በተፋሰሶች አካባቢ የተጠናከረ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በመሥራት ከፍተኛ የሀገር ሀብት ወጥቶባቸው የተሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች (ግድቦች) እና የተለያዩ ብዝሃ ህይወት በውስጣቸው የያዙ ሐይቆችን ከደለል መታደግ እንደሚገባ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው።ደለል ውሃ እንዲይዙ የተሰሩ ግድቦችን የአገልግሎት ዘመን ከማሳጠሩና የሐይቆችንም መጠን ከመቀነስ በተጨማሪ የደለል ክምችትን ለማስወገድ የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት ለግድብ ግንባታ ከሚጠይቀው ወጪ ያልተናነሰ እንደሆነም ይነገራል።
በደለል መሞላት ካጋጠሙ ከብዙ ማሳያዎች አንዱ ጫሞ ሐይቅ ላይ ያጋጠመውን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።እ.ኤ.አ 2019 ላይ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአፈር መሸርሸር መጠንን ለማወቅ ሲያከናውን የቆየውን የምርምር ፕሮጀክት ይፋ ባደረገበት ወቅት ከጫሞ ሐይቅ ተፋሰሶች አንዱ ከሆነው ከኤልጎ ተፋሰስ ብቻ በዓመት ሶስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ቶን ደለል አፈር ወደ ጫሞ ሐይቅ እንደሚገባ በድረ-ገጽ ከተሰራጨው የዩኒቨርሲቲው መረጃ ለመረዳት ችለናል።
እንደ መረጃው የተፋሰሱ የአፈር የተፈጥሮ አይነት፣ የዝናብ ስርጭት፣የመሬቱ ተዳፋትነት፣ የዕፅዋት(ደን) ሽፋን፣የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች አተገባበር በጥናቱ ላይ ተካትተው የተፈተሹ ሲሆን፣እነዚህ አምስት ምክንያቶች ናቸው መጨረሻው ውጤት ላይ ያደረሱት።ወደ ሐይቁ በከፍተኛ ሁኔታ እየገባ ያለው ደለል የሐይቁን የምግብ ሰንሰለት ሥርዓት በማዛባት፣በሐይቁ ውስጥ በሚገኘው ብዝሐ ሕይወት ላይም ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል፣የሐይቁንም የዓሣ ሀብት እንዲቀንስ በማድረግ ጉዳቱ መጠነ ሰፊ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።ከተፋሰሱ የመሬት ክፍልም 80 በመቶ የሚሆነው ለእርሻ የዋለ ሲሆን፣ለአፈር መሸርሸር 63 በመቶ ድርሻ የሚይዘው እርሻ መሆኑም ተጠቅሷል።የመሬት ተዳፋትነትም ተጨማሪ ተግዳሮት ነው።ተዳፋት ለእርሻ እንዲውል አይመከረም።ይሁን እንጂ በአካባቢው ደረጃው 30 በመቶ የሆነው ተዳፋት መሬት በተመሳሳይ እስከ 70 በመቶ ያህሉ ለእርሻ ውሏል።ይህም ለአፈር መሸርሸር ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በአጠቃላይ የደለል ሁኔታ፣የመሬት መራቆት፣የአፈር ክለት ምን ይመስላል ለሚለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጌቴ ዘለቀ ደለል ከየት ነው የሚመጣው? እንዴትስ ይከሰታል? የሚለውን ሀሳብ በማስቀደም እንዲህ አስረድተዋል።አንዱ የኢትዮጵያ የዝናብ ሁኔታ ሲሆን፣የዝናብ ስርጭቱም ሲታይ በጣም ከተወሰኑ የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች በስተቀር በአብዛኛው የሚገኘው የዝናብ መጠን ከ12 ወራቶች ውስጥ ሰኔ፣ሐምሌ፣ነሐሴና መስከረም ወራቶች ብቻ ነው።ጊዜው አጭር ቢሆንም በነዚህ ወቅቶች ከፍተኛ ጉልበት ያለው ዝናብ ነው የሚዘንበው።በነዚህ ወቅቶች እስከ አንድሺ አምስት መቶ ሚሊሜትር የዝናብ መጠን የሚዘንብባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች አሉ።ይሄ መጠን ትልቅ ጉልበት ያለው ማሳያ ነው።ይሄ ትልቅ ጉልበት ያለው የተጠራቀመ ዝናብ የዕፅዋት ሽፋን በሌለበት መሬት ላይ ሲያርፍ አፈሩን ከመሬቱ ውስጥ ፈንቅሎ የማውጣት ኃይል አለው።በሌላ በኩል በአንዴ ብዙ ዝናብ መዝነቡ አፈሩን አጣርቶ የመዋጥ አቅሙን አናሳ እንዲሆን ያደርገዋል።በዚህ ወቅት ደግሞ ወደ ጎርፍነት ይከሰታል።በዝናቡ ኃይል ከመሬት ውስጥ ተነቅሎ የወጣው አፈር ደግሞ በጎርፍ ተጠርጎ ይወሰዳል።ጎርፉ አፈሩን ጠርጎ መውሰድ ብቻ ሳይሆን መሬቱን ወይንም አፈሩን በመቦርቦር ጉዳት ያስከትላል።በዚህ መልኩ ነው ደለል የሚጠራቀመው።ተጠርጎ የመጣው አፈር ደግሞ ሄዶ ሐይቆች ላይ ይጠራቀማል።ደለልም የሚሆነው በዚህ መልኩ ነው።ተጠርጎ የመጣው አፈርም በተወሰነ በወንዞች ላይም ስለሚቀር በተመሳሳይ ደለል ይፈጠራል።አፈር ተጠራቅሞ ደለል የሚሆነው በአብዛኛው በሰው ሰራሽ ግድቦች ነው።
‹‹ከዚህ አኳያ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ሥነምህዳር ምን ይመስላል? የዕፅዋት ሽፋኑና ተጋላጭነቱ ለሚለውም ዶክተር ጌቴ በሰጡት ማብራሪያ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሥነምህዳር ማለትም 85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በእርሻ የሚተዳደር ነው።ሊያውም በዘመናዊ የእርሻ ዘዴ ያልታገዘ።አልፎ አልፎ በተለይም በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር መሬቱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዕፅዋት የተሸፈነ አይደለም።አብዛኛው ለእርሻ ሥራ የሚውል መሬት ነው።የእርሻ መሬት ፈላጊው ከፍተኛ ቁጥር ያለው በመሆኑ ለእርሻ የማይውለው ሁሉ እየታረሰ ነው።ተዳፋታቸው እጅግ ከፍተኛ የሆኑ አካባቢዎች ሁሉ ለእርሻ እየዋሉ ነው።ተዳፋት ለእርሻ ሥራ እንዲውል አይመከርም።ምንም አይነት የመሬት አያያዝ፣እርከንና የዕፅዋት ሽፋን የሌለው ቦታ ሰኔና ሐምሌ ዘር የሚዘራበት ጊዜ ስለሆነ ባዶ ቦታ ነው።በእርሻ መሬቱ ለም በመሆኑ አፈሩ በቀላሉ በጎርፍ ይታጠባል።የዕፅዋት ሽፋን በሌለበት ለሶስት ወር የሚዘንበው ዝናብ በእርሻ ለም የሆነውን አፈር ጠርጎ ለመውሰድ አቅም ያገኛል።እነዚህና ሌሎችም ተፅዕኖዎች በየተፋሰሱ የደለል መጠን እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።በአሁኑ ጊዜም ያለው የደለል መጠን እጅግ ከፍተኛ ነው።
ለአብነትም በደለል ከተሞሉ ግድቦች ቦርከና፣ቆጋ፣ገፈርሳ፣ለገዳዲን መጥቀስ ይቻላል።ውሃ የመያዝ መጠናቸው እየቀነሱ የመጡ ሐይቆችም ጥቂት የማይባሉ ሲሆኑ፣ከነዚህ መካከልም ጣና፣ላንጋኖ፣አብጃታ ሻላ ጥቂቶቹ ናቸው።ሐይቆቹ በዝናብ ወቅት እንኳን ከሚይዙት ውሃ በላይ ጎልቶ የሚታየው ጭቃው ነው።ይሄ የሚያሳየው ወደ ወንዞች፣ሐይቆች፣ግድቦች እየገባ ያለው ደለል እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው።በዚህ ረገድ ማዕከላቸው የተለያዩ ጥናቶችን አካሂዷል።መረጃዎችንም ይዟል።
ደለል የሚያስከትለው ጉዳት እንዴት ይገለፃል? ለሚለው ጥያቄም ዶክተር ጌቴ በሰጡት ምላሽ፤የደለል መከሰት ጉዳት ዘርፈ ብዙ ነው።ደለል በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሰው።ሐይቆች ውሃ እንዲይዙ በተሰሩ ግድቦች ነው።በኢትዮጵያ ውስጥ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ክልሎች ካልሆነ በስተቀር በደለል ምክንያት ረግረግ የሚባሉ አካባቢዎች ጠፍተዋል በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያሉት።ይሄ እጅግ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ነው።ደለል የወንዞችን መፍሰሻ በመሙላትም ጉዳት ያደርሳል።ይሄ ደግሞ ጎርፍ እንዲከሰት ያደርጋል።ከወንዞቹ የሚወጣው ውሃ ጎርፍ ሆኖ የእርሻ ማሳዎችን፣መኖሪያ መንደሮችን፣ ያጥለቀልቃል።እንዲህ ያለው ክስተትም በየዓመቱ እያጋጠመ ሰዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው እያፈናቀለ፣ታርሶ በሰብል የተሸፈነ የእርሻ መሬትንም በማጥለቅለቅና የቤት እንስሳትንም በመጉዳት ለከፋ ችግር እየዳረገ ይገኛል።ለአብነትም የአዋሽ ወንዝ በየዓመቱ እያስከተለ ያለውን ጉዳት መጥቀስ ይቻላል።በዚህ የክረምት ወቅትም የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ መፈናቀል ማስከተሉ ይታወሳል።
እንደ ዶክተር ጌቴ ማብራሪያ የላይኛው ተፋሰስ በአግባቡ አለመያዝ ለተደጋጋሚ ጎርፍ መከሰት አንዱ መንስኤ ነው።በአካባቢው ውሃ ወደ ውስጥ ስለማይሰርግ ጎርፍ አፈሩን ጠራሮጎ ወደታች ይልከዋል።የደለል መጠን መጨመር ጉዳቱ ሰፊ ነው።በሰው ሰራሽ ግድቦችና በሐይቆች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ቢያስከትልም በመሠረተ ልማት ላይ በአጠቃላይ በማህበረሰብ ላይ የሚያሳድረው ጫና እጅግ ከፍተኛ ነው።የጉዳቱን መጠን በግልጽ ለማወቅም ከባድ አድርጎታል።
ደለል ከተከሰተ በኋላ ለማስወገድ የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት እጅግ ከባድ በመሆኑ ደለልን ቀድሞ መከላከሉ ነው የሚመከረው።ዶክተር ጌቴም ኢንቨስትመንቱ እጅግ ውድ እንደሆነ ነው ያረጋገጡት።መከናወን ስላለባቸው ተግባራትም እንዳስረዱት አንዱ በደለል የተሞሉ የወንዝ መፍሰሻ ቦታዎችን መጥረግ፣ውሃው ከወንዙ ውስጥ እንዳይወጣ ወይንም ሰብሮ የሚገባበትን ቦታ በአፈር ወይንም በድንጋይ በመገደብ መከላከል ሌላው ተግባር ነው።በዚህ ረገድም እንደ ሀገር እየተሰራ ነው።መፍትሄው ግን ዘላቂ አይደለም።በዚህ መልኩ የተከናወነ ሥራ ከሁለት ዓመት የበለጠ አገልግሎት አይኖረውም።ወደ ቀድሞ ጉዳት ይመለሳል።ቋሚ መፍትሄ የሚሆነው ደለሉ ከላይ ከመነሻው እንዳይመጣ ወይንም እንዳይነሳ የላይኛውን የተፋሰስ አካል በአግባቡ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ እንዲሰራ ማድረግ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆን ይኖርበታል።
ማዕከሉ ኢትዮጵያ በውሃ፣በጎርፍና በዝናብ ምክንያት የሚከሰተውን የአፈር ክለትና የደለል መጠን ጥናትና ምርምር በማካሄድ፣የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም በማመላከት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል።በኢትዮጵያ ውስጥ ኦብዞርባቶሪ ወይንም የምልከታ ተፋሰሶች የሚገኙ ሲሆን፣አንዳንዶቹ ወደ 40 ዓመት ዕድሜ አስቆጥረዋል።በዚሁ መሠረት ዝርዝር ጥናቶች ይካሄዳሉ።በተፋሰሶቹ ውስጥ የተካሄዱትን ጥናቶች መነሻ ወይንም ሞዴል በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የመሬት መራቆት፣የእያንዳንዱ ተፋሰስ የደለል መጠን በጥናት ተለይቷል።ጥናቱም ማዕከሉ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አስረክቧል።
ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ ከሆኑ ሜጋ ፕሮጀክት ግድቦች አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይጠቀሳል።ግድቡ ከስድስት ሺ በላይ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭም ታሳቢ ተደርጎ ነው በመገንባት ላይ የሚገኘው።ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም እጅግ ሰፊ ነው።ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያም በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ አንዱ ዓላማና ተግባር ሲሆን፣በተጨማሪም ለቱሪስት መዳረሻነት በማዋል ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ከፍ ማድረግ ነው።ግድቡ ሀገራዊ መገለጫም ጭምር በመሆኑ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል።ደለል እንዲህ ዘርፈብዙ ጥቅሞችን ይዞ የተሰራን ግድብ በመጉዳት ሀገር ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም ያሳጣል።ግድቦችንም ሆነ ወንዞችንና ሐይቆችን ከደለል የመከላከል ተግባር በይደር ለነገ መባል እንደሌለበት ከባለሙያዎች የሚነገሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት በሁለት ዙሮች የተከናወነውና በሶስተኛውም ዙር በመከናወን ላይ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በተፋሰሶች አካባቢ ያለውን ልማት ለማጠናከር እጅግ ወሳኝ ነው።የህልውና ጉዳይም ስለሆነ እያንዳንዱ ዜጋ በግንዛቤ አሻራውን በማሳረፍ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።የአረንጓዴ ተፋሰስ ልማት ከማጠናከር ጎን ለጎንም በግድቡ ሊገባ የሚችለውን የደለል መጠን በመከታተልና በመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው አካል በአግባቡ ተግባሩን ከተወጣ ለደለል አደጋ ተጋላጭ የሆኑትን ቀድሞ መታደግ የሚቻልበትን ዕድል መጠቀም ይጠብቀዋል።በተለይም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትም የተፋሰስ አረንጓዴ ልማቱ ይመለከታቸዋል።በዚህ ረገድም የዲፕሎማሲ ሥራውን በማጠናከር የጋራ ሥራ ማድረግ ይገባል።የጋራ ሥራው የጋራ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6/2013