አበው ሲተርቱ “እወቅ ያለው በዓመቱ፤ አትወቅ ያለው በሺ ዓመቱም አያውቅ” ይላሉ። ይህ ምሳሌ በዚህ ወቅት ሸኔ ለተባለው አሸባሪ ቡድን ተስማሚ እንደሆነ ይሰማኛል።
“ሸኔ” ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር የወጣ አንጃ እንደሆነ ሁላችሁም ታውቁታላችሁ ብዬ እገምታለሁ። ኦነግ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በነፃነት በርሃ መክረሙና ከተማ ከገቡ በኋላ በብልጣብልጥነት ገሸሽ መደረጉም ይታወቃል። በአንድ ወቅት ታዋቂ የኦህዴድ አመራሮች እንደተናገሩትም ሸኔ በበረሃ በህገወጥ ንግድና ለውጭ ኃይሎች ተላላኪ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አልነበረውም። ከዚሁ በተመሳሳይ አሸባሪው ህወሓት በበረሃ ቆይታው ሴራ ሲጎነጉን፣ ከፋፋይ ሃሳቦችን ሲያፈልቅና በህዝብ ስቃይና ችግር ሲነግድ ከርሟል።
መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንዲሉ የእነዚህ ሁለት አሸባሪ ድርጅቶች ስም “ነፃነት” እና “አርነት” የሚሉ ውብ ቃላትን የያዙ ናቸው። ይሁንና ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል እንዲሉ በስም ነፃነት ቢንቀሳቀሱም ምግባራቸው ግን ጥፋት፣ ሴራ ውርደትና ጭካኔ ሆኖ ይገኛል።
አሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ለንግግር የሚከብድ ግፍና ጭካኔ ሲፈጽም ኖሯል። ኢኮኖሚውን አውታር ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመቆጣጠር እንደልቡ ሲዘርፍና ሲያዘርፍም ኖሯል። የዚሁ የሽብር ቡድን አመራሮች በዘረፋ ባገኙት ገንዘብ ልጆቻቸውንና ዘመዶቻቸው በዱባይ፣ አውሮፓና አሜሪካ ሲያንደላቅቁ እነሱም ውስኪ እየተራጩ በድሃው ህዝብ ህይወት ሲቆምሩ ኖረዋል። በዚህ ሂደት መላ ኢትዮጵያውያን ግን በሥራ አጥነት፣ በኑሮ ውድነትና ሃብታቸውን በግፍ በመቀማት የስቃይ ህይወት ለመምራት ተገደው ኖረዋል።
አሸባሪው ህወሓት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲያደርስ የነበረውም ግፍ በቃላት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። የኦሮሞ ህዝቦች ኢፍትሃዊነትንና ዘረፋን በመቃወማቸው በዘመነ ህወሓት በገፍ በእስር ቤት እንዲታጎሩና ለመናገር እንኳን የሚዘገንኑ (እግር መቁረጥ፣ ከአውሬ ጋር ማሰር፣ ግርፋት ድብደባ ወዘተ) ግፍ ሲፈጸምባቸው ኖሯል። የማረሚያ ቤት የሥራ ቋንቋ ኦሮምኛ ነው የሚል አባባል እስኪፈጠርም ድረስ የግፍ ጽዋው ሞልቶ ተርፎ ነበር።
አሸባሪው ህወሓት በኦሮሞ አርሶ አደሮች ላይ የፈጸመው ግፍም ጠባሳው ሊሽር የማይችልና ዘግናኝ እንደነበር በተጎጂዎች አንደበት ተደጋግሞ የተገለጸ እውነት ነው። በፊንፊኔ ዙሪያ በርካታ የኦሮሞ አርሶ አደሮች በግፍ መሬታቸውን እየተነጠቁ ለዘበኝነትና ሲብስም ለልመና ተዳርገዋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ህይወት ተመሰቃቅሏል። ይሄን ግፍ የተቃወሙ በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ኢፍትሃዊነትን በመቃወማቸው ብቻ በስናይፐር ግንባራቸው ተመቷል፤ ብዙ ደም ፈሷል፤ ህጻናትና አዛውንቶችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን በግፍ ህይወታቸው ተነጥቋል።
ኢትዮጵያውያን ይሄ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም ዝም ብለው አልተመለከቱም። ይልቁኑ ከገዳይ መሳሪያ ፊት ለፊት በመፋጠጥ ግፍን አውግዘዋል። “በኦሮሚያ የሚፈሰው ደም የእኛም ደም ነው” በሚል በአማራ ክልል የተደረጉ ሰልፎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው”።
የሽብር መንትያ ወንድሙ የሆነው ሸኔም ዕድሜውን ሙሉ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጠላት፣ የሆነ በሰው ደም የሚረካ፣ ርህራሄ የሌለው ዓላማና ርባና ቢስ ስብስብ ስለመሆኑ በብዙ ማስረጃዎች ማሳየት ይቻላል።
ሸኔ የኦሮሞ ህዝብ በህወሓት ጭቆና ውስጥ በነበረበት ዘመን ያልደረሰለትና መላ ኢትዮጵያውያን ከጥፋት ኃይል ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠው የአሸባሪውን ህውሓት ግብዓት መሬት ባፋጠኑበት ትግል ምንም እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽኦ ያላበረከተ የንፍሰ ገዳይ ስብስብ ነው።
ማናችንም እንደምናስታውሰው ጀግናው ሃጫሉ ሁንዴሳ ከፊት ለፊቱ መሳሪያ እየተመለከተና ብዙ ዛቻና ማስፋራሪያ እየደረሰበት የእኔ ህይወት ከህዝብ ጉዳት አይበልጥም በማለት በአደባባይ ኢፍትሃዊነትንና ጭቆናን አውግዞ ህዝባዊ ትግሉ ለፍሬ እንዲበቃ አድርጓል። ሃጫሉ በለውጡ ዘመን “ለኦሮሞ እታገላለሁ የሚል ድርጅት ኦሮሞን አይገድልም” በሚል የዚህን አሸባሪ ድርጅት አካሄድ በመቃወሙ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ተቀናጅቶ ይሄንን ጀግና የገደለው የጥፋት ቡድን ሸኔ ነው።
አገር ሆደ ሠፊ ሆና የፖለቲካ ልዩነቶች በንግግርና በውይይት ሊፈቱ ይችላሉ በሚል እሳቤ ያለፈ ግፍና በደሉ ተትቶለት ወደ አገር ውስጥ የገባው ሸኔ “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንዲሉ ወዲያውኑ የጀመረው ሰዎችን መግደልና የሽብር ሥራ ነበር። ለዚህም መንግስትን ደግፋችኋል በሚል ሰንካላ ምክንያት በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን በአደባባይ ረሽኗል፤ ልክ እንደ ጥፉ አጋሩ ህወሓት መሰረተ ልማትን አውድሞ የኦሮሞ ህዝቦች ጠላት መሆኑን ደጋግሞ አስመስክሯል።
ህዝብ ጠል የሆነው ሸኔ የአማራ ተወላጆችን በማንነታቸው ብቻ እየለየ በወለጋ፣ በቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላና አጣዬ በግፍ ገድሏል። የዕለት ጉርሳቸውን እንኳ በአግባቡ ማግኘት ያልቻሉ ምስኪኖችን ያለምንም ጥፋታቸው ጨፍጭፏል፤ ዘርፏል፣ ቤተሰብም በትኗል። የሽብር መንትያዎች የሆኑት ሁለቱ ድርጅቶች የሚያመሰስሏቸው ዋና ዋና ጉዳዮችን ስናይም፦
ኢትዮጵያ ጠልነት
ሸኔም ሆነ ህወሓት ኢትዮጵያ ጠል ናቸው። ስለሆነም ኢትዮጵያ የሚል ስም እጅግ ያስደነግጣቸዋል። ይኸንን ሃሳብ ይደግፋሉ በሚሏቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይም ያለርህራሄ ካራቸውን መዘው ይዘምታሉ።
አማራ ጠልነት
ሁለቱም ሽብርተኛ ቡድኖች በተለይም የአማራ ብሔረሰብን የጥቃት ኢላማቸው አድርገው ይንቀሳቀሳሉ። ስለሆነም በድብቅም ሆነ በግልጽ የአማራ ብሔረሰብ አባላትን ይገድላሉ፣ ያስገድላሉ።
የህዝብ ጠላትነት
አሸባሪዎቹ ህወሓትም ሆነ ሸኔ በትግራይና በኦሮሞ ህዝብ ነፃ አውጪነት ስም ቢንቀሳቀሱም ሁለቱም ህዝቦችን ለጦርነት በመማገድ በስቃያቸው ከመነገድና ልማታቸውን አደናቅፎ ህይወታቸውን በማጨለም ጠላትነታቸውን ያስመሰከሩ የሽብርተኛ ስብስቦች ናቸው። ህወሓት በስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን እንኳ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የትግራይ ዜጎች የሴፍቲኔት ተረጂዎች ሆነው መኖራቸው ለድርጅቶቹ ፋይዳቢስነት መልካም ማሳያ ነው።
ከፋፋይነት
አንድነትና የህዝቦች አብሮነት አለርጂ የሆነባቸው እነዚህ ቡድኖች ያለምንም ልዩነት ከፋፋይ አጀንዳዎችን ሲያራግቡ መመልከት አዲስ አይደለም። ስለሆነም ሕብረተሰቡን ተበድልሃል፣ ተጨቁነሃል፣ የጨቆነህ ደግሞ እገሌ የሚሉት ብሔርና ንጉስ ነው በማለት ሌት ተቀን ህዝቦች በአንድነት እንዳይቆሙና እንዲከፋፈሉ ይሰራሉ። ይሄንን ሃሳብ የሚቃወምን ኃይልም የጭካኔ በትራቸውን ያሳርፉበታል።
በረሃብና በስቃይ ቁመራ
ህዝብ ሰላም እንዲሆን ለፍቶና ጥሮ ህይወቱ እንዲለወጥ የማይፈልጉት እነዚህ የሽብር ድርጅቶች ራሳቸው በፈጠሩት ችግር ህዝብን ስቃይ ውስጥ ይከታሉ። ይሄንን ተመርኩዞ የሚመጣውን ረሃብና መፈናቀል ለርካሽ ፖለቲካቸው መነገጃነት ያውሉታል።
“Birds with the same feather fly together” እንደሚለው የነጮች ብሂል ሽርና ደም ያጣመራቸው እነዚህ ሁለት ርባናና ፋይዳ ቢስ ድርጅቶች ናቸው እንግዲህ ከሰሞኑ ለሽብርና ተግባር ተዋህደናል ሲሉ ያወጁት። እኛም ደግሞ የትብብር ዜናቸውን ከሰማን በኋላ እንዲህ ልንላቸው ወደድን “ገንፎ ለገንፎ ቢደጋገፍ ተያይዞ ዘፍ”!
አከሲ ከቃሊቲ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም