
. አካል ጉዳተኞች ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፡- የትግራይ ሕዝብ ሲበዘብዘው የኖረውን አሸባሪውን ህወሓት ሊታገለው እንደሚገባ በመከላከያ ሚኒስቴር የሎጂስቲክስ መምሪያ ፋይናንስ ሥራ አመራር ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል አስረስ አያሌው ጥሪ አቀረቡ፡፡ አካል ጉዳተኞች ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረጉ፡፡
ጀኔራል አስረስ በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የትግራይ ሕዝብ ሲበዘብዘው የኖረውን አሸባሪውን ህወሓት ሊታገለው ይገባል፡፡ አሸባሪው የህወሓት የጥፋት ቡድን እየተደመሰሰ ያለው በመላው ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ትብብር ነው፡፡
የትግራይ ሕዝብ ይህን አሸባሪ የጥፋት ቡድን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ሆኖ ሊታገለው ይገባል፡፡
‹‹በውጭ አገር የሚኖሩ የአሸባሪ ቡድኑ አባላትና ደጋፊዎች መስዋዕት አይከፍሉም፤ መስዋዕት ከፈሉ ከተባለም ሲሸነፍ አስፋልት ላይ መንከባለል ነው›› ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል አስረስ፤ መስዋዕት እየከፈለ ያለው የትግራይ ሕዝብ ስለሆነ አሸባሪውን የጥፋት ቡድን ሊታገለው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ የአሸባሪውን ህወሓት በዝባዥነትን ተረድቶ መታገል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
‹‹ለሺህ ዘመናት የተገነባች አገር በአሸባሪው ህወሓት አትፈርስም›› ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል አስረስ፤ አሸባሪው ቡድን ሙሉ በሙሉ ይደመሰሳል፣ ኅብረተሰቡ በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳዎች ሳይሸበር ሊታገለው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን 20 ሚሊዮን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን በመወከል ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርጓል፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን የአካል ጉዳተኞችም የህልውና ጉዳይ ነው በማለት ከሚያገኙት ቀንሰው ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
‹‹የአካል ጉዳተኞች ሀብታሞች አይደሉም፤ ከሚያገኙት ድጋፍ ቀንሰው መከላከያን መደገፋቸው በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው›› ብለዋል ብርጋዴር ጀኔራል አስረስ፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ወይንሸት ሙሉሰው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ መከላከያ ሠራዊት በተለይም ለአካል ጉዳተኞች አለኝታ ነው፡፡ ፀጥታ ሲደፈርስ ግንባር ቀደም ተጎጂ አካል ጉዳተኞች እንደመሆናቸው የአገርን ሰላም ለማስፈን ከአፍ ላይ ተነጥቆም ቢሆን ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
‹‹በጦርነት ወቅት እኛ አካል ጉዳተኞች ሮጠን እንኳን ማምለጥ የማንችል ነን›› ያሉት ወይዘሮ ወይንሸት፤ መከላከያ ሠራዊት እንዲህ ዓይነት አጥፊ ቡድንን ሲከላከል ግንባር ቀደም ተጠቃሚ አካል ጉዳተኛው እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንደገለጹትም፤ አካል ጉዳተኞች ችግርን የለመዱ እና ከችግር የመውጫ ብልሃትንም ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው ብለዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች ከመላው ኢትዮጵያ ጎን በመሆን ለመከላከያ የሞራል ስንቅ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ለሰላም ዘብ ለመቆም ከወር ደመወዛቸው ላይ 100 ሺህ ብር እና 40 በጎችን ለመከላከያ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አቶ አባይነህ ጠቁመዋል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም