ቅድመ – ታሪክ
የገጠር ልጅ ነች። በልጅነቷ የትምህርትን ዕድል አላገኘችም። ዕድሜዋ ከፍ እንዳለ ወላጆቿ የሴትነት ሙያን አስተማሯት። ከእናቷ ስር እየዋለች የቤቱን ሥራ መከወን ልምዷ ሆነ። በአካባቢው እኩዮቿ ደብተር ይዘው ትምህርትቤት ሲሄዱ እነሱን መሆን የተመኘችበት ጊዜ ነበር።
በሰፈሩ እሷን ጨምሮ ብዙ ሴት ሕፃናት ከእናቶቻቸው እንዲውሉ ይገደዳሉ። አጋጣሚው የቀናቸው ጥቂቶች ደግሞ ከወንዶች እኩል ቀለም ቆጥረው፣ ፊደል ለይተው ይመለሳሉ። ይህን የሚያውቁ አንዳንድ ወላጆች ሴት ልጆቻቸው እንዲማሩ ወደው ይፈቅዳሉ። ፈቃዳቸው እምብዛም አይዘልቅም። ልጆቹን በየሰበቡ ከትምህርት ገበታ ያስቀራሉ።
ወይንሸትና ትምህርት ሳይገናኙ ዓመታት አለፉ። እሷ የቤቱ ቁንጮና ባለሙያ ሆና ዘለቀች። ከወላጆቿ በየቀኑ የምታገኘው ምርቃትና ምስጋና እያበረታትም በሥራ ተባተለች።
አንዳንዴ ከከተማ የሚዘልቁ ዘመዶች እነ ወይንሽት ቤት ያርፋሉ። ዘመድ ጠያቂዎቹ ከተሜዎች ገጠር ብቅ ባሉ ጊዜ ልጆች በተለየ ደስታ ይዋጣሉ። የሰዎቹ አለባበስ፣ አነጋገርና ጨዋታ ይስባቸዋል። ሁሌም ከእነሱ የሚቀበሉት የልብስና ጫማ ስጦታ ያስደስታቸዋል። ልጆቹ ታላቅ እህታቸውን ጨምሮ የአዲስ አበባ ዘመዶቻቸው የሚመጡበትን ቀን እያሰቡ በፍቅር ይቀበሏቸዋል።
የወይንሸት አስረኛ ዓመት እንዳለፈ በቤቱ ሰላም ይሉት ጠፋ። እናት አባት ጠዋት ማታ በጭቅጭቅ ታመሱ። ቀድሞ ፍቅር ውሎ የሚያድርበት ጎጆ የንትርክና የጠብ ማሳያ ሆነ። ቤተሰብ ተጨነቀ። ልጆች በሃሳብ በትካዜ ናወዙ፣ጠዋት ማታ ተሳቀቁ።
የባልና ሚስቱን ችግር እንፍታ እናስታርቅ፣ ያሉ ጣልቃ ገቡ። ጥንዶቹ ለጊዜው የሽማግሌዎችን ቃል ሰሙ። ለቀናት በሰላም ውለው በፍቅር አለፉ። ጥቂት ቆይቶ ዳግም ጠብ አገረሸ፣ ጭቅጭቅ ንትርኩ ታደሰ። አሁንም ሽማግሌዎች ለእርቅና ሰላም ጣልቃ ገቡ። የታሰበው አልሆነም። ጥንዶቹ ትዳር ሊያፈርሱ፣ ጎጆ ሊበትኑ ከውሳኔ ደረሱ።
አንድቀን ጠዋት በነወይንሸት ቤት የአዲስአበባ እንግዳ ብቅ አለ። ሰውየው የሩቅ ዘመድና ቤተኞቸው ነው። ለዓመታት ገጠር ሲመላለስ ከቤተሰቡ ውሎ ያድራል። ጨዋታው የዘመድ ነው። ቅርበቱን የሚያውቁ ፣የነወይንሸት ወላጆች ሁሌም ለመስተንግዶው ይጨነቃሉ።
እንግዳው በቤቱ ውሎ እያደረ የመጣበትን ጉዳይ ጨረሰ። አንደኛውን ከመሄዱ በፊትም ከወይንሸት ጋር የጀመረውን ጨዋታ ቀጠለ። ጨዋታውን የወደደችው ታዳጊ በሚነግራት እየተሳበች፣ በሚላት ሁሉ ተስማማች። ሰውየው አዲስ አበባ ልወስደችሽ ባላት ጊዜ አላቅማማችም። በየጊዜው የምትሰማው የከተማ ህይወት በእጅጉ አጓጓት።
የእናት አባቷ ፍቺ እውነት በሆነ ማግስት የልጅቷን አዲስአበባ መሄድ ብዙዎች በበጎ ተረጎሙት። ከገጠር ህይወት መውጣቷን የወደዱ ዘመዶችም ይሁንታቸውን ሰጡ።
የገጠሯ ጉብል ካለችበት ህይወት የከተማው እንደሚሻል አውቃለች። ከተማ ከገባች በልጅነቷ ያጣችውን ትምህርት ታገኛለች። ሁሌ እንደምታያቸው ከተሜዎች ጥሩ ልብስና ጫማ ይኖራታል። ከዚህ በኋላ ገጠር የምትመጣው ዘመዶቿን ለማየትና በሌሎች አድናቆትን ለመቸር ብቻ ነው።
አዲስ ህይወት፡–
ወይንሸት ከአስራ ሦስተኛ ዓመቷ ማግስት ቤቶቿን ተሰናበተች። ተወልዳ ያደገችበትን የደብረ ሊባኖስ ደብርና አካባቢውን ራቀች። ቦርቃ ያደገችበትን ቀዬና መስክ አልፋ የከተማውን መንገድ ልትጀምር ከመኪናው ገባች። የከተሜው እንግዳ የትንሺቱን ልጅ እጅ በእጁ አጥብቆ ከስፍራው ራቀ።
አዲስ አበባ፡–
አሁን ሰውዬውና ወይንሸት መሀል አዲስ አበባ ገብተዋል። የከተማው ግርግር ያስገረማት ሕፃን በትርምስ የታጀበውን መንገድ ከላይ ታች ትቃኛለች። እጇን በእጁ አጥብቆ የያዘው ዘመድ መንገዱን እየመራ ከአንድ አቅጣጫ ደርሷል።
ሰውዬው አዲስአበባ እንደገባ ዓይኖቹ ወደሌላ አማተሩ። ከወረደበት መኪና አለፍ ብሎ ሌላ አውቶቡስ ለመያዝ ተጣደፈ። የት እንዳለች የማታውቀው ወይንሸት በእሱ እየተመራች ተከተለችው። አሁንም ስለአዲስ አበባ ድምቀትና ግርግር እየተገረመች ፣ መደነቅ ይዛለች።
ወይንሸትና ዘመዷ ከአዲስአበባ ርቀው ወደ ደብረ ብርሃን ጉዞ ጀምረዋል። ልጅቷ ስለሁለቱ ቦታዎች ልዩነት አልገባትም። የምትባለውን እየሰማች፣ በምትሰማው እየጓጓች ከታሰበው ደርሳለች። ደብረ ብርሃን ከአንድ ሰፈር ሲደርሱ አንዲት ሴት አገኘቻቸው። ሴትዬዋ ልጅቷን በፈገግታ ተቀብላ ሰውዬውን ሸኘች።
ቀናት እንዳለፉ ወይንሸት ለሠራተኝነት መምጣቷን አወቀች። አሁን የታዘዘችውን እየሠራች ከመኖር ውጪ ምርጫ የላትም። ልጅነቷ ከመባተል አላገዳትም። ገጠር መኖሯ ሥራ ለመውደድ አገዛት፣ ‹‹አቤት፣ ወዴት›› ማለትን አወቀች።
የወይንሸትና የደብረ ብርሃን ዝምድና ርቆ አልተጓዘም። ከአንዲት ሴት ስለ አዲስ አበባ መስማቷ ልቧን አነሳሳው። በልጅነቷ የምትናፍቃትን ከተማ ለማየት ጓጓች። መጓጓቷን ያየችው ወይዘሮ ከነበረችበት አውጥታ እሷ ዘንድ አቆየቻት።
ከቀናት በኋላ ወይዘሮዋና ወይንሸት አዲስአበባ ገቡ። ሳሪስ ከሚባለው ሰፈር ወንድሟ ቤት አስገብታ በሠራተኝነት አስቀጠረቻት። ወይንሸት ካሰበችው በመድረሷ ተደሰተች። የልጅነት ህልሟ በሆነችው ከተማ መኖሯን ወደደችው።
ወይንሸት በሠራተኝነት ጥቂት እንደሠራች አዲስ አበባ የምትኖረው ታላቅ እህቷ አገኘቻት። እህቷ ትንሽዋ ወይንሸት ሠራተኛ ሆና እንድትቀጥል አልፈለገችም። ከሥራዋ አስወጥታ ወደራሷ ወሰዳቻት።
የወይንሸት እህት ከገጠር አዲስ አበባ ከመጣች ቆይታለች። ትዳር ይዛ ልጆች ወልዳ የምትኖረው ፒያሳ አካባቢ ከሚገኝ ሰፈር ነው። እህቷን ተቀብላ እሷ ዘንድ ለማኖር ስትወስን እንደልጇ በማሰብና በመንከባከብ ሆነ።
ወጣትነት፡–
አሁን ወይንሸት በአዲስ አበባ ዓመታትን ቆጥራለች። በልጅነት ትታው የመጣችውን መንደር ረስታ ከአካባቢው ተላምዳለች። ጓደኞች አፍርታ ከብዙዎች ተዋውቃለች። ዕድሜዋ ከልጅነት ወደ ወጣትነት ሲያመራ የምታስበው በረከተ። አሁን እንዳለችበት በእህቷ ቤት መቀጠልን አትሻም። እንዲህ ማሰቧ ከብዙ ዕቅድ ያደርሳታል። የወንድ ጓደኛ መያዝ ፣ወጣ ብሎ መዝናናት ትፈልጋለች። እንደ እኩዮቿ መልበስና ማጌጥም ያምራታል።
ወጣቷ ወይንሸት መተዳደሪያ ሥራ ካገኘች ወዲህ ራሷን መጠበቅና መዋብ ጀምራለች። ይህ ለውጥ ከአፍላነቷ ተዳምሮ ለእይታ እየዳረጋት ነው። ይህን ስታውቅ ራሷን ማክበር፣ ውሰጧን መቆጠብ ትሞክራለች። ተፈላጊነቷን እየሳለች አርቃ ታስባለች። ነገዋን እያለመች፣ ተስፋዋን ታልማለች።
ጥር 11 ቀን 2005 ዓ.ም፡–
በዚህ ቀን ወይንሸት ከቤቷ የወጣችው አረፋፍዳ ነበር። ዕለቱ የጥምቀት በዓል ስለሆነ በአለባበሷ ለየት ብላለች። የሰፈሯን ታቦት ለመሸኘት ባህረ ጥምቀት የተገ ኘችው ወጣት፣ ከሚጋፉ በርካ ቶች መሀል የአንድ ሰው ዓይን እንዳረፈባት አውቃለች። ባሻገር በዓይኑ የሚከተላትን ወጣት እሷም እያየችው ነው። አስተያየቱን በዋዛ ማለፍ የፈለ ገች አይመስ ልም።
ወይንሸትና ወጣቱ ከዓይን እይታ አልፈው በቅ ርበት ተገናኙ። በእይታ የተጀመረው መጠጋጋት በጨዋታ ዳብሮ የሁለቱን ልብ በፍቅር አጣ መረ። ስሙን ተፈሪ ሲል የተዋወ ቃት መንገደኛ ስሟን ተውሶ አድራሻዋን ተቀበለ።
ጎን ለጎን እየሄዱ ብዙ አወጉ። እሷ እይታው ልቧን ገዛው። እሱም በሳቅ ጨዋታዋ ተማረከ። ታቦት ገብቶ ሲለያዩ ሁለቱም የቀኑን አጋጣሚ በመልካም አሰቡት። ምሽቱን ተደዋውለው ብዙ አወጉ። ጨዋታቸው በቁምነገር፣ ተዋዛ፣ ቆይታቸው በመልካም ቃላት ታበሰ።
ወይንሸት በዕለተ ጥምቀት ያገኘችውን ወጣት ስታልመው አደረች። ሁሌም በውስጧ የምትስለው ጉብል እሱ ሆኖ ቢሰማት አርቃ አቀደች። ትዳር የሚሻው ማንነቷ ሲነቃቃ፣ ሲበረታ ተሰማት። ተፈሪ ስልክ ሲደውል ስሜቷን ያወቀባት መሰላት። እሱም ዘንድ የእሷ ዓይነት ትኩሳት መኖሩን ስታውቅ ነፃ ለመሆን ሞከረች።
ወጣቶቹ ጊዜ ወስነው በቀጠሮ ተገናኙ። ዕለቱን የውሳጣቸውን ስሜት ዘርግፈው ተወያዩ። ቀጠሮው ሲደጋገም የፍቅር፣ የአብሮነት ፍላጎታቸው አየለ። ጊዜ መውሰድ አልፈለጉም። ከቀናት በኋላ አልጋ ተጋሩ፣ አንሶላ ተጋፈፉ።
ለፍቅር ታሪክ አዲስ የሆነችው ወይንሸት ጠዋት ማታ ተፈሪን ማሰብና ማለም ልምዷ ሆነ። ፈጽሞ ከእሱ መለየት የማትሻው ወጣት ፍላጎቷን መደበቅ አልቻለችም። ልቧ በፍቅር ነደደ። ማንነቷ በመውደድ ቃል ተገዛ። ሳታስበው በፍቅር ወጥመድ የገባችው ወጣት በቃላትና በድርጊት ሃሳቧን መግለጽ ተሳናት።
