የኤች አይ ቪ ቫይረስ ከ30 ዓመታት በፊት በዓለም ላይ መኖሩ ከተረጋገጠ ወዲህ በማህበረሰብ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ችግሩ እስካሁንም ድረስ ቀጥሎ ወደ 35 ሚሊዮን የሚያህል ህዝብ ለህልፈት ተዳርጓል፡፡ እ ኤ አ በ2017 1.8 ሚሊዮን አዲስ በቫይረሱ የተያዙ እንደሆነና ከዚህም ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ እንደሆኑ በቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ የጸረ ኤች አይ ቪ ህክምና ማእከል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ባህረዲን ባቡሴራ የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የጤና ድርጅት ከአጋሮች ጋር በመተባበር በዓለም የኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከ2016 ጀምሮ ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ለመተግበር እንዲቻልም ሦስቱ 90ዎች መርሀ ግብርን ዘርግቷል፡፡ የመጀመሪያው 90 በመቶም የሚያተኩረው ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከሚገመቱት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑትን የተለያዩ ትምህርቶችን በመስጠት ግንዛቤያቸውን እንዲያዳብሩ በማድረግ ራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡
ለዚህ እንዲያግዝም በርካታ ሰዎች በሚገኙበትና ተጋላጮች ይኖሩበታል በሚባልበት ቦታ በነፃ የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ጣቢያዎችን በማቋቋም ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በፍቃደኝነት የሙያ ምክር በመስጠት ሰዎች ያለ ስጋት ወደ ምርመራ ጣቢያዎች እንዲመጡ በማድረግ ነው፡፡ ለዚህ መርሃ ግብር እገዛ ለመስጠትም ኤች ኤፍ የተባለ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በተለያዩ አካባቢዎች ድንኳኖችን በመትከል እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ዶ/ር በህረዲን አመልክተዋል፡፡
ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከሚገመቱ የህብረተሰብ ክፍሎችም ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ሥራቸውን የሚያከናውኑ፤ የቀን ሠራተኞች፤ በትላልቅ እርሻዎችና ፋብሪካዎች የሚሠሩ ሠራተኞች፤ በማረሚያ ቤቶችና በአካባቢው የሚኖሩ እንዲሁም ሴተኛ አዳሪዎችና ደንበኞቻቸው የሚገኙበት አካባቢ በመዘዋወር ትምህርት በመስጠት እንዲመረመሩ ተደርጎ እስከ 2020 ድረስ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ዶ/ሩ ገለጻ እስከ 2017 ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ የተደረጉት ከ90 በመቶቹ ውስጥ 75 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ናቸው፡፡ ስለሆነም በቀሪው ጊዜ የተቀረውን ለማሟላት ጠንክሮ መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን የታቀደውን ግብ ለማሳካት እንደየሀገሮች የኢኮኖሚ፤ የመሰረተልማት እድገትና የሠለጠነ የሰው ኃይል ደረጃ የሚወሰን ሲሆን፣ በተለያዩ ችግሮች የተጠመዱ ደሀ ሀገሮች ከዚህ አኳያ ብዙ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ይገመታል፡፡
የሁለተኛው ዘጠና በመቶ ዓላማ ደግሞ ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ወዲያውኑ የፀረ ኤድስ መድኃኒት መውሰድ እንዲጀምሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የህክምና አገልግሎትና መድኃኒት ማቅረብ የሚችሉ የጤና ተቋማትን በየቦታው እንዲስፋፉ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብዙ ሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች መድኃኒቱን በአግባቡ እየሰጡ የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም ከላይ የተጠቀሰውን ዓላማ ለማሳካት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የህክምና አገልግሎት ለሚሹ ወገኖች ጥራቱን የጠበቀና ሳቢነት ባለው አቀራረብ አገልግሎት መስጠት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ መድኃኒቱን የጀመሩ ወገኖችም መድኃኒቱን ሳያቋርጡ እንዲቀጥሉ ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት በዓለም ደረጃ ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቶ መድኃኒት ማግኘት የቻሉት ከ 57 እስከ 60 በመቶ ያሉት ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻርም ክፍተቶች እንዳሉ መረዳት አያዳግትም ስለሆነም ግቡን ለማሳካት ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ሦስተኛ ዘጠና በመቶ ደግም ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝ ካወቁት ውስጥ90 በመቶ የሚሆኑት መድኃኒቱን በትክክል ያለማቋረጥ በመውሰድ በደማቸው የሚገኘውን የቫይረስ መጠን ከ1 ሺህ በታች ዝቅ ማድረግና ወደ ሌላ ወገን እንዳይተላለፍ ማድረግ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አንድ ሰው ተመርምሮ ቫይረሱ በደሙ መገኘቱ ተረጋግጦ መድኃኒቱን በአግባቡና በተገቢው ከወሰደ መድኃኒቱን መውሰድ ከጀመረ ከስድስተኛው ወር በኋላ በደም ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ መጠን በጣም ዝቅተኛ ይሆናል፡፡
ይህንን ለማሳካትም ልክ እንደ ሁለተኛው ዘጠና በየአካባቢው የጤና ተቋማትን፤ መድኃኒትንና ሙያተኞችን ማበራከት አስፈላጊ ሲሆን፣ መድኃኒት ተጠቃሚዎች ተሰላችተው መድኃኒት መውሰዱን እንዳያቋርጡም በተቻለ መጠን መንከባከብና ትህትናን ማሳየት ግድ ይላል፡፡ ቤተሰብም ከቫይረሱ ጋር አብሮ የሚኖርን የቤተሰብ አባል ሰዓቱን እያስታወሰ እንዲወስድ ማበረታታት ይኖርበታል፡፡ በተከታታይም የሙያተኞች ምክር የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡
በመጀመሪያው ዘጠና በመቶ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ላይ አተኩሮ ሰዎች እንዲመረመሩና እራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቦታዎች እንዴት ሊመረጡ ቻሉ ይህን አስመልክተው ዶ/ር በህረዲን ሲገልጹ ቦታዎቹ የተመረጡት በአካባቢው ምን አይነት ሰዎች ይኖራሉ፤ ምን ያህል ህዝብስ ይኖራል፤ አኗኗራቸው ምን ይመስላል፤ ገቢያቸውስ ምንድነው፤ በምንስ ይተዳደራሉ የሚለው ሁኔታ ጥናት ተደርጎበት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በዕድሜያቸው ወጣት የሆኑ ሰዎች በብዛት ለሥራ የሚሰማሩባቸው እንደ ዘመናዊ እርሻዎችና ፋብሪካዎች የበዙበት አካባቢዎች ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ከተሜነት ያልተስፋፋ ሆኖ በአብዛኛው ኑሮውን በገጠር የመሰረተ ነው፡፡ የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢ ደግሞ እንደ ጤና ጣቢያ ያሉ መሰረተ ልማቶች ያልተስፋፉበት፤ ውሃና መብራት ያልተስፋፉባቸው መሆኑ የ90ዎችን ግቦች ከማሳካት አኳያ ፈተና ሊያጋጥም አይችልምን ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር በህረዲን ሲመልሱ በርግጥም ይኖራል፡፡ እቅዱም ስትራቴጂ ነው እስካሁንም በአፈጻጸም ረገድ ውስንነቶች ተስተውለዋል ነገር ግን መንግሥት፤ ባለድርሻ አካላትና ሌሎች የህብረተሰቡ ክፍሎች ርብርብ ካደረጉ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ ጉዳዩ ግን ለመንግሥት ብቻ ከተተወ ፈተናው ከባድ ሊሆን ስለሚችል ሁሉም የበኩሉን እገዛ ሊያደርግ ግድ ይለዋል፡፡
በህብረተሰባችን ገበናን የመደበቅ ስር የሰደደ ባህል አለ፡፡ እንኳን በኤች አይ ቪ ጉዳይ ይቅርና በሌላም ጉዳይ ለመወያየት ፈራ ተባ ይላል ሰው፡፡ ይህ ደግሞ የመጀመሪያውን 90 በመቶ ለማሳካት ማለትም ሰዎች በፈቃደኝነት እንዲመረመሩ የማድረግ እቅድ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አለው፡፡ እንደ ዶ/ር በህረዲን አሁንም ሰዎች ለመመርመር ይፈራሉ፤ ለዚህም ምክንያቱ እስከ አሁን በከተማም ሆነ በገጠር፤ በተማረውም ሆነ ባልተማረው የህብረተሰብ ክፍል ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖችን የማግለል ሁኔታ እንዳለ ነው፡፡ ከአስር ዓመታት በፊት ማግለልና መድልኦን ለመቀነስ ብዙ ሥራዎች በዘመቻ መልክ ተከናውነው የተሻሉ ውጤቶች ተገኝተው ነበር፡፡ ነገር ግን ያ እንቅስቃሴ በመዳከሙ ስርጭቱ እንደገና እያገረሸ የሚገኝ ሲሆን፤ ማግለልና መድልዎም እንደዛው አገርሽ ቷል፡፡
ከቫይረሱ ጋር አብረው የሚኖሩ ምናልባት በጣም ለሚቀርቧቸው አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ገበናቸውን ሊገልጹ ይችላሉ እንጂ ለሌላው ለጎረቤት ወይም እንዳለ ለቤተሰብ አባላት አይገልጹም ለዚህም ምክንያቱ መግለልና መድልዎው መኖሩ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የደም ምርመራ የሚያደርጉ የጤና ጣቢያዎች በየቦታው መስፋፋታቸው የአገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት በተጨማሪ ሰዎች ስለራሳቸው ሁኔታ ለማወቅና ቫይረሱ በደማቸው ቢገኝ እንኳን መድኃኒቱን በመውሰድ ራሳቸውን ጠብቀው መኖር እንዲችሉ ስለሚያስችል ስለ ጉዳዩ መተፋፈርና መፍራት ስሜት እየቀነሰ እንዲሄድ ስለሚያስችል ማግለልና መድሎዎም በዚያው መጠን ይቀንሳል፡፡
ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ስለ መኖሩና አለመኖሩ በተለያየ መንገድ ለማወቅ የሚችሉ ሲሆን አንደኛውም ከላይ በተጠቀሰው በየአካባቢው በሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ጋብቻ ለመፈጸም ሲባል የሚደረግ የደም ምርመራ፤ በቅድመ ወሊድና በድሀረ ወሊድ በሚደረግ የጤና ክትትል ሲሆን፣ በመሰረቱም ማንም ሰው ወደ ጤና ጣቢያ ወይም ሆስፒታል ከመጣ አስፈላጊውን የደም ምርመራ ማድረግ መብት አለው፡፡ ነገር ግን በዚህ አካሄድ እንደ ዶ/ር በህረዲን ገለጻ ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ስለሆነም የደም ምርመራው ይበልጥ ማነጣጠር ያለበት ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው በሚባሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መሆን አለበት፡፡
በአጠቃላይ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሚያስችሉ ዘዴዎች ውስጥ እስካሁን በተግባር የተረጋገጠለት በፈቃደኝነት የደም ምርመራ ማድረግ እንደሆነ ተገንዝቦ ህብረተሰቡ በአካባቢው በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ተመርምሮ ራሱን ቢያውቅ ከላይ የተጠቀሱትን አላማዎች ለማሳካት ያስችላል፡፡