በአራት ዓመታት አንድ ጊዜ የሚካሄደውና በግዙፍነቱ (በተሳታፊ አገራትና ስፖርተኞች እንዲሁም የስፖርት ዓይነቶች ብዛት) ቀዳሚ ዓለም አቀፍ የስፖርት ክዋኔ የሆነው የኦሊምፒክ ጨዋታ (Olympic Games) መላው የዓለም ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀውና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችም በሚሳተፉባቸው ውድድሮች አሸንፈው ለአገራቸው ሜዳሊያ ለማስገኘት ብርቱ ፉክክር የሚያደርጉበት ግዙፍ የስፖርት ሁነት ነው።
ዘመናዊ የኦሊምፒክ ጨዋታ መካሄድ ከጀመረበት እ.አ.አ ከ1896 የአቴንስ ኦሊምፒክ ወዲህ ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀውን የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ እስካሁን ድረስ 32 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ኢትዮጵያም ከ1956 የሜልቦርን ኦሊምፒክ ጀምሮ በኦሊምፒክ ተሳትፋ 58 ሜዳሊያዎችን (23 የወርቅ፣ 12 የብር እና 23 የነሐስ) አሸንፋለች። አገሪቱ ሁሉንም ሜዳሊያዎች ያገኘችው በአትሌቲክስ ውድድሮች ሲሆን የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ካደረገችበት ከሜልቦርን ኦሊምፒክስ በስተቀር በተሳተፈችባቸው ሌሎች የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች። በአንፃሩ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1976፣ በ1984 እና በ1988 በተካሄዱት የሞንትሪል፣ የሎስ አንጀለስና የሴዑል ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ አልተሳተፈችም። ዛሬ ለእነዚህ የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎች መገኘት አስተዋጽኦ የነበራቸውን ስፖርተኞችንና ባለሙያዎችን በአጭሩ እንቃኛቸዋለን።
ሀ). አትሌቶች
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ውድድር ሜዳሊያ ማግኘት የጀመረችው በሁለተኛው የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ሲሆን ሜዳሊያውን ያስገኘው ደግሞ በባዶ እግሩ ማራቶን ሮጦ ዓለምን ጉድ ያሰኘው ሻምበል አበበ ቢቂላ ነው። አበበ እ.አ.አ በ1960 በተካሄደው የሮም ኦሊምፒክ ወድድር ላይ ያስገኘው የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል። የአበበ ሜዳሊያ ኢትዮጵያን በወቅቱ በአትሌቲክስ ከፈረንሳይና ቻይና የበለጠ ደረጃ ይዛ እንድታጠናቅቅም አስችሏታል።
ሻምበል አበበ ቢቂላ በራሱ ተይዞ የነበረውን የማራቶን ክብረ ወሰን አሻሽሎ የሮም ድሉን የደገመበት የ1964 (እ.አ.አ) የቶኪዮ ኦሊምፒክም ኢትዮጵያ ተጨማሪ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችበት ነበር። አበበ የአንጀት ቀዶ ጥገና ካደረገ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የቶኪዮውን ማራቶን ማሸነፉ ልክ በባዶ እግሩ ሮጦ እንዳሸነፈው የሮም ኦሊምፒክ ሁሉ አስገራሚ ነበር።
ማሞ ወልዴ በማራቶን የወርቅ እና በ10ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያዎችን ያሸነፈበት የሜክሲኮ ሲቲ ኦሊምፒክ (እ.አ.አ 1968) ኢትዮጵያ፣ በአራተኛው የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ በላይ ሜዳሊያዎችን እንድታገኝ አስችሏታል። አበበ ቢቂላ በከባድ ሕመም/ጉዳት ምክንያት ውድድሩን ሳይጨርስ ቢቀርም ማሞ የአበበን አደራ ተቀብሎ ውድድሩን ማሸነፉ የኦሊምፒክ ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ማረፊያው ኢትዮጵያ እንዲሆን አድርጓል። እ.አ.አ በ1972 የሙኒክ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ የማራቶን እንዲሁም ምሩጽ ይፍጠር የ10ሺ ሜትር ባለ ነሐስ ሆነዋል።
ከስምንት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1980 ሞስኮ ላይ ወደ ግዙፉ የኦሊምፒክ ውድድር መድረክ የተመለሰችው ኢትዮጵያ፣ በማርሽ ቀያሪው በምሩጽ ይፍጠር የ10ሺ እና የአምስት ሺ ሜትር የወርቅ፤ በመሐመድ ከድር የ10ሺ ሜትር እንዲሁም በእሸቱ ቱራ ደግሞ የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም 17ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በወቅቱ የአምስት ሺ ሜትር ውድድር ሁለት፤ የ10ሺ ሜትር ውድድር ደግሞ አንድ ማጣሪያዎች ነበሯቸው። ምሩፅ ይፍጠር በሁለት የፍፃሜ ውድድሮች አሸንፎ ድርብ የኦሊምፒክ ድል ያስመዘገበው ሁሉንም የማጣሪያ ውድድሮች በድል በመወጣት ነበር። በዚህም ምሩፅ በአጠቃላይ የሮጠው 35ሺ ሜትር ነበር። ይህ ክስተትም የምሩፅን የኦሊምፒክ ድል ልዩና አስደናቂ አድርጎታል።
የሎስ አንጀለስንና የሴዑልን ኦሊምፒክ ውድድሮች ያልተሳተፈችው ኢትዮጵያ፣ ከ12 ዓመታት በኋላ፣ እ.አ.አ በ1992 ባርሴሎና ላይ ወደ ኦሊምፒክ ስትመለስ በሴት ተወዳዳሪዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳሊያ ያገኘችበትን ታሪክ አስመዘገበች። ፍልቅልቋ ደራርቱ ቱሉ የ10ሺ ሜትር ውድድርን በበላይነት በማጠናቀቋ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት መሆን ቻለች። ፊጣ ባይሳ እና አዲስ አበበ ደግሞ በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል።
ዝነኛውና አይበገሬው ኃይሌ ገብረሥላሴ በ10ሺ ሜትር እና ፋጡማ ሮባ በማራቶን የወርቅ እንዲሁም ጌጤ ዋሚ በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያሸነፉበት የ1996 የአትላንታ ኦሊምፒክ፤ ፋጡማ ሮባ የኦሊምፒክ ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት መሆን የቻለችበትን ታሪክ ያስመዘገበችበት ውድድር ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ውድድሩ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በወንድና በሴት አትሌቶቿ የወርቅ ሜዳሊያን ማሳካት የቻለችበት ሆኖ ተመዝግቧል። በወቅቱ ኃይሌ የ10ሺ ሜትር ውድድርን ያሸነፈው የርቀቱን የኦሊምፒክ ክብረወሰንን በመስበር ጭምር ነበር።
እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም የተካሄደው የሲዲኒ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ብዙ ሜዳሊያዎችን ካገኘችባቸው የኦሊምፒክ መድረኮች ቀዳሚውና አንዱ ነው። ይህ ውድድር አገሪቱ በኃይሌ ገብረሥላሴ (10ሺ ሜትር)፣ ደራርቱ ቱሉ (10ሺ ሜትር)፣ ገዛኸኝ አበራ (ማራቶን) እና ሚሊዮን ወልዴ (አምስት ሺ ሜትር) አማካኝነት አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘችበት ደማቅ መድረክ ነበር። በተጨማሪም አሰፋ መዝገቡ እና ተስፋዬ ቶላ በ10ሺ ሜትር እና በማራቶን ሩጫዎች ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ሲያስገኙ፣ የአትላንታዋ የ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ጌጤ ዋሚ በበኩሏ በዚህ ውድድር ላይ በ10ሺ ሜትር የብር እና በአምስት ሺ ሜትር ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። ደራርቱ የ10ሺ ሜትር ወርቁን ያጠለቀችው ከአዲስ የውድድሩ ክብረ ወሰን ጋር ነበር።
ቀነኒሳ በቀለ የ10ሺ ሜትር የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን በማሻሻልና ስለሺ ስህንን አስከትሎ በመግባት ያሸነፈበት፣ መሰረት ደፋር በአምስት ሺ ሜትር የድል ባለቤት የሆነችበት፣ እጅጋየሁ ዲባባ እና የባርሴሎናና የሲዲኒ ወርቋ ደራርቱ ቱሉ በ10ሺ ሜትር ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ያጠናቀቁበት እንዲሁም በጊዜው የ19 ዓመት ወጣት የነበረችው ጥሩነሽ ዲባባ (ጥሩዬ) በአምስት ሺ ሜትር ነሐስ ያገኘችበት የአቴንስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያውያንን በደስታ ያስጨፈረ ውድድር እንደነበር አይዘነጋም። በዚህ ውድድር ቀነኒሳ በአምስት ሺ ሜትር ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ተጨማሪ ሜዳሊያ አግኝቷል።
29ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታ (የቤጂንግ ኦሊምፒክ)ም ኢትዮጵያ በጥሩነሽ ዲባባና በቀነኒሳ በቀለ በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች ድርብ ድርብ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያሸነፈችበት፣ ስለሺ ስህን (በ10ሺ ሜትር) እና መሰረት ደፋር (በአምስት ሺ ሜትር) የብር ሜዳሊያ ያገኙበት እንዲሁም ፀጋዬ ከበደ በማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቀበት ውድድር እንደነበር ይታወሳል። አንበሳው ቀነኒሳ ድርብ የወርቅ ሜዳሊያዎቹን ያሸነፈው ድርብ ሪከርድ በመስበር ጭምር ነበር። ጥሩዬም የ10ሺውን ወርቅ በክብረ ወሰን ማሻሻያ አጅባዋለች።
ከሩቅ ምስራቅ ወደ አውሮፓ የተመለሰውና ለንደን ያስተናገደችው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታ፣ ኢትዮጵያ ጥሩ ውጤት ካስመዘገበችባቸው የኦሊምፒክ ውድድሮች መካከል አንዱ ነበር። በዚህ ውድድር ላይ የተገኙት የመሰረት ደፋር የአምስት ሺ ሜትር፣ የጥሩነሽ ዲባባ የ10ሺ ሜትር እና የቲኪ ገላና የማራቶን የወርቅ፤ የሶፍያ አሰፋ የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል እና የደጀን ገብረ መስቀል የአምስት ሺ ሜትር የብር እንዲሁም የጥሩነሽ ዲባባ የአምስት ሺ ሜትር፣ የታሪኩ በቀለ የ10 ሺ ሜትር እና የአበባ አረጋዊ የአንድ ሺ 500 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያውያንን ያስፈነደቁ ደማቅ ድሎች ነበሩ። ‹‹ክብረ ወሰን ካላሻሻልኩ’ማ ወርቁም ወርቅ አይሆንም›› ብላ ወገቧን ያጠበቀችው ቲኪ ገላና፣ አስባም አልቀረችም፤ የኦሊምፒክ የማራቶን ክብረወሰንን አሻሽላ አሸንፋለች።
