“ጭል ጭል ጭል ጭል” ያለማቋረጥ የሚሰማ ድምፅ። ከተንጋለልኩበት ብድግ ብዬ ወደ መፀዳጃ ቤት ሄጄ ቧንቧውን አጥብቄ ዘጋሁት። ተመልሼ እንደነገሩ እላዬ ላይ ብርድ ልብስ ጣል አድርጌ በጀርባዬ ተንጋለልኩ። የቅድሙ ድምፅ ድጋሚ ይሰማኝ ጀመር። “ጭል ጭል ጭል” እምር ብዬ ተነሳሁ። “ኡፍ” ያልተቋረጠ ጭልጭልታ የሚሰለች ድምፅ። የመጸዳጃ ቤቱን በር ከፍቼ እጅ መታጠቢያው ላይ ያለውን ቧንቧ በንዴት እመለከተው ጀመር። እረፍት የነሳኝ ደመኛዬ ይመስል አፈጠጥኩበት።
ተጠግቼ ላጠብቀው ብሞክርም ፈፅሞ ሊቆምልኝ አልቻለም። በእጄ ያዝ አድርጌ ስጫነው ቢቆምም መልሶ ስለቀው የውሃው እንጥብጣቤ ይቀጥላል። ማስቆም እንደማ ልችል ተረዳሁ። ድምጹን እንዴት ማጥፋት እንደምችል ማሰብ ጀመርኩ። እቃ ማጠቢያ ሳህን አጠገብ ያለ እስፖንጅ የውሃው እንጥብጣቢ የሚያርፍበት ቦታ ላይ ሳስቀምጠው ድምፁ ጠፋ። ተመልሼ ወዳልጋዬ ሄድኩ፤ እንቅልፍ ሊወስደኝ ግን ፈፅሞ አልቻለም። ሰውነቴን ድካም ተሰምቶኛል ፤ነገር ግን አይኔ ሊከደንልኝ አልቻለም።
እረፍት የነሳኝ ሃሳብ ነው። ውስጤ የሚለው ፀፀት እንጂ የቧንቧው እንጥብጣቤ ድምፅ ረብሾኝ፤ አልያም መኝታዬ አልመች ብሎኝ አልነበረም። ሰላም የነሳኝ ፀፀት ነው። እምነት ማጉደሌ፣ቃሌን ማጠፌ ነው እንቅልፍ ያሳጣኝ። ቃል ኪዳኔን ሰብሬ በስሜት ፈረስ ስጋልብ መክረሜ ነው ሰላሜን ያራቀብኝ። አይኔ ተጨፍኖ በእውር ድንብር የማያደርጉት ነውረኛ ተግባር መፈፀሜ ነው እረፍት የነሳኝ። ራሴን ጠላሁት። ሰው መሆኔ አንገሸገሸኝ። ራሴን ክፉኛ ተፀየፍኩት። አካሌን ብርቀውና የኔ መሆኑን ብከዳው ብዬ ተመኘሁ።
ስለምን መታመን አቃተኝ? እንዴት ያፈቀረችኝን ፍቅሬን ንፁህ ፍቅር አነተብኩ። ለምንስ ሳትሰስት የቸረችኝን ፍቅሯን አጎደፍኩ? አቤት ይህንን ተግባሬን ብታይ ምን ትል ይሆን? ሥራዬን ብትደርስበት እንዴት አይነት ስሜት ይሰማት ይሆን? ማሰቡ ከበደኝ። ከሀሳቤ ለመገላገል ስልኬን ከፍቼ የኢንተርኔት መስመሩን ገና ሳበራ የበዙ መልዕክቶች ገቡልኝ። ቃል ኪዳን ውድዋ ፍቅሬ እምነትዋን የበላሁባት ስለኔ ስትደክም ቃልዋን የሰበርኩባት የወደፊቷ ሚስቴ ቴሌግራም ላይ “ፍቅር በጣም ናፍቀኸኛል” ብላ መልዕክት አስቀምጣለች።
መልዕክቷን ሳየው ስልኬን ወረወርኩት፤በፀፀት ትራሱን መደብደብ ጀመርኩ። ከቃል ኪዳን ጋር ተጋብተን ሁለት ዓመት አብረን ቆይተን ነበር። ኑሮዋችንን መለወጥ እንዳለብን ቁጭ ብለን ተነጋገርን። ወደፊት በምን መልኩ መቀየር እንዳለብን አወራን። እኔማ ስለምንም ግድ የለኝም። በወር የማገኘው ጥቂት ገቢ ለወጪና ለቤት ኪራይ ከበቃ ነገን ተጨንቄበት አላውቅም። እስዋ ለውጥን አብዝታ መመኘትዋ በረታ። መቀየር ማሰብዋን ሁሌም ትነግረኛለች። ቃል ኪዳንም እንደኔው አንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት ላይ ብትሰራም የሁለታችንም ደመወዝ ተደምሮ የቤት ወጪና የቤት ኪራይ ክፍያ ከመቻሉ ውጪ ተርፎ ለመቆጠብ የሚያስችል አልነበረም።
