እንደ አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ከተሞች ሁሉ በሀዋሳ ከተማም የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትን ማየት አዲስ አይደለም። እነዚህ ህጻናት በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ ናቸው፡፡ ማስቲሽ መሳብ ጫት መቃም ሲጋራና መጠጥ የየእለት ተግባሮቻቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ህጻናት በራሳቸው ላይ በጎዳና ከሚደርስባቸው የተለያዩ ችግሮች ባለፈ እነሱም የእለት ጉርሳቸውንና ሱሳቸውን ለመሸፈን ከስርቆት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን ይሰራሉ። ከችግሩ ስፋት አንጻር ግን በቂ ውጤት ማስመዝገብ ባይቻልም የከተማ መስተዳድሩ ችግሩን ለመቅረፍ በራሱና ከተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። በዚህ ስራ ከተሰማሩት ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ደግሞ አጁጃ የህጻናት መርጃ ማህበር አንዱ ነው፡፡ እኛም ለዛሬ የቤተሰብ አምድ እትማችን የማህበሩን እንቅስቃሴ ከማህበሩ ፕሮግራም ኮኦርድኔተር አቶ ተሾመ ተፈሪ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የማህበሩ መስራችና ዋና ዳይሬክተር ቄስ እያሱ ጣጊቾ ይባላሉ፡፡ ማህበሩን የመሰረቱት እሳቸው ከባለቤታቸውና ከቅርብ ጓደኞቻቻው ጋር በመሆን ነው፡፡ ከአስራ አንድ ዓመት በፊት ሲቋቋም አጁጃ- የሚል ስያሜ (በሲዳምኛ ቋንቋ ራዕይ) ተብሎ የተሰየመው የረጅም ጊዜ እቅድ ስለሰነቀም ነበር። ምንም እንኳን ማህበሩ ከማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ ኤጀንሲ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ የተመሰረተው በ2002 ዓ.ም ቢሆንም ከዛ በፊትም መስራቹ ከጓደኞቻቻውና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ሲሰሩ ነበር፡፡
ቄስ እያሱ በወቅቱ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የስራ ባልደረባ በመሆናቸው በስራ ምክንያት በነበራቸው እንቅስቃሴ በዛን ወቅት ቤተሰብ ያልነበራቸው ህጻናት ይደርስባቸው የነበረውን ችግር በማየት ይህንን የረጅም ጊዜ እቅድ ሰንቀው ወደ ተግባር የገቡት፡፡ በዛን ወቅት ደግሞ ከከተማ ወደ ጎዳና የሚወጡት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ አጎራባች ከተሞች ወደ አዋሳ ይመጡ የነበሩት ህጻናት ልጆች ቁጥርም ከፍተኛ ነበር፡፡ የእነዚህን ህጻናት ሰቆቃ የሚታደግ አንዳች ነገር መስራት እንዳለባቸው ያሳሰባቸው አንዱ ምክንያትም ይኸው ነበር፡፡ ምንም እንኳን እንደዚህ አይነት ስራዎችን መስራት ከተነሳሽነት ባለፈ ከገንዘብና ከቁሳቁስ ጀምሮ በርካታ ነገሮች እንደሚያስፈልጉት ግልጽ ነው። ቄስ እያሱ ግን «ሁሉም በጊዜው ይደረስበታል ስለዚህ አቅማችን በፈቀደና በአካባቢያችን ባለው ነገር እንጀምር» ብለው ነበር ወደ ተግባር የገቡት፡፡ ይህን ብለው ሲጀምሩም ዓላማቸው ያደረጉትም እነዛን በአዋሳ ከተማ መንገዶች ላይ በችግር በርሀብና በብርድ እየተቆራመቱ የሚኖሩ ህጻናትን መታደግ ነበር፡፡
ከአስራ ሶስት ዓመት በፊት ህጻናቱ ከተለያዩ የከተማዋ አጎራባች አካባቢዎች ይመጡ የነበረው ቤተሰብ እየተበተነ በችግርና ማረፊያ ስለሚያጡ ብቻ ሳይሆን፤ ወቅቱ የውጭ ሀገር ጉድፌቻ በጣም የተስፋፋበት ስለነበር አንዳንዶቹ በቤተሰብም ድጋፍ ነበር፡፡ ችግሩን መቅረፍ ባይቻልም በከተማ አስተዳደሩ በኩልም በዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ ከሞቀ ቤታቸው የሚወጡትን ህጻናት ለመታደግና የከተማዋንም ገጽታ ለማስተካከል የሚሰሩ ስራዎች ነበሩ፡፡ በዚህ አይነት የሚመጡት ህጻናት በሙሉ ደግሞ እንደሚታሰበው ነገሩ አልጋ በአልጋ ሆኖ ከሚፈልጉበት ከሀገር የመውጣት እቅድ አይደርሱም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የአብዛኞቹ ህጻናት መጨረሻ የሚሆነው ለጎዳና ህይወት መዳረግ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ህጻናቱ ከገጠር እንደመምጣታቸው የከተማውን ሁኔታ ስለማያውቁ ለደባል ሱስ መጋለጥ፤ ለአስገድዶ መደፈር መዳረግ፤ ለጉልበት ብዝበዛና ሌሎች ችግሮች መጋለጥ ነበር። በተለይም በዛን ጊዜ ካላቅማቸው የከተማዋን ቆሻሻ በማጽዳት ስራ የሚሰማሩት ልጆች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህም ለተለያዩ በሽታዎች ስለሚዳርጋቸው በጤና የሚቆዩበትም እድሜ እጅግ አጭር ይሆንና በየጎዳናው ዳርቻ በህመም የሚያሳልፉት ጊዜ የበዛ ነበር።
እናም በወቅቱ ይህንን በህጻናቱ ላይ እየደረሰ ያለውን አስከፊ ችግር ቢያንስ ወደቤተሰባቸው በመመለስ ለማስቆም በማሰብ ነበር ቄስ እያሱ እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት፡፡ ለዚህም እንዲረዳቸው በከተማው በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ተሰማርተው ከነበሩ ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ከተማዋ የሚመጡትን ህጻናት ውለው ሳያድሩ፤ የተለያዩ ችግሮች ሳይገጥሟቸውና በሱስ ሳይለከፉ ተመልሰው ከቤተሰብ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራቸውን መስራት ይጀምራሉ፡፡ ልጆቹን ወደቤተሰብ የመመለሱ ስራ ግን ከገንዘብና የሰው ጉልበት ባለፈ የቤተሰብ አድራሻ አፈላልጎ እስኪላኩ ድረስ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ጥቂት ቀናትም ቢሆን በጎዳና ላይ መቆየታቸው የግድ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ ደግሞ ላልታሰበ ችግር የሚያጋልጣቸው በመሆኑ ምንም ችግር ሳይገጥማቸው እንዲቆዩ ማረፊያ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ይወስናሉ፡፡ እናም በቀዳሚነት ምግብና መጠለያ በማዘጋጀት ልጆቹን ከቤተሰብ የማገናኘቱን ስራ መስራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በ2000 ስራቸውን ሲጀምሩ ተቋሙ ህጋዊ እውቅና ስላልነበረው ሰብስቦ ሊታደጋቸው የቻለው ስልሳ ህጻናትን ብቻ ነበር። ለእነዚህም ድጋፍ የሚያደርጉት በዋናነት በከተማዋ የነበሩት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ በጎ አድራጎት ድርጅቶችም ለእነሱ ተጠቅመው የተረፋቸውን አልባሳት ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ እንደ ወተት ያሉ ነገሮችንና ሌሎችን ቁሳቁሶችን ይልኩ ነበር፡፡ ቄስ እያሱ በዚህ ሁኔታ የጀመሩትን ስራ እየሰሩ እያለ ሌሎች ሁለት ሃሳቦች ያጭሩባቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ያላቸውን ልምድ መነሻ በማድረግ የህጻናቱን ፍልሰትና ለችግር መዳረግ በአጭር ጊዜ ሊቆም የማይችል መሆኑን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ማህበሩን በህጋዊ መንገድ አቋቁመው በራስ አቅም ገቢ እያፈላለጉ መስራት ካልተቻለ የህጻናቱ መከራ የማይቋረጥ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በህጋዊ መንገድ ማህበሩን በመመስረት መንቀሳቀሳቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ተቋሙ ከጅምሩ አንስቶ በአንድ ዓላማ ሳይወሰን አቅሙ በፈቀደ መንገድ ላይ ተጥለው የተገኙትን ህጻናት ከማሳደግ፤ ከቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ጋር ከማቀላቀል ባለፈ የአቅመ ደካሞችን ቤት የመጠገን ቤትም ይሰራ ነበር፡፡ በዚህም ሁኔታ እራሱን እያደረጃ በመምጣት የቦርድ አባል የአስተዳደር ሰራተኞችና ሌሎችንም በማሟላት ስራው ጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በአሁኑ ወቅትም አጁጃ ዘጠኝ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል በዋናት በድርጅቱ ስር እያሳደጋቸው ያሉትን ሃምሳ አራት ህጻናት መንከባከብ ነው፡፡ እነዚህንም ህጻናት እየተንከባከበ ያለው በሰባት ሺ ካሬ ሜትር ላይ ራሱ ባስገነባው ህንጻ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ህጻናት ተቋሙን የሚቀላቀሉት በሁለት አይነት መንገድ ሲሆን አንደኛ ተጥለው የተገኙና አባትም እናትም የሌላቸው ተጣርቶ በፖሊስ አማካይነት ሲቀርቡ ተቋሙ የሚቀበል ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሴቶችና ህጻናት ቢሮ በኩል የሚከናወን ሲሆን እነዚህ ህጻናትም አባት ቢኖሯቸውም በተለይ በወሊድ ምክንያት እናት ስትሞትና አባት ለመቅበር ሄዶ አልያም በሌላ ምክንያት ህጻናቱን መያዝ የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ተቋሙ ተቀብሎ አስፈላጊውን መሰረታዊ ፍላጎት ሁሉ እያሟላ የሚንከባከባቸው ናቸው፡፡ ተቋሙ ለእነዚህ ልጆች ጤና እንክብካቤ አንድ በተፈለገ ጊዜ የሚገኝ የትርፍ ሰአት ሰራተኛ የህክምና ዶክተር እንዲሁም ሁል ጊዜ ከልጆቹ የማይለዩ ሶስት ነርሶች አሉት፡፡ በተጨማሪ እነዚህ ልጆች ከቁሳዊ ፍላጎታቸው ባለፈ በአእምሯቸውም ሰላማዊና ደስተኛ ሆነው እንዲያድጉ ድጋፍ የምታደርግላቸው አንድ የስነ ልቦና ባለሙያ አለቻቸው፡፡ ተቋሙ ሙሉ ስራውን የሚሰራው ከህብረተሰቡ ጋር በከፍተኛ ደረጃ በመቀራረብ በመሆኑም ይህንን የሚሰሩ ሁለት የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በተጨማሪ በተቋሙ የተለያዩ ልዩ ፍላጎትና የአእምሮ እድገት ውስንነት የገጠማቸው ልጆች አሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ራሳቸውን ችለው ምንም የሚያደርጉት ነገር የለም፡፡ አንዳንዶቹ ምግብ ለመመገብ እንኳን በሞግዚት አማካይነት ከሁለት ሰአት በላይ የሚወስድባቸው ናቸው። እነዚህን ለመንከባከብ ደግሞ ለአንድ ህጻን አንድ ሞግዚት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ዛረም ድረስ የተቋሙ ከፍተኛ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
ተቋሙ ስራውን ሲጀምር ማህበረሰቡ የውጭ ሀገር ጉድፌቻ በስፋት ተለምዶ ስለነበር እሱ ሲቆም በሀገር ውስጥ ለመውሰድ ብዙ ችግር ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ጾታ ይመርጣሉ፤ ሌሎች ደግሞ እቤት ውስጥ እንዲያገለግሏቸው ሴቶች ሆነው ከፍ ከፍ ያሉትን ብቻ ይመርጣሉ አብዛኛዎቹ ደግሞ ጤነኛ ብቻ የሆኑትን ይመርጣሉ፡፡ ተቋሙ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በማህበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤ ለመፍጠር በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ስራዎቹን ውጤታማ ለማድረግም እድሮችን የሃይማኖት ተቋማትን በመጠቀም በተሰራው ሰፊ ስራ ለውጥ በመምጣቱ ዛሬ የእኔ ልጅ አደርገዋለሁ ብለው የሚመጡት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡
እነዚህን ስራዎች ሲሰሩ ከፖሊስና ከሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ በኩል ከፍተኛ ትብብር እየተደረገለት ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ወሳኝ ኩነት ምዝገባን ጨምሮ የመንግስት ተቋማትን የሚመለከት ጉዳይ ሲገጥም ግን በርካታ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ ይህም የግንዛቤ ክፍተት በመሆኑ አንዳንድ ቢሮዎች ስብሰባ እንኳን ሲጠሩ ለመገኘት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹም ተቋሙን ህጻናትን ለመታደግ፤ የህብረተሰቡን የጋራ ችግር ለመቅረፍ ሳይሆን ለራስ ጥቅም የተቋቋመ የሚመስላቸውም አሉ፡፡ የዚህ አይነት እሳቤ ያላቸው ብዙ በመሆናቸው የመሬት ጥያቄ ቀርቦ እንኳን ለአራት ዓመት ያህል መልስ ሳይሰጠው ቆይቶ አሁንም ቦታ ያገኘው ከከተማው ዳርቻ ከአርሶ አደሮች ጋር በመነጋገር በግዢ ነው፡፡
ተቋሙ በማእከሉ ከሚንከባከባቸው ልጆች ባለፈ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል። ተቋማዊ ድጋፍ ፤ መልሶ ማቀላቀል ፤ ልጆቻቸውን ለማስተማር ለማይችሉ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ወደጎዳና እንዳይወጡ ለ540 ልጆች በስፖንሰር ሺፕ በየወሩ አራት አራት መቶ ብር እየተሰጣቸው ባሉበት ድጋፍ ማድረግ፡፡ የውጭ ሀገር ጉዲፌቻ ከቆመ በኋላ ወላጅ ያልተገኘላቸው ልጆች ሙሉ ህይወታቸውን በማቆያው ማሳለፍ ስለሌለባቸው በሀገር ውስጥ ጉዲፌቻ ፕሮግራም አዲስ ቤተሰብ ማገናኘት፡፡ (የሀገር ውስጥ ጉዲፌቻው የሚከናወነው በተቀመጠው ህግ መሰረት ከጤና ጀምሮ አስፈላጊውን መስፈርት ሁሉ አሳዳጊው አሟልቶ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡) ቤታኒያ ክርስቲያን ሰርቪስ በሚባል ድርጅት ድጋፍ ጊዜያዊ ቤተሰብ ለልጆቹ ማገናኘት፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የደሃ ደሃ የሆኑና ያረገዙ እናቶችን መንከባከብ፤ ሴቶችን በማደራጀትና አራት አራት ሺ ብር በመስጠት ስራ ፈጥሮ ራሳቸውን እንዲችሉ ማብቃት፡፡ ለህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች ማከናወን። ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን መንከባከብና በዋናነት የቤት እድሳት ማከናወን ለዚህም እንደ ቤቱ ሁኔታ እስከ ሶስት መቶ ሺ ብር ወጪ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪ በጸጉር ስራ ለስላሳ አንድ ሴቶች ስልጠና ተሰጥቶ እቃ ተሟልቶና የቤት ኪራይ ለስድስት ወር ተከፍሎ ራሳቸውን እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም በአስራ አራት ወረዳዎች በሁለት ዙር አምስት መቶ ለሚደርሱ እናቶች በአቅም ማጎልበቻ ፕሮግራም የስራ አድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ ለአርባ ሁለት ዜጎች በቋሚነት የስራ እድል በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ተቋሙ እስካሁን ሲሰራ የነበረው አብዛኞቹ ህጻናት ከአጎራባች አካባቢዎች የሚመጡ በመሆናቸው በዋናነት አዋሳ ከተማን መነሻ በማድረግ (በወቅቱ) የሲዳማ ዞን የሚባለውንና ከፊል ጌዲኦ፤ ሀድያ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ህጻናትን መታደግ የቻለ ቢሆንም ሁሌም ቢሆን ለልጆች ማደጊያ የሚመረጠው ተቋም ሳይሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ሆነው መሆኑን ያምናል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ በስፋት ማህበረሰቡ ውስጥ በመስራት ልጆች ከቤተሰብ እንዳይለዩ ማስተማር፡፡ በተለያዩ ከባድ ምክንያቶች ከወላጆቻቸው ጋር መቆየት የማይችሉበት ሁኔታ ከተፈጠረም እዛው በዘመድ አልያም ጎረቤት ጋር ሆነው ከማህበረሰቡ ሳይለዩ እንዲደገፉ ለማድረግ የሚሰራ ይሆናል፡፡ በተለይም እድሜያቸው ከፍ ከፍ ያሉ ልጆችን ተቋማትም ሆነ ግለሰብም የመቀበል እድሉ ዝቅተኛ በመሆኑ እነዚህን ለመታደግም ተቋሙ የራሱን ፕሮግራም ለመቅረጽ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ሲሉ ፕሮግራም ኮኦርድኔተሩ አቶ ተሾመ ተፈሪ ተናግረዋል፡፡
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12/2013