ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሐ.ወ.ሓ.ት) በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃን ስለጉዳዩ የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ነው። ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ስለጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤ ከእውነታው በእጅጉ የራቀ ሆኖ ታዝበናል። ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) አድርጎ ነበር፤ አሁንም ስለሕግ ማስከበር እርምጃው የተሳሳተ ግንዛቤ ያለው ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ክፍል ጥቂት የሚባል አይደለም።
ይህ የውሸት መረጃን የማሰራጨትና የተሳሳተ ግንዛቤን የመያዝ ችግር የተፈጠረው በመንግሥት ድክመት እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እንዲሁም በመንግሥታት ዓላማና የግል ፍላጎት ምክንያት ነው። መንግሥት ስለጉዳዩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልፅ ከማሳወቅ አንፃር የሰራው ስራ በቂ የሚባል አልነበረም (በእርግጥ መንግሥት ሁሉንም ኃላፊነት ብቻውን ሊወጣ አይችልም፤ አይገባምም። በተለይ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የዘመቻና የቅስቀሳ ስራ በሚፈልጉ ተግባራት ላይ የምሁራን፣ የተቋማት በአጠቃላይ የዜጎች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው)።
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት የራሳቸው ዓላማ አላቸው። እነዚህ አካላት በሌሎች አገራት የሚፈጠሩ ክስተቶችን የሚመለከቱትና ብያኔ የሚሰጡት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታም የሚመዝኑት ዓላማቸውንና ጥቅማቸውን መሰረት አድርገው ነው። ምዕራባውያን አገራትም ሆኑ ለመንግሥታቱ ቅርብ የሆኑት መገናኛ ብዙኃን ሰብዓዊነት፣ እውነት፣ የጋዜጠኝነት መርህ … የሚባሉትን ነገሮች ፈፅሞ አያውቋቸውም። ለእነዚህ አካላት ሰብዓዊነት፣ እውነት፣ የጋዜጠኝነት መርህ … ማለት የተቋማቸውና የመንግሥቶቻቸው ጥቅምና አቋም እንጂ በመርህ የሚነገሩት የጽንሰ ሃሳቦቹ ትክክለኛ ትርጉም አይደለም።
ሕ.ወ.ሓ.ት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ባሉ አጋሮቹ በኩል አገሪቱ ልትበታተን እንደሆነና የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀ አስመስሎ በርካታ የውሸት መረጃዎች እንዲሰራጩ አድርጓል። እነዚህን መረጃዎች ያዳመጡና የተመለከቱ ብዙ የውጭ አገራት ሰዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ መረጃዎቹን እንደወረዱ በመቀበል እንዲሁም ቡድኑ ‹‹ጥቅማችንን ያስጠብቅልናል›› ከሚለው እሳቤያቸው አንፃር ከእውነት የራቀ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ተስተውለዋል።
በሌላ በኩል ሕ.ወ.ሓ.ት አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፣ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተመራማሪ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ወዳጆችን አፍርቷል። እነዚህ ሰዎች ያልተደረገውን ነገር እንደተደረገ አድርገው የ‹‹በሬ ወለደ›› ውሸት በማሰራጨት ወዳጃቸውን ከሞት ለማትረፍ ሲታትሩ ከርመዋል።
እነዚህ መገናኛ ብዙኃንና ‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋች›› የሚባሉ ‹‹አክቲቪስቶች›› በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከሕ.ወ.ሓ.ት ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ፀብ አለን›› የሚሉ፣ ራሳቸውን አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ዲፕሎማት፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፤ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተመራማሪ ብለው የሾሙና በዚሁ ጭምብል የሚንቀሳቀሱ ጥራዝ ነጠቅ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አምባሳደሮች ናቸው። የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች እጅግ አሳዛኝም አሳፋሪም ናቸው። የሀገራችን ሰው ‹‹ነጭ ውሸት›› እንደሚለው ዓይነት መረጃ እያሰራጩ ነው።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው ዓላማ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙኃንን ያህል የተቀናጀ ዘመቻ የከፈተ አካል የለም። ቢቢሲን ጨምሮ፣ ሮይተርስ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ዘ ቴሌግራፍ፣ ሜይል ኤንድ ጋርዲያን፣ ዘ ኢንዲፔንደንትና ሌሎች በርካታ መገናኛ ብዙኃን (ድረ-ገፆችን ጨምሮ) … እነዚህ ሁሉ ‹‹መገናኛ ብዙኃን›› የውሸት ዜና በማሰራጨት ዘመቻ ተጠምደው ከርመዋል።
የእነዚህ ‹‹መገናኛ ብዙኃን›› የሐሰት ፕሮፓጋንዳና ውንጀላ ጠቅለል ያለ ምክንያት ‹‹አፍቅሮተ-ሕወሓት›› ወይም ‹‹ፀረ-ኢትዮጵያዊነት›› ነው። ይህ ሕ.ወ.ሓ.ትን የመውደድና ኢትዮጵያን የመጥላት አባዜ እንግሊዝ ከሕ.ወ.ሓ.ት ጋር ካላት ወዳጅነትና ኢትዮጵያን ከማዳከም የዘመናት ሴራዋ የሚመነጭ ነው። በመቅደላ ዝርፊያ፣ በሄዌት (ዓድዋ) ስምምነት ሴራ፣ በዓባይ ወንዝ ስምምቶች፣ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ፣ በድህረ-ፋሺስት አስተዳደርና በሌሎች ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የኢትዮጵያ ክስተቶች ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተሳተፈችው እንግሊዝ የኢትዮጵያ አንድነትና ጥንካሬ ምንጊዜም ቢሆን እንቅልፍ ይነሳታል። የሕ.ወ.ሓ.ት ዓላማና የእንግሊዝ ምኞት የተራራቀ አይደለም።
ከእንግሊዝ በተጨማሪ የሌሎች አገራት መገናኛ ብዙኃንም በዚህ የፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል። በዚህ ረገድ የአሜሪካ፣ የአውስትራሊያና የአረብ አገራት መገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ ተጠቃሾች ሆነው እናገኛቸዋለን። እነዚህ አገራት የእንግሊዝ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች እንደነበሩና ዓላማቸውም ከእንግሊዝ በኢትዮጵያ ላይ ካላት ፖሊሲ የራቀ አለመሆኑ ሲታወስ የእንግሊዝን ተልዕኮ ተቀብለው በፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻው ላይ ተሳታፊ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይሆንም።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምስቅልቅል ሴረኛ አሻራቸውን ያኖሩት፣ እ.አ.አ ከ1989 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩትና ዛሬ የተናገሩትን ነገ የማይደግሙት አቋመ ቢሱ ኸርማን ኮኸን፣ ጋዜጠኛና ተመራማሪ ብሎ ለራሱ ሹመት የሰጠው ዊልያም ዴቪሰን፣ ‹‹ተንታኝ፣ ጋዜጠኛ፣ ኢኮኖሚስት … ነን›› የሚሉት ሲሞን ማርክስ፣ ዊል ሮስ፣ ረሺድ አብዲ፣ ዊል ብራውን፣ ዴክላን ዎልሽ፣ ደቪድ ፓይሊንግ፣ ቶም ጋርድነር፣ ሎረን ታይለር፣ ጁሊያ ፓራቪቺኒ፣ ዋሲም ኮርኔት፣ አብዲ እስማኤል ሰመተር፣ ጂዮፍሪ ዮርክ፣ ዛሚራ ራሂም፣ ላቲሺያ ባደር (የሂውማን ራይተስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ሆና ሳለች ለወንጀለኞች ጥብቅና የምትቆም)፣ ኒዛር ማኔክ፣ ጀምስ ባርኔት፣ ትሬቨር ትሩማ፣ ቶቢያስ ሃግማን፣ ፊሊፕ ማይን፣ ጀምስ ዶርሴይ፣ አና ካራ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች … አሳፋሪውን ውሸታምነታቸውንና ወገንተኝነታቸውን ደጋግመው ዐሳይተውናል።
እነዚህ አካላት የሕ.ወ.ሓ.ት ባለስልጣናት ጭምር ያረጋገጡትን መከላከያ ሰራዊትን የማጥቃት የክህደት ተግባር ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ‹‹ጦርነቱን የጀመረው ማን እንደሆነ ስላልታወቀ በገለልተኛ አካል ይጣራ›› ብለው የጻፉ ጉደኞች ናቸው። ሕ.ወ.ሓ.ትን የዲሞክራሲና የመርህ ጠበቃ፤ የኢትዮጵያን መንግስት ደግሞ ፀብ ፈላጊና ራሱን መቆጣጠር የተሳነው አካል አድርገው አቅርበዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ከመመስረት ጀምሮ ለተቋማቱ ያላትን ክብርና አበርክቶ የዘነጉ የክህደት ዶሴዎችን ሲያዥጎደጉዱም ነበር። የትግራይ ሕዝብ የሽምቅ ውጊያ እንዲያርግና የተራዘመ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ለራሱም፣ ለፌደራል መንግሥትም በአጠቃላይ ለመላው ኢትዮጵያ ተጨማሪ ችግር እንዲሆን የጅል ምክር መክረዋል።
ላለፉት ወራት ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው እውነቱንም ውሸቱንም (ጥቂት እውነትና ብዙ ውሸት) ሲቀባጥሩ የከረሙት የምዕራብ መገናኛ ብዙኃን ሕ.ወ.ሓ.ት ከትግራይ አልፎ ወደ ዐማራና አፋር ክልሎች ወረራ ሲፈፅም ዐይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ፀጥ ብለዋል። ‹‹ሴቶች ተደፈሩ፣ ንብረት ተዘረፈ …›› እያለ ሲጮህ የከረመው ብዕራቸው/አፋቸው የዐማራና የአፋር ሕዝቦች ሰቆቃ ግን ደንታ አልሰጠውም። በአፋር ክልል ከ200 በላይ ንጹሃን ሲጨፈጨፉና ከሁለቱ ክልሎች ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ሲፈናቀል ወገንተኞቹ የምዕራብ ቴሌቪዥኖችና ጋዜጦች ግን አንዲትም ቃል ትንፍሽ አላሉም። ሕ.ወ.ሓ.ት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ጥሶ በርካታ ሕፃናትን ለጦርነት ሲያሰልፍ፣ ንፁሃንን ሲገድል፣ ሲዘርፍና ሲያፈናቅል እነዚህ ‹‹ጋዜጠኞች››ና ‹‹አክቲቪስቶች›› ግን የሕ.ወ.ሓ.ትን ‹‹ድል›› በኩራት እየዘገቡ ነበር።
ሕ.ወ.ሓ.ት ከፌደራል መንግሥት በተቃራኒ ሕገ-ወጥ ምርጫ ማድረጉን፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግድያዎችና መፈናቀሎች እንዲፈፀሙ ማስተባበሩን፣ ሉዓላዊት አገር በሆነችው ኤርትራ ላይ ጭምር ጥቃት መሰንዘሩን፣ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፍቶ ግድያ፣ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ እና እገታ መፈፀሙን እንዲሁም በማይካድራ ከአንድ ሺ በላይ ንፁሃንን መፍጀቱን … ሊነግሩን አይፈልጉም።
መገናኛ ብዙኃኑ መርጦ አልቃሽ/ወገንተኛ ብቻ አይደሉም፤ ውሸታሞችም ናቸው። ያልተደረገውን ነገር እንደተደረገ፤ ያልተባለውን ነገር እንደተባለ አድርገው ዜና በመስራትም የተካኑ የውሸት ቋቶች ናቸው። ‹‹የጋዜጠኝነት መርህ ፈጣሪዎች ነን›› ብለው የሚመፃደቁለት ወሬያቸው ከንቱ ቀረርቶና አስመሳይነት እንጂ እንደሚጮሁለት የእውነት መግለጫ አይደለም።
የ144 ዓመታት የእድሜ ባለፀጋ እንደሆነና 69 የፑሊትዘር ሽልማቶችን (Pulitzer Prizes) እንዳሸነፈ የሚነገርለት የአሜሪካው ዘ ዋሺንግተን ፖስት (The Washington Post) ጋዜጣ ሰሞኑን በድረ-ገፁ ባሰራጨው ዘገባ ወልዲያ ከተማ በሕ.ወ.ሓ.ት ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደገባች ገልጿል። ይህ የጋዜጣው ዘገባ ነጭ ውሸት ነው። ከዚህ ዜና በተጨማሪም ጋዜጣው ለዘገባው የሰጠው ርዕስም እጅግ የሚያሳፍር ነው። ይህን ዘገባ የተመለከቱ አንድ ምሁር ‹‹ … Ironically, the motto of Washington Post is ‹Democracy Dies in Darkness›. They better modified it as፡ “Democracy Dies in Darkness and Washington Post is the Darkness”›› በማለት ጽፈዋል።
በነገራችን ላይ አሜሪካና አጋሮቿ ሕ.ወ.ሓ.ትን ከወደቀበት ለማንሳት የሚሯሯጡት ‹‹ለትግራይ ሕዝብ አዝነው›› የሚመስለው ካለ በእጅጉ ተሸውዷል። አሜሪካ አፍጋኒስታንን፣ ሊቢያን፣ የመንን፣ ሶሪያንና ኢራቅን በመውረር አገራቱን የዜጎቻቸው ሲኦል ያደረገችው የአፍጋናውያን በታሊባን መጨቆን፣ የሊቢያውያን በጋዳፊ አገዛዝ ነፃነት ማጣት፣ የየመናውያን በአብደላ ዳሌህ መረገጥ፣ የሶሪያውያን በአሳድ መማረርና የኢራቃውያን በሳዳም መከፋት አሳስቧት እንዳልሆነ ዛሬ አገር አልባ ሆነው የሚሰቃዩት የእነዚያ አገራት ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ወራሪዎቹ እነ ጆርጅ ቡሽ፣ ባራክ ኦባማ፣ ሳማንታ ፓወርና ጓዶቻቸውም ያውቃሉ። ጉዳዩ ሌላ ነው … ነገሩ ‹‹ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ›› የሚባል አጀንዳ ነው!
በእርግጥ ለምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን፣ መንግሥታትና ተቋማት ‹‹እውነት›› ማለት ብሔራዊ ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው ነው። የሌሎች አገራት ዜጎች የመብት ጥሰት፣ ረሀብ፣ አፈናና ግድያ ጉዳያቸው እንዳልሆነ ደግመን ደጋግመን ዐይተናል። ይህን ሴረኛ ስልታቸውን በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና በደርግ መንግሥታት ዘመንም ሰርተውበታል።
በአጠቃላይ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ብንረሳቸው እንኳ ያለፉት ጥቂት ወራት የሰብዓዊነት፣ የጋዜጠኝነት መርህና የእውነት ጠበቃ እንደሆኑ የሚያወሩት ምዕራባውያን ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና መንግሥታት ከሰብዓዊነት፣ ከእውነትና ከጋዜጠኝነት መርሆች ጋር ፈፅሞ እንደማይተዋወቁና ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ ከሃዲዎች፣ ውሸታሞችና ወገንተኞች እንደሆኑ በግልጽ ያረጋገጥንባቸው ወቅቶች ናቸው።
ሕግ የማስከበሩ እንቅስቃሴ ብዙ የሴራ ትንታኔዎችን የሚጋብዝና ነገሩ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ስለሆነ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃንን ሴራ ከግምት ውስጥ ያስገባ ጠንካራ የመረጃ ዝግጅትና ጥንቃቄን የሚፈልግ ተግባር እንደሆነ ከዚህ ቀደም ጠቅሻለሁ። የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መረን የለቀቀ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ከመንግሥት ጥረት ባሻገር የምሁራንንና የዳያስፖራውን ኅብረተሰብ ጨምሮ የመላ ዜጎችን ተሳትፎና ንቅናቄ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን በድጋሚ ማሳሰብም ተገቢ ይሆናል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013