የፍርድቤቱ ችሎት በሰአቱ ተሰይሟል። ዳኞች፣ ዓቃቤ ህግና ጠበቆች ስፍራቸውን ይዘዋል።ስማቸው ሲጠራ በየተራ የሚመጡ፣ በምስክር ሳጥን ውስጥ እየቆሙ እማኝነታቸውን ይሰጣሉ።ተከሳሹ ተጠርጣሪ በሆነበት የወንጀል ጉዳይ ላይ የሚሰማውን ክስ በጥንቃቄ ያዳምጣል፡፡
የመጀመሪያው የዓቃቤ ህግ ምስክር ስሙ ተጠራ። ሰውዬው ከመቀመጫው ተነስቶ ወደ ምስክር ሳጥኑ ቀረበ። ዓቃቤ ህጉ ካባቸውን እያስተካከሉ ወደምስክሩ አተኮሩ። በቅድሚያ ስሙን ጠየቁት። ፈጠን ብሎ አስከ አባቱ ነገራቸው፤ ዓቃቤ ህጉ ተረጋግተው ወደምስክሩ እያዩ በዚህ ስፍራ ለምን እንደመጣ ጠየቁ፡፡
ሰውዬው በአትኩሮት ወደእሳቸው እያየ ፍርድቤት የመጣው ለምስክርነት መሆኑን ተናገረ።ዓቃቤህጉ በጥያቄያቸው ቀጠሉ፡፡
በተጠቀሰው ዕለት ማን ነው የሞተው? አንተስ ምን አየህ ?
ምስክሩ ለመረጋጋት ሞከረ።ከአፍታ ዝምታ በኋላም ‹‹ እ. እ .እ… የሞተው አበበ ደስታው፣ የሚባለው ነው ። አዎ ! ደስታ ፣ ደስታው … እየተጣደፈ ‹‹ደስታና ደስታው›› ሲል ሁለት የአባት ስሞችን አጣምሮ መለሰ፡፡
ዓቃቤ ህጉ ወደእሱ እያስተዋሉ ‹‹በትክክል የምታውቀው ከሆነ የአባቱን ሰም ለይተህ ተናገር።አልያም አላውቅም ብለህ መልስ›› አሉት።ምስክሩ እንደገና ለመረጋጋት ሞከረ፡፡ጥቂት አሰብ አድርጎም ‹‹ እ. እ. እ. ሲባል የሰማሁት እንደዛ ነው›› ሲል ሃሳቡን ደመደመ፡፤
ዓቃቤህጉ ወደሚቀጥለው ጥያቄ አመሩ፡፡
‹‹ግድያው መቼና የት ተፈጸመ›› ?
ምስክሩ ከቆመበት ስፍራ እንዳለ በሃሳብ ነጎደ።አእምሮውን ወደፊት ወደኋላ እያመላለሰም ቀኑንና በዕለቱ የሆነውን ድርጊት ሊያብራራ ተዘጋጀ።
‹‹እለቱ ግንቦት 9 ቀን 2004 ዓ.ም ነበር ።የዚያን ቀን ምሽት ስድስት ሰአት ላይ የእግር ኳስ ጨዋታ ይታይ ነበር።ጨዋታውን ለማየት እኔና ጓደኞቼ አዲስ ከተማ መናኸሪያ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ አምሽተናል።ጨዋታው ካለቀ በኋላ ደስታና እኔ ማለትም ሟች ጓደኛዬ በአካባቢው ሻይ ወደሚሸጥበት አንድ ስፍራ አመራን።ከእኛ ጋር የደስታ ባለቤት አብራን ነበረች።በባልና ሚስቱ መሀል ቅሬታ ስላደረ ሁለቱን ለማስታረቅ ብዙ ስመክርና ሳስማማ ነበር፡፡
ከእናንተ ሌላ ማን አብሯችሁ አመሸ ? ዓቃቤ ህጉ ጥያቄ ሰነዘሩ።ምስክሩ ወደ ተከሳሹ ሳጥን ደጋግሞ እየጠቆመ ‹‹እሱ ፣ እሱም ነበር እሱ›› አለ።ዓቃቤ ህጉ ዓይናቸውን ከምስክሩ ሳያነሱ ‹‹እሱ ማለት ማነው? አስቲ ስሙን ግለጽልኝ›› አሉት።ምስክሩ ፈጠን ብሎ ‹‹መሀመድ ሰይድ›› ሲል ተናገረ።ዓቃቤህጉ ሆኗል ያለውን ሁሉ አንድ በአንድ እንዲናገር እድል ሰጡት፡፡
‹‹መሀመድ የዛን ቀን ምሽት ወንዴ ከሚባል ጓደኛውና ከአንዲት ሴት ጋር ነበር።እኛ ከነበርንበት ትይዩ ተቀምጦ መሳደብ ጀመረ።ሁላችንም ስድቡን እየሰማን ዝም አልነው።ሲደጋገምብን ትኩረታችን ተሳበ።እኔም ስድቡ ከቃላት አያልፍም በሚል ወደ እርቀ ጉዳዩ ለመመለስ ሞከርኩኝ፡፡
ጥቂት ቆይቶ መሀመድ እኔን የሚመለከት ስድብ ሲጥል ደስታ ከጆሮው ደረሰ። መታገስ አልቻለም።ከወንበሩ ተነስቶ ለምን ትሰድበዋለህ ? ምክንያትህ ምንድነው ? ሲል ጮኸበት።እኔ አሁንም ስለስድቡ አልጨነቀኝም።ሁለቱ እንዳይካረሩ መሀል ገብቼ ለማስማማት ሞከርኩ፡፡
ደስታና መሀመድ አንገት ለአንገት ተያያዙ።እኔን ጨምሮ ሌሎች ሊገላግሉ መሀል ገቡ።ሁለቱም ለጥቃት እጆቻቸውን ሰነዘሩ።በማናቸውም ላይ ጉዳት አልደረሰም።ከግልግሉ በኋላ መሀመድና ጓደኛው ስፍራውን ለቀው ሄዱ።ጓደኝዬው መሀመድን ደጋግሞ ወቀሰ፣ እኛም ደስታን እየተቆጣን ቆየን ፡፡
እነሱ ከሄዱ በኋላ ወደ ባልና ሚስቱ እርቅ ገባሁ።ሁለቱን በየተራ እያናገርኩ፣ ሰላም እንዲያወርዱ ፣ አብረው እንዲቀጥሉ ተቆጣሁ፣ መካከርኩ።ጥቂት ቆይቶ የመሀመድ ጓደኛ ወንዴ እኛ ወዳለንበት ተመልሶ መጣ።እሱን ተከትሎም መሀመድ ከኋላው ደረሰ፡፡
መሀመድ እኛ ዘንድ ሲቀርብ ቀጥታ ወደ ደስታ አመራ። ሁለቱም እንደገና ጠብ ጀመሩና ተያያዙ ።እኛ ሻይ የሚፈላበት ምድጃ አጠገብ እንደተቀመጥን ነበር። ጠቡ ሲጋጋል የተቀጣጠለው የከሰል እሳት ተገልብጦ በላዩ የነበረው ሻይ ተደፋ።እንደገና ለግልግል ተነሳን። ጓደኝዬው አብሮት የነበረ ጓደኛችንን እጅ ይዞ ለማስቀረት ሞከረ።ይህን ያየው ደስታ ተበሳጨ።‹‹አንተን አያገባህም›› ሲልም ጮኸ ።በዚህ መሀል መሀመድ ደብቆት የቆየውን ጩቤ አውጥቶ ሰነዘረ። ጩቤው በደስታ የግራ ጎን ላይ አረፈ፡፡
ዓቃቤ ህጉ የምስክሩን ቃል አድምጠው ተከታዩን ታሪክ እንዲነግራቸው ጠየቁት። ምስክሩ የዛን ቀን ምሽት የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ እያስታወሰ መናገሩን ቀጠለ፡፡
‹‹ጩቤውን በደስታ የግራ ጎን ላይ የሰካው መሀመድ ዞር ብሎ ቁስለኛውን ተመለከተው። ደስታ ወደ እኔ እየያ ‹‹እንዳትለቀው፣ ወግቶኛል! ወግቶኛል!›› እያለ ይጮህ ነበር።ይህኔ መሀመድ የእጁን ጩቤ አጥብቆ ከስፍራው ሮጠ።ልይዘው ከኋላው ተከተልኩት።ስሜን ጠርቶ አያገባህም ፣ ዞር በል ፣ እያለ ወደፊት ፈጠነ። ደስታ ቁስሉን ደግፎ፣ ደሙን እያዘራ ጥቂት ለመሮጥ ሞከረ። አልቻለም። በቁሙ ወደቀ፡፡
መሀመድን እየተከተልኩ በጨለማው ፈጠንኩ። ላገኘው አልቻልኩም።ተመልሼ ሻይ ቤቱ ስደርሰ ደስታ ሆስፒታል መወሰዱን ሰማሁ። የሄደበት ሆስፒታል በሩጫ ገሰገስኩ ።ከስፍራው ስደርስ ህይወቱ እንዳለፈ ሰማሁ።
በተከሳሽ ሳጥን ውስጥ የቆመው መሀመድ ለምስክሩ መስቀለኛ ጥያቄዎችን አቀረበ፤ የዓቃቤህግ ምስክሩ በዕለቱ ያየውንና የሆነውን እውነት በማስረጃ እያጣቀሰ መለሰለት።ምስክሩ ቆይታውን አጠናቆ ችሎቱን ለቀቀ፡፡
ዓቃቤህጉ ሁለተኛውን ምስክር አስጠርተው ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ።በምስክር ሳጥን ውስጥ የቆመው ወጣት በስፍራው ሻይ እየሸጠ የሚተዳደር ነው።የዛን ቀን ምሽት እሱ በሚሰራበት ቦታ ስለተፈጸመው ወንጀል በዝርዝር ተናገረ።ምሽቱን ለሽያጭ ያዘጋጀው ሻይና ዕንቁላል እንደተደፋበት ገልጾ ተጠርጣሪው ሟችን በጩቤ ሲወጋ በዓይኑ ስለማየቱ መሰከረ።