የላቲን አሜሪካዋ ብራዚል ያዘጋጀችው የ2016 የሪዮ ዲ ጄኔሮ ኦሊምፒክም ከኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ውጤት አንፃር ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት ነበር። አዲስ የኦሊምፒክ ክብረ ወሰን የተመዘገበበት የአልማዝ አያና የ10ሺ ሜትር ድል ከወርቅም በላይ ነበር። ገንዘቤ ዲባባ በአንድ ሺ 500 ሜትር እና ፈይሳ ሌሊሳ በማራቶን ያስገኟቸው የብር እንዲሁም ማሬ ዲባባ በማራቶን፣ ሐጎስ ገብረ ሕይወትና አልማዝ አያና በአምስት ሺ ሜትር፣ ጥሩዬና ታምራት ቶላ በ10ሺ ሜትር ያስመዘገቧቸው ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያ በሪዮ የተቀዳጃቸው ተጨማሪ ድሎች ናቸው።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ተራዝሞ የነበረውና ላለፉት ሁለት ሳምንታት ያህል በሩቅ ምስራቋ አገር ጃፓን አስተናጋጅነት ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀው የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከ20 ዓመታት (ከአራት ኦሊምፒኮች) በኋላ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበችበት ሆኖ ቢጠናቀቅም የሰለሞን ባረጋ የወርቅ፣ የለሜቻ ግርማ የብር እንዲሁም የጉዳፍ ፀጋይ እና የለተሰንበት ግደይ የነሐስ ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያን ከሩቅ ምስራቅ ባዶ እጇን ከመመለስ ታድገዋታል።
እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ነገር ኢትዮጵያ ሜዳሊያ እንድታገኝ ካስቻሉ አትሌቶች በተጨማሪ የሜዳሊያ አሸናፊዎቹ ባለድል እንዲሆኑ የቡድን ስራ በመስራትና ሌሎች አገራትን የወከሉ ተፎካካሪዎችን በማዳከም ለድሉ አስተዋፅኦ ያበረከቱና ለኢትዮጵያ የተለመዱ ባልሆኑ የስፖርት ዓይነቶች ኢትዮጵያን ወክለው ተሳታፊ ማድረግ የቻሉ አትሌቶች ጉዳይ ነው። እነዚህ አትሌቶች ራሳቸው የወርቅ፣ የብር አልያም የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፍ ባይችሉም የሜዳሊያ ባለቤት መሆን የቻሉ ኢትዮጵያውያንን በማገዝና ተፎካካሪዎቻቸውን በማዳከም ለኢትዮጵያ ታላቅ ውለታ የዋሉ ጀግኖች ናቸው። ብዙ የኢትዮጵያ አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ሲዘመርና የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማም በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የእነዚህ የቡድን ስራ ሞተር የሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደማቅ ተጋድሎም አብሮ ከፍ ብላል። የሕዝብ መዝሙሩን የሰንደቅ ዓላማውን ከፍታ ያደመቀው የእነዚህ ጀግኖች አኩሪ ተግባር ነው።
ለ). አሰልጣኞች
ስፖርተኞች ውጤት እንዲያስመዘግቡ የአሰልጣኞች ሚና ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያም በኦሊምፒክ ውድድሮች ተሳትፎዋ ውጤት ካስመዘገቡ አትሌቶቿ ጀርባ የአሰልጣኞቻቸው አሻራ በደማቁ ተጽፏል። ከእነዚህ አንጋፋ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ኦኒ ኒስካነን ናቸው። ስዊድናዊው አሰልጣኝ ኒስካነን ኢትዮጵያ በሮም እና በቶኪዮ ኦሊምፒኮች የወርቅ ሜዳሊዎችን ስታሸንፍ የአትሌቲክስ ቡድኑ አሰልጣኝ ነበሩ።
ኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን በጀመረችበት የሜልቦርን ኦሊምፒክ ላይ የአጭር ርቀት ተወዳዳሪ የነበሩት ንጉሴ ሮባ፤ በቶኪዮ፣ በሙኒክ፣ በሞስኮና በባርሴሎና ኦሊምፒኮች የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ቡድን በረዳት አሰልጣኝነትና በዋና አሰልጣኝነት የመሩና ውጤት እንዲመዘገብ የተጉ ባለሙያ ናቸው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወርቃማ ዘመን መሪ የነበሩት፤ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ አትሌቶች ጋር ስማቸው ሁልጊዜም አብሮ የሚነሳው፤ ሩጫን፣ በተለይም መካከለኛና ረጅም ርቀቶችን፣ በተወዳዳሪነት/በሯጭነትና በአሰልጣኝነት ከእግር እስከ ራሱ ድረስ ጠንቅቀው የሚያውቁት፤ በአሰልጣኝነታቸው አገርን ያኮሩትና ስማቸው የገነነው፤ አሰልጣኝነታቸው ባሕር ማዶ ድረስ በተሻገረና እስከ ዶክትሬት ዲግሪ በደረሰ ዘመናዊ ትምህርትና ስልጠና የታገዘ፤ ከሙኒክ እስከ ቤጂንግ ኦሊምፒኮች ድረስ የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ቡድን በረዳት አሰልጣኝነትና በዋና አሰልጣኝነት በመምራት ኢትዮጵያ 25 ሜዳሊያዎችን እንድታሸንፍ ያደረጉት፤ በጥብቅ ዲስፕሊን የታጀበ ጠንካራ የልምምድ መርህንና አባታዊ አቀራረብን መለያቸው የነበሩት … አንጋፋው፣ ጠንቃቃው፣ ኮስታራው፣ ታታሪውና ስኬታማው አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ከኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ድሎች ጋር በቀዳሚነት አብረው የሚጠቀሱ ባለሙያ ናቸው።
በተጨማሪም ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ (አትላንታ፣ ሲድኒና አቴንስ)፣ ዶክተር ይልማ በርታ (ባርሴሎና፣ አትላንታ፣ ሲድኒ፣ አቴንስ፣ ቤጂንግና ለንደን)፣ ኮማንደር ሑሴን ሺቦ (ከሲድኒ ጀምሮ) እና ሻምበል ዘላለም ደስታ (ሲድኒ፣ አቴንስና ቤጂንግ) በተለያዩ የኦሊምፒክ መድረኮች የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ቡድን በረዳት አሰልጣኝነትና በዋና አሰልጣኝነት በመምራት ኢትዮጵያ ደማቅ ታሪክ እንድትጽፍ ያደረጉ ባለሙያዎች ናቸው። ከእነዚህ አሰልጣኞች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ረዳት አሰልጣኞችም ለኢትዮጵያ ድሎች ጉልህ አስተዋጽኦዎችን አበርክተዋል።
ሐ). ሐኪሞችና ጋዜጠኞች
ከዚህ በተጨማሪም ዶክተር አብርሃም ተድላ፣ ዶክተር ያየህይራድ ቅጣው፣ ቺፍ ሳህሌ ሙሉነህ፣ አቶ ጥላሁን እሸቴ፣ ዶክተር አያሌው ጥላሁን፣ አቶ ቃሲም ገመዳና ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎችም ስፖርተኞችን በማከም፣ በማበረታታትና በመንከባከብ ለድሉ በዋጋ የማይተመን አስተዋጽኦዎች ነበሯቸው።
ይንበርበሩ ምትኬ፣ ጎርፍነህ ይመር፣ ዓለሙ መኮንን፣ ደምሴ ዳምጤ፣ ፍቅር ይልቃልና ሌሎች ጋዜጠኞች ደግሞ የኢትዮጵያን ድሎች ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሬዲዮና በቴሌቪዥን አድርሰዋል። ለመሆኑ የደምሴ ዳምጤን የአገር ፍቅር ስሜት የፈጠረው ፈንጠዝያ፣ ጩኸትና ጭንቀት ማን ይረሳዋል?!
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረኮች ያስመዘገበችው ውጤት የስፖርተኞች ብቻ ሳይሆን የአሰልጣኞች፣ የሐኪሞች፣ የጋዜጠኞችና የሌሎች በርካታ ባለሙያዎች ድምር የልፋት ውጤት እንደሆነ ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም! የኦሊምፒክ ባለውለታዎችም እነዚህ ሁሉ ባለሙያዎች ናቸው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2013