ስራን የጀመሩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ገና በለጋ እድሜያቸው ነው። በትምህርታ ቸው እስከ ማስተርስ ዲግሪ የደረሱ ቢሆንም ትምህርቱን ለቢዝነስ ስራቸው ተጠቀሙበት እንጂ ተቀጥረው አልሰሩበትም። የጉምሩክ አስተላላፊ ፍቃድ ወስደው ስራ ከጀመሩ በቁጥር ጥቂት ከሆኑ ትራንዚተሮች ውስጥም አንዱ ናቸው።
ይህ ስራቸውም ከትንሽ ወደ ትልቅ ደረጃ እያደገ ሄዶ ውስብስብና እጅግ ፈታኝ በሆነው የሎጀስቲክ ንዑስ የስራ ዘርፍ በተለይም በእቃ ጭነትና ማጓጓዝ ስራ ላለፉት ሀያ አንድ አመታት ቆይተዋል።ታዲያ በነዚህ ዓመታት ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልሆነላቸውም።ይልቁንም በባዶ እግር የተሰባበረ ብርጭቆ ረግጦ የመሄድ ያህል በብርቱ ተፈተኑ እንጂ።
ይሁንና ያጋጠማቸውን ውጣውረዶች ሁሉ ተቋቁመውም ዛሬ ላይ በሀገሪቱ በቁጥር አምስት እንኳን ከማይሞሉና በጥልቅ ከተደራጁ ብሎም በተሟላ ቁመና አለም አቀፍ የእቃ አስተላላፊነት ስራን ከሚከውኑ ኤጀንት ባለቤቶች ውስጥ አንዱ ለመሆን በቅተዋል። ኢንተርናሽናል ሙቨርና ወርልድ ካርጎ አሶሲየሽን ጥላ ስር ከሚሰሩ ኤጀንቶች ውስጥም አንዱ ለመሆን ችለዋል። በሃያ አንድ አመት ጉዟቸውም ከራሳቸው አልፈው ዛሬ ላይ ለሌሎችም በሙያቸው ተርፈዋል፤ ለዜጎችም ሰፊ የስራ እድል ፈጥረዋል።
እኚህ በአለም አቀፍ ደረጃ ዝናቸው ከናኘ እቃ አስተላላፊ ኩባንያዎች ተርታ ለመሰለፍ ራእይ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙትና በቀጣይ በሀገሪቱ ትላልቅ የደረቅ ወደብ ግንባታዎች ላይ በስፋት በመሳተፍ ለበርካቶች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ ይዘው እየታተሩ ያሉት የሀገር ልጅ የሰለሞን ዘውዱ ሺፒንግ ኤንድ ፍራይት ፎርዋርዲንግ ኤጀንት ባለቤትና ኤክስኪዩቲቭ ማናጀር አቶ ሰለሞን ዘውዱ ናቸው።
አቶ ሰለሞን ዘውዱ ቤተሰባቸው ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ ቢሆንም እርሳቸውን የወለዷቸው በስራ ምክንያት ወደ አሰበ ተፈሪ አቅንተው ነው።ሆኖም ገና የአስር አመት ልጅ እያሉ ቤተሰባቸው ስራቸውን ቀይረው ወደ አዲስ አበባ በመመለሳቸው እዚሁ ሸገር አድገዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በአፄ ናኦድ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታውን ደግሞ በኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። በመቀጠልም ፍቃድ አውጥተው የጉምሩክና ወደብ አስተላላፊ ስራ እየሰሩ ባላቸው ትርፍ ግዜ ግሬስ በተሰኘ የግል ኮሌጅ ውስጥ በመግባት ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሊደርሺፕ አግኝተዋል።
ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ከጉምሩክና ወደብ አስተላላፊ ስራ ጋር የተዋወቁት አቶ ሰለሞን፤ በግዜው ስራውን ሲጀምሩ ለስራው ማከናወኛ ከጉምሩክ ፍቃድ ከማውጣት በዘለለ የጠየቃቸው የገንዘብ ካፒታል አልነበረም።ስራውንም ቢሆን የጀመሩት ለብቻቸውና አብዛኛውን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉምሩክ አስተላላፊ በኩል በማንሳት ነበር።
ከልጅነታቸው ጀምሮ በውስጣቸው ያለው ፍላጎትና ስብእናቸውም የተገነባው ለብዙዎች መኖር በመሆኑና ተቀጥረው ቢሰሩ የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ እንደማይችሉ ማወቃቸው ደግሞ የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩና ወደዚህ የስራ መስክ እንዲገቡ ይበልጥ ገፋፍቷቸዋል።ይሁንና ነገሮች ቀላልና አልጋ በአልጋ አልሆኑላቸውም፡፡
በ1991 ዓ.ም ስራውን ሲጀምሩ የጉምሩክ አስተላላፊ ንግድ ፍቃድ ወስደው በቁጥር ጥቂት ከነበሩ ትራንዚተሮች ውስጥ አንዱ ሆነው ነው።ስራቸውንም ሲያከናውኑ የነበሩት በአንድ ኮንቴይነር ውስጥ ከሌሎች አምስት እቃ አስተላላፊዎች ጋር ተከራይተው ነበር።ከውጪ ሀገር የሚገቡና ወደ ውጪ ሀገር የሚሄዱ እቃዎችን የሚያከማቹትም በተከራዩት መጋዘኖች ነበር።ምቹ የሆነ የስራ ስፍራና ቢሮዎችም አልነበሯቸውም።
ቀስ በቀስ ግን ስራው በሀገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ከግዜ ወደግዜ እየሰፋ በመምጣቱና ከትንሽ ወደ ትልቅ እያደገ በመሄዱ በኢትዮጵያም እስካሁንም ድረስ የሎጀስቲክ ዘርፉ ከወደብ አጠቃቀምና ከገቢ እቃዎች አኳያ መንግስት ትኩረት ሰጥቶበት እየሰራበት ያለ በመሆኑ እርሳቸውም የድርሻቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት በዚሁ የስራ ዘርፍ ገፉበት።
በሂደትም የሀገርን ምስል የሚቀይሩ ስራዎችን ማከናወን ቀጠሉ። አለም አቀፍ ፍቃዶችን በመውሰድም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችን ተቀብለው ያሉትን አሰራሮች በማሟላትና ህጎችን በመከተል እንዲሁም በጅቡቲ በኩል ያለውን የወደብ ክሊራንስ ጨርሰው አዲስ አበባ ላይ ያሉ ደምቦችንና መመሪያዎችን ተከትለው እቃው የሚመለከተው ግለሰብ ድረስ የማድረስ ስራዎችንም ሰሩ።
ይህም በኢትዮጵያ በእንዲህ አይነቱ መንገድ በአለም አቀፍ ደረጃ የኢንተርናሽናል ሙቨርና ወርልድ ካርጎ አሶሲየሽን ጥላ ስር ስራውን ከሚያከናውኑ በጣት የሚቆጠሩ ኤጀንቶች ውስጥ አንዱ ለመሆን አበቃቸው። በዘርፉ እንደሀገር አቅም ከመፍጠራቸውም በዘለለ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩም መጡ። ስራቸውን እየሰሩ የተማሯቸውን የካውንስሊንግና የሊደርሺፕ ትምህርቶችን በስራቸው ላይ ተግባራዊ በማድረግም በሚገባ ተጠቀሙባቸው፤ ቢዝነሳቸውንም ይበልጥ አሻሻሉ።
በትንንሽ ቢሮዎችና በንግድ ፍቃድ ብቻ ስራውን የጀመረው ሰለሞን ዘውዱ ሺፒንግ ኤንድ ፍራይት ፎርዋርዲንግ ኤጀንት ቀስ በቀስ ራሱን አሳድጎ ከዚህ ቀደም ለስራ የማያመቹ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተከራያቸውን ቢሮዎችንና መጋዘኖችን ትቶ ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ ባስገነባው ባለ ሶስት ፎቅ ህንፃ ላይ አብዛኛዎቹን ስራዎቹን ማከናወን ጀመረ። ይህም ህንፃ በርካታ ቢሮዎችና ማከማቻ ክፍሎች ያቀፈ በመሆኑ ስራውን ይበልጥ አሳለጠ። ከዚህ ውጪ ስራውን የሚያከናውንባቸው ከባድና መለስተኛ ሃያ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ባለቤት ለመሆንም በቃ።
ኩባንያው ከ121 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም በተለያዩ መስኮች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን በራሱ ያስገነባው ህንፃና ተሽከርካሪዎቹ እንዳሉ ሆነው አጠቃላይ ካፒታሉ 100 ሚሊዮን ብር ተጠግቷል። በዚህ ሁሉ ሂደት ታዲያ ኩባንያው ያሳካው ትልቁ ነገር ቢኖር በስድስት መቶ ካሬ ሜትር ሰፊ ቦታ ላይ የራሱን ህንፃ በ35 ሚሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ከመጋዘንና ከቢሮ ኪራይ መላቀቁ ነው።
የራሱ የስራ ተሽከርካሪዎችና ለስራ አጋዥ የሆኑ ማሽነሪዎች ያሉት መሆኑም ስራውን በጥልቀት ለማከናወን ትልቅ አቅም ፈጥሮለታል። ይህም በዚህ ደረጃ ላይ ቆሞ ሌሎች እድሎችን እንዲመለከት አስችሎታል። በአጭር ግዜ ውስጥም በዚሁ የሎጀስቲክ ዘርፍ ያለውን ችግር እንደሀገር፣ እንደተቋምና እንደግለሰብ የመፍታት ደረጃ ላይ ደርሷል።
እንደ አንድ የሎጀስቲክ ዘርፍ የመጓጓዝና የጭነት ስራ ከባድና ውስብስብ ከመሆኑ አንፃርና ትልቅ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ኩባንያው አንድን እቃ ከአንድ ሀገር ለማንሳት ሲዋዋል በአለም አቀፉ የኢንተርናሽናል ሙቨርና ወርልድ ካርጎ አሶሲየሽን ጥላ ስር በመሆን ነው። ይህም በአለም አቀፍ ደረጃ ከየትኛውም ቦታ እቃዎችን አንስቶ፣ የዛን ሀገር የጉምሩክ መመሪያዎችን ጨርሶ፣ ወደብ ገብቶ ኮንቴይነሩ ተጭኖ፤ ጅቡቲ ከደረሰም በኋላ በራሱ ቢሮዎች ሁኔታዎችን አመቻችቶና የጉምሩክ መመሪያዎችን አሟልቶ እቃውን ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርብ አስችሎታል።
በአሁኑ ወቅትም ኩባንያው በዋናነት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና ከሀገር የሚወጡ እቃዎችን ያጓጉዛል። አብዛኛውን ሥራ የሚያከናውነውም በኢትዮጵያ ከሚገኙ የዲፕሎማት ማህበረሰብ በተለይም ከሃምሳ ካላነሱ ኢምባሲዎች ጋር ነው። ከዚህ ውጪ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የግልም ሆኑ የመንግስት ተቋማት ቢሯቸውን ሲቀይሩ እቃዎቻቸውን ሙሉ ሃላፊነት ወስዶ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ያጓጉዛል። በዚህ ዓመትም የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ቢሯቸውን ሲቀይሩ እቃዎቻቸውን አጓጉዟል።
ከእነዚህ ውስጥም የኢትዮጵያ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ ይገኙበታል። አስፈላጊውን የጉምሩክ ቅድመሁኔታዎችን ያሟሉና በኤርፖርትና በደረቅ ወደቦች አካባቢ የሚገኙ እቃዎችንም አንስቶና አጓጉዞ ለሚመለከተው አካል ያስረክባል።
ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ልዩ ልዩ እቃዎችን አሽጎ በመጋዘኖች ውስጥ ያከማቻል። ጭነቶችን /እቃዎችን/ የማስተላለፍ ስራዎችንም ያከናውናል። የደረቅ ካርጎ ትራንስፖርት አገልግሎቶችንም ይሰጣል። ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡም ያደርጋል። የትራንዚት፣ እቃዎችን ገቢና ወጪ የማድረግ ስራዎችንም አያይዞ ይሰራል።
በቀጣይም ኩባንያው በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዝናን ካተረፉና በዚሁ ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ተርታ ለመሰለፍ ራእይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በተለይ ደግሞ መንግስት እያከናወናቸው ባሉት የደረቅ ወደብ ግንባታ በስፋት ገብቶ የመስራት እቅድ ይዟል።በዚሁ የደረቅ ወደብ ግንባታ ሥራም መንግስትን ከማገዝ በዘለለ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ እድል የመፍጠር ውጥንም አለው።
እቃዎችን የማጓጓዝና የጭነት አገልግሎት አንዱ የሎጀስቲክ ንዑስ የስራ ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን ዘርፉ ጠለቅ ያለና አቅም የሚጠይቅ ብሎም በዘርፉ የተማሩ በርካታ የሰው ሀይል የሚጠይቅና በዚህ ላይ ተንተርሶ መስራትን የሚፈልግ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሰለሞን በተለይ በኢትዮጵያ ስራውን ለማከናወን እንቅፋት የሆኑና አሳሪ ህጎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ዘርፉን ከሌሎች የስራ ዘርፎች ጋር ጨፍልቆ የማየትና በጋራ ህግ እንዲወጣለት የማድረግ ችግሮች እንደሚስተዋሉም ያመለክታሉ። ከዚህ አኳያ ለዚህ የስራ ዘርፍ ራሱን የቻለ፣ ጥራት ያለውና ሊያሰራ የሚችል ህግ መውጣት እንደሚገባውም ይጠቁማሉ።
የውጤት መለኪያ መስፈርቱ ብዙ ቢሆንም አቶ ሰለሞን ባለፉት ሀያ አንድ አመታት በዚህ የስራ ዘርፍ በርካቶች እውቀት እንዲኖራቸው በማድረግና የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ውጤታማ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ በዚህ ውስብስብና ውጣውረድ በበዛው የስራ መስክ አብዛኛዎቹን ፈተናዎች ተቋቁመው እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ለእርሳቸው ትልቅ ውጤት መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ ውጤት የመጣው ግን እንዲህ በቀላሉ እንዳልሆነና መስዋዕትነት ጭምር ተከፍሎበት እንደሆነ ይጠቁማሉ።
‹‹በአሁኑ ግዜ የአብዛኛዎቹ ወጣቶች ፍላጎት ተቀጥሮ ሰርቶ፣ ታሽቶ፣ እውቀትና ልምድ ይዞ ወደራስ ቢዝነስ የመግባት ፍላጎት ሳይሆን በአቋራጭ መንገድ የመክበር ነው›› የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ወጣቶች የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስና ውጤት ማምጣት ስራን መውደድ፣ ተቀጥሮ በመስራት ራስን መፈተሽ፣ ልምድ መያዝ፣ ትእግስትና በፈተናዎች ውስጥ ማለፍ የግድ እንደሚላቸው ይመክራሉ።
እኛም አቶ ሰለሞን በዚህ ፈታኝና ውስብስብ በሆነው የሎጀስቲክ ንዑስ የስራ ዘርፍ በተለይም በእቃ አስተላላፊነት ስራ ዘርፍ ትልቅ ጥረት አድርገው በዋናነት ደግሞ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠርና በዚሁ የስራ ዘርፍ የሀገሪቱን በጎ ገፅታ በመገንባት ረገድ እያደረጉ ያሉትን ትልቅ አስተዋፅኦ በማድነቅ ብዙዎች ከእርሳቸው ተምረው ዘርፉን እንደሚያሳድጉት እንተማመናለን። ሰላም
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013