ተመሳሳይ ህይወት ለውጥ የሌለው ኑሮ ከኔ ቀድሞ ቃልኪዳን ሰለቻት። እናም ምን እናድርግ ብለን ተነጋገርን። እሷ ያቀረበችው ሀሳብ መጀመሪያ ብያስደነግጠኝም በኋላ ላይ ደጋግማ ስትሞግተኝ ተቀበልኳት። አንድ የውጭ ድርጅት ላወጣው ማስታወቂያ አመልክታ ከሰው ጋርም በቀላሉ ትጋባባ ስለነበር ተሳክቶላት ወደውጭ ሄደች። መጀመሪያ ላይ ወደ ውጭ አገር ሄዳ መስራት እንደምትፈልግና ለተወሰኑ ዓመታት ተለያይተንም ቢሆን መቆየት እንዳለብን ስትነግረኝ አኩርፌያት ሁሉ ነበር። በኋላ ሳልወድ ተቀበልኩ። እስክትመለስ እኔም ዲግሪዬን ወደ ሁለተኛ ዲግሪ ወይም ማስተርስ እንዳሳድግ ተነጋገርን።
ፈጣሪ ፈቅዶ የሄደችበት ሥራ እድገት ያለውና ገቢውም ደህና ነበር። እስዋ በምትልከው ብር በአንድ ዓመት ከግማሽ ብቻ ቤት መግዛት ቻልን። አሁን የምኖረው እዚያ ቤት ውስጥ ነው ። ከጀሞ አለፍ ብሎ የሚገኝ ፉሪ በተባለ አካባቢ የገዛሁት አንድ ግቢ ቤት፤ ቃልኪዳንን ስትመጣ የምቀበልበትና ወደፊት ያሰብነውን አሳክተን ቤተሰብ መስርተን የምንኖርበት ነው። መኖሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ አንድ ሰርቪስ ቤት አለው። ሰርቪስ ቤቱ እንዲሁ ከሚቀመጥ ብዬ አከራየሁት።
በእርግጥ መጀመሪያ ላይ ለማከራየት ያሰብኩት ብር ፈልጌ ሳይሆን ግቢው ብቻዬን ውዬ ሳድርበት ስለከበደኝና ከሰው ጋር ግቢ ውስጥ ልኑር ብዬ ነበር። በተጨማሪም ሥራና ትምህርት ቤት ስመላለስ ግቢው ባዶ እንዳይሆን ማሰቤ ሌላ ምክንያቴ ነበር። ፡ ሰርቪስ ቤቱን የተከራየችው ወጣት ከውጭ አገር የመጣችና እረፍት ፈልጋ ለ6 ወር እንደምትቆይ ደላላው ሲነግረኝ መከራየት እንደምትችል ነግሬው ገባች። ተከራይዋ ሀና ከግቢው ሳትወጣና ቤት ውስጥ ማዘውተር ዋና ብቸኛ መሆንዋ ይገርመኝም ያሳስበኝም ነበር።
አንድ ቀን ወደምሽት ላይ ወደቤት ስገባ በርዋ ላይ በሚያምር መልኩ ቄጠማ ጎዝጉዛ ቡና ስታፈላ ደረስኩ። ቡና ጠጣ ብላ ጋበዘችኝ፤ እኔም አላሳፈርኳትም። ከሰላምታ ውጪ ተነጋግረን አናውቅም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ከስዋ ጋር ብዙ አወራን። ከዚያን ቀን ወዲህ ተግባባን። ስለስዋ ብዙም አልጠየኳትም። ስለኔና ስለ ቃልኪዳን ሁሉንም ነገር ነገርኳት። ከልቤ እንደምወዳትና ስትመጣ ልንጋባ መሆኑን ሁሉ አወራኋት።
ቀስ በቀስ ከሀና ጋ በጣም ተቀራረብን። እኔ ቤት ገብታ ምግብ መስራትና ቤቴን ማስተካከል ጀመረች። ንፁህ እህታዊና ወንድማዊ ፍቅር በመሀላችን ተፈጥሮ እንወያያለን። አንድ ቀን ከሥራ ውዬ እቤት ስመለስ ቤትዋን በልዩ መልኩ ዲኮር አድርጋ ጠበቀችኝ። ምንድነው ስላት ልደትዋ መሆኑን ነገረችኝ። ባለማወቄ ስጦታ ስላልገዛሁላት ተናደድኩ። ያዘጋጀችውን ምግብ በልተን እየተጫወትን ወይን ከፍታ መጠጣት ጀመርን። ሳናውቀው ብዙ አወራን። ይባስ ብላ ከመሳቢያ ውስጥ ከውጭ ሀገር ይዛው የመጣችው ውስኪ ቀድታ እየተጫወትን ብዙ ቆየን። ከዚያ በኋላ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም። ጠዋት ላይ ስነቃ አልጋዋ ላይ አብረን ተኝተን ራሴን አገኘሁት።
