
ኢትዮጵያ ከቀደምት ጀግኖች አባቶችና እናቶች ለዛሬው ትውልድ የተሰጠች፤ በሕዝቦቿ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴት የተገነባች፤ በአፍሪካም ሆነ በመላው ዓለም ለሚገኙ ሕዝቦች የነፃነት እና የአንድነት ተምሳሌት የሆነች አገር ናት።
በጣሊያን ወረራ ወቅት ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተሰባስበውና ህብረታቸውን አጠናክረው ወራሪውን ጠላት በዱር በገደሉ አሳደው ድል አድርገውታል። ለዚህ ድል ያበቃቸው ደግሞ ለአገራቸው መስዋዕት ለመሆን ቆርጠው መነሳታቸው ነበር። እስከዛሬም እንደ አገር መቆም የቻለችው ያጋጠሟትን ፈተናዎች እና የተጋረጡባትን ጨቋኝ ኃይሎች ሁሉ ድል በማድረግ ታፍራና ተከብራ ነፃነቷን በማስጠበቋ ነው። ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የውጭ ወራሪዎችን ብቻ ሳይሆን የውስጥ ባንዳዎችን በማንበርከክ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነፍሳቸውን ሰውተዋል፡፡ በየዘመኑ ከሃዲዎች ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመበታተን በውስጥም በውጭም ጥረት ማድረጋቸው ከማንም የሚሰወር አይደለም፡፡
በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ህወሓት በአገዛዝ ዘመኑ የለመደውን የፖለቲካ ሴራ አሁንም በሕዝቦች መካከል ግጭት በመፍጠርና አገር እንዳይረጋጋ በማድረግ አመፅንና ሽብርን መተዳደሪያው አድርጓቸዋል። ይህ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ክህደት መፈጸም የጀመረው «ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው» በማለት የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያውያን ጋር እንዲለያይ ለማድረግ ሙከራ ከጀመረ ዕለት አንስቶ ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ በገጠሟት ችግሮች ሁሉ የቁርጥ ቀን ልጆቿ እጃቸውን አጣጥፈው ከመቀመጥ ይልቅ በተስፋ ጽናት ጠላቶቿን ለማሳፈር አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው አቆይተዋታል።
ዛሬም የእናት ጡት ነካሽ የሆነው አሸባሪው ህወሓት፣ አገርን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፡፡ የመንግሥትን የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ ለሚሸርበው ሴራ እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ የትግራይን ሕዝብ በግድ ወደ ጦርነት በመማገድ ትውልድን እያስጨረሰ ይገኛል፡፡
ይህ የሽብር ቡድን ዋነኛ ትጥቁ ውሸት ሲሆን ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም አገር አፍራሽ ውሸቶችንና ጥላቻን በመንዛት ላይ ተጠምዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ አሸባሪ ቡድን ሕፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ፣ ርዳታን በማስተጓጐል፣ እናቶችና ወጣት ሴቶችን በመድፈርና የእምነት ተቋማትን የጦር መሣሪያ መጋዘን በማድረግ ላይ ተጠምዷል፡፡ ይህ አሸባሪ ቡድን አላማ አድርጎ የተነሳው ኢትዮጵያን እንደ ዩጎዝላቪያና ሶሪያ፣ ሶማሊያና ሊቢያ ያሉ አገራት የመበታተን አደጋ ውስጥ ለማስገባት እንደመሆኑ ሕዝቦችን እርስ በእርስ የሚያጋጩ ሃሳቦችን እየረጨ፣ የሽብር ነጋሪቱን እየጎሰመ የሞት ሽረት ዘመቻውን ቀጥሏል።
በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ የአባቶችን ህብረት፣ አንድነትና አገራዊ ፍቅር በማሰብ አገሪቱ ከተደቀነባት ሴራ በተግባር በማሳየት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። የተሸረሸረውን አንድነት፣ ሕብረትና ኢትዮጵያዊ እሴት ወደ ቀደመው ለመመለስ ቃል በመግባት አሸባሪነትን በተባበረ ክንድ መዋጋት የዚህ ትውልድ ኃላፊነትም ግዴታም ነው፡፡
በአንድነት ስንቆም የተጋረጡብንን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ማሳፈር እንችላለን፡፡ ጠላቶችን ማሳፈር ስንችል ደግሞ ችግሮቻችንን በጋራ መፍታት እንችላለን፡፡ ይህን የተጠናከረ አንድነት መልካም በመሆኑ፣ ያገኘውን መልካም ዕድል ወደ ተሻለ ድል ለመለወጥ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና መጫወት በሚገባው ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
አገሪቱ እንደቀድሞዋ የተረጋጋች፣ ሰላሟና እድገቷ የተረጋገጠ ሆና እንድትቀጥልም ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ማንኛውም አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ያለምንም ልዩነት እንደ ቀድሞ አባቶቹ ዛሬም የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዘብ መቆምና ሰላማዊ አገር ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ቆርጦ መነሳት አለበት፡፡
ካለፈው ትውልድ የተረከብናትን አገር የተሻለችና የተመረጠች አድርገን ለመጪው ትውልድ የማስረከብ ርብርብ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም የእናት አገርን ጥሪ ተቀብለው በዱር በገደሉ አሸባሪውን ህወሓት የሚፋለሙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችን በገንዘብና በሃሳብ መደገፍ እንዲሁም የጠላትን ሴራ ተከታትሎ ማክሸፍ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ይህንንም በማድረግ የአሸባሪውን ህወሓት ሴራ በተባበረ የአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ክንድ ላይመለስ መስበር ይቻላል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013