ ይችላል።
• ሀብትን ንብረትን በተለይ ጉልበትን ያባክናል።
• ህብረትን ወይም የቡድን ሥራን ይበጠብጣል።
• ፉክክርና መበላለጥን ወይም ጤናማ ያልሆነ መቀዳደምን ያመጣል።
• ያለንን ሁሉ ነገር ዋጋ ባዶ ወይም በዜሮ ያባዛል። የመንፈሳዊ ህይወት እድገትም ሆነ የህብረት ፀር ነው።
መፍትሔው
1ኛ. መቅናትን ለማቆም ስሜትን በማቆም በምክንያትና በእውቀት መመራት መጀመር።
2ኛ. ከመገመት ይልቅ መጠየቅ ቅናትን ቦታ ለማሳጣት ይረዳል። ማለት ካለው ሁኔታ ተነስተን ባለጉዳዩን ሳንጠይቅ በራሳችን ለመደምደምና ለመፈረጅ ከመነሳት ይልቅ መጠየቅ፣ ከእነሱ በኩል ያለውን ለማወቅና ከራሳቸው አንደበት ለማድመጥ መጣር ተመካሪ ነው።
3ኛ. ራስን መቆጣት መልመድ ከቅናት ያድናል። ማለት የማይገባንን፣ የእኛ ያልሆነውን፣ የማይጠቅመንን ወይም የሌሎችን ውስጣችን በኃይል መፈለግ ሲጀምር እያባበሉ ከማባባስ ይልቅ “ተው…ተይ…” በማለት መገሰጽና ወደ እውነታው በመመለስ እውነታውን እንዲቀበል ማድረግ ጥሩ ብልሐት ነው።
4ኛ. መቅናትን ለማቆም ራስን መሆን ወይም ማስመሰል ማቆም ተመካሪ ነው። ሌሎችን ለመመሰል መመኮር “ከእነሱ ይልቅ እኔ ይገባኛል፤ ምን ያንሰኛል!” ወዘተ የሚልን ግንዛቤ ስለሚፈጥር ቅናትን ያመጣል።
የሚቀኑ ሰዎችን ለመለየት የሚረዱ ብልሃቶች፡-
1ኛ. ከአንገት በላይ የሆነ ሙገሳ እና የውሸት አድናቆት ደጋግመው ያሳያሉ።
2ኛ. ቀናተኛ ሰዎች እጅግ በጣም አስመሳይ ናቸው።
3ኛ. ስኬታቸው ካስገኘው ጥቅም በላይ አግንነው ያወራሉ። ወይንም ያገኘነውን በማቅለል የራሳቸውን ደግሞ ያንቆለባብሳሉ።
4ኛ. ድንገት ሳይታሰብ መጥፎ ወይም አደገኛ ምክር ሹክ ሊሉ ይችላሉ።
5ኛ. በጣም ይፎካከሩናል/ይወዳደራሉ።
6ኛ. አብዝተው ይተቻሉ፣ ያጣጥላሉ ወይም ያንቋሽሻሉ።
7ኛ. የእቅዳችሁ አደናቃፊ ይሆናሉ።
8ኛ. ሰዎች ፊት ያናንቆታል፤ ያለምንም ምክንያት ይጠሉዎታል። ስኬትዎን ማጣጣልና በስኬትዎ ጊዜና ወቅት በፍጹም በአካባቢዎ አይገኙም።
በመሆኑም እነዚህን መነሻ ምክንያቶችና አካሄዶች ከግምት በማስገባት ራስዎን በምክንያታዊነት በመጓዝ በቅናት ወደ ጥፋት ከመግባት መከላከል ያለብዎት ሲሆን፤ በቅናት ስሜት ውስጥ ከሚጓዙ ሰዎችም ራስዎንና ሌሎችን መጠበቅ ይችላሉ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013