የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ለተለያዩ ዘርፎች በግብዓትነት ያገለግላል። ለአንድ አገር የልማት እንቅስቃሴ መስፋፋትና የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከፍተኛ ሚናን የሚጫወት እና የላቀ አስተዋጽኦ ያለው ነው። ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያም ከዓመት ዓመት ከፍተኛ የሚባል እድገትን እያስመዘገበ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርን ጨምሮ በአጠቃላይ ልማት እና ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ ድርሻን እያበረከተ ይገኛል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢንቨስትመንቱ እየተስፋፋ በተለይም ያለቀላቸው ጥሬ ዕቃዎችን በማስገባትና እሴት በመጨመር ለማምረት የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ዕድገት እያሳዩ መጥተዋል። ይሁንና የነፍስ ወከፍ የብረት ፍጆታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገትን ተከትለው የሚከሰቱ ፍላጎቶች በአገር አቀፍ ደረጃ የብረታ ብረት ግብአት እጥረት አስከትለዋል።
የአቅርቦት እጥረቱም ላይ ውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲደመር ደግሞ ኢንዱስትሪው መራመድ የሚገባውን ያህል መራመድና በሙሉ አቅሙ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል። የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግና የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይታል። በመጨረሻም የብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች የስክራፕ ምርት በገበያ ዋጋ እንዲያገኙ ውሳኔን አስተላልፏል።
በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብረታ ብረት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ መለሰ አድማሱ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹትም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ። ይህም በተለይ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ በማማጣት ሂደት በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የራሱ ጫና አሳድሯል። ከሁሉ በላይ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ በግብዓት ዕጥረት ምክንያት ፈተና ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል።
ይህ በመሆኑ መንግሥት ኢንዱስትሪው ለሥራ ዕድል ፈጠራና የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ እያከናወነ ነው። ስክራፕ ምርት ከመንግሥት ተቋማት በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ውድቅዳቂ ብረታ ብረት ሽያጭ በሚከናወንበት የገበያ ዋጋ እንዲያገኙ ለማስቻል ውሳኔ አሳልፏል።
በተለይ ብረት በማቅለጥ የሚያመርቱ አማራቾች ቁርጥራጭ ብረቶችን እንደ ግብአት የሚጠቀሙበት አማራጭ ስለመኖሩ የሚጠቁሙት አቶ መለሰ፣ ውሳኔውም ማቅለጫ ያላቸው አንዳንድ አምራቾች ከውጭ የሚመጣውን ግብአት በአገር ውስጥ የሚያገኙበትና ምርታቸውን ቀጣይ እንዲያደርጉ ሁኔታ ለማመቻቸት ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ነው ያመላከቱት።
‹‹የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ቁርጥራጭ ብረቶችን የሚፈልጉ አማራቾች ከተቋማት ጋር የሚገናኙበትን የሚገበያዩበትን ትስስር ፈጥራል›› ያሉት አቶ መለሰ፣አንድ አቅላጭ ካምፓኒ ምን ያክል ስክራፕ ይፈልጋል፣ በተለያዩ ዙሮች ምን ያህልስ መግዛት ይችላል የሚለውን የሚያጠና ድልድል የሚሠራ ኮሚቴም ከራሳቸው በተወጣጡ አካላት መዋቀሩንና በዚህ ሂደት እየተሠራበት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል የውድቅዳቂ ብረታ ብረት ክምችት የሚገኝባቸውን የመንግሥት መስሪያ ቤቶችንና የልማት ድርጅቶችን በመለየት ለአቅላጭ ኢንዱስትሪዎች ምርቱ በገበያ ዋጋ በሚቀርብበት ሁኔታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል።
የኢንስትቲዩት ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹትም፣የተለየዩ አገራት ቁርጥረጭ የብረት ግብአቶችን የሚጠቀሙ በርካታ ኢንዱስትሪዎች አሉ። የስክራፕ ምርቶችም ትርፍ ናቸው ተብሎ ውድቅ አይሆኑም። በዚህም አገራት በርካታ ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ። ከወጪም ያድናሉ።
እንደ አቶ ፊጤ ገለጻ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ከውጭ ማስገባት ያልተቻለውን ጥሬ ዕቃ እንደ ሌላው ዓለም በውድቅዳቂ ብረት ተጠቅሞ ማምረት የሚቻል ነውና ኢትዮጵያም ስክራፕን በመጠቀም ሂደት ላይ ትገኛለች።
ቁርጥራጭ ብረቶች የግብአት የእጥረት መተኪያ ብቻም አይደሉም። በተለይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ባለባት አገር ትልቅ ሀብት እና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋታቸውም ዘርፈ ብዙ ነው። ለተቋማት ምቹ የሥራ አካባቢ ከመፍጠር በተጓዳኝ ተጨማሪ ገቢን ማግኘት ያስችላል። በዚህ ሂደትም ከተለያዩ ልማት ድርጅቶች፣ከከፍተኛ የትምህርት ፣መከላከያ እና ሌሎችም ተቋማት ጋር የውድቅዳቂ ብረታ ብረት ሽያጭ ስምምነት ለመፈፀም የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
አቶ ፊጤ፣ ግብአቱን የሚጠቀሙ ድርጅቶች ወደ ግዥው ሂደት የገቡት በተፈጠረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከውጭ ጥሬ ዕቃን በግዥ ማስገባት ስላልተቻለ መሆኑን አፅእኖት ሰጥተዋል። የአጭር ጊዜ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በውይይትና በመግባባት የአገር ውስጥ ውድቅዳቂ ብረትን መጠቀም መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢንዱስትሪዎችን የግብዓት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ በጊዜያዊነት በቂ የሆነ የስክራፕ ምርት ከመከላከያ ተገኝቷል። በመሆኑም ብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች ከተቋሙ በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ውድቅዳቂ ብረታ ብረት ሽያጭ በሚከናወንበት የገበያ ዋጋ ገዝተው በማምረት ለገበያ እንዲያቀርቡ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል።
ኢንዱስትሪዎች በራሳቸው ሠራተኛ እና ትራንስፖርት ቁርጥራጭ ብረቶችን ክምችቱ ካለበት ቦታ ድረስ በመሄድ የሚረከቡና ጥሬ ዕቃን ካገኙ ምርቶችን በገበያ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ገበያን በማረጋጋት ድርሻቸውን የሚወጡ ይሆናል።
በውድቅዳቂ ብረታ ብረት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና አያያዝ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው። በመሆኑም የውድቅዳቂ ብረታ ብረት ክምችት የሚገኝባቸው ተቋማትን እንዴት መለየትና ማደራጀት እንደሚገባቸው ግንዛቤ ለመፍጠር ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱም ከኢንስቲቲውቱ የተገኘ መረጃ አመላክቷል።
የብረታ ብረት የሀብት ክምችት የያዙ ተቋማትም ያለ ጥቅም ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀበት ከጥቅም ውጪ እየሆነ ያለውን ውድቅዳቂ ብረትን ለአቅላጭ ድርጅቶች በማቅረብ ተባባሪ እንዲሆኑ ተጠይቋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013