ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ናት።ምናልባትም አገሪቱ ብዙ ችግሮችን ካየችባቸው የታሪክ አጋጣሚዎቿ መካከል የአሁኑ አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።ከአሸባሪዎች ጋር የሚደረግ ጦርነት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የውጭ መንግሥታት ጫና፣ የፀጥታ መደፍረስ፣ የምጣኔ ሀብት መዳከምና የኑሮ ውድነት በአንድ ጊዜ ተደራርበውባታል።አገሪቱ ከዚህ ቀደም ገጥመዋት የነበሩ ችግሮችን አልፋ እዚህ ደርሳለችና አሁን የገጠማት ፈታኝ ወቅትም ማለፉ አይቀርም።ችግሮቹን አልፋ ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትራመድ ግን የሕዝብና የመንግሥት ዕርምጃዎች ብስለትና ጥንቃቄ የተሞላባቸው ሊሆኑ ይገባል።
በችግሮቹ መብዛትም ይሁን በሌሎች ምክንያች አገሪቱን ከገጠሟት ፈተናዎች መካከል አንዳንዶቹ ተገቢውን ትኩረት እያገኙ እንዳልሆነ ታዝበናል።ሕዝብና መንግሥት ትኩረታቸው ወደ ፀጥታ ማስከበር ስለሆነ ምንም ዓይነት ዕርምጃ አይወሰድብኝም ብሎ በሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ ዋጋ ጨምሮ ሕዝብን የሚያማርር ነጋዴና ደላላ፤በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ ችላ ብሎ መመሪያውን የሚጥስ ዜጋ፤ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የሕዝብን ደህንነትና የአገርን አንድነት የሚያናጋ አክቲቪስት … እነዚህ ሁሉ የአገሪቱ ችግሮች እንዲራዘሙ የሚያደርጉ የሕዝብ/የአገር ጠላቶች ናቸው።
በመላው ዓለም ከ211 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አዳርሶ ከአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ለሕልፈት የዳረገውና በኢትዮጵያ ደግሞ ከ293 ሺ በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ከአራት ሺ 500 በላይ ሰዎችን የገደለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።በአሁኑ ወቅት ሦስተኛው ዙር የቫይረሱ ስርጭት ለመከሰቱ የሚጠቁሙ አመላካቾች (በጥናት የሚረጋገጡ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) እየታዩ እንደሆነ ተገልጿል።ከዕለታዊ የቫይረሱ ተጠቂዎች ሪፖርት እንደምንመለከተው ቫይረሱ የሚገኝባቸውና ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።የጽኑ ታካሚዎች ቁጥር በእጅጉ ማሻቀቡ ደግሞ ይበልጥ ያስፈራል።የኤካ ኮተቤ ሆስፒታልም ሁሉም የጽኑ ህሙማን መታከሚያ ክፍሎች በቫይረሱ ተጠቂዎች እንደተያዙ ካስታወቀ ሳምንታት ተቆጥረዋል።
ከሁሉም በላይ አስፈሪ የሚሆነው ደግሞ ወቅታዊው የአገሪቱ ሁኔታና የአየር ፀባይ ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሆናቸው ነው።ለሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚደረጉ የድጋፍ ሰልፎችና ተያያዥ ሁነቶች ሰዎች በብዛት የሚሰባሰቡባቸው መድረኮች ስለሆኑ የቫይረሱን ስርጭት እንዳያባብሱት መጠንቀቅ ያስፈልጋል።በተጨማሪም ወቅቱ ሙቀት የማይገኝበት የክረምት ጊዜ ስለሆነ ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፤ በመሆኑም የምናደርገው ጥንቃቄም ይህን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት።
ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት ቫይረሱ በሦስተኛ ዙር ወጀቡ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ያስፈራል።የቫይረሱ ስርጭት በኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ሳለ፣ ስርጭቱን ክፉኛ በሚያባብሱ ተግባራት ላይ መሳተፍና የቫይረሱን መስፋፋት ለመቆጣጠር የወጡ መመሪያዎችን አለማክበርና በትኩረት አለማስፈፀም በሌላው ዓለም ያየነውና የሰማነው አሰቃቂ መከራ በኢትዮጵያም እንዲከሰት ፈቃድ እንደመስጠት የሚቆጠር እጅ አደገኛ ተግባር ነው።
ስለሆነም በሕክምና ባለሙያዎች የሚመከሩትን የመከላከያ ዘዴዎች (በተለይም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን) እንዲሁም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ በመተግበር የአስከፊውን ቫይረስ ስርጭት መቆጣጠርና ሌሎች አገራት ያጋጠማቸውን አስከፊ ቀውስ ላለማስተናገድ መጣር ይገባል! የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው አካላትም ኃላፊነታቸውን ሊወጡና አርዓያ ሊሆኑ ይገባል።የቫይረሱ ስርጭት ችላ ከተባለ አገሪቱን እየፈተኗት ላሉ ሌሎች ችግሮች ጉልበት መስጠት ስለሚሆን ስለሆነ የቫይረሱ ጉዳይ በእጅጉ ሊያሳስበንና ስርጭቱን መቆጣጠር ይገባል።
በየጊዜው ማሻቀብ እንጂ ዝቅ ማለት ያልሆነለት የዋጋ ንረት የሕዝቡን፣ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ኑሮ እጅግ የከበደ እንዲሆን አድርጎታል።ለዋጋ ንረቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ቆይተዋል።የዶላር የምንዛሬ ዋጋና የነዳጅ ዋጋ መጨመር እንዲሁም የምርት ግብዓቶችና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት ተደጋግመው ሲነገሩ የኖሩ የዋጋ ንረቱ ምክንያቶች ናቸው።
እነዚህ ምክንያቶች ተደጋግመው ይገለጹ እንጂ ኑሮ ናላውን ላዞረው ኅብረተሰብ በሚፈለገው ደረጃ መፍትሔ አላስገኙም።‹‹ኑሮውን አልቻልነውም … የዋጋ ንረቱ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል …›› የሚሉና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲደመጡ የቆዩ የኅብረተሰብ ድምፆች ዛሬም እየተስተጋቡ ነው።አንዳንድ ግለሰቦች የዘንድሮው የዋጋ ንረት ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁሉ የተለየ ስለመሆኑ ተናግረዋል።በአንዳንዶቹ ምርቶች ላይ ደግሞ በገበያ የሚታየው የዋጋ ንረት ጠዋትና እና ከሰዓት በኋላ የዋጋ ልዩነት እስከማሳየት የደረሰ ነው።
እጅግ የሚያስገርመው ነገር አገሪቱ ከበቂ በላይ የምታመርታቸው ምርቶች ሳይቀሩ ዋጋቸው ሰማይ መድረሱ ነው።ለአብነት ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከበቂ በላይ ተመርተው ከማሳ የሚያነሳቸው አጥተው ለብክነት እንደሚዳረጉ የምርቶቹ ባለቤቶች ይናገራሉ።በከተሞች ያለው የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ግን ‹‹ጆሮ አይስማ›› የሚያሰኝ ነው።
ከዓመት ዓመት መጨመር እንጂ መቀነስ ለማያሳየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መንስዔዎቹ መሠረታዊ የሆኑ የምጣኔ ሀብት መዋቅሮች አለመስተካከል፣ የምርት አቅርቦት እየቀነሰ መምጣት እንዲሁም የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ እንደሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ተደራርበው የኑሮ ውድነትን ማክበዳቸውንም ይገልጻሉ።
የኑሮ ውድነት የሕዝቡን ጓዳ ፈትሿል።በየቀኑ እየተሰቀለ የሚሄደው የዕቃዎችና የአገልግሎቶች ዋጋ ሕዝቡን በእጅጉ አስጨንቋል።ከላይ እንደተጠቀሰው የኑሮ ውድነቱ ምክንያቶች ዓይነተ ብዙ ቢሆኑም ጉዳዩ ጠንካራ የሆነ መንግሥታዊ ቁርጠኝነትን የሚፈልግ ወሳኝ አጀንዳ ነው።የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በአገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኝ ከቀጠለ አገሪቷን ውስብስብ ወደ ሆነ ችግር ሊመራት ይችላል። ስለሆነም መንግሥት ሰላምን በማስፈን ለኑሮ ውድነቱ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎችን ማበጀት ይጠበቅበታል።ጉዳዩ ትኩረት መነፈጉ ደግሞ ጫናው ከዚህ የባሰ እንዳይሆንም ያሰጋል።
መንግሥት ከመጠን በላይ የሆነ ምርት ያከማቹ አምራቾችንና አስመጪዎችን በመለየት፤ ተፈላጊ የሚባሉትን ምርቶች ለይቶ በብዛት ወደ ገበያው እንዲቀርቡ በማድረግ፤ ምርት ያቆሙና የቀነሱ ፋብሪካዎችን በመደገፍ በብዛት እንዲያመርቱ በማበረታታትና ዋና ዋና ምርቶችን በራሱ ድርጅቶች በኩል አስመጥቶ በማከፋፈል የዋጋ ንረቱን መቀነስ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይመክራሉ።ኅብረተሰቡም ሁልጊዜም ሕገ-ወጥነት ሲከሰት ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሚገባውም ያሳስባሉ።
የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ የሚያደርገው አደገኛው የኢኮኖሚ አሻጥር እንዳይስፋፋ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትም ይገባል።‹‹የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመፍጠር ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ፣ ሰዉ ሠራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት በሚፈጥሩና የህዝቡን የተረጋጋ ኑሮ ለማወክ ብሎም አገር ለማፍረስ በሚሠሩና በሚተባበሩ የህዝብና የአገር ጠላቶች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንወስዳለን። ዛሬ ይህንን ተግባር በበላይነት የሚመራና የሚከታተል በፌዴራል መንግሥት እና በከተማ አስተዳደሩ የተዋቀረ ግብረኃይል አቋቁመናል። በመሆኑም መላው የከተማችን ነዋሪ በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ እየተሳተፉ ያሉ ተቋማትና ግለሰቦችን በመጠቆምና በማጋለጥ እንደከዚህ ቀደሙ አብሮን እንዲሠራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ›› ለሚለው የምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ መልዕክት ጆሮ መስጠት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ አገሪቱ ሌሎች ችግሮች ስላሉባት የኑሮ ውድነቱ ተጨማሪ ችግር እንዳይሆን መሥራት ያስፈልጋል።
የሕግ ማስከበርና የፀጥታ ማስፈን ተግባሩን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል።ለዚህ የሚመጥን አመራር ማደራጀት ደግሞ ወሳኙ ግብዓት ነው።ሕዝቡም አሁን እያደረገ እንዳለው ሁሉ በሚችለው አቅጣጫ የፀጥታ ኃይሉን መደገፍ ይጠበቅበታል።ግጭቱ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በእጅጉ ይዳከማል፤ አሸባሪዎቹም የሚፈጥሯቸው ችግሮች ተራዛሚ ይሆናሉ።
ትኩረት ለሚያሻቸው ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ትኩረት አለመንፈግም አገሪቱ ከችግሮቿ ለመውጣት የምታደርገውን እልህ አስጨራሽ ትግል በድል ለማጠናቀቅ ያግዛታል።በዚህ ረገድ የግብርና ጉዳይ ተጠቃሽ ነው።ወቅቱ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመኸር እርሻ ሥራ የሚከናወንበት ጊዜ ነው።ስለሆነም የእርሻ ሥራው፣ የግብዓት አቅርቦቱና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዕለታዊ ክትትል ይፈልጋሉ።የጎደለውን መሙላት፤የተበላሸውን ማስተካከል ያስፈልጋል።