ውሎ ሲያድር ተፈሪ አንድ ሃሳብ አመጣ። በየቀኑ ውጭ ከመገናኘት ቤት ተከራይተው መኖር እንደሚሻል መከራት። ይህን ስታውቅ ደስታዋ ወሰን አጣ። በቀጠሮ የምታገኘው ፍቅር በቤቷ ውሎ እንደሚያድር እያሰበች ለቤት ኪራዩ ተቻኮለች።
ሽሮሜዳ አካባቢ የተከራየችው ቤት ለእሷና ለእሱ ማረፊያ በቂ ነበር። በሥራ የሚባትለው ፍቅረኛዋ አመሻሽቶ ሲገባ፣ እንደወጉ ተቀብላ ታኖረዋለች። የትዳር ፍላጎቷ በእሱ ፍቅር መስመሩ ቢገባት፣ ወይንሸት የልቧ ሃሳብ የሞላ የውስጥ ፍላጎቷ የሰመረ መሰላት።
ወራትን ያስቆጠረው የወጣቶቹ ፍቅር እንደጅማሬው አልሆነም። በመሀላቸው መተማመን ጠፋ። ተፈሪ በሥራ ሰበብ ከእሷ መራቁን ወይንሸት ልታምን አልፈለገችም። ከጀርባዋ ሌላ ሴት መኖሯን እያሰበች በቅናት ነደደች። እሱ ይህ ስሜቷ ሲገባው ሊርቃት፣ ወሰነ። ደጋግሞ የሚጠራ ስልኳን ባለማንሳት ከንግግር ተቃበ።
በአንድ ወገን ፍቅር መንደድ የጀመረችው ወይንሸት አሁን ስሜቷ በእልህ ተይዟል። ፍቅረኛዋን ባሰበችው ቁጥር እልህና ንዴት ይወርሳታል። የቅናት ዛር ያንገላታታል። ከእሱ የነበራትን ዕቅድና ፍላጎት እያስታወሰች ትብሰለሰላለች። ጊዜ ወስዳ ልታናግረው ባሰበች ጊዜ ለሃሳቧ ያለመገዛቱ እያበሳጨ ያስለቅሳታል።
መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም፡–
አዲሱ ዓመት ከባተ ሁለት ቀናት ተቆጥረዋል። ወይንሸት ዕንቁጣጣሽን በደስታ አላሳለፈችም። የተፈሪና የእሷን ሁኔታ እያስታወሰች በትካዜ ውላለች። በዚህ ቀን እንደሌሎች ቀናት ሁሉ ዕንባ ዕንባ ሲላት ውሏል። ሁሌም እንደዋዛ በጅምር የቀረው ፍቅርና የወደፊት ህይወቷ ያስጨንቃታል። ከዚህ ሃሳብ ስትዘልቅ በቀላሉ አትመልስም። እልህ፣ንዴትና የከፋ ኀዘን ይከተሏታል። አሁን ግን ከዚህ ጭንቀት የሚገላግል አንድ ውሳኔ ለዓይምሮዋ ደርሷል።
ዛሬ መስከረም 3 ነው። አዲሱ ዓመት ለእሷ ትርጉም የሚሰጣት አልሆነም። በዚህ ቀን አመሻሹ ላይ ወይንሸት ያሰበችውን ለማድረግ ከውሳኔ ደረሰች። ለተፈሪ መላልሳ ስልክ መደወሉ እንደማይበጅ ገብቷታል። ደጋግማ ሰዓቷን ተመለከተች። ጊዜው እንዳሰበችው አልፈጠነም። ስትንቆራጠጥ ከራሷ ስታወራ ስትጣላ ቆየች። አሁንም ሰዓቱ እጥፍ የሆነ መሰላት። ምሽት አራት ሰዓት ገደማ ቤቷን መለስ አድርጋ ከግቢው ወጣች። ወዴት እንደምትሄድ ታውቃለች። በልብሷ የሸሽገችውን ጉዳይ በጥንቃቄ እየነካካች ዕርምጃዋን አፋጠነች።
የሽሮሜዳን ቁልቁለት አልፋ ተፈሪ ወደሚሠራበት ጠጅቤት ስትሻገር አብሯት የከረመው የንዴት ስሜት ውሰጧን እያተንተከተው ነበር። በአካባቢው መብራት ጠፍቷል። ይህ አላገዳትም። በጨለማው ከላይ ታች እያለች ቆየች። እስከአሁን የምትሻውን አላገኘችም። ኮረኮንቹን አለፍ ብላ ተፈሪ ወደሚሠራበት ቤት ተጠጋች።
አሁን እንዳሰበችው ሆኗል። ጨረቃዋ ተፈላጊውን በቅርበት አሳየቻት። ብቻውን አይደለም። በቤት ኪራይ አብሮት የሚኖር ጓደኛው ከጎኑ ነበር። ወደቤት እየሄዱ መሆኑ ገባት። እየፈጠነች ከኋላቸው መከተል ያዘች። ተፈሪ አመጣጧን ሲያስተውል ጓደኛውን ይቅርታ ጠይቆ ወደእሷ ቀረበ።
የተፈሪ ጓደኛ የሁለቱን መጠጋጋት ሲያስተውል የእጅ ስልኩን አውጥቶ ፈንጠር ብሎ ቆመ። ምስጢራቸውን ላለመስማት ነበር። ወዲያው ግን የኃይለ ቃል ጭቅጭቃቸው ከጆሮው ደረሰ። ተፈሪ እየደጋጋመ ‹‹እባክሽ ተይኝ ፣ተይኝ›› ይላል። እሷም እየጮኸች ነው።
ሁኔታቸው አላምር ቢለው ጠጋ ብሎ ነገ እንዲያወሩ ሊያሳምናቸው ሞከረ። ይህን የሰማችው ወይንሸት ከእሱ ጋር ማውራት እንደማትፈልግ ገልጻ ከአጠገባቸው እንዲርቅ አሳሰበችው። እንደተባለው አደረገ። ደጋግሞ ሞባይሉን እየነካካ ራቅ ብሎ ቆመ። ንግግራቸው አላጠረም። ድምፃቸው አልቀነሰም። ተጨነቀ። ጥቂት ቆይቶ የወይንሸት ‹‹እናትህ አፈር ትብላ›› ስድብ ጎልቶ ተሰማው።
ባልንጀራው ቃሏን ተከትሎ ወደእነሱ አነጣጠረ። ተፈሪ በጀርባው ወድቆ እያቃሰተ ነው። ከወይንሸት ቀኝ እጅ ላይ ትልቅ የቻይና ቢላዋ ብልጭ ሲል ታየው። ተፈሪን በወደቀበት ተራምዳው ወደፊት እየሮጠች ነው። ጠጋ ብሎ ተመለከተ። ጓደኛው በደም ተነክሮ በስቃይ እያጓራ ነው። ራሱን ይዞ እየጮኸ በኮረኮንቹ ተከተላት። አልደረሰባትም። መለስ ብሎ ለዕርዳታ ሰዎችን ጠራ። ጩኸቱን የሰሙ ተሰበሰቡ። መኪና ለምነው ተጎጂውን ሆስፒታል አደረሱ።
የፖሊስ ምርመራ፡–
የወንጀሉ መፈጸም ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ ከስፍራው ተገኝቶ መረጃዎች ማጣራት ሲጀምር ተፈሪ ለሊቱን ህይወቱ አልፎ ነበር። ፖሊስ ከስፍራው የነበሩ በሰጡት እማኝነት ታግዞ ተፈላጊዋን አሰሰ። አላጣትም። ወይንሸትን ተከራይታ ከምትኖርበት ቤት እንዳለች አገኛት። መርማሪው ረዳት ኢንስፔክተር ታፈሰ ዘበርጋ የዕምነት ክህደት ቃሏን ተቀበለ። ድርጊቱን ስለመፈጸሟ አመነች። መርማሪው ያለችውን በወንጀል መዝገብ ቁጥር 193/06 በተዘጋጀው ዶሴ አስፍሮ የክስ መዝገቡን አደራጀ።
ውሳኔ፡–
ሀምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በቅናት መንፈስ ተነሳስታ የፍቅረኛዋን የቀኝ አንገት በስለት በመውጋት በገደለችው ወጣት ላይ የመጨረሻ ውሳኔውን ለመስጠት በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድቤቱ ተከሳሽዋ የፈጸመችውን ወንጀል በበቂ ማስረጃዎች አረጋግጦ በሰጠው ብይንም ወይዘሪት ወይንሸት ድንቁ እጇ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ አራት ዓመት ጽኑ እስራት ‹‹ትቀጣ›› ሲል ወስኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013