“አፈር ይዞ ምድሩ አረንጓዴ፣ ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?” ሲል የክቡር ዶክተር ቴዎድሮስ ካሳሁን በመድረክ ስሙ “ቴዲ አፍሮ” አቅንቅኗል። ተወዳጁ የሙዚቃ ንጉስ “ጥቁር ሰው በሚለው” አልበሙ ላይ ባካተተው በዚህ ዘፈን ያነሳው ጥያቄ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በልካችን የተሰፋና ሁሌም ህሊናችንን እየደቆሰ የሚሞግት መልእክት የሚያስተላለፍ ነው።
ሌላኛውንም “ለምለሚቷ አገሬ” የሚለውን ተወዳጅ ዜማ አሁንም ድረስ እየኮመኮምን ጥቁር ወርቅ ላይ ተቀምጠን ይስራ መንፈሳችን ከመሬቱ ጋር ተዋዶ እያለ በመሬቱ ሳንሰራበት የቀረበት ምክንያት ለምን እንደሆነ ከመለኮታዊ ሃይል ምላሽ ሳይፈልግ የሚቀር አይመስልም? እንደ ሰውማ ሲጠየቅ ኖሯል፤ መሬት ላይ የሚታይ ምላሽ ግን የለም።
በእዚህ ጉዳይ ብዙዎቻችን የምንብሰከሰክበት ቢሆንም፣ በአንድ በኩል ለዘመናት በስናፍና በእርዳታ ጠባቂነት ውስጥ ተዘፍቀን ኖረናል፤ አሁንም ይሄው ቀጥሏል፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘረኝነትና ግጭት ምርጫ ተደርጎ ተወስዷል። የዘረኝነትና ግጭት ነጋዴዎች ህገወጥ ተግባር የልማት ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል። ሀብት በዛረፋና በህገ ወጥ መንገድ ማግኘት ተለምዷል።
በዚህ የተነሳም እምቅ አቅማችንን ማልማት በትኩረት ሊሰራበት አልተቻለም፤ የመሻሻልና መለወጥ ጉዳይ ከወሬ አለፈ ሲባል ይቆማል፤ ይሰናከላል፤ ብዙዎች አሁንም ከተለመደው ከልማት ዘይቤ ያልወጡ በመሆናቸው ድህነቱን መቀነስ አልተቻለም፤ በዚህ ላይ ሙስናው አያድርስ ነው። በተሳሳተ መንገድ መጓዝ እየበዛ ነው።
አሁን ትልቅ ችግር እየሆነ ያለው ጎራ ለይቶ መናከስ ሆኗል። አርሶ አደሩ ግብርናውን አዘምኖ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከድህነት እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ ማሳው ላይ መትረየስ ጠምዶ ፣ ታንክ እያንከባለሉ ሰው መጨረስን መሰረተ ልማት ማውደምን ምርጫቸው ያደረጉ አካላትን እየተመለከተን ነው።
ለዘመናት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የፈተነው የሃያላን መንግስታት ሴራ ነው። እነዚህ መንግስታት ራሳችንን ችለን እንዳንቀሳቀስ መስራታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፤ ጎራ ለይተን እንድንናከስ እያረጉ ያሉትም እነሱ ናቸው፤ ባንዳዎችን ፈጥረውብናል። አንዳንዶችን በእርዳታ፣ በመደለያና በመሳሰሉት በመጥለፍ እያፋሱ፣ እያስታጠቁ ለእኩይ አላማቸው ያሰልፏቸዋል። እነዚህ ባንዳዎች የእናታቸውን ጡት ይነክሳሉ፤ የሐገራቸውን ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት ምንም አያቅማሙም። የእነዚህ ሀይሎች ሴራ ለምን ይሆን ሊገባን ያልቻለው? እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ ለምን እምቅ ሀብታችንን አውጥተን አንጠቀምም? ስንፍና ለምን ወረሰን ? ጥላቻና ምቀኝነት ለምን ይጫወትብናል?
ባለቅኔዎቻችንና ሙዚቃኞቻችን “እምዬ ኢትዮጵያ ጋራው ሸንተረርሽ አውድማሽ ማማሩ” እያሉ የተሰጠንን ፀጋ ሊያሳዩን ቢጥሩም፣ አውድማውም፣ ጋራ ሸንተረሩም የውድ ህይወታችንን መጥፊያ እየተደረገ ያለው ለምን ይሆን? ነጥቆ መብላት፣ የሴረኞች የጋሪ ፈረስ በመሆን አገር ለማፍረስ ይህን ያህል በጥፋት ተግባር ውስጥ የተገባውስ ለምድንነው ?
የመጣንባቸውን መንገዶች ሁሉ ሳስታውስ አንድ ጥበበኛ አባት ልጆቻቸው ከስንፍናና ከብልሃት ወጥተው ጠንካራ ሰራተኞች እንዲሆኑ ያደረጉበት ታሪክ ይታወሰኛል። እኛም አባቶቻችንን፣ ጥበበኛ በለቅኔዎቻችንን በዚህ ታሪክ መንገድ ተረድተን፣ ከጥላቻ፣ጎራ ለይተን ከመባላት ወጥተን የተፈጥሮ ሀብታችንን ለልማት አውለን የምናድግ የምንሰለጥንበት ዘመን ይናፍቀኛል። እስቲ የእኚህን ብልሃተኛ አባት ታሪክ ላጋራችሁ።
ባለታሪኩ አራት ወንድ ልጆች አሏቸው። አራቱም ልጆቻቸው ግን በጣም ሰነፎች ናቸው። አባትየው እድሜያቸው በመግፋቱና በህመም ምክንያት አልጋ ላይ ውለዋል። እያደር ግን ጤናቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ይህቺን ምድር ሊሰናበቷት መቃረባቸውን ሲያስቡ የልጆቻቸውም ጉዳይ በእጅጉ ያስጨንቃቸዋል፤ እጣ ፈንታቸው እረፍት እየነሳቸው ይመጣል።
ልጆቻቸው ስራ አይወዱም፤ ሰርቶ ከማግኘት ይልቅ በሆነ አጋጣሚ እንደሚያልፍላቸው የሚያምኑ ናቸው። አዛውንቱ አባታቸው ግን ይህን በፍፁም አይቀበሉትም። ጤናቸውም እያሳሰባቸው መጥቶ በልጆቹ እጣ ፈንታ ላይ ከራሳቸው ከልጆቹ ጋር ለመነጋገር ይወስናሉ። ሀሳቡንም ለአራቱም አማከሯቸው።
ልጆቹ ግን የአባታቸውን ሀሳብ ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበሩም። በመጨረሻም አባትዮው ልጆቹ የሥራን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ለማድረግ አንድ ብልሃት ሊያጫውቷቸው ወሰኑ። በድጋሚ ለአንድ ትልቅ ቁምነገር እንደሚፈልጓቸው በመንገር ሁሉንም ልጆቻቸውን ጠርተው አጠገባቸው እንዲቀመጡ አደረጉ። ወዲያውም የወርቅ ሳንቲሞች እና ውድ ዕንቁዎች የያዘውን የግምጃ ሣጥን እንዳላቸው ነገሯቸው። በሳጥኑ ውስጥ ያለውን ሀብት ለአራቱም እኩል ለማካፈል መወሰናቸውን ገለጹላቸው። ወጣቶቹ በአባታቸው ውሳኔ ተደሰቱ፤ ወዲያውኑም አባታቸው ሳጥኑን የት እንዳስቀመጡት ጠየቁ።
አዛውንቱም “ሀብቱን የደበቅኩበትን ቦታ በትክክል ማስታወስ አልቻልኩም። በግቢያችን ባለው ሰፊ መሬት የሆነ ቦታ ውስጥ ግን ቀብሬዋለሁ። አውነቴን የምላችሁ ሳጥኑን የደበቅኩበት ቦታ እርግጠኛ አይደለሁም” በማለት መለሱላቸው።
ሰነፎቹ ልጆች በአባታቸው ውሳኔ ቢደሰቱም ሀብቱ የተደበቀበትን ቦታ በመርሳታቸው አዘኑ። አባትዬው ከጥቂት ቀናት በኋላ ህመሙ ጠንቶባቸው ብዙም ሳይቆዩ አረፉ። ልጆቹ ከለቅሶ እንደተነሱም የግምጃ ሣጥኑን ለማግኘት መሬቱን ለመቆፈር ወሰኑ። መሬታቸውን በጣም ቢቆፍሩትም፣ ምንም ዓይነት የግምጃ ሣጥን ማግኘት ግን ሳይችሉ ቀሩ።
አሁንም መቆፈራቸውን ቀጠሉ፤ ከተቆፈረው ስፍራ አንድ ለየት ያለ ቦታ ተመለከቱ። ያን ስፍራም በጥልቀት ለመቆፈር ወስነው ቁፋሮውን ጀመሩ። የተባለው ሀብት በዚያ ቦታ እንደ ተቀበረ አምነው ነበር። ቁፋሮውን ሲጨርሱ ግን ከውሃ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር ማግኘት አልቻሉም። በሁኔታው በእጅጉ ተበሳጩ፤ አባታቸው የተናገሩትን ውሸት ብለውም ማዘን ጀመሩ።
በዚያው ቅፅበት ግን አንድ የመንደሩ ነዋሪ በአካባቢው ሲያልፍ ይመለከታቸዋል፤ እያደረጉ ባሉበት ነገር ይገረማል፤ ይቀርባቸውናም ለረጅም ጊዜ ሳይቆፈር የቆየው ቦታ በሙሉ በሚገርም ሁኔታ ተቆፍሮ በማየቱ መደሰቱን ነገራቸው። ከሁሉም የበለጠ በቁፋሮው ወቅት ያገኙት ምንጭ ውሃ ብዙ እንደሚጠቅማቸው ይገልጽላቸዋል፤ ትልቅ እድል እንደገጠማቸውም ያመለክታቸዋል። መሬቱ እና ምንጩ ለእርሻ ስራ ምቹ መሆኑንም አስረዳቸው። አትክልቶችንና የፍራፍሬ ችግኞች ቢተክሉ፣ ሰብል ቢያለሙ፣ ጥሩ ገቢ ሊያገኙ አንደሚችሉም ጠቆማቸው።
ልጆቹ ወዲያው የተሰጣቸውን ምክር ስራ ላይ ማዋል ይጀምራሉ። የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ተከሉ፤ ሁሉንም ውሃ እያጣጡ እየኮተኮቱ መንከባከቡን ቀጠሉበት። በጥቂት ጊዜያት ውስጥም አካባቢው አረንጓዴ ለበሰ፤ ስፍራው የአትክልት ስፍራ መሆን ቻለ። አትክልቶች ደርሰው መመገብና መሸጥ ጀመሩ።
በልማቱ ጥሩ ገንዘብ እያገኙ መጡ። ቀስ በቀስም በአባታቸው “የግምጃ ሣጥን”’ ተብሎ የተላለፈላቸው ውርስ ይህ ትልቅ ሀብት መሆኑን ተገነዘቡ። ስንፍናቸውን አሸንፈው ጠንክረው መስራታቸውን ቀጠሉ፣ ብዙ ገንዘብ እያገኙ በደስታ መኖርም ጀመሩ። ጠንክሮ መሥራት ሁል ጊዜ ዋጋ እንደሚከፍልም ከአባታቸው ተገነዘቡ።
ከዚህ ታሪክ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ መማር ይኖርብናል። ከስንፍና፣ ከመከፋፈልና መነቋቆር ከመጫረስ ይልቅ ተፈጥሮ የለገሰችንን ውብ አገር አልምተን ስለመለወጥና ማደግ እንድናስብ ይረዳናል። በእጃችን ያለውን ወርቅ እንደ መዳብ እየቆጠርነው መሆኑን እንድናስተውል ይጠቅመናል። ይህን ማወቅ ከቻልን “አፈር ይዞ ምድሩ አረንጓዴ ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?” የሚለውን የባለቅኔውን ዜማ ለመፍታት አይቸግረንም። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013