ዓቃቤህጉ በተከሳሽ ሳጥን ውስጥ ያለውን መሀመድ መስቀለኛ ጥያቄ ይኖረው እንደሆን ጠየቁ። ተከሳሹ በሁለተኛው ምስክር ላይ ምንም ጥያቄ እንደሌለው ተናገረ።ዓቃቤህግ የምስክሮች ቃል ተገልብጦ ከክስ መዝገቡ ጋር እንዲያያዝ ትዕዛዝ ሰጡ። የዕለቱ ችሎት ከመጠናቀቁ በፊት ዳኛው ቀጣዩን የቀጠሮ ቀን አሳውቀው መዶሻቸውን አነሱ፡፡
መሀመድ ሁሴን
መሀመድ ሁሴን በ1982 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ። ያደገበት ሰፈር ኮልፌ ልኳንዳ ከሚባል አካባቢ ነው።ዕድሜው ከፍ እንዳለ ወላጆቹ ትምህርት ቤት አስገቡት፤ ከእኩዮቹ ጋር ቀለም እየቆጠረ ወደ ቤት ሲመለስ የነገ ተስፋን ይዞ ነበር፡፡
የመሀመድ ቤተሰቦች በኑሮ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ አይደሉም። ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ገቢያቸው ከልጆች ቀለብና ከዕለት ወጪ አልፎ አያውቅም።መሀመድ በችግር መሀል ሆኖ አስከ ስድስተኛ ክፍል ተማረ። ወደቀጣዩ ደረጃ ለማለፍ ግን የቤቱ ችግር አላራመደውም። ትምህርቱን ሊያቋርጥ ራሱን ሊያስተዳድር ግድ አለው።
መሀመድ ራሱንና ቤተሰቦቹን ለመርዳት ደብተሩን ከጣለ በኋላ በአውቶቡስ ተራ ተገኘ። ስፍራውን መዋያ ሲያደርግ የሸክም ስራ መተዳደሪያው ሆነ ። ውሎ ሲያድር ከቤት ወጥቶ ጎጃም በረንዳ አካባቢ በቀን ሂሳብ የአልጋ እየከፈለ ማደር ጀመረ። ይህ አጋጣሚ ከብዙዎች አገናኘው።የውሎ አዳሩ ሁኔታ ግን ከፖሊሶች ዓይን አላዳነውም።በሌብነት መጠርጠሩ፣ ለክስ አቀረበው። ለቀናት ከጣቢያ የቆየው መሀመድ ጉዳዩ ሲጣራ ተመክሮ በነጻ ተሰናበተ፡፡
የስራ ባህረይውና የኑሮው ሁኔታ አንዳንዴ ከሰዎች ያጋጨዋል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ጠቡን እንዳመጣጡ ለመመለስ ይሞክራል፤ ባስ ካለም በድበድብና በጭቅጭቅ ማሳለፍ ልምዱ ነው። መሀመድ አዲስ ከተማ አካባቢ ከሚገኙ የመንገድ ዳር ሻይ ቤቶች ጎራ ማለትን ለምዷል። ከጓደኞቹ ጋር ሲዝናና ባመሸ ጊዜ ሻይ ቤቶቹን መጎብኘት ፣ አመሻሽቶ መግባት ደሰ ይለዋል።
መሀመድ መጠጥ ቤት ሲያመሽ ከባልንጀሮቹ ጋር ነው። እነሱ አንዳች ነገር ቢገጥመው መከታ ይሆኑታል። ከሌሎች ቢጋጭ ለመደረብ ፣ጠቡ ቢብስ ለመገልገል ቅርብ ናቸው። ይህ ሁኔታ መጠጥ በቀመሱ ጊዜ ይገለጣል፡፡
ግንቦት 9 ቀን 2004 ዓ.ም
በዚህ ቀን ከስራ መልስ መሀመድና ጓደኞቹ ተገናኝተዋል፤ እንደለመዱት ከአንድ ቤት ተቀምጠው ቢራ እየጠጡ ነው፤ ምሸቱን መዝናናት ሲያምራቸው አንድ ቦታ ብቻ መቀመጥ አይፈልጉም ፤ የገቡበትን እየለቀቁ፣ ካሻቸው ማዳረስ ልምዳቸው ነው። የዛን ቀን ምሽቱን ካጋመሱበት ሆቴል ጨርሰው እየወጡ ነበር። መንገድ ሲጀምሩ ሌላ ቤት የመቀየር ሃሳብ ተነሳ። በሃሳቡ ሁሉም ተስማምተው ወደተመረጠው ሆቴል መንገድ ጀመሩ። ሆቴሉ ከመድረሳቸው በፊት ከመሀመድ ጋር ወንዴ የተባለው ጓደኛው ብቻ ቀረ፡፡
ከወንዴ ጋር ወዳሰቡት ሆቴል መቃረብ ሲጀምሩ እነደስታን ከሻይቤቱ ተቀምጠው አዩዋቸው። መሀመድና ጓደኛው የሆቴል መሄዱን ሃሳብ ሰርዘው ወደ ሻይ ቤቱ በረንዳ አመሩ።ውስጥ ሲገቡ ደስታ ጓደኛውና አንዲት ሴት ጨዋታ ይዘው ነበር፡፡
መሀመድ ሞቅታ ውስጥ ነው። ሶስቱን ሰዎች እንዳያቸው ነገር ነገር አለው።ጥቂት ቆይቶም ስድብ ጀመረ።ሁኔታውን ያዩት ሶስቱ ለአንድ አፍታ ደንገጥ አሉ።ጨዋታቸው ተቋርጦም በዝምታ ተዋጡ።መሀመድ አሁንም መሳደቡን ቀጠለ።ትኩረቱን በደስታ ባልንጀራ ላይ አድርጎም ጸያፍ ቃላት ሰነዘረ።
የደስታ ባልንጀራ ለጊዜው እርቁን አቁሞ አጸፋውን ሊመልስ ሞከረ።የመሀመድን ንግግር ያዳመጠው ደስታ ውስጡ በንዴት ጋየ።ራሱን መቆጣጠር ቢያቅተው ከስድቡ እንዲታቀብ ሰዉንም እንዲያከብር፣ አጠንክሮ ገሰጸው።
መሀመድ በደስታ ንግግር በእጅጉ በሸቀ።ሁኔታውን ያየው ደስታ በንዴት ለጠብ ተጋበዘ።ሁለቱ መያያዝ ሲጀምሩ ገላጋዮች ገቡ።ለጊዜው ጠቡ በርዶ መሀመድ ሲወጣ ሁኔታዎች እንደነበሩ ቀጠሉ።ጓደኛውና መሀመድ ተመልሰው እስኪመጡ ድረሰ ቀጥሎ የሚሆነውን ያወቀ አልነበረም፡፡
የፖሊስ ምርመራ
ደስታ በመሀመድ የጩቤ ስለት ጉዳት አጋጥሞት ሆስፒታል እንደገባ ፖሊሶች በስፍራው ደረሱ።ስለነበረው ሁኔታና ስለ ተፈጸመው ወንጀልም ከእማኞች ጠየቁ።ጉዳዩን አይተናል ያሉ ለማስረጃነት ቃላቸውን ሰጡ።የደስታ ህይወት ማለፍ እንደታወቀ ተፈላጊው መሀመድ ከፖሊሶች እጅ ገባ፤ መርማሪው ምክትል ሳጅን ሲሳይ ተሾመ ተጠርጣሪውን አቅርቦ ጠየቀ።መሀመድ ለጠቡ መነሻ የሆነው ሟች ደስታ በያዘው ምላጭ አስቀድሞ አገጩን ስለጫረውና በዚሁ ምክንያት በመናደዱ መሆኑን አስረዳ።በወቅቱ ባደረሰበት የመቁረጥ ጉዳትም አገጩ ይደማ እንደነበር ተናገረ፡፡
ከግልግሉ በኋላ ወደሚያድርበት ቦታ ፈጥኖ የመጣው መሀመድ ሲመለስ የእንጨት መያዣ ያለውና በአንድ በኩል ስለት በሆነ ጩቤ መሰል ቢላዋ እንደወጋው ገለጸ።ጩቤውን ከዚህ ቀደም መሬት ወድቆ እንዳገኘውም አልደበቀም።የተጠርጣሪውን ቃል በመዝገብ ቁጥር 676/04 ላይ የመዘገበው መርማሪ የክስ ምርመራዎቹን አጠናቆ መዝገቡን ለዓቃቤ ህግ አሳለፈ፡፡
ውሳኔ
ሀምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በከባድ ሰው መግደል ተጠርጥሮ የቀረበውን ተከሳሽ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተገኝቷል።ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በቀረበበት የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ጉዳዩን መርምሮ ጥፋተኝነቱን አረጋግጧል።በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የዘጠኝ ዓመት ጽኑ አስራት ይቀጣልኝ ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013