
ሰላም በመንሳት የራሱ ያልሆነ አጀንዳ ተሸክሞ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል የሚደረግ ሩጫ መቋጫ ሊበጅለት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ከአብራኩ የወጡ ልጆቹ ትልቁን ኃላፊነት ወስደው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
የትግራይ ሕዝብ የሰላም ሀሁ የሚሰበክ ሕዝብ አይደለም፤ ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ብዙ ዋጋ ለመክፈል ከተገደዱ የሀገራችን ሕዝቦች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነውና። ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ የአብራክ ክፋዮቹን፤ ሀብት ንብረቱን አጥቷል። ስደትን፣ መከራ እና እንግልትን አይቷል። ብዙ ተስፋ ያደረጋቸውን ቀናቶች ተነጥቋል።
የሕዝቡ የትናንትም ሆነ የዛሬ መሻት ሰላም እና ልማት ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። እነዚህን ፍላጎቶቹን ተጨባጭ ለማድረግ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ብዙ ዋጋ ከፍሏል። ጠብመንጃ አንግቦ በረሃ ለበረሃ ተንከራቷል፤ ብዙ ልጆቹን በፍትህ እና በነጻነት ስም ለተካሄዱ ትግሎች ገብሯል። ብሩህ ነገዎችን ተስፋ አድርጎ ብዙ አስጨናቂ ቀናትን በጽናት አሳልፏል።
ይህም ሆኖ ግን ትናንት ላይ ብዙ የተዘመረላቸው የተስፋዎቹን ቀናቶች የራሱ አድርጎ እፎይ ማለት አልቻለም። ከጠባቂነት/ ከተመጽዋችነት አልወጣም፤ ስለነጻነት የወደቁ ልጆቹን ገድል እየተረከ የራሱን ዕድል በራሱ የሚወስንበትን ነጻነት መቀዳጀት ሳይችል ቀርቷል፤ የፍትህ ዜማዎችን እያዜመ የፍትህ ናፋቂ ሆኖ ዘመናትን እየተሻገረ ነው።
መሠረታዊ ለሆነው የሰላም እና የልማት ጥያቄው ምላሽ መስጠት ያልቻሉ ጽንፈኞች በስሙ ብዙ እየማሉ እና እየተገዘቱ፤ ተረጋግቶ የራሱን ሕይወት በምርጫው እንዳይኖር ዛሬም ፈተና ሆነውበታል። የራሱ ያልሆነ አጀንዳ ተሸክሞ ዛሬውን ብቻ ሳይሆን በብዙ ተስፋ የሚያደርጋቸውን ነገዎቹን ጭምር እንዲያጣ እያደረጉት ይገኛሉ።
እነዚህ ጽንፈኞች ለትግራይ ሕዝብ ጭምር አዲስ የተስፋ ብርሃን ይዞ የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ በኃይል ለመቀልበስ የትግራይን ሕዝብ መሣሪያ አድርገው ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ግልጽ የእብሪት ጦርነት ቀስቅሰው የትግራይን ሕዝብ ለከፋ መከራ እና ስቃይ፤ ሀገርንም ለብዙ ውድመት ዳርገዋል።
ፌዴራል መንግሥት ለሰላም ከነበረው እና ካለው የጸና ፍላጎት በመነሳት ጦርነቱን በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንዲቋጭ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል። ከፍ ያለ ድፍረት በሚጠይቀው በዚህ ውሳኔውም የሀገሪቱን የፖለቲካ ባህል የለወጠ የአዲስ ታሪክ ጅማሬን አብስሯል።
እነዚህ ጽንፈኞች ጦርነቱ በሰላም ስምምነት መቋጫ ካገኘ ማግስት ጀምሮ፤ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን ብዙ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሕዝቡን ዳግም መያዣ አድርገው የቡድን ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም በብዙ ተንቀሳቀስቀሰዋል።
የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዳይሆን በየወቅቱ እንቅፋቶችን በመፍጠር፤ ሕዝቡ ዘላቂ ሰላም አግኝቶ የዕለት ተለት ሕይወቱን እንዳይመራ አድርገውታል፤ ስለጦርነት እና የጦርነት ወሬዎች በስፋት በማሰራጨት፤ በሕዝቡ ሥነልቦና ላይ ጫና አሳድረዋል።
ወጣቱ ነገን ተስፋ አድርጎ ተረጋግቶ እንዳይኖር በማድረግ ለከፋ ስደት ዳርገውታል። ገበሬው የሰላም አየር እየተነፈሰ ወደ እርሻ ሥራው እንዳይሰማራ ፈተና ሆነውበታል። እናቶች ስለልጆቻቸው የወደፊት እጣ ፈንታ አስበው እንዳያርፉ የእለት ተእለት ጭንቀት ሆነውባቸዋል።
ከዚህ በከፋ መልኩ እነዚህ ጽንፈኞች ለቡድን ፍላጎታቸው ስኬት የውጪ ኃይሎችን አጀንዳ ተሸክመው የትግራይ ክልልን ዳግም የጦርነት አውድማ ለማድረግ ያለ ይሉኝታ መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። የትግራይን ሕዝብን የጦርነት ሰለባ ለማድረግም በአዲስ ፉከራ እና ቀረርቶ ክልሉን እያወኩ ይገኛሉ።
የትግራይ ሰላም የመላው ሕዝባችን ሰላም ነው። የነዚህ ጽንፈኞች የጦርነት መሻት ተጨባጭ ወደሆነ ጥፋት ሳይሸጋገር ሁሉም ዜጋ ስለሰላም ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይገባዋል። በተለይም የክልሉ ሕዝብ የሰላም መሻቱን በአደባባዮቹ ከፍ ባለ ድምጽ ጮሆ ማሰማት ይጠበቅበታል።
ለእነዚህ ሃይሎች የጥፋት አቅም የሆኑት የትግራይ የጸጥታ ሃይሎችም ቢሆን የተልእኮ መሠረታቸው ለትግራይ ሕዝብ ፍላጎት መሆኑን ተረድተው፤ ለሕዝቡ ፍላጎት ደንታቢስ ለሆኑ ጽንፈኞች የቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ከመሆን ራሱን ሊታደግ ይገባል።
ወቅቱ የጥፋት ሃይሉ ስለጥፋት ራሱን እያዘጋጀ ያለበት በመሆኑ፤ የሰላም ፈላጊ ኃይሎች ርብርብ ወሳኝ ነው። ከእዚህ አንጻር የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ስለሰላም ወደ ትግራይ ያደረጉት ጉዞ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ፤ የመላው ሕዝባችን የሰላም መሻት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የጉባዔው የሰላም ተልእኮ በትግራይ ምድር አንድም ዜጋ በጦርነት ሕይወቱ እንዳይቀጠፍ የሚያሳስብ፤ የትግራይ ሕዝብም ሆነ የመላው ሕዝባችን መሻት ሰላም እና ከሰላም የሚመነጭ የተረጋጋ ሕይወት እንደሆነ የሚያመላክት፤ ከከፋ ጥፋት መታደግ የሚያስችል ተጨማሪ ዕድል ነው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም