በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛ የሆነው ኒያላ በስፋት ለስፖርት አደን ተፈላጊ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለአደን የሚውል አንድ ኒያላም እስከ 15 ሺህ ብር ዋጋ ያወጣል። ለስፖርት አደን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትም በዓለም ላይ እውቅና ያላቸው በገንዘብ አቅማቸውም ከፍተኛ የተባሉ ናቸው። በስፖርት አደን የሚደሰቱና የሚዝናኑ ስለሚያድኑት የዱር እንስሳት አይነትና ብቸኛም ስለመሆኑ እንዲሁም እንስሳውን ያገኙበትን ሀገር ጭምር ለሌሎች እንደትልቅ ጀብድ ያወሩላቸዋል። እነርሱ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ በስፖርቱ በመዝናናት ጊዜያቸውን ሲያሳልፉና ሲደሰቱ፤ የተከለለ የአደን ቦታን በማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ ለሚፈጥሩላቸው ሀገራት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደጊያና የኢኮኖሚ ምንጭ ነው። በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ አንዱ በሆነው የስፖርት አደን ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ስትሆን ፣ በስፖርት አደን ውስጥ ያሉት ተዋናዮች የተለያዩ በመሆናቸው የኢኮኖሚ ጥቅም መገለጫዎችም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው።
የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሙያ (ዋይልድ ላይፍ ኢኮሎጂስት) ዶክተር ዘላለም ተፈራ እንደነገሩን ፤ የስፖርት አደን ቱሪስቶች ለአደን ተብሎ የተከለለውን ቦታና የተመረጠውን እንስሳ ቀድመው መረጃ በመሰብሰብ ነው የሚንቀሳቀሱት። ለአደን ሲንቀሳቀሱም አሳዳኝ ባለሙያ አብሮት ይኖራል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም የስፖርት አደን ሥፍራዎች በባሌ ተራራ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በደቡብ ክልል የአደን ቀበሌዎች የሚገኙ ሲሆን፣ እያንዳንዱ የአደን ቀበሌም ኮታ ስላለው በኮታው መሠረት የስፖርት አደን ቱሪስት ወደ ሀገር ሲመጣ ያስተናግዳሉ። አሳዳኝ ድርጅት ለአደን ወደተከለለው ሥፍራ ቱሪስቱን ይዞ ከመሄዱ በፊትም በቅድሚያ ክፍያ ይፈጸማል። ከክፍያው የአካባቢው ማህበረሰብም ተጠቃሚ ነው። ከአደኑ በተጨማሪም ለቱሪስቱ መጓጓዣ ፈረስ በማከራየትና በአካባቢያቸው መስህብ የሆኑ ነገሮችን በማቅረብ ገቢ ያገኛሉ። የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ድርጅትም እንዲሁ ከአደኑ ገቢ ያገኛል። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው የስፖርት አደን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው።
በተደጋጋሚ እንደሚባለው ኢትዮጵያ ወቅትን መሠረት ያደረገ የቱሪስት ፍሰት ነው የምታስተናግደው። የስፖርት አደንም እንዲሁ ወቅትን መሠረት ያደረገ ነው የሚል ጥያቄ ለዶክተር ዘላለም አንስቼላቸው እሳቸውም ይህን መልሰዋል። ‹‹አደን ዓመቱን ሙሉ እንዳይካሄድ የሚገድብ ነገር የለም። ነገር ግን እንስሳቱ በሚራቡበትና በሚዳቀሉበት ወቅት የስፖርት አደን ማካሄድ አይፈቀድም።ቱሪስቶችም መንቀሳቀስ የሚችሉበትን የአየርፀባይ ስለሚመርጡ ይህም ግምት ውስጥ ይገባል። በተለይም ከአየር ፀባይ ጋር በተያያዘ ከጥቅምት እስከ መጋቢት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ መንቀሳቀስ ይመርጣሉ። አብዛኛው ቱሪስት እነዚህን ወቅቶች ይመርጣል። ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም በማንኛውም ጊዜ የሚመጣ ቱሪስትም አይጠፋም›› በማለት ያስረዳሉ ።
የስፖርት አደን ቱሪዝም በኢኮኖሚው ላይ ምን ያህል አበርክቶ እንዳለው በአሀዝ የተደገፈ መረጃ ለማቅረብ ባይቻልም የማይናቅ ሚና እንዳለው ግን ከባለሙያው መረዳት ይቻላል።ይህ ዘርፍ በዓለም ላይ በተከሰተው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ምክንያት እንቅስቃሴው መዳከሙንና ገቢም እየነጠፈ መሆኑን በዘርፉ ከተሰማሩ ሰዎች ያገኙትን መረጃ መሰረት አድርገው ዶክተር ዘላለም ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የኮቪድ 19 ክትባት እስኪዳረስና ቱሪስቱም እምነት ጥሎ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ወደቀድሞው ለመመለስ ጊዜ ይፈልጋል። አሁን ላይ ለቱሪዝሙ መቀዛቀዝ እንደምክንያት የሚነሱት ቀጣይነት እንደማይኖራቸው ታሳቢ በማድረግ የዱር እንስሳት መኖሪያዎችን አረንጓዴ በማልበስና በመንከባከብ ጠብቆ ማቀየት ይገባል። ከዚህ አንጻር በሁለት ዙሮች የተካሄዱትንና አሁን በሦስተኛው ዙር በመካሄድ ላይ ስላለው አረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ ለዱር እንስሳቱ ስለሚኖረው ጠቀሜታ እንዳስረዱት፤ የዱር እንስሳት መኖሪያ ደን እየተመናመነና ለእርሻም እየዋለ በመሆኑ የዱር እንስሳቱ መኖሪያቸውን ለቀው ለመሰደድ ይገደዳሉ። ደን በማልበስ አካባቢዎችን ማሻሻል ያስፈልጋል። የተተከሉት የዛፍ ችግኞችም ሆኑ በመተከል ላይ ያሉት ፀድቀው የአካባቢ ስነምህዳር መጠበቅ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የዱር እንስሳቱ ሰፋ ወዳለ ቦታ ለመሄድና ለመራባት ጥሩ ይሆንላቸዋል። አረንጓዴ ልማቱ ሲጠናከርና ደን መሆን ሲጀምር በዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢ ከብቶች ማሰማራት፣ግጦሽ ማካሄድ፣ለማገዶና ለተለያየ ነገር ደን መጨፍጨፍና ማቃጠል እንዲቀንስም ያግዛል።
በደንብ ከተሰራ የቱሪዝም ምርት የማይሆን ነገር የለም። የመፍጠር፣የተፈጠረውን ደግሞ ገበያ ላይ በማዋል ተጠቃሚ ለመሆን አቅም ነው የሚያስፈልገው። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የቱሪዝም መስህብ የሚሆኑ ብዙ ሀብቶች አሏት። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን እንደ አንድ የቱሪዝም ምርት በሚገባው ልክ ተጠቅማለች የሚል እምነት የለኝም። ለቱሪዝም ልማት አንዱ የተፈጥሮ ሀብት ነው ካልን የዱር እንስሳት ሀብት ይጠቀሳል። በዚህ ዘርፍ እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም ተገኝቷል ብሎ ደፍሮ ለመናገር ያስቸግራል በማለት ሀሳባቸውን የሰጡኝ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ከሙራ ዋቅጅራ ናቸው።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የዱር እንስሳት ሀብት ከሚጠበቅባቸው መንገዶች አንዱ ፓርኮችን ማቋቋም ነው። ዕፅዋቱ፣ እንስሳቱ በአጠቃላይ የብዝሃ ህይወት ስብጥሩ የመልክዓ ምድር አቀማመጡ፣ ለቱሪዝም መስህብነት ያለው አቅም፣ በዙሪያው ያሉ ባህላዊ እሴቶች በአንድ ላይ መስተጋብር የሚፈጥሩ ከሆነ የዱር እንስሳቱን ማዕከል አድርጎ ጥበቃና ልማቱ ይቋቋማል።በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም ዓለም አቀፍ መስፈርቱን መሠረት በማድረግ የዱር ስንስሳት ልማት ጥበቃዎች በስፋት ሲከናወን ቆይቷል። አብዛኞቹ የዱር እንስሳት ፓርኮችም እስከ 60 ዓመት ያስቆጠሩ ዕድሜ ጠገብ ናቸው። ይሁን እንጂ የልማትና የጥበቃ ሥርዓትን ለመተግበር የሚያስችሉ ፖሊሲ፣አዋጅና ሌሎች ማዕቀፎች ቢኖሩም ከማህበረሰብ እስከ መንግሥት መዋቅር ድረስ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። በመሆኑም በዘርፉ እንደሀገር በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል ለማለት አያስደፍርም። የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም በቂ ባለመሆናቸው ነው ውጤቱ አናሳ የሆነው።
የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ንግድ ነው እስከተባለ ድረስ እንደማንኛውም ምርት በገበያው ውስጥ በማስተዋወቅና በመሸጥ በውድድር ውስጥ ማለፍንና ማሸነፍን ይጠይቃል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ገበያውን ሰብራ የመግባት አቅም አልፈጠረችም።ውድድሩ ከጎረቤት ሀገራት ኬኒያ፣ታንዛኒያና ሌሎችም የዱር እንስሳት የቱሪዝም ሀብት ካላቸው ሀገራት ጋር ነው። ሀገራቱ በዘርፉ የሚገኙበትና አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በንጽጽር ሲቀርብ አይደራረሱም። ሀገራቱ በዱር እንስሳት ቱሪዝም የላቁ ሲሆን፣ውጤቱም የዱር እንስሳት መኖሪያ ወይም ፓርክና ለዘርፉ የሚያስፈለግውን መሠረተ ልማት በማልማት፣ ዘርፉን በመምራት ጭምር ይገለጻል።
በኢትዮጵያ በዘርፉ ላይ በትኩረት እየተሰራ ያለው ሀብቱን ማዳን ነው።በአሁኑ ጊዜ የተሻሉ ተብለው ከሚጠቀሱ እንደ ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ያሉትን ከአስጎብኝ ድርጅቶችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በማስተዋወቅ ለገበያ የማቅረብ ሥራ በመሰራት ላይ ይገኛል። በቂ ነው የሚባል ባይሆንም ከተለያዩ ዓለማት ቱሪስቶችን ለመሳብ ጥረት ተደርጓል።
በዚህ መንገድ እንቅስቃሴ ቢደረግም የስፖርት አደኑም ሆነ የዱር እንስሳት ፓርኮች የቱሪዝም እንቅስቃሴ በኮቪድ 19 ወረርሽኝና ከወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተዳክሟል። የዘርፉ ችግር ጫና የበዛበት ቢሆንም እስካሁን የነበሩት እንቅስቃሴዎች ወደፊት ተስፋ የሚያሳድሩ አይደሉም ወይ ለሚለው ጥያቄ ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ ቅድመ ኮቪድ የነበረውም እንቅስቃሴ ዜሮ ነበር የሚል መደምደሚያ የለም። በንጽጽር የሚቀርብ መረጃ ካልሆነ በስተቀር በየዓመቱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተመዝግበዋል።በአመት እስከ 80 ሺህ ድረስ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፓርኮችን ይጎበኛሉ። ዕድገቱም በአማካይ እስከ 10 በመቶ ደርሷል። አሁንም ቢሆን ሌሎች ሀገሮች በቀን የሚያስተናግዱት የቱሪስት ብዛት መጠን በኢትዮጵያ በዓመት የሚያስተናገድ ሊሆን ይችላል። በጎረቤት ሀገራት እስከ አንድ መቶ ሺህ ቱሪስቶችን ያስጎበኛሉ። ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት በአንድ ፓርክ ብቻ የሚገኝ ነው። የጎብኚው ቁጥር በዓመት እስከ ሚሊየን ይደርሳል። ንጽጽሩም ከዚህ አንጻር ነው። ንጽጽሩም የበለጠ ለመሥራት የሚያግዝ በመሆኑ ማሳየቱ ጠቃሚ ነው። ጎረቤት ሀገሮች የደረሱበት ደረጃ መድረስ ባይቻል እንኳን ለመቀራረብ ጥረት መደረግ አለበት። ጥረቱ ደግሞ በተግባር መከናወን ይኖርበታል። በተለይም መንገድ፣ መብራት፣ ስልክ፣ኢንተርኔት የመሳሰሉትን መሠረተ ልማቶች እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀና የተሟላ አገልግሎት ያላቸው ማረፊያዎች ለቱሪዝም መዳረሻ ወሳኝ ናቸው። አሁን እንደ ሀገር የተጀመረው ገበታ ለሀገር እንቅስቃሴ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተነሳሽነት የተሰሩትና በሂደት ላይ ያሉት ፓርኮችም ለዘርፉ ትልቅ ማነቃቂያዎች ናቸው።
ድህረ ኮቪድ ጫናው ዓለም አቀፋዊ ነው። የኢትዮጵያን የተለየ የሚያደርገው አነስተኛ የነበረውን እንቅስቃሴ የበለጠ እንዲዳከም ማድረጉ ነው። የኮቪድ ክትባቱ በተዳረሰባቸው አካባቢዎች እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ይኼ ለኢትዮጵያም ተስፋ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። እንዲያውም በተቃራኒው ክትባቱ ሙሉ ለሙሉ ከተዳረሰ በኋላ የቱሪስት ፍሰቱ በጣም ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። ከቦታ ቦታ ብቻ ሳይሆን ከቤቱም እንዳይወጣ ታፍኖ የቆየ በመሆኑ በሩ መከፈት ሲጀምር ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ያጋጥማል የሚል ግምት አለ። የተፈጠሩ ሀብቶች ያሉበትን ሁኔታ ለይቶ በመጠበቅና በመንከባከብ አልምቶ ዝግጁ ማድረግ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት።
በአሁኑ ጊዜ እንደተቀዛቀዘ መቀጠል ስለሌበት ቀጣይ አቅጣጫዎች ትኩረት ማግኘት አለባቸው። ከዚህ አንፃር ባለሥልጣኑ ምን አቅዷል የሚለው ተከታዩ ጥያቄ ነበር። ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ ዕድገት አንዱ ምሶሶ መሆኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግሥት ልዩ ትኩረት አግኝቷል። የተሰጠውን ትኩረት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም እስከ ታች ድረስ ወርዶ ሥራዎችን መሥራት ከተቻለ ዘርፉን ማሳደግም ሆነ ጥቅም ማግኘት ይቻላል። በዘርፉ ላይ እየተነሱ ያሉ ክፍተቶች በአሥር ዓመቱ ሀገራዊ መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው አንፃር መከናወን ያለባቸው ሥራዎች በዝርዝር በመሥፈራቸው። በዚህ ሰፋ ያለ የዕቅድ ሥራም ውጤታማ ተግባር እንደሚከናወን ይጠበቃል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013