ማዝገሚያ፡- ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ቱማታ፤ ታላላቅ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ሲጠቀሙባቸው ከኖሩት አባባሎች መካከል አንዱ፤ “ዓለማችን በቀዳሚ ዘመናት በዋነኛነት ስትመራ፣ ስትታመስና ስትተረማመስ የኖረችው በአንደበትና በጣት ፊትአውራሪነት ይመስላል” የሚለው ሀቲት (Theory) በእጅጉ ተዘውትሮ ሲጻፍበትና ሲተነተን የኖረ መሪ ሃሳብ ነው፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ጋር የተቆራኘውን ይህንን ፈርጠም ያለ ሃሳብ ከዛሬው ዓለም አቀፍ አውነታዎችና ከራሳችን ጉዳዮች ጋር እያጎዳኘን በጥቂቱ ለማፍታታት እንሞክራለን፡፡
ወደኋላችን ትተነው በመጣነው በሩቅ ዘመናትና በቅርብ ጊዜያቱ ተሞክሮ ዓለማችን በዋነኛነት ስትናጥ የኖረችው በአንደበት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በተካኑና የጠመንጃ ቃታ እየሳቡ ለሰላም ፀር በሆኑ አምባገነኖች አማካይነት ነበር፡፡ የምላሱ ዘመቻ (ፕሮፓጋንዳው) በጣት ከሚሳበው የጠመንጃ ላንቃ ጋር በማበር ሲፈጸም የኖረው የጉልበተኞች የጦርነት ወረራ ምን መልክ እንደነበረው የዓለማችን ታሪክ መረጃውን በገፍ ይዘረግፍልናል፡፡
ይህ ዘመን ያሸበተው የአንደበት ፕሮፓጋንዳና የጠብመንጃ ጉልበት በሌላው ገጽታ መተዋወቅ የጀመረው በፈጣን ሩጫ ላይ የሚገኘው የቴክኖሎጂ ዕድገት ሥር እየሰደደ መሄድ ሲጀምር ነው፡፡ በዚህ ፈጣን የዓለማችን የሳይንስ ሩጫ እንደ ካሁን ቀደምት ዘመናት በመጀመሪያ የምላስ ፕሮፓጋንዳ ቀጥሎ የጠብመንጃ ቃታ እየተሳበ “ሕጋዊ መልክ ተላብሶም ሆነ ይሁነኝ ተብሎ በአምባ ገነኖች ‹ተልካሻ› ዓላማ በመገፋፋት ጦርነት አይጋጋልም”፡፡ ዘመኑም፣ ትውልዱም፣ ቴክኖሎጂውም መጥቋል፣ ተራቋል፡፡ ይሞከር ቢባልም እንኳ አንድም ጅልነት አለያም በራስ እጅ የራስን መቃብር የመቆፈር ያህል የከፋ ይሆናል፡፡ ይህንን ወፈር ያለ ሃሳብ ጥቂት እንገላልጠው፡፡
የኮምፒውተር ቴክኖሎጂና እውቀት በዓለማችን ላይ መተዋወቅ በጀመረበት “የጨቅላነት ዘመን” በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚጎርፉ መረጃዎችን በአንድ ቋት ማጨቅ (File/Store) ሲጀመርና በዋነኛነትም ለሚዲያ ፍጆታነት ለማዋል መቀራመት ሲጀመር “ዓለማችን እንደ አንድ አነስተኛ መንደር እየጠበበች” መሆኗን ለማብሰር “Global Village” የሚል ስያሜ መተዋወቅ ጀመረ፡፡ ይህንን ስያሜ እ.ኤ.አ በ1962 ዓ.ም በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ ያስተዋወቁት በብዙኃን መገናኛ ዘርፍ ምርምርና ጥናት በማድረግ አንቱታን ያተረፉትና በዘርፉ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ካናዳዊው የሚዲያ ቲዮሪስት ማርሻል ሚክልሃን (Marshal McLuhan) ናቸው፡፡
በመቀጠልም የተራቀቁ የቴሌቪዥንና የዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮች ተፈብረከው በስፋት አገልግሎት ላይ በመዋል የእያንዳንዱ ቤተሰብ መገልገያ መሆን ሲጀምሩና እንደ ልብ መረጃዎችን መቀበልና መላክ ሲጀመር ዓለም ከአንድ አነስተኛ መንደር ጠባ የቤት ያህል ማነስ ጀመረች እየተባለ “መዘመር” ጀመረ፡፡ ይህም ሀቲት (Theory) እሶሶ እየተባለ የተንቆለጳጰሰው ለጥቂት ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ በጭናችን ላይ አስቀምጠን የምንገለገልበት የላፕቶፕ (Laptop) ኮምፒውተር (Lap ማለት ጭን ማለት መሆኑን ልብ ይሏል) መተዋወቅ ሲጀምር “ዓለም ከቤትም ጠባ ወደ ጭናችን ቀረበች” እየተባለ አድናቆቱ መዥጎድጎድ ጀመር፡፡
