ዛሬ ስለ “ሎሚ ተራ ተራ …” ለማውራት አቅደን አይደለም ጉዳዩን በርእሳችን ያነሳነው። ያነሳነው የሚገጥም ነገር ስላጋጠመን ነው።
በአዲስ አበባ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እንቅስቃሴ ከሚታወቁት መካከል ዋናው ንግድ ነው። ንግድ ደግሞ ገበያ ይፈልጋልና ከገበያዎቹም አንዱና ዋናው አትክልት ተራ ነው። ዛሬ ከመሀል ፒያሳ ወደ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ከተዛወረም በኋላ ይሁን ከመዛወሩ በፊት “አትክልት ተራ” የከተማዋ ከፍተኛ የገበያ ማዕከል ሲሆን ልዩ አቅርቦቱም ልክ እንደ ስሙ አትክልትና ፍራፍሬ ነው፤ ሎሚ ተራም እዚሁ አለ። በቃ፣ በዚህ ዘርፍ (በይዘቱ የተለየውን መርካቶ ሳይጨምር) እስከአሁን እሱን የሚያስንቅ ወይም ከእሱ የተሻለ ሁሉን አቀፍ የገበያ ስፍራም ሆነ “የሥራ ዕድል” የፈጠረ ቦታ በከተማው የተገኘ አይመስልም። ባጭሩ፣ ዘርፉን በተመለከተ “እናት ገበያ” ነው ማለት ይቻላል። በተለይ ቦታው ላይ ሆኖ ሁሉን ለተመለከተ “እናት ገበያ” የሚለው ሲያንሰው እንደሆነ ይገነዘባል።
አትክልት ተራ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች የሆኑ ሁሉ የሚገኙበት፣ በዓይነት በዓይነት 1 2 3 … ተብለው የሚቆጠሩበት የገበያ ማዕከል/ስፍራ ሲሆን፤ የሻጭ-ገዥውም ዓይነትና ብዛት በዚያው ልክ የተለያየ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ሎሚ ሻጭና ገዥው ከፍል አንዱ ነው።
አትክልት ተራ የአትክልትና ፍራፍሬ ዓይነቶች ሁሉ የሚገኙበት፣ ደንበኞች የአትክልትና ፍራፍሬ አምሮታቸውን የሚወጡበት ብቻ ሳይሆን ለበርካቶች የሥራ ዕድል አቅራቢ ስፍራ ነው።
በዚህ የአትክልት ተራ የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች በጣም በርካታና ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ሲሆኑ አብዛኞቹም ወጣቶች፤ በተለይም ታዳጊ ወጣቶች ናቸው።
አትክልት ተራ የሥራ ዕድል፣ የገቢ ምንጭና የኑሯቸው መሰረት ከሆኗቸው ዜጎች መካከል ከወላይታ ሶዶ፣ አረካ የመጡት ታዳጊዎች የ16 ዓመቱ ታዳጊ ቴዎድሮስ አረባ እና የ17 ዓመቱ ታዳጊ ምህረቱ ዋና የዛሬው የ”እንዲህም ይኖራል” አምዳችን እንግዶች ናቸው። እንደሚከተለው አነጋግረናቸዋል።
እነዚህን ሁለት ወጣቶች ያገኘናቸው በአራት ኪሎና በአምስት ኪሎ መካከል በምትገኘው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ሸዋ ዳቦ ፊት ለፊት ሲሆን፤ የእነሱ ዓይነት ሥራ ላይ የተሰማሩ የተወሰኑ ታዳጊዎች ተመሳሳይ ሥራዎችን በሚሠሩባቸው ስፍራ ነው።
(ከዚያ በፊት ግን ዘርግተው እየሸጡ ባሉባት በዛች ሁለት ክንድ በሁለት ክንድ በሆነች ስፍራ ላይ ይህ ጋዜጠኛ እያናገራቸው እያለ ደንቦች ድንገት ከኋላቸው መጥተው የያዙትን ሎሚ በእግራቸው ብትንትኑን አወጡባቸው። ልጆቹም ተበተኑ። በአካባቢው የነበረው ሰው ሎሚዎቹን ሰብስቦ ማዳበሪያቸው ላይ አደረገላቸው። እንደገና መጡና ንብረታቸውን ወስደው ቦታ ቀይረው ለመዘርጋት በመሞከር ላይ እያሉ እንደገና ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ በመሆን በተቀዛቀዘ ስሜት ካቋረጥንበት ቀጠልን። ብዙ እሚሰጡን መረጃ እንዳላቸው እያስታወቀ በተወሰደባቸው ዕርምጃ ምክንያት ወደ ውስጣቸው እንደመለሱት ፀሐፊው መገንዘቡን መግለጽ ይፈልጋል።)
የ16 ዓመቱ ታዳጊ ቴዎድሮስ አረባ እና የ17 ዓመቱ ታዳጊ ምህረቱ ዋና ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ገና አንድ ወር አካባቢ ቢሆናቸው ነው። ላየ ለተመለከታቸው ግን ከዚያ በላይ ከከተማዋ ጋር ትውውቅ ያላቸው ይመስላሉ፤ አማርኛውን ወደ ማቀላጠፉ እየሄዱ ነው። ከመኪና ጋር መገፋፋቱንና “ሽል” እያሉ ማቋረጡን ሁሉ ተክነውታል። ለምንም ነገር እንግዳ አይመስሉም። ከብዙ የአካባቢው ልጆች ጋር ይተዋወቃሉ፤ ሰላምታም ይለዋወጣሉ። ቀልጣፎችና ደፋሮች ናቸው። በደረሰባቸው የመበተንም አደጋም ይሁን በተወሰደባቸው ዕርምጃ ብዙም የተደናገጡ አይመስሉም። ባጭሩ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እሳት የላሱ የከተማዋ ነጋዴ፣ ወይም ተማሪ ወይም ሌላ እንደሚሆኑ ከወዲሁ ለመገመት አስቸጋሪ አይሆንም።
ቴዎድሮስና ምህረቱ ጓደኛሞች ናቸው። ከዚያም ባለፈ የንግድ ሸሪኮች ናቸው። የያዙት ሎሚ የጋራቸው ሲሆን፤ ሁለቱም ይሸጣሉ፤ ሁለቱም ገንዘቡን ይይዛሉ፤ ማታ ከወጪ ቀሪ በመተሳሰብ በተለመደው መሰረት ተግባራቸውን ያከናውናሉ።
በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ የተባበረኝ የበስተግራው ቴዎድሮስ ሲሆን፤ በከተማዋ የአንድ ወር ቆይታ ብቻ ያላቸው መሆኑን ከተናገረ በኋላ፤ ወደዚህ ሥራ የገቡት በቅርቡ መሆኑን፤ ከዚያ በፊት ምንም ሥራ እንዳልነበራቸው፤ ከትውልድ አካባቢያቸው እንደመጡ “ቦርኮ” (በረንዳ አዳሪ ለማለት ይመስላል) ሆነው ሁሉ እንደነበር፤ ከዚያ በኋላ ቀስ እያሉ ወደዚህ ዓይነቱ የሎሚ ንግድ እንደገቡና አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ይናገራል። (ጓደኛው ቴዎድሮስም በየመሀሉ እየገባ ማረጋገጫውን ይሰጥ ነበር።)
እነ ቴድሮስ የቢዝነስ ታሪካቸውን፣ የቢዝነሳቸውን አካሄድ፣ ትርፍና ኪሳራውን፣ የእነሱን ውሎና አዳር ወዘተ በተመለከተም አጫውተውናል።
እነ ምህረቱ እንደሚናገሩት ከሆነ በአዲስ አበባ ኑሮ በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህንንም የኑሮ ክብደት ሲያስረዱ የሚጀምሩት ከቤት ኪራይ ሲሆን፤ እሱም በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ ላይ የማደራቸው ጉዳይ ነው። (በነገራችን ላይ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችም ከእነሱ በኋላ ለመጡት የላስቲክ ቤታቸውን እንደሚያከራዩ ይታወቃል።)
በአሁኑ ሰዓት፣ ምናልባትም የህዝብ ቁጥር ማደግን ተከትሎ ሊሆን ይችላል፣ ድሮ ያልነበረ ነገር እየታየ ሲሆን፤ እሱም ገንዘብ ለማግኘት ሲባል የጅምላ ኪራይ ቤት መኖሩ ነው።
ከተለመደው ውጪ በአንድ ቤት ውስጥ እስከ 20 እና 25 ሰዎችን የሚያሳድሩ (ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እያስገቡ በጠዋቱ 11:30 የሚያስወጡ) አከራዮች እንዳሉ በስፋት ይነገራል። የእነምህረቱም ኑሮ ከእነዚህ ይመደባል። የቤቱ ኪራይ የሚከፈለው በግል ሲሆን፤ በወር 400 ብር (ለእያንዳንዳቸው) ይከፍላሉ።
እነ ምህረቱ “ይህንን ብር ከየት ታገኛላችሁ?” ለሚባሉትም መልስ አላቸው።
ምህረቱና ጓደኛው በአንድ ቃል የነገሩን መሰረታዊ የቢዝነሳቸው ገፅታ ቢኖር መግዛት፤ አትርፎ መሸጥ። በቃ።
ከአትክልት ተራ አንድ ኪሎ በ30 ብር ይገዛሉ። ግዥው የሚፈፀመው ከትላልቅ ነጋዴዎች ሳይሆን እዛ አትክልት ተራ ከዚህም ሆነ ከዛ ብለው ከሰበሰቡ ንኡስ ነጋዴዎች ሲሆን፤ እዚህ እነሱ ባቋቋሙት ሎሚ ተራ አራቱን አስር ብር ይሸጣሉ። ውጤቱንም በአጠቃላይ “በቀን ብዙ እናተርፋለን” በማለት ይናገራሉ።
እነ ቴዎድሮስ በለሊት ወደ አትክልት ተራ ሄደው በተለመደው መሰረት ጉዳያቸውን አጠናቀው ተመልሰው እዚህ ያቋቋሙት ሎሚ ተራቸው እስኪደርሱ በርካታ እንቅስቃሴዎችን የሚያከናውኑ ሲሆን፤ ትልቁና የከበዳቸው ግን የታክሲ ክፍያ ነው። “ለሎሚያችን ሳይቀር ውድ ያስከፍሉናል” ነው የሚሉት።
እነ ምህረቱን እንድናደንቅ፣ ሌሎችም ተምሳ ሌትነታቸውን እንዲከተሉ እዚህ ስናቀርባቸውና ተምሳሌት ስናደርጋቸው ያለ ምክንያት ሳይሆን በቂ ምክንያት ስላለን ነው። ይህ በቂ ምክንያታችንም ከመግዛትና መሸጥ ሥራቸው በዘለለ ርእይ ያላቸው መሆናቸው ቀዳሚው ነው።
እነ ቴዎድሮስ ርእይ አላቸው፤ ርእያቸውም ገና ወደ እዚህ፣ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ይጀምራል። እሱም አዲስ አበባ ሄዶ፤ የተገኘውን ሥራ ሠራርቶና ገንዘብ አጠረቃቅሞ ወይ ብስክሌት፣ ጥሩ ከተሠራና ተቀማጩ ከፍ ያለ ከሆነ ደግሞ ሞተር ሳይክል፤ ከዛ ከፍ ካለ ባጃጅ ገዝቶ ወደ ትራንስፖርት ሥራ መሰማራት ነው። ለዚህም ጥርስን ነክሶ ገንዘብ መያዝ፤ መቆጠብ።
እነ ምህረቱ እንደሚናገሩት ይህን ዓላማ ለአንድም ጊዜ ከልባቸው ፍቀውት አያውቁም። ሁሌም በልባቸው ተፅፎ ያለ ለራስ የተገባ ቃል ኪዳን ነው። በመሆኑም ይህን ቃል ኪዳን ለማክበርና ርእያቸውን ለማሳካት በየቀኑ ከሚያገኙት 100 ብር ላይ 50 ብር (በየግላቸው) ተቀማጭ ያደርጋሉ። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ተምሳሌት አለ?
ሌላው እነ ቴዎድሮስን ለየት የሚያደርገውና አርአያ ይሆኑ ዘንድ የሚያስጠቅሳቸው እነሱን መሰል ወጣቶች ሳያስቡት ወደ ጎዳና ህይወት ወጥተውና በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው እዛው የሚቀሩ መሆናቸው ሲሆን፤ እነሱ ግን ከዛ ህይወት ውስጥ መንጭቀው በመውጣት ሠርተን መብላት ይሻለናል በማለት ወደ ሥራ መሰማራታቸው ነው። ይህ ውሳኔያቸው አሁን ከማህበራዊም ሆነ ሌሎች ችግሮች አኳያ እጅግ አስቸጋሪ የሆነና ችግሩንም ለመፍታት ውስብስብነቱ ያስቸገረ ከመሆኑ አኳያ እነ ቴዎድሮስ የወሰዱት ከችግሩ እራስን የማውጣት እርምጃ ሊደነቅና ሌሎችም ሊከተሉት የሚገባ ተምሳሌት ነው።
እነ ቴዎድሮስን አሁን ምንድነው የሚቸግራችሁ፣ ምንስ እንዲደረግላችሁ ነው የምትፈልጉትና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ጠይቀናቸው ፍላጎታቸውን ነግረውናል።
እንደነ ምህረቱ መልስ ከሆነ አሁን የሚደግፋቸው ሰው ወይም ድርጅት ቢያገኙ እንዲያደርግላቸው የሚፈልጉት የሊስትሮ ዕቃ ቢሰጣቸው ወይም ቢያሟላላቸው በቀጥታ ወደ ሊስትሮ ሥራ በመግባት ውጤታማ መሆን ይችላሉ። ወይም መንግሥት ትንሽ የመሸጫ ቦታ ቢሰጣቸው በተረጋጋ ሁኔታ እዛች ቦታ ላይ ሆነው ይህንን አሁን የሚሠሩትንና ሌሎች ሥራዎችን በመሥራት እቅዳቸውን ማሳካት ነው።
እኛም ከትጋታቸው፣ ርእያቸው፣ የእርስ በእርስ ትብብራቸውና ተተኪ ትውልድ ከማፍራት አኳያ ይህ ምኞታቸው እንዲሳካላቸው፤ ለስኬታቸውም አለሁ የሚላቸው እንዲያጋጥማቸው እየተመኘን ወደ ፊት ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰው እንደምንገናኝ ተስፋ በማድረግ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013