ከቤትዋ በጠዋት ወጥቼ እቤቴ ገብቼ ራሴን ስረግምና ሳለቅስ ዋልኩ። የቆሸሸ ሰውነቴን ደጋግሜ ብታጠብም፤መንፃት አቃተኝ። ያደፈው ተግባሬ በውሃ አልታጠብ አለኝ። ውሎ ሲያድር ቤቴ ገብታ ይቅርታ ጠየቀችኝ። የሁለታችን ስህተት ስለነበር አልተቀየምኳትም። ቀናት አለፉ። እኔ ቃልኪዳንን የከዳኋት ስለመሰለኝ እቤት እየዋልኩ መጠጣት ማዘውተርን ተያያዝኩት። ነገር ግን ከሀና ጋር የነበረን አብሮነት አልተለወጠም ። ቀርባኝ ይበልጥ ሌላ ስህተት እንድሰራ አደረገችኝ። የምውልበት መጠጥ በትክክል እንዳላስብ አደረገኝ። ቃል ማፍረሴ ለየለት፤ ክህደቴ ተደጋገመ፤ መሳሳቴ ይበልጥ ተደጋገመ።
አንድ ቀን በጠዋት ተነስቼ ሁሉን ነገር ለማስቆም ያሰብኩትን ለማድረግ ወሰንኩ። ሀና ቤት እንድትፈልግና ከግቢው እንድትወጣ ነገርኳት። ከስዋ የሰማሁት ነገር ግን እጅግ አስደንጋጭ ነበር። እንደ ፀነሰችና ልትወልድ እንደምትፈልግ ነገረችኝ። ይሄኔ ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ።
ሀና ሆን ብላ እንዳጠመደችኝ ገባኝ። ስለ ቃል ኪዳን ሁሉንም ነግሬያት ስለነበር በቅርበታችን ስልክዋን ከኔ ስልክ ላይ ወስዳ ሁሉን ነገር ልታበላሽብኝ እንደሆነ ታሰበኝ። አልቄሼ ፍቅሬን እንድትታደግልኝ ለመንኳት። ሀና እንደ ወደደችኝና ልታጣኝ እንደማትፈልግ ነገረችኝ። ምንም ዘመድ እንደሌላትና ውጭ ከመሄድዋ በፊት ያሳደጋት እንደ ሞተ ሚስትዬውም ታሰቃያት እንደነበር የትም መሄጃና ዘመድ እንደሌላት እያለቀሰች ነገረችኝ። ተናድጄ ስለነበር እንባና ልመናዋ የውሸት መስሎኝ ከቤቴ እንድትወጣ ጨከን ብዬ ተናገርኳት። ገብቼ በሬን ዘጋሁ።
ከሳምንት በኋላ ጠዋት ላይ የውጭው በር በኃይለኛው ሲንኳኳ ወጥቼ ከፈትኩት። ያ ሀናን ይዟት የመጣው ደላላ ነበር። ስንወጣና ስንገባ መቀራረባችን ገብቶት ነበርና። እየፈራ አንድ ወሬ ነገረኝ። በሰማሁት ተደናገጥኩ። ብርክ ይዞኝ እዚያ በር ላይ ተንሸራትቼ ተቀመጥኩ። ሰማይና ምድሩ ዞረብኝ። ሀና አዲስ የተከራየችው ቤት ላይ ታንቃ መሞትዋና ዘመዴ የምትለው ሰው እንደሌላት ማዘጋጃ ቤት አስክሬንዋን እንደ ወሰደው ነገረኝ።
ይሄን ከሰማሁ በኋላ ሥራና ትምህርቱ ሁሉ አስጠላኝ። የሰው ልጅ ምድር ላይ የመቆየቱ ትርጉምና ጣዕም ጠፋብኝ። ተስፋ ቆረጥኩ። ሀናን ለዚህ የዳረኳት እኔ የሆንኩ ስለመሰለኝ በፀፀት ራሴን ቀጣሁ። እንቅልፍ አጥቼ ራሴን በህሊና ፀፀት በመግረፍ ሌሊቱን አነጋለሁ። ቀኑን ሙሉ ለዚህ ሁሉ ስህተት በዳረገኝ መጠጥ ውስጥ ራሴን እደብቃለሁ። … ተፈፀመ::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013