
አዲስ አበባ፡- ወደ ማሰልጠኛ ማዕከላት የገቡ ምልምል ሰልጣኞች የውትድርና ሙያ የሚጠይቀውን ብቃትና ዲሲፕሊን ይዘው እንዲወጡ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የአዋሽ ውትድርና ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ኮሎኔል ተረፈ ጨሪሶ አስታወቁ።
የማዕከሉ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ተረፈ ጨሪሶ እንዳስታወቁት፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በውትድርና ብቃቱ የተመረጠ እና በወታደራዊ ዲሲፕሊኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የሆነ ሰራዊት ነው። አሁንም የሀገርን ህልውና ጥሪ ተቀብለው ወደማሰልጠኛ ማዕከላት የገቡ ወጣቶች ሙያው የሚጠይቀውን አስፈላጊ ብቃትና ዲሲፕሊን ይዘው እንዲወጡ የሚያስችል ስልጠና እየተሰጣቸው ይገኛል።
ውትድርና ሙያ ከፍ ያለ ጽናትን እና የአሸናፊነት ስሜትን የሚጠይቅ ሙያ ነው ያሉት ኮሎኔል ተረፈ፤ በፍቃደኝነት ማዕከሉን የተቀላቀሉ ሰልጣኞችም የሚፈለገውን ትምህርትና ስልጠና አግኝተው እንዲወጡ አስፈላጊው ጥረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሰልጣኞቹ ጊዜያዊ ሳይሆን ቋሚ የሀገር ክብርን የማስጠበቅ ፍላጎትን ይዘው የመጡ ወጣቶች ናቸው፤ ወጣቶቹ ከቤተሰብና አካባቢያቸው ተለይተው ሰራዊቱን ሲቀላቀሉ መከላከያ ሰራዊት ደግሞ በምላሹ ሀገራዊ ግዳጅን ሊወጡ በሚችሉበት አቋም ልክ እንዲገኙ የማነጽ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በማሰልጠኛ ማዕከሉ የሚገኙ አሰልጣኞች ለምልምል ወታደሮች ሙያዊ ክህሎታቸውን እና ዕውቀታቸውን በማስተላለፍ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮሎኔል ተረፈ፤ አዳዲሶቹ ሰልጣኞችም የተሰጣቸውን ትምህርት የመቀበል አቅማቸው ጥሩ የሚባል መሆኑን አስታውቀዋል።
የአሸባሪው የህወሓት ቡድን እና ሌሎች ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አልመው መነሳታቸውን የተረዳው ወጣቱ ከየአቅጣጫው እየተመመ ሰራዊቱን በመቀላቀል ላይ ይገኛል። ከተለያየ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ማንነት የመጡትን ሰልጣኞች በበለጠ ሀገራዊ ስሜት ለማነጽ እና በውስጣቸው ያለውን የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ለማጎልበት የሚደረገው ጥረት ሳይስተጓጎል መቀጠሉንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት ታሪኩ በዓለም አቀፍ ደረጃም የተመሰከረለት ነው ያሉት ኮሎኔል ተረፈ፤ በተሰማራባቸው የጦር አውዶች የፈጸማቸውን ጀብዶችም በውትድርናው ሙያው አዲስ ነገር አውቆ ለመተግበር ያለውን ጥልቅ ፍላጎት የሚያሳይ እና የጥንካሬዎቹ ምንጭ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አዳዲሶቹ የመከላከያ ምልምል ሰልጣኞችም በማዕከላት በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ ተግባራዊ እና ክህሎት ተኮር እንዲሁም የስነአዕምሮ ክህሎት ማሳደጊያዎችን እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ኮሎኔል ተረፈ ከሆነ፤ አሸባሪው ህወሓት ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ሕፃናትን በጦር ግንባር በማሰለፍ በትውልዱ ላይ እየተጫወተ ይገኛል። መከላከያ ይህን እኩይ ቡድን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ሀገራዊ ግዳጆችም በብቃት የሚወጡ ተጨማሪ አባላትን በማሰልጠን ላይ ነው። ለዚህም መከላከያ አስፈላጊውን ግብአቶችን በሚችለው አቅም በማሟላት እየሰራ ይገኛል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም