
አዲስ አበባ፡- መቀመጫቸውን ሊቢያ በማድረግ ሰዎችን በማገት፣ በማሰቃየትና ገንዘብ በመቀበል ወንጀል የፈፀሙ 4 ግለሰቦች ከ12 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እስራት መቀጣታቸውን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ግለሰቦቹ መቀመጫቸውን ሊቢያ አገር በማድረግ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሱዳን ዜግነት ያላቸው ሰዎችን አግቶ በማስቀመጥ ወደ ቤተሰቦቻቸው ስልክ በማስደወል እያንዳንዳቸው 1 ሺ 500 ዶላር እንዲከፍሉ ማድረጋቸውን ደርሶበታል፡፡
ከዚህ ባለፈም ግለሰቦቹ የታጋቾቹን እጅና እግር አስሮ በመግረፍና በውሃ ጥም በማሰቃየት እንዲሁም በሚጠጡት ውሃ ላይ ጋዝ በመጨመር የስምንት ሰዎች ሕይወት በግፍ እንዲያልፍ አድርገዋል፡፡
አጋች ግለሰቦቹም፣ ታጋቾቹን ወደ ቤተሰቦቻቸው ስልክ በማስደወልና የስቃይ ድምፃቸውን በማሰማት ቤተሰብን ቤት፣መኪና እና ሌሎች ንብረት በማሸጥ ገንዘብ እንዲላክላቸው አድርገዋል፡፡ የተጠየቁት ገንዘብ በወቅቱ ያልሞላላቸው የታጋች ቤተሰቦች ደግሞ ከሰው ለምነው ያገኙትን ገንዘብ ቢከፍሉም የልጆቻቸውን ሕይወት መታደግ እንዳልቻሉ በወንጀል ምርመራ ቢሮ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የምርመራ ክፍል መግለጹ ታውቋል፡፡
በመሆኑም የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ለ4 ወራት ከምርመራ ቡድኑ ጋር ተቀናጅቶ ባከናወነው የምርመራ መዝገብ በማደራጀት ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመላክ ክስ እንዲመሰረትባቸው አድርጓል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክሱን ከተመለከተ በኋላ ግለሰቦቹ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ኪዳኔ ዘካሪያስ የተባለው በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እና በ1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ መቀጮ፣ አማኑኤል ይርጋን በ18 ዓመት ፅኑ እስራት፣ ሲሳይ ወዳፍይን በ16 ዓመት እንዲሁም ሳባ መንደር የተባለውን በ12 ዓመት እና በ75 ሺህ ብር መቀጮ እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡
መሰል የወንጀል ድርጊቶች ሲፈፀሙ ኅብረተሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ከፍለው ልጆቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ውጭ አገር ከመላክ እንዲቆጠቡ ሲል የወንጀል ምርመራ ቢሮው መልዕእክቱን ማስተላለፉን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም