አትሌት ስለሺ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆን እንዲያገለግል ተመርጧል። ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 28ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤም የቀድሞዋን ጀግና አትሌት መሰረት ደፋርን ጨምሮ ሌሎች ፌዴሬሽኑን ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚመሩ አዳዲስ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በመምረጥ ትናንት ተጠናቋል።
ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ከስድስት ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የቀረቡ እጩዎች በምርጫው የተፎካከሩ ሲሆን፤ ከኦሮሚያ ክልል የተወከለው አትሌት ስለሺ ስህን ከ26 ድምፅ 11ዱን በማግኘት ማሸነፍ ችሏል። በቀጣዮቹ አራት ዓመታትም የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚመራ ይሆናል።
የቀድሞ የፌዴራል ማረሚያ ቤት አትሌት ስለሺ በአቴንስ እና ቤጂንግ ኦሊምፒኮች የ10ሺ ሜትር ውድድር የብር ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ ማስመዝገቡ የሚታወስ ሲሆን፤ በፓሪስ፣ ሄልሲንኪ እና ኦሳካ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎችም 3 የብር እና አንድ የነሀስ ሜዳሊያ ማጥለቁ ይታወቃል። በተጨማሪም በመካከለኛ ርቀት 3 ሺህ ሜትር፣ በረጅም ርቀት 5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር፤ በ10፣ 15 እና 20 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎች፤ በሀገር አቋራጭ፤ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች ከ15 ዓመታት በላይ በመወዳደር ስኬታማ ነበር።
ስለሺ ስህን የአትሌትነት ጉዞው ካበቃም በኋላም የቀድሞ ክለቡን እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበርን በፕሬዚዳንትነት ማገልገል ችሏል። አትሌቱ ካለው የረጀም ጊዜ የአትሌቲክስ ውድድር ልምድ እና ግለሰባዊ ሥነ-ምግባር አንፃር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያጋጠመውን ስብራት በመጠገን ወደ ቀድሞው ገናናነቱ ይመልሰዋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔው ፍፃሜ ላይ ባለፉት ስምንት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ያገለገለችው ተሰናባቿ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ አትሌቲክሱን ያገለገሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትም የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ዕውቅናውንም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ በመድረኩ ተገኝተው አበርክተዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ቢሮ ከከተማው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች አንጋፋዋን አትሌት በስፖርቱ ላበረከተችው አስተዋጽኦ የምስጋና ስጦታ አበርክተዋል።
ኢንጂነር ጌቱ ገረመው፣ ቢንያም ምሩጽ፣ አድማሱ ሳጂ፣ ዶክተር ትዕዛዙ ሞሴ፣ አትሌት መሠረት ደፋር፣ ሳራ ሀሰን፣ አበባ ዮሴፍ እና ዶክተር ኢፍረህ መሀመድ ተመርጠዋል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላላ ጉባኤው ከቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ አባላቱን ጨምሮ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ረዳት ኮሚሽነር ማርቆስ ገነቴ፣ ፎዚያ ሀሰን እና አትሌት መሠለች መልካሙን የክብር አባል በማድረግ አካቷል።
በፕሬዚዳንትነት ለመጪዎቹ አራት ዓመታት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ እንዲመራ የተመረጠው አትሌት ስለሺ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ለመምራት እድሉን ስላገኘሁ አመሰግናለሁ። ከሥራ አስፈጻሚውና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለስፖርቱ እድገት እንሠራለን ሲልም ቃል ገብቷል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም