በዓለማችን በተለይም በሀይማኖት ተቋማት እና በቤተመጽህፍት ውስጥ ብዙ ሺህ ዓመታትን ያስቆጠሩ ታሪካዊ የእጅ ጽሁፎች ይገኛሉ። እነዚህ የእጅ ጽሁፎች በብራና ላይ በእጅ የተጻፉ ሲሆኑ፣በዘመናችን እምብዛም በማይነገሩ ቋንቋዎች የተጻፉ ከመሆናቸው ባሻገር ናቸው። እነዚህን የሰው ልጅ ታሪካዊ ዘገባዎች ለመጠበቅ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ያሉ ጽሑፎች በዓለም ዙሪያ ባሉ ቤተ -መጻህፍት እና ገዳማት ውስጥ ተጠብቀው ይገኛሉ።በእነዚህ ስብስቦች ውስጥ የተወሰኑት በዲጂታል ምስሎች (በዲጂታል ኢሜጄሪ) አማካይነት ለጠቅላላው ህዝብ ይፋ ተደርጓል።ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን በዓለም ላይ በተለያዩ አካባቢዎች፣ገዳማት እና አድባራት እንዲሁም በቤተመጽሃፍት ውስጥ የሚገኙ ፈጽሞ ያልተነበቡ የእጅ ጽሁፎች በርካታ ናቸው።እነዚህ የእጅ ጽሁፎችን ማስተዋል ለዓለም ህዝብ ትልቅ ሀብት ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ሳይሰራ ቆይቷል።
ችግሩ በተለይም ከምዕራቡ ዓለም ውጭ ባሉ አካባቢዎች እጅግ በከፋ ደረጃ ላይ ይገኛል። ብዙ ሺህ ዓመታትን ያስቆጠሩ የጥንት የእጅ ጽሁፎችን መንከባከብ እና ጥቅም ላይ ማዋል ቀርቶ መቶ ዓመታትን ያስቆጠሩ ጽሁፎች ጭምር በዲጂታል(በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ዘዴ) በወጉ ተሰንዶ ማየት የተለመደ አይደለም።
አሁን ላይ ብዙ ተናጋሪ፣አንባቢ እና ፀሃፊ በሌላቸው ጥንታዊ ቋንቋዎች የተጻፉ የእጅ ጽሁፎች ብዙ ሚስጥራትን እንደያዙ ቢገመትም በነዚህ ቋንቋዎች የተጻፉ ጽሁፎችን ለማንበብ እና ሚስጢራቱን በመገንዘብ ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየቱ በብዙዎች ዘንድ ቁጭትን ፈጥሮ ነው የኖረው።ሊህቃን የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የኖተርዳም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ውስብስብ የሆኑ ጥንታዊ የእጅ ፅሁፎችን ማንበብ የሚችል አርቴፊሻል ኒዩራል ኔት ወርክ (ሰው ሰራሽ የነርቭ አውታረ መረብ) በማበልጸግ ላይ ናቸው።
አርቴፊሻል ኒዩራል ኔት ወርክ (ሰው ሰራሽ የነርቭ አውታረ መረብ) የሰው አንጎል መረጃን የሚመረምርበትን እና የሚያስኬድበትን መንገድ በሚመስል መንገድ የተቀየሰ የኮምፒውተር ስርዓት ነው። አልጎሪዝም (ስልተ ቀመሮችን) በመጠቀም ፣ የተደበቁ ቅጦችን እና ትስስሮችን መለየት፣ መሰብሰብ፣መመደብ፣ከጊዜ በኋላ – ያለማቋረጥ መማር እና ማሻሻል የሚያስችል ስርዓት ነው።
ይህ አርቴፊሻል ኒዩራል ኔት ወርክ አሁን ላይ ብዙ ተናጋሪ በሌላቸው ጥንታዊ ቋንቋዎች የተጻፉ መዛግብቶችን ለማንበብ የሚያስችል መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩተር ሳይንስ እና ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዎልተር ሺረር ያስረዳሉ። የአጻጻፍ ስልቱም ዘመኑን የሚመስል በመሆኑ የፅሁፉን ምንነት ለመለየት አዳጋች በመሆኑ ጥቅም ላይ ሳይውሉ መቆየታቸውን ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ጨምረው መግለጻቸውን ቴክ ኤክስፕሎር አስነብቧል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቱ ጥንታዊ ፅሁፎችን የሚመራመሩ ባለሙያዎችን ግንዛቤ በማመሳሰል ትርጉም ወደሚሰጥ ንባብ እንደሚቀይር የተገለጸ ሲሆን፤ ሥርዓቱ የተለመደውን የማሽን ለርኒንግ ስልት ቪዥዋል ሳይኮፊዚክስ (visual psychophysics) ከተባለ (በተጨባጩ ዓለም እና በሰው ልጅ ባህርይ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠና) ዘርፍ ጋር በማጣመር ተግባር ላይ ተብሏል።
“ብዙ ዘመናት ወደ ኋላ በመመለስ እና እንደ ላቲን ባሉ ቋንቋዎች የተጻፉ ከረጅም ጊዜ ጅምሮ ከጥቅም ውጭ በሆኑ ቋንቋዎች የተፃፉ ታሪካዊ ሰነዶችን ጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል” ያሉት በኖተርዳም ዩኒቨርሲቲ የዴኒስ ኦው ዶውዝ ኮሌጅ የኮምፒተር ሳይንስ እና ምህንድስና ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዋልተር ሺረር እንደሚሉት፤የእነዚህን የእጅ ጽሁፎችን የሚያምሩ ፎቶዎችን ማግኘት የሚቻል ቢሆንም፤ ነገር ግን ለአንባቢዎች እና ለተመራማሪዎች ምቹ በሆነ ሁኔታ በጽሁፍ መልክ ማግኘት ከባድ ነው ብለዋል።የኖተርዳም ዩኒቨርሲቲ ቡድን መሰል ጽሁፎችን አውቶሜት በማድረግ ለአንባቢዎች እና ተመራማሪዎች ምቹ በሆነ ሁኔታ በጽሁፍ ለመሰነድ እቅድ እንዳላቸው ነው ያብራሩት።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ሺረር ስለ ፓሬርን አናላይሲስ እና ስለ ማሽን ኢንተለጀንስ በኤሌክትሪክ እና በኤሌክትሮኒክስ መሐንዲሶች ኢንስቲትዩት መጽሔት ላይ ባሳተሙት የምርምር ጽሁፍ ላይ እንዳብራሩት በቡድኑ የተዘጋጀው አርቴፊሻል ኒዩራል ኔት ወርክ (ሰው ሰራሽ የነርቭ አውታረ መረብ) የማሽን መማር ባህላዊ ዘዴዎችን ከቪዡዋል ሳይኮፊሲክስ ጋር እንዴት እንዳዋሃደ አብራርተዋል።ማሽን ለርኒንግ ሲስተም በመጠቀም የጥንት ጽሑፎችን ለመቅዳት ጥልቅ ትምህርትን መጠቀም በማህበራዊ ሳይንስና ሁማኒቲስ አካባቢ ላሉት ምሁራን በጣም የሚስብ ነገር ከመሆኑም ባሻገር ከዘርፉ ሊህቃን ከፍተኛ አድናቆት እየተቸረው ነው።
“እነዚህን ጥንታዊ ጽሁፎችን ፎቶግራፎችን በማንሳት ለመደነቂያነት ከመጠቀም በተጨማሪ እነዚህን ጥንታዊ ጽሁፎችን ፕሮግራም አውጥቶ በማንበብ ከእውቀት ማዕድ መጋራት የተለያዩ ነገሮች ናቸው” ያሉት በዩኒቨርሲቲው የጥንታዊ መዛግብት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሂልደጉንድ ሙለር፤በጥናቱ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉት አብዛኞቹ ጽሁፎች የዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የእጅ ጽሑፎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ያ የመካከለኛው ዘመን የመጀመሪያ ዘመናት መሆናቸውንም አውስተዋል።
ይህም ማለት ማተሚያ ቤቶች ስራ ከመጀመራቸው ከረጅም ዓመታት በፊት እንደነበር እና ያ ዘመንም በጣም ብዙ የእጅ ጽሑፎች የተፈጠሩበት ዘመን መሆኑን ጠቁመዋል። በእነዚህ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ የተደበቁ ሁሉም ዓይነት መረጃዎች መኖራቸውንና በነዚህ ጽሁፎች ውስጥም ከዚህ በፊት ማንም ያላየው ያልታወቁ ጽሑፎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ፈታኝ ሁኔታዎች እንዳሉ የተናገሩት ሺረር ቡድናቸው የጽሑፍ ግልባጮችን ትክክለኛነት ለማሻሻል፣ በተለይም በተበላሹ ወይም ባልተሟሉ ሰነዶች ምክንያት የትርጉም መዛባት እንዳይከሰት፤ እንዲሁም ለኔትወርኩ ግራ የሚያጋቡ ገጾችን ወይም ሌሎች የገፅ ገጽታዎችን እንዴት ለማስተካከል ጥረት በማድረግ ላይ ነው።ቡድኑ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የእጅ ጽሁፎችንም ለመተርጎም የሚያስችል ፕሮግራም ለማዘጋጀት መቻሉን ያብራሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሂልደጉንድ ሙለር፤ ይህም ለተጠቃሚዎች መረጃን የመገልበጥ እና የመተርጎም ችሎታ ያለው ፕሮግራም ለማዳበር የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
እንደ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሂልደጉንድ ሙለር፤“እነዚህ የእጅ ጽሁፎች በእርግጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ናቸው።እያንዳንዱ ጥሩ የስነ -ጽሑፍ ሥራ በብዙ ታሪካዊ ኩነቶች የተከበበ ነው ፣ ግን በእርግጥ ጠቃሚ የሚሆነው እነዚህ ታሪካዊ ማህደሮች ዙሪያ ምርምሮች ሲካሄዱ ነው” ብለዋል ሙለር። እነዚህን ጹሁፎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ። ጥረቶቹ ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
ስለ መካከለኛው ዘመን እና ከመካከለኛ ዘመን በኋላ ስላሉት ስለ መጀመሪያዎቹ ዘመናት፣ ታሪካዊ ክስተቶች ዝርዝሮች እና ውጤቶች ለመረዳት ከተፈለገ እነዚህን ጥንታዊ የእጅ ጽሁፎችን መመልከት የግድ ነው፤ በወቅቱ የነበሩ ነገሮችን በቅጡ ለመረዳት እነዚህ የእጅ ጽሁፎች ብቸኛ ሀብቶች ናቸው ብለዋል።
ጥንታዊ ጽሁፎችን በመጠቀም ረገድ በምዕራቡ ዓለም አካባቢ በአንጻሩ የተሻለ ሁኔታ ቢኖርም፤ እነዚህ ሀብቶችን ያለመንከባከብ እና ያለመጠቀም ችግር ከምዕራቡ ዓለም ውጭ የበለጠ አሳሳቢ መሆኑን ያነሱት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ የችግሩን ጥልቀት ለመረዳት በመጥፋት ላይ ባሉ ባህሎች ውስጥ እየጠፉ ያሉ ቋንቋዎችን ማሰብ ብቻ በቂ ነው ይላሉ።ችግሮችን ለመከላከል ደግሞ በቅድሚያ ቋንቋዎቹንና በቋንቋው የተጻፉ ጽሁፎችን መጠበቅ የግድ ነው። በመቀጠልም ተደራሽ ማድረግ እና በተወሰነ ደረጃ ትርጉሞችን ማካተት አለብን፣አስፈላጊም ነው ። አሁንም በመካሄድ ላይ ያሉ የባህላዊ ሂደቶች አካል እንዲሆኑ ለማድረግ ከጊዜ ጋር እሽቅድድም ውስጥ ነን ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ያልተቋረጠ ብዙ ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ የእጅ ጽሁፍ ታሪክ ያላት ብቸኛዋ ሀገር መሆኗ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ በግዕዝ የተጻፉ ብዙ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ይገኛሉ።አብዛኞቹ የእጅ ጽሁፎች እጅግ የቆዩ በመሆናቸው ያለቴክኖሎጂ መሳሪያ ድጋፍ ለማንበብ እንኳ የሚያዳግቱ ናቸው።ከእነዚህ ውስጥ በርካታ የእጅ ጽሁፎች በተለያዩ ወቅቶች በስርቆት እና በዝርፊያ ወደ ምዕራቡ ዓለም ተወስደዋል።የተወሰዱትን ሀብቶች ለማስመለስ በተደረገ ጥረትም የተወሰኑ ተመልሰዋል።
ሆኖም በሀገራችን ውስጥ ያሉትን የእጅ ጽሑፎች ወደ ዲጂታል ሊለውጡ በሚችሉ የኦፕቲካል ገጸ -ባህሪ (ኦሲአር) ስርዓቶች እጥረት ምክንያት በቤተክርስቲያን ውስጥ ጥቅም ላይ ከመዋል ባሻገር በሰፊው ለጥናትና ምርምር ሲውል አይታይም። በመሆኑም እነዚህን የእጅ ጽሁፎችን ለመጠቀም አዳጋች አድርጎት ቆይቷል።
እነዚህን የጥንት ሰነዶችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ጥረቶችን ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት በሚፈለገው ልክ ሳይንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በዘርፉ ጥረቶችን እያደረጉ ያሉ የሀገራችን ምሁራን ጥንታዊ የእጅ ፅሁፎችን ማንበብ የሚችል አርቴፊሻል ኒዩራል ኔት ወርክ (ሰው ሰራሽ የነርቭ አውታረ መረብ) በማበልጸግ ላይ ካሉት የኖተርዳም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩበት ሁኔታ ቢመቻች ኢትዮጵያ ሀብቶቿን በአግባቡ እንድትጠቀም እድል ሊከፍት ይችላል።
ጽሁፎቹን ለመጠቀም ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በቤተክርስቲያን፣መስጊዶች እንዲሁም በተለያዩ ቤተመጽሃፍት ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ የሥነ-ጽሑፎች አብያተ-መጻሕፍት፤ የአንድ ሀገር፤ አህጉር ብሎም የሰውን ልጅ የእድገት ታሪክ ያዘሉ በመሆናቸው እንክብካቤ እና ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013