
አዲስ አበባ:- ሕዝቡን በማስተባበር የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን ግብዓተ መሬት እንዲፋጠን እየሰራ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ገለጹ።
አቶ በለጠ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አብን መላው ሕዝብን በማስተባበር የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን ግብዓተ መሬት እንዲፋጠን እየሰራ ይገኛል።
የህወሓት የሽብር ቡድን ሴራና የውጭ ጣልቃ ገብነት ፍላጎትን በማጋለጥ ማህበረሰቡን በማስተባበር በአንድነት በመሰለፍ አገር የማዳን ተልዕኮን እንዲወጣ ፓርቲው የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል አቶ በለጠ።
አገር አፍራሹን የትህነግ ቡድን እና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመከላከል ረገድ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የአገርን ሉዓላዊነት እስከመጨረሻው እንዲያስጠብቅ ፓርቲው እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሽብር ቡድኑ በሥልጣን ዘመኑ አገሪቱን ለማፈራረስ የሄደበትን ረጅም ርቀት የሚያሳይ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገር የማዳኑን ሥራ ሊደግፉት ይገባል ብለዋል።
አገርን ከሽብር ቡድኑ የማዳን ጥሪን ተቀብለው በጦር ግንባር የሚገኙት አቶ በለጠ፤ የህወሓት የሽብር ቡድን በሥልጣን ዘመኑ ብዙ ጉዳቶችን በአገር ላይ አድርሷል፣ ከሥልጣኑ ከተወገደ በኋላም በግልጽ አገር የማፍረስ ድርጊቱን ቀጥሎበታል ሲሉም አስረድተዋል።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ ይህ የሽብር ቡድን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በገሃድ ከመናገሩም በላይ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ሳይቀር በመተባበር እኩይ ፍላጎቱን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ስለሆነም አሸባሪ ቡድኑ እስከመጨረሻው እንዲጠፋ ከተፈለገ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጎች በአንድ ላይ በመቆም የህልውናውን ዘመቻ ማጠናከር ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ያህል የፖለቲካ እና የአመለካከት ልዩነት ቢኖረንም በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ጊዜ በአንድ መቆምን እናውቅበታለን ያሉት አቶ በለጠ፤ አሁንም ጠላቶቻችንን በጋራ ክንድ በመመከት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እስከወዲያኛው እናስጠብቃለን ብለዋል።
አብን ማህበረሰቡን በማንቃት አገሩን ከአሸባሪዎች እና ከውጭ ጣልቃ ገቦች በመመከት ለመጪው ትውልድ ነፃነቷን በራሷ ያወጀች አገር ለማስረከብ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ሚዲያዎቻቸው እውነትን ከመዘገብ ይልቅ የሽብር ቡድኑ አጋዥ ሲሆኑ በተደጋጋሚ ታይተዋል። ይህ የሆነው ኢትዮጵያን በተለያየ የዓለም ክፍሎች ወክለው የሚገኙ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እውነታውን በሚገባ መግለጽ አልቻሉም፣ የሽብር ቡድኑና አጋሮቹ የሚጠቀሟቸው የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችም በልጠው ተገኝተዋል ብለዋል።
ስለሆነም መንግሥት እራሱን በመፈተሽ ማሻሻያዎችን በፍጥነት የማያደርግ ከሆነ አስቸጋሪ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንገባለን፤ የማንወጣው ማህበራዊ ቀውስ ውስጥም ይከተናል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
መሰረት በኃይሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም