
አዲስ አበባ፡- አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን በማፍረስ ምኞት ውስጥ ሆኖ በአማራ እና በአፋር ክልሎች እያደረሰ ያለውን ጉዳት በመከላከልም ሆነ ችግሩ ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይሰፋ በማድረግ ሂደት ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲሰለፉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ጥሪ አቀረበ፡፡
በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ አሸባሪው ህወሓት አሁን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰ ያለውና አደጋ የደቀነው በአማራና በአፋር ክልሎች ቢሆንም፤ ችግሩ ቸል ከተባለ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል፡፡ በመሆኑም ችግሩን ከመቀልበስ አኳያ ሁሉም በአንድነት በመቆም ሊመክተው ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ እውነት ይዛ በአሸባሪው ህወሓት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የውጭ ኃይሎች ጭምር በተቃራኒ እንዲቆሙ የሆኑበትን ሁኔታ እውነቱን በማጋለጥና ትክክለኛ ዘገባዎችን ወደ ሕዝብ በማድረስ ሂደቱን ለመቀልበስ መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ አበበ፤ የተጋረጠብንን አደጋ በብቃት ለመመከት መንግሥት ሁላችንንም በአንድነት ሊያስተባብር ይገባል ያሉት ኃላፊው፤ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎችን ማገዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ህወሓትን ከዚህ እኩይ ተግባር ለመግታት፣ ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ደህንነት ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ተቋማትና ግለሰቦች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በግንባር ለተሰለፉት የሠራዊት አባላት የምናደርገው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ በያለንበት አካባቢያችንን በንቃት መጠበቅ ያስፈልጋሉ ያሉት አቶ አበበ፤ በሰርጎ ገቦች አንድነታችንን ለማላላት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በትኩረት በመከታተል አገር የማዳን ርብርብ ውስጥ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ አገርን ከሚጎዱ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ዜጎች ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
በማን አለብኝነት አገርን ለማፍረስ የተነሱ አሸባሪ ኃይሎችን ለመከላከል ወጣቱ ቀዳሚ ተሰላፊ እንደሚሆን አንጠራጠርም፣ ወጣቶች በግንባር ከመሰለፍ ባለፈ ከመንግሥትና በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በአሸባሪው ህወሓትም ሆነ በሌሎች ሸሪኮች ሊፈጠር የሚችል ስጋትን በተጠንቀቅ መከታተልና መመከት እንደሚኖርባቸው አቶ አበበ አሳስበዋል፡፡
የአሸባሪዎችን እብሪት ለማስተንፈስ በሚደረገው እንቅስቃሴ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በመተው አባሎቻቸውም እንዲሳተፉ በማሳሰብም፤ ኢዜማ እንደ አገራዊ ፓርቲ የአገር ህልውናን ለማስከበር የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ፓርቲው በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ድጋፍ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እንደሚያስረክብም ጠቁመዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም