
ጦላይ፡- አገርን ለማተራመስ በሽብር ሥራቸው በጋራ የተሰለፉትን የህወሓት ጁንታ እና ተላላኪውን ሸኔ በጋራ እንቀብራቸዋለን ሲሉ በጦላይ ማሰልጠኛ ማዕከል ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ ምልምል ወታደሮች ተናገሩ፡፡ እየተሰጠ ባለው የወታደራዊ ሳይንስ ሥልጠና መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኝ ምልምል ወታደሮቹ፣ አሸባሪው ህወሓት ለመናገር የሚከብዱ አሰቃቂ የሆኑ በደሎችን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ማድረሱን አስታውሰው፤ ዳግም አገርን ለመቆጣጠር የሚያደርገው መንጠራራት እንደማይሳካለትና ይልቁንም እርሱንና አሽከሩ ከሆነው አሸባሪ የሸኔ ቡድን ጋር እናጠፋቸዋለን ሲሉ ነው በጋራ ባሰሙት መፈክር ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ብቁ የሚያደርጋቸውን ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውንና የስልጠና አሰጣጥ ሂደቱም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

በራሷ ፈቃድና ተነሳሽነት ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል በሥልጠና ላይ እንደምትገኝ የምትናገረው የብርጌድ ሁለት፣ ሻለቃ ሁለት፣ ጋንታ ሦስት ምልምል ወታደር ማርታ ኤርቦ፤ ለአገር ህልውና ሲባል ማንኛውንም ዋጋ እንደምትከፍል ለዚህም ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡
ምልምል ወታደር ማርታ፣ ለአዲስ ዘመን እንዳለችው፤ ከውጭ ጠላት ጋር አብረው ኢትዮጵያን ሠላም የሚነሷት አሸባሪውን ጁንታና አሽከሩን ሸኔ ከአፈር ለመደባለቅ በጥሩ ወታደራዊ ቁመና ላይ ትገኛለች፡፡ የሥልጠናው አሠጣጥ ሂደትም አስደሳችና ወደ ፊት ለሚሰጣቸው ተልዕኮ እጅግ ወሳኝ እንደሆነ አመላክታለች፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ ምልምል ወታደር ታሪኩ ደሳለኝ በበኩሉ፤ ሥልጠናውን በአግባቡ እየተወጡት መሆኑን በመግለጽ፤ በቆይታው ባገኘው ልምድ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በቀጣይ ሁለቱን አሸባሪዎች ህወሓት እና ተላላኪውን ሸኔን እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የሚሞክሩትን ማናቸውንም ኃይሎች ለመመከት ብሎም ለማጥፋት በሁሉም ነገር ዝግጁ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ወደ ሥልጠናው የመጣሁበት ዋነኛ ዓላማ ጁንታውን እንዳይናሳ ለመቅበር ቢሆንም፤ ከጁንታው ጋር በጥምረት አገርን አፈርሳለሁ የሚለውን የሽብር ኃይል ሸኔም አብሮ ለመቅበር መዘጋጀቱን የሚገልጸው ምልምል ወታደር ታሪኩ፤ ከዚህም ባሻገር አገር ከእርሱ የምትጠብቅባቸውን የትኛውንም ዓይነት ተልዕኮ ለመቀበልና ለአገር አንድነትና ሠላም ለመቆም የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡ በአገር ሽማግሌና በሃይማኖት አባቶች የተሠጠውን አደራ ተቀብሎም ግዳጁን በአግባቡ በመወጣት እንደሚፈጽም መዘጋጀቱን ነው የጠቀሰው፡፡
በትልቅ ሞራል ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል ወስኖ ማሰልጠኛ እንደገባ የሚናገረው ምልምል ወታደር ብሩክ በየነ በበኩሉ፤ ኢትዮጵያን በማወክ እንዳሻው መፈንጨት የሚያስበውን አሸባሪ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፋለም ያለውን ዝግጁነት ገልጿል፡፡ ለዚህም በሥልጠናው ወቅት የሚያካብተውን ልምድ መጠቀም ተገቢ በመሆኑ ሥልጠናውን በሚገባ እየወሰደ እንደሆነና በዚያም ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሰሞኑን ወደማሰልጠኛው በመሄድ ለምልምል ወታደሮቹ የሞራል ድጋፍ ያደረጉላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞም፤ ምልምል ወታደሮቹ በተለይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሥፍራው ተገኝተው ባደረጉላቸው የሞራል ድጋፍና ወኔ ቀስቃሽ ትእይንቶች መደሰታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በወቅቱም ጁንታውንና ተላላኪውን ሸኔ በጋራ እንቀብራቸዋለን የሚል የጋራ መፈክር አሰምተዋል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም