የነሐሴ መጀመሪያ የህፃናት ሰቆቃ ቀን ሆኗል። የመንግሥትን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደ ጎን በማለት ህጻናትን ጭምር በማስታጠቅ የአፋር እና የአማራ ክልሎች ላይ ትንኮሳ እየፈጸመ ያለው አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል 107 ህጻናትን መግደሉን አልጀዚራ ዘግቧል። አልጀዚራ በዘገባው ላይ እንዳለው፤ ይህ ቡድን ቃሊ ኩማ በተባለ የአፋር ክልል ውስጥ 240 ንጹኃንን ገድሏል። ከእነዚህ ሟቾች መካከልም 140ዎቹ ህጻናት ናቸው።
የአሸባሪው ታጣቂዎች ወደ መንደሯ በመግባት በከባድ መሳሪያዎች በፈጸሙት ድብደባ ንጹኃኑን ገድለዋል ብሏል አልጀዚራ። የአልጀዚራው ዘጋቢ ሀሰን አብደል ራዛቅ እንዳለው ህወሓት አሁንም በአፋር ክልል ላይ የሚያደርገውን ትንኮሳ ቀጥሎበታል። ይህን ዜና እንዳደመጥን ነበር ጦርነት በህፃናት አስተዳደግ ላይ ስለሚያሳድረው ተፅእኖ የባለሙያ ምክር የጠየቅነው።
የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት እና የልጅ በእድሉ አይደግ መፅሀፍ ደራሲ ዶክተር ሄኖክ ዘውዱ እንደተናገሩት ሁል ጊዜም በጦርነት ቀዳሚ ተጎጂዎቹ ህፃናት፤ ሴቶች፤ አቅመ ደካሞች ናቸው። በአንድም በሌላም መልኩ የተለያዩ ጉዳቶች የሚደርስባቸው እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። በተለይም ህፃናት በጦር ቀጠና መኖራቸው በራሱ ከባድ የስነ ልቦና ጫና ከመፍጠሩም ባሻገር በወትድርና ላይ ተሳትፈው መገኘታቸው ደግሞ የማይሽር የስነ ልቦና ጠባሳ ጥሎባቸው እንደሚያልፍ ይናገራሉ።
ህፃናት በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሲኖሩ ለተለያዩ ስነ ልቦናዊም ሆነ መሠረታዊ ፍላጎቶችን የማጣት ችግር ይገጥማቸዋል። በተለይ በጦርነት ቀጠና ውስጥ መኖር መሠረታዊ ነገሮች እንደ ምግብ ልብስ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ ያደርጋል።
ልጆች ከሚኖሩበት ቦታ ወደ ሌላ ሊያውም ባልተረጋጋ መንፈስ የመፈናቀል ሁኔታ ሲደርስባቸው በስጋት ውስጥ ለመሆን ይገደዳሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከወላጅ መነጠል ደግሞ ሌላ አስከፊ የስነ ልቦና ጫና የሚፈጥር ጉዳይ ነው። ከዚህም ሌላ በካምፕ በጋራ ሲኖር ለተስቦና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ ይሆናሉ። በመማሪያ እድሜያቸውም ከትምህርት ይታጎላሉ ከቤተሰብ ጋር ከተነጠሉም ለጭንቀት ይዳረጋሉ። ይባስ ብሎም አካል መጉደልና ህይወት ላይ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ከዚህ ባለፈ ለፍርሀትና ሰቆቃ ለድህረ አደጋ ጭንቀትና ድባቴ ይጋለጣሉ።
ህፃናቱ በጦር ቀጠና ውስጥ መኖራቸው ከሚያስከትለው ስነ ልቦናዊ ጫና በተጨማሪ ህፃናት ወታደሮች ደግሞ ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል በጥቂቱ እንመለከታለን። በዓለም ላይ ከ 4 ህፃናት አንዱ ጦርነት ወይም ግጭት ባለበት አካባቢ ይኖራል። በዓለም አቀፍ ደረጃም ከ300,000 በላይ ህፃናትና ታዳጊዎች በወታደርነት ተመልምለው ጦርነት ውስጥ ይገባሉ።
ህፃናት ወታደሮች በአብዛኛው ተገደው ወይም ተታለው በወታደርነት፣ በጦር ቀጠና ውስጥ በሰራተኝነት እንዲሁም በሰላይነት እና በመሳሰሉት መልኩ በግዳጅ ያገለግላሉ። ይህም ለከፋ የጤና፣ የስነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ይዳርጋቸዋል።
እንደተባበሩት መንግስታት (UN) መመሪያ መሠረት ማንኛውም ከ18 ዓመት በታች ያለ ህፃን ጤናው ተጠብቆ የመኖርና ከማንኛውም አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ተጠብቆ መኖር እንዳለበት በግልጽ ተቀምጧል። በመሆኑም ህፃናትን በወታደርነት መመልመልና ማሠልጠን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ጭምር የሚያስቀጣ ወንጀል ነው። ነገር ግን አንዳንድ ሀገራት ከ16 ዓመት እድሜ ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎችን ለወታደርነት በመመልመል ስልጠና ይሰጣሉ ለአብነትም እንግሊዝ ተጠቃሽ ናት። በመሆኑም በዋነኛነት ህፃናት ወታደሮች ብለው የሚጠሩዋቸው ከ15 ዓመት በታች ያሉትን ነው። እነዚህ ህፃናት ወታደሮች ላይ የሚገጥሟቸው ከትምህርት ገበታ መስተጓጎል እና ከሚደርስባቸው የኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘለለ ለከፋ የማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ይዳረጋሉ።
በጦር ሜዳ ውሎ ላይም ቢሆን የሚያሠቅቁ ነገሮችን ማየት፤ ፆታዊ ጥቃት፤ አዕምሮን ለሚጎዱ ነገሮች (ኬሚካሎች) መዳረግ (በተለይም ህፃናቱ የሚያደፋፍሩ መድሃኒቶች ከተሰጣቸው) በግዳጅ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው። በተለይ በእነዚህ ህፃናት ላይ ስር የሰደደ የስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ቀውሶች መከሰት በወደፊት ህይወታቸው ላይ ጥቁር ጠባሳን ያስቀምጣል።
በዋነኛነት የሚታዩ ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ ችግሮች መካከል ድባቴና ጭንቀት፤ ድህረ አደጋ ጭንቀት (PTSD)፤ የመገለል ችግር፤ ጥላቻ፤ጥቃት አድራሽ መሆን፤ የሀዘን ስሜት ውስጥ መሆን፤ ራስን ዝቅ አድርጎ መሳል፤ ራስን ከሌሎች መነጠል ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።
በዚህ ጉዳይ ላይ በሴራሊዮን የእርስ በርስ ግጭት (1991-2002) በተሳተፉ ከ500 በላይ ህፃናት ወታደሮች ላይ የተደረገ ጥናት 47 በመቶ የሚያክሉት በድባቴና ጭንቀት ሲሰቃዩ 27 በመቶ ያህሉ ደሞ ድህረ አደጋ ጭንቀት (PTSD) ታይቶባቸዋል። ተመሳሳይ ግኝትም በዩጋንዳው አማፂ ሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ ታዳጊ ወታደሮች ላይ ተዘግቧል። እናም ህጻናትን ለጦርነት ባለማሰለፍ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። እነዚህ ህፃናትና ታዳጊ ወታደሮች ከጦር ሜዳ በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ብዙ ችግሮች፣ መገለልና ተቀባይነት ማጣት ይገጥማቸዋል። በመሆኑም ማህበረሰቡ አለማግለል፤ ተገደው እንደገቡበት መረዳትና መቀበል እንደ ጥፋተኛ አለመቁጠር፤ የጦር ሜዳ ውሎዋቸውንና ምስላቸውን አለማጋራት (ማህበራዊ ሚዲያ ላይ) በመንግሥት ደረጃም የማገገሚያና መማሪያ ማእከላትን በማቋቋም የስነልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ማመቻቸት ያስፈልጋል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ሄኖክ ገለፃ ህፃናት በሰላም የመኖር መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩና በጦርነት ምክንያት ከሚደርስባቸው የስነ ልቦና ጫና ለመከላከል፤ በሁሉም የግጭት አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ አካላት ለሰላም የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወን ይገባቸዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013