አዲስ አበባ፡- በ2003ዓ.ም ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪነት የተሸጋገሩ በኤሌክትሪክ አቅርቦች ችግር ምክንያት ስራችንን አቁመናል ሲሉ አማረሩ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ችግሩ መኖሩን አምኖ ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡ የንብ ብረታብረትና እንጨት ስራ ማህበር መስራች ወጣት ወንድያፍራው የዋግሹም ድርጅታቸው ከስምንት ዓመት በፊት ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ሲሸጋገር በተደራጀ ሁኔታ የተለያዩ የኮንስትራክሽንና የግብርና ማሽኖች ለመስራት ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ የኤሌክትሪክ መስመር ባለመዘረጋቱ ስራቸው በእጥልጥል ላይ መቅረቱን ይናገራሉ፡ ፡ይኸው ችግር የሊዝ ማሽን እንዳይወስዱ አድርጓቸዋል፡፡
ድርጅታቸው የብሎኬት ማሽኖች፣ ሚክሰሮች፣ ውሃ ከጉድጓድ ማውጫ ማሽኖችን፣ የሩዝና የቡና መፈልፈያ ማሽኖችን ለመስራት የንግድ ፈቃድ አውጥቷል፡፡ በዚህም ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማዳን እንደሚቻል አስታወሰው፤ ድርጅታው እነዚህን ማሽኖች የሚተክልበት 2500 ካሬ ሜትር ላይ ህንጻ ቃሊቲ አካባቢ የገነባና ከሶስት ዓመት በፊትም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኝት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ የፈጸመ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፡፡ የሊዝ ፋይናንስ ማሽን ውሰዱ ተብለው ያልወሰዱት ያለ ስራ ከሚቀመጥና ወለድ እንዳይጨምርባቸው በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ድርጅታቸው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በማስመዝገብ በ2003ዓ.ም ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገረ ቢሆንም ከዚህ በኋላ በርካታ ችግሮች አሳልፈናል የሚሉት አቶ ያረጋል ገሰሰ በበኩላቸው፤12 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ክፍያ ቢፈጸምም ፖል ብቻ ቆሞ፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለማግኘታቸው ስራ ፈት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ኤሌክትሪክ ከሌለ ተጨማሪ ዕዳ ስለሚሆንባቸው የሊዝ ፋይናንስ ማሽን አለመውሰዳቸው አስታወሰዋል፡፡ ወጣት ጌታነህ ዝናቡ በበኩሉ በቃሊቲ አካባቢ የመስሪያ ህንጻውን ቢያጠናቅቅም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሊያገኝ ባለመቻሉ ስራ አቁሟል፡፡
የተለያዩ የብረታ ብረትና እንጨት ምርቶችን ለማምረት ቢያቅድም ኤሌክትሪክ መስመር ሊዘረጋለት ባለመቻሉ ስራ ፈት ሆኗል፡፡ ችግሩን በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢያመለክቱም ‹‹ከዛሬ ነገ ይገባላችዋል›› ከሚል ምላሽ ውጭ በተግባር ጠብ ያለ ነገር እንዳላገኙ አስታወሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ከ60 ሺ በላይ ድርጅቶችና ግለሰቦች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ክፍያ የከፈሉ ቢሆንም አገልግሎቱን ማግኘት አለመቻላቸውን አምነዋል፡፡
የስርጭትና የማከፋፈያ መስመሮችን በወቅቱ የማሻሻል ስራዎች ባለመሰራታቸው የአገልግሎቱ ፈላጊዎችን ጥያቄ ማስተናገድ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ ክፍያ ፈጸመው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥያቄ መመለስ ያልተቻለው በግብዓት ችግር ምክንያት ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ60ሺ በላይ ዜጎች ለአገልግሎቱ ክፍያ ፈጸመው ኤሌክትሪክ ሀይል እንዲገባላቸው እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡ ፡ ይህን ችግር ለመፍታትም ሰባት የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ግብዓት አምራቾችን በጨረታ አወዳድረው ግዥ በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የትራንስፎርመሮች፣ የኤሌክትሪክ ገመድና ቆጣሪዎች በመረከብ ክፍያ ለፈጸሙ ደንበኞች ኤሌክትሪክ የማስገባት ስራ ተጀምሯል፡፡ የመካከለኛ ኢንዱስትሪዎችም በዚህ ሂደት ችግራቸው እየተፈታ ይሄዳል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም አንድ ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት አቅደው እየሰሩ መሆኑን አስታወሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ጌትነት ምህረቴ