የግብርናው ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ስለሆነ የዚህ ወሳኝ ዘርፍ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል።እነዚህ ጉዳዮች የማይካዱ ጥሬ ሀቆች ሆነው ሳለ በተግባር የምናየው ግን ሀቆቹን የሚደግፍ አይደለም።የጊዜው ዋነኛ ትኩረት ከግብርናው ይልቅ በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሆነ ታዝበናል።
የዘንድሮው ግብርና ባለፈው ጊዜ በተከሰቱት የአንበጣ መንጋ እና የተፈጥሮ አደጋዎች (በተለይ ጎርፍ) ምክንያት ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው።በአንበጣ መንጋና በጎርፍ ምክንያት ባለፈው ዓመት ምርት የቀነሰባቸውን አካባቢዎች ዘንድሮ የተሻለ ምርታማ በማድረግ ማካካስና ከዘርፉ የሚጠበቀውን አገራዊ የምርት መጠንም ማሳደግ ያስፈልጋል።
የግብርናው ዘርፍ ለአፍታም ቢሆን ትኩረት ሊነፈገው አይገባም።ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግብርና ዘንግተው መኖር አይችሉም።[ቢያንስ ለዓመታት በምኞት ላይ የኖረው ‹‹ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ›› እውን እስከሚሆን ድረስ ግብርናውን መዘንጋት አንችልም]
ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችም ትኩረት ሊነፈጋቸው አይገባም።መሰል አደጋዎች ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስተው በሰው ሕይወትና በንብርት ላይ ብዙ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል።ስለጉዳዮቹ ማስታወስና ስለቅድመ መከላከል ዕርምጃዎች መነጋገር አደጋዎቹ ዘንድሮም ተመሳሳይ ጥፋት እንዳያስከትሉ መፍትሔ ለመፈለግ የሚከናወነው ሥራ የመጀመሪያ ዕርምጃ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ጉዳይም ሳይነሳ መታለፍ የለበትም።ይህ ጉዳይ አገሪቱ ከገጠሟት ችግሮች በቶሎ እንዳትላቀቅ ከማድረግ ባሻገር ተጨማሪ ችግሮች ውስጥ እንድትገባ የሚደርግ አደገኛ መሰናክል ነው።ስለሆነም መንግሥት እውነተኛና ወቅታዊ መረጃን ለሕዝብ ማቅረብ ይገባዋል።ሕዝቡም የራሱ ኃላፊነት አለበት።የመረጃዎቹን ምንጮች ታማኝነት መገምገም፣ ምንጮቹ ከዚህ ቀደም ስለነበራቸው ልምድ/ታሪክ ማጣራት፣ የመረጃዎቹ ዓላማዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰላሰል፣ የታወቀ የመንግሥት አካል ማረጋገጫ እስከሚሰጥ ድረስ መረጃዎቹን ለሌሎች አለማጋራት እንዲሁም አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድ ግፊት ማድረግ ከሕዝቡ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ናቸው።እነዚህ የመፍትሔ ዕርምጃዎች ሐሰተኛ መረጃዎቹ ሊፈጥሩ የሚችሏቸውን አደጋዎች ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይችሉ እንኳ አደጋዎቹን ለመቀነስ ግን ያስችላሉ።
በአጠቃላይ አገሪቱን ያጋጠሟት ችግሮች ተመጣጣኝ ትኩረት ካላገኙና የሕዝብና የመንግሥት ትኩረት በአንዱ ወይም በጥቂቶቹ ጉዳዮች ላይ ብቻ ከተወሰነ ችግሮቹ የበለጠ እየተስፋፉና የአገሪቱን ሕልውናና አንድነት የከፋ አደጋ ላይ የሚጥል ሌላ መከራ ይፈጠራል።ስለሆነም ችግሮቹ ተመጣጣኝ ትኩረት ሊያገኙ ይገባል፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ ችግር የሚመዘንበት ዕይታና የሚበጅለት መፍትሔ በጥንቃቄና በብስለት የተቃኘ መሆን ይጠበቅበታል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013