
አዲስ አበባ፡- ዛሬ ላይ ጫና ፈጣሪ ነን የሚሉ አገራት ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ከመሆኗም በተጨማሪ የምታደርገውን ጠንቅቃ የምታውቅ፣ በየዘመኑ የተነሱባትን ጠላቶች አሳፍራ የመመለስ ታሪክ ያላት አገር የመሆኗን ታሪክ በአግባቡ ባለማወቃቸው ምክንያት እየሳቱ ናቸው ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌዴሌቦ ገለጹ፡፡
ፕሮፌሰር ላጲሶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ከመሆኗም በተጨማሪ የምታደርገውን ጠንቅቃ የምታውቅ አገር ነች፡፡ በየዘመኑ የተነሱባትን ጠላቶችም አሳፍራ የመመለስ እንጂ የሽንፈትና የተላላኪነት ታሪክ ያላት አገር አይደለችም፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን ላይ ጫና ፈጣሪ ነን የሚሉ አገራት እየተሳሳቱ ያሉት ታሪክን በአግባቡ ባለማወቃቸው ነው፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ላጲሶ ገለጻ፤ የአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ኃይል ግዛቴን አላስደፍርም በሚል ተጋድሎ ያደረጉበትና ድንቅ ድል ያስመዘገቡበት ህያው ምስክር ነው፡፡ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር የአሸባሪው ህወሓት እና ጀሌዎቹን ህልውና በማቆየት የራስን ፍላጎት ለማሳካት የሚደረገው ያልተገባ ጫናም ይሄን ታሪክ ካለመገንዘብ የሚመነጭ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የአልደፈርና አልበገር ባይነት የታሪክ ገጽ የሚነበበው ድል አድራጊነት ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ላጲሶ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በባህሪው መገዛትን የማያውቅ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም የቋንቋ ብዛት ሳይለየው ለሚመጣው ነገር ሁሉ የሚተባበር፣ በህብረት ቆሞም ድል የሚያደርግ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በየትኛውም ዘመን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ለማንም ተገዝቶ ካለማወቁም በላይ ስለ አፍሪካ ነፃነትና አንድነት የሚያቀነቅን መሆኑን በማውሳትም፤ የአጼ ኃይለሥላሴ አፍሪካን አንድ አድርገው ያስተባበሩበትን አካሄድ ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ። በዚህ ተግባራቸውም የኢትዮጵያ ነገስታትና መሪዎች በየትኛውም መልክ ጠላት ኢትዮጵያን ለመድፈር በተነሳ ጊዜ የየራሳቸውን ተጋሎ ፈጽመው የዛሬዋን ኢትዮጵያ ለትውልድ ያቆዩ፤ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ያሉትም ኢትዮጵያውያንን አንድ ለማድረግና ለማስተባበር ተነስተው ለዓላማቸው እስከመሰዋት የደረሱ ስለመሆናቸውም ያስረዳሉ።
ዛሬ ላይ በሽብር ተግባር ላይ የተሰማራው ህወሓት ቀደም ሲልም ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲወጋ እንደነበር ያስታወሱት ፕሮፌሰር ላጲሶ፤ ወደሥልጣን የወጣውም በአሜሪካን መንግሥት ድጋፍ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ፕሮፌሰር ላጲሶ እንደሚገልጹት፤ በአሸባሪው ህወሓት እና በአሜሪካ መካከል እንደታየው ጥምረት ዓይነት ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጪም ለማጥፋት የሚሞክሩት በጣም ብዙ ናቸው። ዛሬም እየታየ ያለው ጫና የዚሁ ታሪካዊ ጥምረት ሂደት ሲሆን፤ ሌሎች ሊያውቁት ባይፈልጉም፣ ተጽዕኖው በአሜሪካም ሆነ በሌላው በኩል ቢበረታም ኢትዮጵያውያን ሸብረክ የማለት ባህሪ ዛሬም ሆነ ትናንት የሌላቸውና የማይኖራቸው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
አሜሪካም አሁን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ በማድረጉ በኩል ከልክ ያለፈ ጫና እያደረገች መሆኑን የሚያስረዱት ፕሮፌሰር ላጲሶ፤ አሁን እየተደረገ ያለው ጫናም ዋናው ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አገር እንዳይወስኑ ለማድረግ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ያብራራሉ። አሁን እየታየ ያለ ጫናና መሰል ተጽዕኖ ለታላቋ አገር ኢትዮጵያ ምንም እንዳልሆነ ሊረዱት ይገባል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል የመሻገር እንጂ የተሸናፊነት ታሪክ የላትም።
ዓለም የትግል ሜዳ ነው። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አምስት ታላቅ መንግሥታት ተነስተዋል። እነሱም እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ሩስያ እና ቻይና ናቸው። እነዚህ አምስት ታላላቅ መንግሥታት ባሉበት ስፍራ ደግሞ ኢትዮጵያ ኃያል ሆና ማሸነፍ ችላለች። ለማሳያም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሲደርስባት የነበረውን ጫናና ውጣ ውረድ ተሻግራ አሳይታለች። ስለዚህም ነው የቱንም ያህል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተለያየ ጫና በተለያዩ አካላት ቢደርስም ኢትዮጵያ ግን አሸናፊ ሆና የምትታየው።
በኢትዮ-ሶማያ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ መሣሪያ ለመግዛት ለአሜሪካ በከፈለችው ገንዘብ አሜሪካ መሣሪያውን አልሰጠም ማለቷን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ላጲሶ፤ ከዚህ በኋላ ግን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫና ልታደርስ የምትችልበት መንገድ እንደሌለ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ አሜሪካ ትናንት በፈጸመችው ክህደት ኢትዮጵያን ለማዳከም ባሰበችበት ወቅት አጋር የነበረችውን ሩስያን ጨምሮ ቻይና እና ቱርክን የመሳሰሉ አገራት ዛሬም ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸው አሜሪካ እንዳሻት ተጽዕኖዋን ለመተግበር እንዳትችል የሚያደርጋት መሆኑን ያስረዳሉ።
የእነዚህ አገራት ድጋፍና አጋርነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለኢትዮጵያ አሸናፊነት መሰረቱ አማራ ወይም አፋር ተነካ ሲባል ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደተነካ አምኖ በአንድ መሰለፉ መሆኑን የሚገልጹት ፕሮፌሰር ላጲሶ፤ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ሳያስደፍሩ ለመኖራቸው፤ አሁንም የማያስደፍሩ ስለመሆናቸው ህያው ምስክር ስለመሆኑ ያብራራሉ። የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ታሪክም ተረት አይደለም፤ በመሆኑም ጫና ፈጣሪ ነን የሚሉ አካላትም ታሪክን በአግባቡ ባለማወቃቸው ነው እየሳቱ ያሉት፤ በመሆኑም ይህንን ሊያውቁ ይገባል ሲሉም ያስረዳሉ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም