የፈረደብህ መንግሥታችን ሆይ እባክህ ስማን!?
ጦርነት የታሪክ ውርስ ብቻም ሳይሆን የዕለት ክስተት ከሆነባቸው ሀገራት መካከል የእኛዋ ያልታደለችው ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ጦርነት ለአያቶቻችን እንግዳ፣ ለአባቶቻችንም የሩቅ ዜና አልነበረም። የገድላቸው ታሪክ ድል በድል ነው። በእኛ የትውልድ ዓመታትም ዘመቻ የየዕለቱ መሪ ወሬያችን እንደሆነ ወደ ሁለት ፀጉር እየተሸጋገርን አለን። ከእኛም አልፎ ተርፎ በአረር መፋለሙ ሊቋረጥ ስላልቻለ እንደ በጎ ቅርስ ከአብራካችን ለወጡት ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የጠብመንጃ አወላወል አስተምረናቸው “ና ደሞ ገለል!” የሚለውን ቀረርቶ አብረን እያንጎራጎርን የእርስ በእርሱን የፍልሚያ ሰልፍ እንዲቀላቀሉ ግድ ብለናቸዋል። ይብላኝላቸው ለአረመኔዎቹ አሸባሪ የትህነግ እኩይ አፈ ቀላጤዎች፤ ይህን መሰሉን የወንድማማቾች የደም ሸማ መጣጣል እንደ ክብር ወግ ቆጥረው “ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው!” እያሉ ሲፎክሩ ህሊናቸውን አይሰቅቃቸውም። “ያዳቆነ ሰይጣን” እንዲሉ፤ ጦርነት የሞት ድግስ እንጂ የልደት ብስራት አለመሆኑ ጠፍቷቸው ነው ማለት አይቻልም።
ከጠብመንጃ ማህጸን የተወለደው ይህ ሕወሓት ይሉት ቡድን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ የሀገሪቱን ታሪክ ሲጽፍ የኖረው “በቀለህ ደም እየጠቀሰ ነበር” ቢባል ከእውነት አያርቅም። የተወለደው በባሩድ ጭስ ታጥኖ፣ ወጣትነቱንም የገፋው በደም ግብር ጠግቦ፣ በጉልምስናና በስተእርጅና ዘመኑም ወደ መቃብር እየተንደረደረ ያለው ብረት እንደነከሰ የሞት መልአክ ያከናነበውን የከፈን ጨርቅ እንደተጎናፀፈ ነው።
የሀገሪቱን ደም እየመጠጠ ዕድሜውን ያራዘመው ይህ ካንሰር ይሉት ቡድን የሕዝብ ጠላት ሆኖ የኖረው ከበረሃ እስከ ቤተመንግሥት በተጓዘባቸው ዓመታት ውስጥ ሁሉ እንደነበር የታሪክ ምዕራፎቹ ምስክሮች ናቸው። የገደለውና ያስገደለው፣ ያሰቃየውና ያኮላሸው፣ የዘረፈውና ያዘረፈው፣ ያወደመውና ያስወደመው ተግባሩ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ሰይጣናዊ ተግባሩ ለምድራዊ ዳኝነትም ሆነ በሰማያዊው የፈጣሪ ችሎት ፊት ምን ብያኔ እንደሚያሰጥ ለመገመት ከአእምሮ በላይ ነው።
የዚህ ቡድን መሪዎችና ጀሌዎች ሊገለጹ የሚገባቸው ሰብዓዊ ክብር ተሰጥቷቸው እንደ ሰው እየተቆጠሩ ሳይሆን እንደ ግሪካዊያኑ የተረት ገፀባህርያት ግማሽ ሰው ግማሽ አውሬ እንደነበረውና የቴበስ ከተማን በመቅሰፍት እንደመታው ሲፊኒክስ ተወክሎ ቢሆን የተሻለ ይሆናል። እኒህን መሰል የግማሽ ክፍለ ዘመን እኩይ ሴራዎቹንና ውጤቱን ስናሰላስል ነው ቡድኑ በዜጎች ላይ የተጣበቀ ፍርጃ ነው፤ ለመንግሥትም “በላ” ነው የምንለው።
ዛሬም እንዳለፉት ዓመታት “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” የሚለው መፈክር እንደ አዲስ ታድሶ የሕዝብ ጎርፍ ወደ ዘመቻ እየተመመ ያለው በዚሁ ሴረኛ ቡድን ቆስቋሽነት መሆኑ ተደጋግሞ ተገልጧል። የጦርነት ወሬና ነጋሪት እየተሰማ በትውልዶች መካከል ቅብብሎሹ ከሚቀጥል የተጠየቀው ዋጋ ሁሉ ተከፍሎ ልጆቻችንን መቤዠት ምድራዊ ብቻም ሳይሆን ሰማያዊ ክብር የሚያጎናጽፍ ጽድቅ ጭምር ነው። ስለዚህም ነው “ከዘላለማዊ ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት!” በማለት ጀግኖቹ የሀገሬ ልጆች በጦር ሜዳ ውሏቸው ጠላትን እያርበደበዱ ያሉት።
ይህ ፀረ ሕዝብና ፀረ ሀገር የሆነው የሽብር ቡድን ጥቃት እየፈጸመ ያለው በጦር ግንባር ጀሌዎቹን አሰልፎ ብቻ አይደለም። የፈጠራ ፕሮፓጋንዳውና የውሸት ምላሱ ውቂያኖስና ባህር ባሻገራቸው ሆድ አደሮች አማካይነት በእጅጉ የረዘመ ነው። የትራዤዲና የኮሜዲ ተውኔቱን እንዲያዳምቁለትም በረብጣ ዶላሮች የገዛቸው አንዳንድ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ቅጥረኞችና “ሎቢስት” ተብዬዎች ቅጥፈት ውሎ አድሮ የህሊና ቅጣት እንደሚያስከትልባቸው ይጠፋቸዋል ለማለት ያዳግታል። የ“አለንህ!” ባዮቹ የጥፋት ተባባሪዎች መንግሥታት፣ ቡድኖችና ግለሰቦችም ያፈጠጠውና ያገጠጠው ተግባራቸውም ውሎ አድሮ ታሪካቸውን እንደሚያጠቁር የተገነዘቡት አይመስልም። በአሸባሪው ቡድን የውስጥ አርበኞች እየተፈጸመ ያለው የኢኮኖሚ አሻጥርና ተንኮልም የታወቀና ከዕለት ወደ ዕለት ሀገሪቱን እያቆሰለ መሆኑን በቅርብ እየተከታተልን ነው።
ሀገራዊ ውጥረቱ ከግራና ከቀኝ የከፋ ስለመሆኑ ከዚህ በላይ ማብራሪያ አያስፈልገውም። የጦርነት ወቅት በምን በምን አቅጣጫ እንደሚፈተን ለመተንተን የግድ የዘርፉ ባለሙያ መሆን አያስፈልግም። ሕግ ለማስከበርና ወረራውን ለመቀልበስ ሲባል እስካሁን እየፈሰሰ ያለው የሀገር አንጡራ ሀብትም ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ይጠፋናል ማለት አይደለም።
ለህልውና ዘመቻው እየወጣ ያለው ሀብት ምን ያህል ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ልዩ ልዩ የልማት ተቋማትን ሊሰራ እንደሚችል ማሰቡ ይበልጥ ቁጭትና ፀፀት ላይ ይጥላል። በዚህም ምክንያት ነው ይህ እኩይ ቡድን በለኮሰው የጦርነት እሳት ራሱ ተለብልቦ ወደ አመድነት እስኪለውጥ ድረስ የሕይወትም ሆነ የሀብት መስዋዕት ቢከፈል አግባብ ነው የሚሰኘው።
ችግሩ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ሆኖ ወቅቱን ተገን አድርገው ሕዝብ እንዲማረርና እንዲቆጣ፣ አልፎም ተርፎም በመንግሥት ላይ እምነት እንዲታጣ የሚፈጸመው የኢኮኖሚ አሻጥር እንደ ቀላል መታየት የሚኖርበት አይመስለንም። በተለይም ሕዝቡ የዕለት እንጀራ እንኳን ተቃምሶ እንዳያድር እየተፈጸመ ያለው የንግዱ ክፍለ ኢኮኖሚ አሻጥር “በቆይ ብቻ ፉከራ” የሚታለፍ እንዳልሆነ ማሳሰቡ ግድ ይላል።
የደርግ መንግሥት በውስጥና በውጭ የውጥር ተይዞ ሀገሪቱ ከፍተኛ አደጋ ላይ በወደቀችበት የአብዮቱ የመጀመሪያ ዓመታት ግድም የበርበሬ ምርት ደብቀው ሕዝቡን ለእዮታ የዳረጉ የዘመኑ ስግብግብ ነጋዴዎች በምን ዓይነት ቅጣት እንደተቀጡ አይዘነጋም። ምንም እንኳን ዛሬም ሕዝቡን ለሚያስጨንቁት የኢኮኖሚ “ሳቦታጂስት” “የፍየል ወጠጤ” ቀረርቶ ይስተጋባላቸው ባይባልም ያለ ርህራሄ ተገቢው ማስተማሪያና ማረሚያ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚገባ ግን ውዴታ ሳይሆን ግድ ነው።
የግንባሩን ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸንፎ በቀናት ውስጥ የድል ብስራት እንደምንሰማ ምንም ጥርጥር የለውም። አሸባሪውን ቡድን “ግፋ በለው!” እያሉ የሚዘምሩለት የተለያዩ ኃይላትም የእፍረት ሸማ ተከናንበው ወደየጎሬያቸው እንደሚመለሱ በሕዝባዊ መሃላ እናረጋግጥላቸዋለን። በቀላሉ ለማሸነፍ የተገዳደረን በሴረኛ ነጋዴዎች የተተበተበው የንግዱ ሥርዓት ነው። ደፈር ብለን መግለጽ ካለብንም በኑሮ ወድነቱ ጦርነት ሕዝቡ ተስፋውም አቅሙም ተመትቶ ተሸንፏል። የዕለት እንጀራ ጉርሻ ብርቅ እስከ መሆን እየተንደረደረ እንዳለም እያስተዋልን ነው።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መ/ቤት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር በቅርቡ ለሚዲያ የሰጡት የአሀዝ መረጃ እንደሚያመለክተው ለ72 ሺህ 571 ህገወጥ ነጋዴዎች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። በ45 ሺህ 523 የንግድ ድርጅቶች ላይ የእሽግ ውሳኔ ተላልፏል። የ620 የንግድ ድርጅቶች ፈቃድም ተሰርዟል። በ104ቶች ላይም የንግድ ፈቃድ እገዳ ተፈጽሟል። በ1230 የንግድ ተቋማት ላይም ክስ ተመስርቶ 12,806,435.00 ብር ገቢ መደረጉ ተገልጾልናል። ሚኒስቴር መ/ቤቱ ስራውን ሠርቷል ቢሰኝም በዚህ ጸሐፊ እምነት ግን ውሳኔዎቹ የሀገራዊ ችግሮቹን ሥርና መሠረት ነቅለው ይጥላሉ የሚል እምነት የለውም። እንኳንስ ሊያስወግዱ ችግሮቹን ስለመቅረፋቸውም እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ሚኒስቴር መ/ቤቱ የቅጣቱን ሪፖርት ከማወጁ በፊት ነጋዴውንና ሕዝቡን ምን ያህል አስተምሯል? ሀገሪቱ በየጊዜው ከውጭ የምታስገባውን የሸቀጥ ብዛትና የስርጭት ሥርዓት በተመለከተ ሕዝቡ በአግባቡ አውቆ “ለምን ተወደደ? ሸቀጡስ የት ሄደ?” ብሎ እንዲጠይቅ አስችሎታል ወይ? ሕዝቡ በስግብግብ ነጋዴዎች ዘረፋ ሲፈጸምበት እንዴትና በምን ዘዴ ቅሬታውን እንደሚገልጽና ተቀጭዎቹ እነማን እንደሆኑና በምን ምክንያት ቅጣት እንደተላለፈባቸው ለመማሪያ እንዲሆን ዋና ዋናዎቹን በሕዝብ መገናኛ ዘዴዎች ለማጋለጥ ተሞክሯል ወይ? መዋቅራቸው ተዝረክርኮ ተግባራቸውን ባግባቡ ከማይወጡትና ለተጠቃሚዎችና ለአምራቾች ቆመናል ከሚሉ መንግስታዊ ድርጅቶችስ ጋር ሚኒስቴር መ/ቤቱ ምን ያህል ተናቦ እየሰራ ነው? የዕለት እንጀራ ችግር የሚፈታው በዕለት ተዕለት ክትትል እንጂ የሐምሌ ወርን ብቻ ጠብቆ እንደ ተራራ የገዘፈ ዓመታዊ ሪፖርት በመዘርገፍ አይደለም። እውነት እንነጋገር ከተባለ ሪፖርት አቅራቢው መ/ቤት በእርግጡ ተቋማዊ ጥንካሬው 113 ዓመታት እንዳስቆጠረ አንጋፋ ሚኒስቴር ነው? ራሱንና ዙሪያውን ቢመረምር አይከፋም። የፈረደብህ መንግሥታችን ሆይ ምንም እንኳን የግንባሩ ጦርነት ሰቅዞ ቢይዝህም ለተሸነፍንበት የዕለት እንጀራ ጦርነትም የምትመራቸውን መሰል ተቋማት ፈትሽልንና መፍትሔ ስጠን እያልን የምንቃትተው የፈረደብን ዜጎችህ በአንድነት በመጮኽ ነው።
የመብራትና የውሃ ችግሮቻችንን በአመኔታ ተቀብለን ምርኮኛ ከሆንን ዓመታት ተቆጥረዋል። ለዚህ ችግራችን የመደብነው እንባ ፈሶ ስለደረቀ ብሶታችንን በአግባቡ ለመግለጽ እንኳን አቅም አንሶናል። ይሁን ግዴለም! የህዳሴው ግድብ እውን ሲሆን ችግራችን ይቀረፋል ብለን “ተው ቻለው ሆዴ፤ ሲያልፍ ለሚያልፍ ቀን፤ ምነው መናደዴ” ብለን እየተጽናናን ነው። ልጆቻችን የሚያጠኑበትና የሰዓታት ብርሃን የሚሰጠንን አንድ ዘንግ ሻማ ለመግዛት ግን ሕዝብ አቅም አጥቷል ሲባል አያሳዝንም፣ አያሳፍርም!?
መቶ ግራም የማይሞላ ዳቦ ሰባት ብር ሲሸጥ፣ ስምንት ሽንሻኖ (ስላይስ) ዳቦ አፍ ሞልቶ አርባ ብር ሲባል፣ ሀገሪቱ በብቸኝነት የምታመርተው የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ የዓመት ደመወዝ ሲጠየቅበት፣ አንድ ዕንቁላል 10 ብር የመግባቱን መርዶ ተቆጣጣሪው ተቋም አልሰማም ብንል አያሳፍርም? ምንም ጥርጥር በሌለው መልኩ ዜጎች ክፉ ፍርጃ ወድቆብናል። ሕዝብ ብቻም ሳይሆን መንግሥትንም ፈርዶበታል።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰሞኑን ባደረገው ስብሰባ የቀረቡለትን ሪፖርቶች በሙሉ ጭብጨባና አድናቆት አክሎ በታላቅ ስኬትነት መዝግቦ መቀበሉን ስንሰማ ያከበርናቸውን ታታሪ ክብርት ከንቲባ ምነው ለሰለሱ ብለን ማማታችንንና መቀየማችንን ባንገልጽ ደግ አይሆንም። ለመሆኑ ወደ ቅርቡ የከተማችን ተቋም ጣቴን ልቀስርና የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ የስኬት ሪፖርት አቅርቦ ሲጨበጨብለት አልተሸማቀቀም? አላፈረም? አልባነነ ከሆነ ማስረጃውን እነሆ!
