
አዲስ አበባ:- በሥነ-አእምሮ ላይ ከሚደርሱት አደጋዎች ሁሉ በጦርነት፤ በተለይም በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የሚደርሰው አደጋ የከፋ እንደሆነ የሥነ-አእምሮ ባለሙያው ዶክተር ዳዊት አሰፋ አስታወቁ።
ዶክተር ዳዊት አሰፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ በአሁኑ ሰዓት የአእምሮ አደጋዎች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ ነው። በአጠቃላይ ችግሩ በፊት ከነበረበት ከ10 እስከ 15 በመቶ ጨምሯል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችና ጦርነቶች ናቸው።
የሰው ልጅ ሥነአእምሮ በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ይደርስበታል፤ ይሁን እንጂ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በሚደርስ አደጋ ከሚጎዳው ይልቅ በጦርነት ምክንያት የሚጎዳው እንደሚበልጥ አስታውቀዋል።
ከጦርነትም ከውጭ ጠላት ጋር በሚደረግ ጦርነት ከሚጎዳው በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የሚደርሰው የሥነ ልቦና ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ያስታወቁት ዶክተር ዳዊት፣ ለዚህም ሆነ ተብሎ፣ በማንነት ላይ ተመስርቶ የሚፈጸም ጥቃት በመሆኑ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የአእምሮ ህመምን ስናስብ የአእምሮ ደህንነትንም አብረን ማሰብ እንደሚገባ፣ በምናከናውናቸው ተግባራት ሁሉ የሰዎችን የሥነ-አእምሮና የሥነ-ልቡና ጉዳይ ማእከል አድርገን መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ጦርነት በተለይም የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት የሚያስከትለው የድህረ ጦርነት ሥነአእምሯዊ አደጋ፤ ከሕፃናት ጀምሮ ባሉት የኅብረተሰብ አባላት ላይ የሚያደርሰውን የጤና እክል በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ዳዊት፣ ከዚህ የተነሳም ግጭቶች በአስቸኳይ የሚቆሙበት ሁኔታ ሊታሰብበት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተለይ በጦርነት ወቅት በስፋት የሚሰራጨውና የሚናፈሰው የሀሰት መረጃ ከሥነ አእምሮ ህክምና አኳያ ሲመዘን ተገቢ ያልሆነ ተግባርና በማንኛውም ደረጃ ያሉ ሰዎችን ለሥነ አእምሮ አደጋ፣ ለጭንቀትና ለመሳሰሉት በማጋለጥ ያልተፈለጉ እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስገድድ የጤና ችግር ሊያመጣ እንደሚችል አስታውቀዋል።
ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት ፍፁም ትክክል እንዳልሆነ፤ ያልተፈለገ ፍርሀትን፣ ጥርጣሬንና አለመተማመንን በመፍጠር ያልተገባ ውሳኔ ላይ እንዲደረስ ያደርጋል፣ ከዚህ አንጻር ለተለያዩ ፍላጎታቸው ሲሉ ይህንን የሚፈፅሙ ወገኖች ከዚህ ተግባራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እነዚህ አካላት ለአገርና ሕዝብ ሲሉ ትክክለኛ መረጃን ብቻ ለሕዝብ ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶክተር ዳዊት፣ ኅብረተሰቡም የትኛው ትክክል እንደሆነና እንዳልሆነ በአግባቡ በመለየት ትክክለኛውን ብቻ መውሰድ ያለበት መሆኑን አመልክተዋል።
በአገሪቱ ያለውን የሥነአዕምሮ ጤና ህክምና አገልግሎት የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ የሥነአዕምሮ ጤና ስትራቴጂ ያስፈልጋታል ያሉት ሀኪሙ፣ ይህ ካልሆነ እየጨመረ የመጣውን የሥነ አእምሮ ህክምና ጤና ፍላጎት መፍታትም ሆነ አገልግሎቱን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደማይቻል ጠቁመዋል።
በተለይም በእንደዚህ ዓይነት የጦርነት ወቅትና ከጦርነት በኋላ የሚከሰቱ ሥነ-አእምሯዊ አደጋዎችን (ትራውማ)ና ሥነልቦናዊ ችግሮችን የተመለከቱ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ በረጅሙ አቅዶ መስሯት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
አሁን የገጠመንን ሥነአእምሯዊ አደጋን ከመወጣት አኳያ ኅብረተሰቡ በተቻለ መጠን መረጋጋት፣ ተገቢ የሆነ መረጃን ብቻ በመውሰድ ተገቢውን እንቅስቃሴ ማድረግና የቀውሱ አባባሽ ወገኖችም ለሕዝብና ለአገር ሲሉ ከአባባሽ ተግባራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም