በየዕለቱ ጭማሪ የሚወልደው የሸቀጦች ዋጋ ልጓም ያለው አይመስልም። በተለይም ሀገሪቷ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት ምክንያት በማድረግ ገበያው ብቻ ሳይሆን ሸማቹ ሕብረተሰብም የተረጋጋ አይመስልም። አለመረጋጋቱ ማንኛውም ምርት አቅርቦት ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድር አድርጎታል የማያባራው የዋጋ ንረትም ሌላው የሸማቹ ስጋት ምንጭ ነው።
አቧሬ ገበያ አካባቢ መንደር ውስጥ ባለ አንድ መደብር የዳቦ ዱቄት ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ቦሰና ዘውዴም በሁለቱ ምክንያቶች ነገሮች ተምታቶባቸው አስተውለናል። ባለመደብሩ ያዘዙትን አምስት ኪሎ ዱቄት ከሰጣቸውና ወደ ቤታቸው ይዘው ለመሄድ መራመድ ከጀመሩ በኋላ ወደ ቤታቸውም፤ ወደ ሱቁም መመለስ በሚፈልግ ዓይነት ማመንታት ውስጥ ገቡ። ባለ መደብሩ ቢቸግረው በአግራሞት ምነው አላቸው። ከራሳቸው ጋር ሲመክሩ የቆዩ በሚመስል ስሜት ትንሽ ቆዩና ‹‹አይ ዱቄት ልጨምርና ልግዛ ወይስ አልጨምር እያልኩ ነው›› አሉት። መጨመር የፈለጉት አንድም ቆየት ሲል የዱቄቱ ዋጋ ሊጨምር መቻሉ፤ ሁለትም ሊያልቅ ይችላል የሚለው አስግቷቸው መሆኑን አፍርጠው ነገሩት። ይህም ሀገሪቱ ካለችበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ በግልጽ አለመረጋጋት ውስጥ እንዳስገባቸው ከፊታቸው ይነበባል። ከዚህ ስጋት የተነሳ ብዙ ሸማቾች ባላቸው አቅም ማናቸውንም ምርቶች ገዝተው ሲያከማቹ ይስተዋላል።
ነጋዴውም ከዛሬ ይልቅ ነገ በተሻለ ዋጋ እንደሚሸጠው እርግጠኛ በመሆኑ ገዝቶ በማከማቸቱም ያከማቸውን በመደበቅም ኢኮኖሚያዊ አሻጥር መሥራትን ተክኖበታል። የአቧሬው ዱቄት ነጋዴ ከድር ሸምሱ ራሱን በዚህ ቁመና መግለጽ ባይፈልግም ሌሎች እንዲህ ዓይነት ነጋዴዎች መኖራቸውን ባስተዋልነው በወይዘሮዋና በእሱ መካከል የነበረ ግብይት አጋጣሚ ገልጾልናል። ከዚህ ግብይት ሂደት እንደተረዳነው ለዋጋ ንረቱ መባባስ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ከጦርነት ጋር የተያያዘ ሁኔታ የራሱን ጫና ፈጥሯል። ሸማቹ ተረጋግቶ እንዲገበያይ ካለማስቻሉ ባሻገር ስጋት ውስጥም እየከተተው መሆኑንም በግልጽ ማየት ይቻላል።
የኢኮኖሚክስ ባለሙያዋ ምዕልተወርቅ ታፈሰወርቅ እንደሚናገሩትም በጥናት ያልተደገፈ ግምታቸው ቢሆንም 90 በመቶው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ምንጩ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ያልተረጋጋ ሁኔታ ነው። አሥር በመቶው ደግሞ በስግብግብ ነጋዴዎች የመጣ መሆኑንም ይጠቁማሉ። የአቅርቦት እጥረትንም ከዚሁ ጋር አሰናስለው ያነሳሉ። እንደሚጠቁሙት የምርት እጥረት ቢኖርም አሁን ባለው ሁኔታ መጋነኑ ግን ስግብግብ ነጋዴዎች ባርከፈከፉት ቤንዚን ነው። በየዕለቱ እንደሚጨምር ያውቃሉ። በመሆኑም ያለውን በተመጣጣኝ ዋጋ አቅርቦ አዲስ ምርት ከማስገባት ይልቅ በተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ ማከማቸቱን ይመርጣሉ። ይህም በግልጽ እየታየ ነው የሚገኘው። የምርት እጥረቱም በአብዛኛው ጠባቂ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመጣ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ሌላው የምርት እጥረቱም ሆነ የዋጋ ንረቱ ምክንያት ነው ያሉት ጠባቂው መብዛቱን ነው። አሁን በሀገራችን ባለው ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች አምራቹ ለማምረት ሚያስችለውን ምቹ ሁኔታ አለማግኘቱም ይደመራል። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ራሱ ሀገሩን ለማዳን ወደ የሚያስችል ጦርነት እየገባ ነው። እሱም ከአምራችነት ወደ ገበያ ጠባቂነት እየተሸጋገረ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም በማምረት ሂደት ውስጥ አይደለም።
አብዛኞቹ ቻይናዊያን ከገበያ ጠባቂነት ለመላቀቅ በሰማይ ጠቀስ ሕንፃቸው ላይ ከቃርያና ጎመን ጀምሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አምርቶ የመጠቀም ልምድ አላቸው። በእኛ ሀገር ይህ ባለመለመዱ ሁሉም የገበያ ጠባቂ ነው። አንዳንድ አካባቢዎች የከተማ ግብርና ቢኖርም እንዲህ ባለ ምርት ስርዓት የዘመነ አለመሆኑ ለዋጋ ንረቱና ኑሮ ውድነቱ መባባስ አስተዋፅኦ አድርጓል። ባለሙያዋ እንዳወሱት የትራንስፖርቱ ንረትም ከምክንያትነት አይዘልም።
ባለ ሀብቱ ባለው የጦርነት ሁኔታ ንብረቱን በራስ መተማመን መንፈስ እንዲልክ አላስቻለውም። ደረቅ የጭነት መኪኖች በአብዛኛው ቆመዋል። ስጋቱ ከወደብ ላይ መነሳት አላስቻላቸውም። በሱዳንና ሌሎች በሮች ወደ ሀገር በሚገቡ ምርቶች በአብዛኛው ስጋት ባለባቸው የሀገራችን አካባቢዎች በሚመላለሱት ቢወሰንም ስጋት በሌለባቸው እንደ ቡና ያሉ የሀገር ውስጥ ምርቶች ዋጋ ሊንር የቻለበትን ምክንያት አያካትትም። በመሆኑም በመንግሥት መታየት አለበት። ‹‹ነዳጅ ባለፉት ሦስት ወራት ባለበት ነው ያለው›› የሚሉት ባለሙያዋ ምክንያት እንደማይሆንም ይጠቅሳሉ። እንደ ባለሙያዋ ለዋጋ ንረቱና ኑሮ ውድነቱ መባባስ ዋንኛው ነፃ ገበያው ነው። ነፃ ገበያ የሚስፈልገው ከፍተኛ የምርት አቅርቦት ላላቸው ሀገራት ነው።
በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱን አባብሰውታል። ስለዚህ ገበያውን ለማረጋጋትና የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት በገበያው ጣልቃ መግባት አለበት። የምርት አቅርቦት መጨመር አለብን። ከቻይና ልምድ በመውሰድ ሁሉም ዜጎች የገበያ ጠባቂ ከሚሆኑበት አባዜም መውጣት ያስፈልጋል። በተለይም ኢትዮጵያ ተረጋግታ ኢኮኖሚዋን እንዳትገነባ ያደረጋትን እንዲሁም ለገበያው አለመረጋጋትና ለኑሮ ውድነት መንስኤ የሆነውን ሀገርን የማስከበር የህልውና ዘመቻ መስዕዋትነት ከፍሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጨት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013