በኢትዮጵያ ታሪክ ተፈጽሞ በማያውቅ ሁኔታ “በአፍሪካና በዓለም ደረጃ በቀንድ ከብቶች ሃብቷ ምንትስኛ” በምትሰኘው ኢትዮጵያ የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋ የአንድ ወር ደመወዝ እንደሚጠየቅበት የከተማው ንግድ ቢሮ ኃላፊዎች ወደ ተጎራባቾቻቸው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ወደሚገኙት ልኳንዳ ቤቶች ብቅ ብለው ይጎብኙ። በቅርብ ዓመታት ልኳንዳ ቤቶች የቅንጡዎች መዝናኛ እንጂ ለተራው ምስኪን ዜጋ “ቅንጣቢ” ሻጭነታቸው ታሪክ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በሁለት ጉርሻ ሌማቱ የሚራቆተው የሽሮ ምግብ ዋጋ ይህንን ያህል ደርሷል ብሎ ለመናገር መሞከር ለመስካሪዎቹ ዜጎች ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገርም ውርደት ነው።
የክረምት ጣሪያ የሚጠገንበት ሚስማርና ተራ ቆርቆሮ፣ ብረታ ብረቶችና የሲሚንቶ ምርቶች የሚተመንላቸው የወርቅ ዋጋ ያህል መሆኑ ተደጋግሞ በኡኡታ ስለተገለጸ ደግሞ ማንባረቁ ጆሮ ማደንቆር ይሆናል። በእዚህን መሰሉ የዕለት እንጀራ መሠረታዊ ጦርነት ለምን እንደተሸነፍን ከሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም የሚፈስልን ምክንያት የፈረደበት የውጭ ምንዛሪ ችግር ነው። በአንጻሩ ከረቫት ለባሾቹ ጎምቱ ሚኒስትሮቻችን በየሚዲያው ብቅ እያሉ “ከአሁን ቀደም ባልታየ መልኩ የውጭ ምንዛሪና የምንትስ ገቢ አግኝተናል” እያሉ ይሸነግሉናል። ምን ነበረበት እንደለመዱት ዝም ብለው ሪፖርታቸውን በሼልፍ ላይ አሽገው ቢያስቀምጡት። የሕዝብ ሙግት ሲበረታባቸው የውጭ ምንዛሪ ተገኘ ማለት አኮ …እያሉ በኢኮኖሚክስ ቀመር ግራ ያጋቡናል። መንግሥታችን ሆይ ፍርጃው ከብዶብናል። አንተንም እንደፈረደብህ ከተረዳን ሰንብተናል።
ስለዚህም ነው በኤሎሄ መቃተት መንግሥታችን ሆይ ራስህንም ዜጎችህንም ለመታደግ ጨከን ብለን ያለመታከት የምንጮኸው። በአንዲት የቅርባችን አፍሪካዊት ሀገር በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ያለ መንግሥት ፈቃድ ጥቂት ሳንቲሞች በዳቦ ዋጋ ላይ ጭማሪ በመደረጉ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ከተማውን እንዴት እንዳወደመ ሳንሰማ የቀረን አይመስለንም። ምስጋና ለጨዋው ሕዝባችን ይሁንና የጎረቤቶቻችን የቁጣ መንፈስ ቢጋባብን ኖሮ የሀገሪቱ ልኳንዳ ቤቶች፣ የዳቦ መሸጫ መደብሮች፣ የዘይትና የመሠረታዊ ሸቀጦች ደጃፎች በጠንካራ ብረት ታጥረው ልዩ የጥበቃ ኃይል በቆመላቸው ነበር። ለዚህን መሰል ጥፋት ለማይዳፈረው ደጉና ምስጉኑ ሕዝባችን ደግመን ደጋግመን የተባረከ ይሁን እንላለን። በኑሮ ጦርነቱ ተሸንፈን ምርኮኛ ብንሆንም የሀገራችንን ሉዓላዊነት ማስከበሩ ግን ከዕለት እንጀራም ያለፈ ታላቅና አይተኬ የህልውና አደራ ስለሆነ ግንባራችንን አጥፈን አንንበረከክም። “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤ በነፃነት ክብርም እንጂ!” መንግሥታችን ሆይ ይህ መልዕክት ይደርስህ ይሆን? አደራ ፈጥነህ ታደገን! ሰላም ይሁን
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2013