የላፕቶፕ ኮምፒውተር እየመሸበት በመዳፍ ላይ አስቀምጠን የምንገለግልባቸው የእጅ ስልኮችና ኮምፒውተሮች (Palm top computers) ተፈብርከው በስፋት አገልግሎት ላይ መዋል ሲጀምሩ ሀቲቱ “ዓለም በመዳፋችን ገባች” በሚል ፉከራ ተለወጠ፡፡ አለመታደል ሆኖ ይህን መሰሉ ቀረርቶ የሰነበተው ለተወሰኑና ለጥቂት ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ በሁለት ጣቶች ብቻ ተይዘው የሚዘወሩ ሚጢጢ ኮምፒውተሮች (Finger top computers) የዓለምን ገበያ ማጥለቅለቅ እንደጀመሩ “ዓለም በሁለት ጣቶቻችን ውስጥ ተማረከች” እየተባለ ማስተጋባት ተጀመረ፡፡
ዓለም እንደ መንደር፣ እንደ ቤት፣ እንደ መዳፍ መጥበብ ብቻም ሳይሆን በሁለት ጣታችን ውስጥ ገብታ የመወሸቋን እውነትነት የምናረጋግጠው ዛሬ የደረስንበትን ደረጃ ዋቢ በማቆም ነው፡፡ ምን ማለት ነው? ጥቂት እናብራራው፡፡ የትኛውም የዓለም ዜጋ ዕሜና የእውቀት ደረጃ ሳይገድበው ዛሬ የእጅ ስልኩን በመነካካት ብቻ መረጃውን ከፈለገበት ቋት ፈልፍሎ በማውጣት በሰኮንዶች ጊዜ ውስጥ ዓለምን ወደ ማሰስ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ያለ ምንም ማጋነን እኛን ጨምሮ የትኛውም የዓለማችን ዜጋ ለመረጃ ሀሰሳና ለግንኙነት የእጅ ስልኩን በጣቱ ሳይነካካ የሚውል ማግኘት ብርቅ የመሆን ወቅት ላይ መደረሱም አዲስ ነገር አይደለም። ስለዚህም ነው ዓለማችን በጣታችን ውስጥ ገብታ እያሾርናት ነው የሚባለው፡፡
ለሥነ ምግባራቸው ያልታመኑ ሚዲያዎች፤
በመንደርደሪያው ክፍል ለማመላከት እንደተሞከረው የዛሬዋ ዓለማችንም እየተናጠች ያለችው ቅርጹ ቢለያይም የይዘት ተመሳሳይነት ባለውና በፍጥነት እየተራቀቀ ባለው ቴክኖሎጂ አማካይነት በየሰኮንዱ በሚዥጎደጎደው የአላባና የገለባ ክምር መረጃዎችና የፈጠራ ወሬዎች አማካይነት ነው፡፡ ስለዚህም ይመስላል የዘርፉ ባለሙያዎች የዘመናችንን የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች “A blessing in disguise” በማለት የሚገልጹት፡፡ ይህንን ሃሳብ በእኛው ቋንቋ በተቀራራቢነት እንተርጉመው ካልን “በረከተ መርገም” ልንለው እንችላለን፡፡
ይህ ዘመነ ሳይንስ ወቴክኖሎጂ “ሉላዊ ዓለም- Global World” በተለይም ለእኛ መሰል ታዳጊ ሀገራት የበረከትነቱ ዳረጎት እንደተጠበቀ ሆኖ ይበልጥ ግን በአስካሪ እንክርዳድ ተመስሎ መርገምትነቱ የገነነ ይመስላል፡፡ “ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ፈጃት፤ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” እንዲል ብሂሉ እኛም ከዚህን መሰሉ ዘመን ወለድ ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ራሳችንን ለመከላከል አቅም አዳብረናል ብለን በድፍረት መናገር አንችልም፡፡
በተለይም ዛሬ ሀገራችን የምትገኝበት ፈታኝ ወቅት ይበልጥ እንዲወሳሰብ በዋነኛ ምክንያትነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል አንድ ሁለቱን ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚከተለው መጠቃቀስ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ተግዳሮት ከአሸባሪው ትህነግ ውሸታም መንታ ምላሶች በየሚዲያው የሚርከፈከፈው የሥነ ልቦና ጦርነቱና ፕሮፓጋንዳው በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ነፍሱ ልትወጣ በማጣጣር ላይ ያለው ይህ የጥቂት ርዝራዦች ቡድን “ጉድጓዱ ተምሶ፤ ልጡ ርሶ” እስትንፋሱ ጭል ጭል እያለ የሚንፈራገጠው ዓለም አቀፋዊውና ማሕበራዊ ሚድያውን እየተጠቀመ በውሸት ልሳኑ በመርበትበት እንጂ “የጠብመንጃው ቃታ አፉ ሊዘጋና” አቅሙ ተልፈስፍሶ አፈር ሊከናነብ የቀረው አንድ ሐሙስ ብቻ ነው፡፡
በተለይም ከሕዝብ በዘረፈው ሀብት ባደራጃቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ባንዳ የፕሮፓጋንዳ ሰብዓዊ ማሽኖቹ አማካይነት ሲያርከፈክፍ የሚውላቸው የውሸት ዜናዎች ክምር ከማንም የተሰወሩ አይደሉም። ከዚህ ጎን ለጎን የሙያ ሥነ ምግባራቸውን ባረከሱና የኅሊናቸውን ክብር ለሽያጭ ባቀረቡ የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያ “ጋዜጠኛ ተብዬዎች” አማካይነት የምላስና የብዕር ጦርነቱ ምን መልክ እንዳለው በግላጭ እያስተዋልን ነው። የእነዚህ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ድርጊት የሉዓላዊነትን ክብር መዳፈር ጭምር ስለሆነ የጠብመንጃ ቃታ ከሳቡብን የአሸባሪዎች ድርጊት ጋር በምንም መልኩ ልዩነት የለውም፡፡
የተከበረውን የጋዜጠኝነት ሙያ እንደ ሸቀጥ ምርት የሞቱን ቀን እየተጠባበቀ ካለው ትህነግ ገበያ እየገዙና እየቸረቸሩ የሚሸቃቅጡት እነዚህን የገዘፈ ስም ያላቸው የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እያዋረዱ ያሉት ራሳቸውን፣ ሥነምግባራቸውንና በዓመታት መካከል የገነቡትን መታወቂያቸውን ጭምር ነው፡፡
ለአብነት ያህልም የየተቋማቱ የውስጥ ኤዲቶሪያል ፖሊስ እንደተጠበቀ ሆኖ የአሜሪካ ኮንግረስ የቅርብ ክትትል የሚያደርግበትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን በሙሉ ሥልጣን የሚቆጣጠረው የFederal Communication Commission ሕግ በግልጽ የሚያስቀምጠው ያለ ማንምና ምንም ተጽእኖ በገለልተኛነት ሙያቸውን እንዲከውኑ ነው፡፡ ሕጉን ተላልፎ ወለም ዘለም የሚል ባለሙያም ሆነ የሚዲያ ተቋም የሚያርፍበት ሕጋዊ በትርና መቀጮ በቀላሉ እንደማይታይ በዝርዝሩ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ ሕግ ሥር የሚተዳደረው የCNN ቴሌቪዥን ባለፉት ወራት ስለ ሀገራችን ሲዘግብ የሰነበተው ምን ዓይነት የተዛቡ ይዘቶች ያላቸውን ዜናዎች እንደነበር ልብ ይሏል፡፡
የBBC የሚዲያ ተቋምም እንዲሁ በባዕድ ቋንቋዎች ብቻም ሳይሆን በራሳችን ቋንቋዎች ጭምር የሚፈበርካቸው ዜናዎች ምን ይዘት እንዳላቸው ዕለት በዕለት እያስተዋልን ነው፡፡ ተቋሙ ከሚተዳደርበት የ“Royal Chartere” ባፈነገጠ መልኩና “አመኔታ ሀብታችን ነው!” እያሉ ከሚፎክሩበት እሴት ባፈነገጠ መልኩ “ጋዜጠኞች ተብዬዎቹ” በወቅታዊ የሀገራችንን የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ በተመለከተ የውሸት ማስረጃ እያጠናቀሩ ዓለምን ሲያደናግሩ ጥቂትም ቢሆን ኅሊናቸውን አይኮሰኩሳቸውም፡፡ ለምን ቢሉ “ትህነግ በሚያቀርብላቸው ርካሽ ጥቅማ ጥቅሞች የተነሳ ባለሙያ ነን ባዮቹ እየተደለሉ ስለረከሱ” የሚለው መላ ምት ለእውነታ ይቀርባል፡፡
በአልጄዚራ ቴሌቪዥን ኤዲቶሪያል ፖሊስ ውስጥም ጎላ ብሎ የተጠቀሰው “በእውነትና በግልጸኝነት እናገለግላለን!” የሚል ማረጋገጫና የመሃላ ያህል የከበደ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ለዚህን መሰሉ ቃል ኪዳን ተገዢዎች ነን ብለው በፊርማቸው ያረጋገጡ የተቋሙ አንዳንድ ጋዜጠኞች የትህነግ ጉርሻ እያማለላቸው እንደምን የውሸት ዘመቻ እየከፈቱ ሲፈታተኑን እንደሰነበቱ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡
በReuters ፖሊሲ ውስጥም የተጠቀሰው “Reuters news operations are based on the company’s trust principles which stipulates that the integrity, independence and freedom from bias of Reuters must be upheld at all time” የሚለው ተመሳሳይ ሃሳብ ነው፡፡
ይህን መሰሉ አስገዳጅ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የቋንቋ አጠቃቀም በየትኞቹም ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማትም ሆነ በሁሉም ሀገራት የሚዲያ አሠራር ውስጥ የተለመደ አገላለጽ ነው፡፡ አስገዳጅ እየተባለ የሚሞካሸውን ይህንን መሰሉን የሙያ ሥነምግባር ቃል ኪዳን በውሸት ዘገባ በማርከስ እነዚህን መሰል ሚዲያዎች ከአሸባሪው ቡድን ጋር በመወገን የዓለምን ማኅበረሰብ እያሳሳቱ እንዳለ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም “ቅጥረኝነትና አሸባሪነት” ስያሜያቸው ካልሆነ በስተቀር ተግባራቸው እንደማይለያይ በጥሩ ማሳያነት ቢጠቀሱ አግባብ ይሆናል፡፡
በምላሱ እየወሸከተና በጣቱ ቃታ እየሳበ መርዝ እንደቀመሰ ውሻ የሚክለፈለፈው አሸባሪው ትህነግ እነዚህን ሚዲያዎችና የእርሱን ጉርሻ ናፋቂ የውስጥና የውጭ ባንዳዎች በመጠቀም እያደረሰ ያለው ጥፋት ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ከውጤቱ እየተመለከትን ነው። “ቼ!” እያለ የተፈናጠጣቸውን እነዚህን ኃይላት ጭምር ይዞ ወደ ሞት የሚጋልበው ይህ የታሪክ ጉድ ከእብሪት ኮርቻው ላይ ተንከባሎ በመውደቅ ግባ መሬቱ መፈጸሙ እንደማይቀር እንኳንስ እኛ ባለጉዳዮቹ ቀርቶ ራሱም ቢሆን በሚገባ እንደሚገነዘበው አይጠፋንም፡፡
የውሸት ፕሮፓጋንዳ የማለዳ ፀሐይ ብቅ ስትል እንደሚከስም ጤዛ ነው፡፡ ፈካ ብላ የምትወጣው ፀሐይ ሞቅ ደመቅ ማለት ስትጀምር ጤዛው በንኖ እንደሚጠፋ ተፈጥሮ ራሷ በሚገባ አስተምራናለች፡፡ ጤዛ የሙሉ ቀናት ዕድሜ የለውም፡፡ የትህነግ እኩይ ድርጊት የሚያስታውሰንም ይህንኑ የተፈጥሮ ክስተት ነው፡፡
ሺህ ንፁሃንን አርዶ እጁን በደም መለቃለቁ፣ ሕጻናትን ለእሳት እየማገደ በግፍ እብሪት መሟሟቁ፣ ሰላማዊ ዜጎችን በማፈናቀልና በመዝረፍ ማቅራራቱ፣ የግለሰቦችን ነዋይ፣ የሀገርን ቅርስና ሀብት እያወደመ መፎከሩ የማታ ማታ ውርደትና ሽንፈት እንደሚጋት ሳያውቀው ቀርቶ አይደለም፡፡ የዓየር ሞገዳቸውን ለጊዜያዊ ጥቅም የሚሸጡ የሚዲያ ባለሙያዎችን ከጎኑ እያሰለፈም በውሸት የሚሰክረው ብቻውን ላለመሞት የሚያደርገው የጣእረ ሞት መንፈራገጥ ግድ እያለው እንጂ ሕዝባዊውን ጦርነት አሸንፋለሁ ብሎ ከልቡ ስለሚያምንም ላይሆን ይችላል፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎቹም ሆኑ ለእርሱ እኩይ ዓላማ ያደሩት የማኅበራዊ ሚዲያ ሰልፈኞቹ ቆም ብለው በማሰብ ወደ ኅሊናቸው ተመልሰው በእውነት ሽታ ጠረናቸውን እንዲለውጡ ሙት መንፈሳቸውን ለማንቃት ይህን መልእክት አስተላልፈናል፡፡ ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ ናት! ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12/2013