በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙት 2ሺ89 ትምህርት ቤቶች 1 ሺ 620ዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች መሆናቸው የከተማዋ ትምህርት ቢሮ አሀዛዊ መረጃ ያመላክታል። 460 ዎቹ ደግሞ የመንግስት ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ከመረጃው መረዳት ይቻላል። በ2014 የትምህርት ዘመን የትምህርት አለሙን አዲስ የሚቀላቀሉ ልጆች ስለሚኖሩ አጠቃላይ አህዛዊ ቁጥሩ እንደሚጨምር ይታመናል።
በአዲስ አበባ ትምህርትን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የግሉ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ መያዙን ቁጥሮች ይናገራሉ። በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የሚታየው የሥነ-ምግባር ጉድለት አሳሳቢ መሆኑን ሳንዘነጋ መንግስት ፍፁም ያልተሳካለትን የትምህርት ጥራት በአንፃሩ በማሳየት ረገድ የተሻለ ተሞክሮ እንዳላቸው በየትምህርት ዘመኑ የስምንተኛ፣ የአስረኛ እና የአስራ ሁለተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናዎች ውጤት ትንተና ሪፖርት ያመለክታል።
በመንግስት ትምህርት ቤቶች እየታየ ካለው የትምህርት ጥራት ችግር አኳያ ከፍለው ማስተማር የሚችሉ በርካታ ወላጆች ብቸኛ ምርጫቸው የግል ትምህርት ቤቶች ሆነዋል። ይሁንና ትምህርት ቤቶቹ በየትምህርት ዘመኑ በትምህርት አገልግሎት ክፍያ ላይ በሚያደርጉት ጭማሪ የተነሳ የወላጆች ምሬት ከፍ ብሎ መሰማት ጀምሯል። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መስሪያ ቤት ከዓመት በፊት በሰራው ጥናት፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ 56 በመቶ የሚሆኑት በየዓመቱ በአማካይ ከ20-25 በመቶ በሚሆን መጠን የትምህርት አገልግሎት ክፍያ እንደሚጨምሩ ያመለክታል።
የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የወጣውን መመሪያ ተከትሎ የጭማሪው ደረጃ ወደ 35 በመቶ አድጓል። ይህን ተከትሎ ቁጥራቸው የበዛ ወላጆች “የቀጣይ ዓመት የልጆቼን የትምህርት ቤት ክፍያ እንዴት ልወጣው ነው?” የሚለውን ከባድ ማህበራዊ ጥያቄ ከወርሃዊ የገቢ መጠናቸው ጋር እያነፃፀሩ ክረምቱን በምሬት መግፋት ተለምዷዊ የኑሮ ዘይቤ አድርገውታል።
የዘንድሮው ክራሞትም ከአለት ከጠጠረው የኑሮ ውድነት ጋር ተጋምዶ የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ ተራራን የመግፋት ያህል የከበዳቸው ወላጆች ተበራክተዋል። በዚህ መሰል አታካች የኑሮ ሂደት ውስጥ በየትምህርት ዘመኑ መጀመሪያ ላይ በርከት ያሉ የግል ትምህርት ቤቶች “አስገዳጅ” በሚሏቸው ምክንያቶች (የትምህርት ቁሳቁስ መወደድ፣ ለመምህራን ደመወዝ ጭማሪ፣ የቤት ኪራይ መጨመር) የተለመደውን የትምህርት ቤት ክፍያ በመጨመራቸው የሸገር ወላጆች ችግር “በእንቅርት ላይ . . .” ሆኖባቸዋል።
በአዲሱ ገበያ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ መሰረት ደነቀ ይህን በመሰለው የኢኮኖሚ ፈተና ከወደቁት ወላጆች መካከል አንዷ ናቸው። በመንግስት ስራ የሚተዳደሩት ወ/ሮ መሰረት፤ በቅድስተማሪያም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሁለቱንም ሴት ልጆች እያስተማሩ ይገኛሉ። ባለቤታቸው በህይወት ስለሌሉ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሁለት ልጆች ለብቻቸው እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል። ”ለልጆቼ ጥየው የማልፈው ጥሪት የሌለኝ ሰው በመሆኔ፣ ዕውቀትን አውርሻቸው ልለፍ በሚል ከጓደኞቼ በታች እየኖርኩኝ ልጆቼን በግል ትምህርት ቤት ለማስተማር ተገድጃለሁ” የሚሉት ወ/ሮ መሰረት “መስከረም ወር በመጣ ቁጥር ድህነቴ ይበልጥ ይሰማኛል” ሲሉ በምሬት ይናገራሉ።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብነት ግርማ በተመሳሳይ የችግሩ ሁኔታ መፍትሄ ካልተበጀለት የሕዝብ ምሬትን በማባባስ ሃገርን ወደ ቀውስ የሚያመራ መሆኑን ይናገራሉ። ከአጸደ ህጻናት ጀምሮ እስከ አሁን በግል ትምህርት ቤት እያስተማሩ የሚገኙ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አብነት የችግሩን ስር መስደድ እንደሚከተለው ያብራራሉ። “ሦስት ልጆን የሚያስተምሩት አቶ አብነት ትልቁ የ11ኛ ክፍል፣ መካከለኛው ደግሞ ዘጠነኛ ሲሆን የመጨረሻው ልጅ ደግሞ ሰባተኛ ክፍል ነው።
ልጆቹን የሚያስተምሩት በአንድ ትምህርት ቤት ነው። የትምህርት ቤት ክፍያ በየጊዜው ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ተዳርገናል። ትምህርት ቤቱ የልጆቹን ከክፍል ክፍል መሸጋገር መሰረት አድርጎ በየዓመቱ ከ200 እስከ 350 ብር ጭማሬ ያደርጋል። ዘንድሮ ይባስ ብሎ፤ በእያንዳንዳቸው ላይ 100 ብር በተርም ጭማሬ ተደረገብን። ይሕ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረው እጅግ በጣም አስደንግጦኛል። አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ ደግሞ የተደረገውን ጭማሪ ተቀብሎ ልጆቼን የግል ትምህርት ቤት ማስቀጠል አዳጋች ሆኖብኛል። ልጆቹን ከለመዱበት ትምህርት ቤት ማስወጣቱ የሚኖረው የስነ ልቦና ተጽእኖው ደግሞ ይበልጡኑ እረፍት ነስቶኛል” ሲሉ በግል ትምህርት ቤቶች በየጊዜው የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ አሳሳቢ መሆኑን አጫውተውናል።
ዮዝ አካዳሚ በተሰኘ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማረው ልጃቸው፤ አንደኛ ክፍልን ሲቀላቀል 300 ብር ወርሃዊ ክፍያ ብቻ መክፈላቸውን በማስታወስ ንግግራቸውን የሚጀምሩት ደግሞ ወ/ሮ መቅደስ ዘውዴ፤ ከአራት ዓመት በኋላ ወርሃዊ ክፍያው በሶስት እጥፍ መጨመሩን ያብራራሉ። ለ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ባለፈው ሳምንት ክፍያ ሲፈጽሙ 1500 ብር ወርሃዊ ክፍያ እና የመመዝገቢያ 500 ብር መክፈላቸውንም ይገልጻሉ።
በግል ትምህርት ቤቶች የሚፈጸምብንን ያለ አግባብ ዝርፊያ እና መበዝበዝ መንግስት መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል። “በአብዛኛዎቹ ት/ቤቶች በወርሃዊ ክፍያዎች ወይንም በየትምህርት ተርሙ በሚደረጉ ክፍያዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ለማድረጋቸው የሚሰጧቸው ምክንያቶች” ወቅቱ የዋጋ ንረት፣ በመምህራን ደሞዝና በልዩ ልዩ ወጪዎች ላይ የሚደረገው ክፍያ በመጨመሩ” የሚሉት ናቸው። ይሕ ደግሞ ሁልጊዜ የሚቀርብ ነው። ስለዚህ መንግስት በየአመቱ በተመሳሳይ ምክንያቶች የትምህርት ቤት ክፍያ የሚጨምሩበትን ልማድ፤ ስርአት ማስያዝ ይኖርበታል። በተጨማሪም ራሱን የቻለ አሰራር በመፍጠር እና ስርአት በመዘርጋት ከችግር ሊታደገን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ከመንግስት ባሻገር ደግሞ የትምህርት ቤት ባለቤቶች እና የወላጅ ኮሚቴዎች የችግሩ ምንጭ መሆናቸውን የሚናገሩት ወ/ ሮ እህቴነሽ ሙሉ ናቸው። በሃገሪቱ የነፃ ገበያ መር ኢኮኖሚ ስርዓትን የምታራምድ ቢሆንም፤ የትምህርት ቤት ባለቤቶችም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በየጊዜው ክፍያ ይጨምራሉ። ይሕ ከሞራል የራቀ ስግብግብነት ጫፍ መርገጡ ችግሩ ተወልዶ፣ አድጎ ወደ ህዝብ ዋነኛ የቅሬታ እና ምሬት ምንጭነት ሊያድግ መቻሉን ትናገራለች።
ሌላው ደግሞ የወላጅ ኮሚቴ ሲሆን፤ የትምህርት ቤት ባለንብረቶች እና በተማሪ ወላጆች መካከል ያለው የድርድር አቅም በጣም ደካማ በመሆኑ ክፍያዎች ይንራሉ። በአብዛኛዎቹ ላይ ግን የማይሰራ የወላጅ ተማሪ ህብረትም ያለ ሲሆን፤ በከፊል ደግሞ የኮሚቴዎች ገለልተኛ አለመሆን እና የጥቅም ትስስሮች መኖራቸው ለችግሩ መባባስ ነዳጅ ሆነዋል። ስለዚህ የወላጅ ኮሚቴዎች በትምህርት ቤቱና በወላጅና ተማሪ መካከል ድልድይ ሆነው መልካም ሥራ እንዲከናወን የመደራደር አቅም ከፍ ማድረግና በተጠና መልኩ በማዋቀር መገንባት የሚያስፈልግ መሆኑን ይጠቁማሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ እንደተናገሩት፤ የ2014 ዓ.ም በጀት አመት የትምህርት አገልግሎት ክፍያን በተመለከተ ባለስልጣኑ የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ማስፈጸሚያ ማንዋል በማዘጋጀት የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪ ማህበር፣ የተማሪ ወላጅ ህብረት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተገኙበት ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል።
ማንዋሉን መሠረት በማድረግም ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው መመሪያ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ ወደ ታች የወረደበት መሆኑን አመልክተዋል። በዚህም ማንኛውም ት/ቤት የመመዝገቢያ ክፍያ ሲያስከፍል ከሚከፈለው ወርሐዊ የአገልግሎት ክፍያ 25% ብቻ እንዲሆን መደረጉን ጠቅሰዋል። ለ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ክፍያ ለመጨመር ካስገቡት አንድ ሺ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 162 ትምህርት ቤቶች የመመዝገቢያ ክፍያ ከ25% መብለጥ የለበትም የሚለውን በፕሮፖዛላቸው ውስጥ ባለማስገባታቸው ድጋሚ እንዲያስተካክሉ የተደረገበት መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013