
አዲስ አበባ፡- የአሸባሪውን ህወሓት ግብዓተ መሬቱን ለማፋጠን ሁሉም ሀገር ወዳድ በጋራ ሊረባረብ እንደሚገባ በአሜሪካ አገር የቀድሞው የሀገር መከላከያና ፖሊስ ሠራዊት ማህበር አባል ሻለቃ አበበ ይመኑ አሳሰቡ።
ሻለቃ አበበ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን በሽብርተኝነት የተፈረጀ በመሆኑም በሽብር ሥራው ከመበሳጨት ግብዓተ መሬቱን ለማፋጠን ሁሉም ሀገር ወዳድ በጋራ ሊረባረብ ይገባል።
ከለውጡ በኋላ በተደራጀው የመከላከያ ሠራዊት አሸባሪው ህወሓት አጥፍቶት የነበረውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት መመልከታቸውን ያስታወቁት ሻለቃ አበበ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በድጋሚ ተቀላቅሎ ወደ ውጊያ ከመግባት ጀምሮ ሀገር በምትፈልጋቸው በማንኛውም መስክ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እኔ ሥልጣን ካልያዝኩ ሀገር ይፍረስ በሚል ሀገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ለመመከት ለሀገር ለመሞት ዝግጁ መሆናቸውን ያመለከቱት ሻለቃ አበበ፣ ‹‹ይሄ ዝግጁነት የእኔ ብቻ ሳይሆን እዚያ የሚገኙ የሁሉም ጓደኞቼ ነው፤ የእኛ ፍላጎት ምንጊዜም ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ነው ብለዋል። ››
ከዚህ ቀደም ወያኔ ሥልጣን ከመያዙ በፊት ለአራት ዓመታት ከቡድኑ ጋር መዋጋታቸውን ያስታወሱት ሻለቃ አበበ ‹‹እነሱ ምንጊዜም ቢሆን ሳይችሉ ሲቀሩ ውጊያውን ወደ ሕዝቡ እንደሚያስተላልፉት አስታውቀዋል።
ከዚያ በኋላ በአቦሰጥ ነው እንደልምድ አዋላጅ በዚህ ቦታ ሂዱ ያዙ ብለው የተወሰነ ሰው ይልካሉ። እነዚያ የተላኩ ሰዎች እንደምንም ተሽሎክልከው የሆነ ቦታ ይይዛሉ። በዚህም ወደፊት እየገሰገስን ነው በሚል ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡ ወደ ጦርነቱ እንዲገባ ያደርጋሉ። ሕዝቡ በዚህ የቆየ ፕሮፓጋንዳ መታለል እንደሌለበት አመልክተዋል።
የቡድኑ ደጋፊዎች ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል በችግር እየኖረ ከሀገር በተዘረፈ ገንዘብ በተለያዩ ሀገራት በድሎት መኖራቸው አልበቃ ብሏቸው፤ ከሀገር እና ከወገን በተሰረቀ ገንዘብ ዓለም አቀፍ ተፅእኖ ለመፍጠር እየተራሯጡ መሆኑን ገልፀዋል።
ሕፃናትን በጦርነት ማሳተፍ እና ስደተኞች ላይ ጉዳት ማድረስ ዓለም አቀፍ ወንጀል ቢሆንም፤ የጁንታው ቡድን በሽብርተኝነት የተፈረጀው በዚህ እና በሌሎች የሽብር ሥራው በመሆኑ ከመገረም ይልቅ ለግብዓተ መሬቱ ሁሉም ሀገር ወዳድ በጋራ ሊረባረብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም