ክረምትና በጋ ፣ ቆላና ደጋ የየራሳቸው ተፈጥሯዊ ባህሪ አላቸው:: ሰው ኑሮውን ለማሸነፍ ሲል ወቅቱ ወይም አካባቢው የሚፈልገውን ስራ እየሰራ ይኖራል:: በቆላማው የአየር ንብረት የሚፈለግ አንድ ነገር በደጋማው የአየር ንብረት ላይፈለግ ይችላል:: የምግብ ሸቀጦችና አልባሳት በበጋ እና በክረምት ያላቸው ተፈላጊነት እንደ ወቅቱ ሁኔታ ይወሰናል::
በክረምት ወቅት ሙቀትን የሚሰጥ አለባበስና አመጋገብ እንደሚያስፈልግ ይታመናል:: ምናልባት በዚህ ሰዓት ጀላቲና ስስ ልብሶችን ለመሸጥ የሚዘጋጅ ነጋዴ ቢኖር እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም ላያገኝ ይችላል:: ለዚህ ነው ወቅትን ማየትና ፍላጎትና አቅርቦትን ማጥናት የነጋዴዎች ቀዳሚ ተግባር የሚሆነው:: ብልህ ነጋዴዎች ሁኔታዎችን እያነበቡ ስራቸውን በማቀያየር ኑሯቸውን ለማሸነፍ ይጥራሉ::
የዛሬው እንግዳችን እራሱን ለማኖርና ቤተሰቦቹንም ለመርዳት ሲል ክረምትና በጋ ሲፈራረቁ እርሱም የተለያዩ ስራዎችን እያቀያየረ በመስራት ኑሮውን ለማሸነፍ የሚጥር ነው::
ከሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ ሌስትሮነት፣ የታክሲ ረዳትነት፣ የጉልበት ሰራተኝነት፣ ቅቅል በቆሎ ሻጭነት የሚጠቀሱ ናቸው:: ሁሉንም እንደአዋጭነታቸው የስራ ወቅት መድቦላቸው እያቀያያረ ይሠራል:: ወጣቱ ልክ ክረምት ሲገባ በየዓመቱ የሚሰራውን ስራ አቋርጦ በቆሎ እየቀቀለ በመሸጥ እንደሚተዳደር ይገልጻል::
ሌሊት መርካቶ ተገኝቶ ከክፍለ ሀገር እሸት በቆሎ ጭነው ከሚመጡ መኪኖች ላይ የሸክም ስራ ይሠራል:: ለሚሰራው የጉልበት ስራም ይከፈለዋል:: በዚህ የስራ ሂደት ውስጥ ሆኖ ባደረገው ጥናት መሰረት ሌላ ስራ መስራት ችሏል:: በሸቃቀለው ብር እዚያው ከነጓዴዎቹ ላይ በቆሎ ገዝቶ እየቀቀለ በመሸጥ ቀኑን ያሳልፋል::
ወጣቱን ከሌሎች ለየት የሚያርገው በአንድ ስራ ላይ ተወስኖ ከመቀመጥ ይልቅ እንደሁኔታው ቶሎ ቶሎ ስራውን እየቀያየረ ገቢው እንዳይነጥፍ የሚጥር መሆኑ ነው:: የስራ ተሞኩሮው አስተማሪ በመሆኑ የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርገው ወደናል::
ደበበ ማማዬ ይባላል:: ትውልዱና እድገቱ ደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ጊምቢቹ ወረዳ ልዩ መጠሪያው ሚኖ በሚባል የገጠር ቀበሌ ነው:: ለቤተሰቦቹ ስድስተኛና የመጨረሻ ልጅ ሲሆን ቤተሰቦቹ አርሶ አደር ናቸው:: ደበበ እራሱን ማወቅ ከጀመረ ወዲህ በጎችና ላሞችን በማገድ ጉልጓሎና አረም በማረምና በመላላክ ቤተሰቦቹን በስራ ያግዝ እንደነበር ይናገራል:: እድሜው ለትምህርት የደረሰ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት ቤት የገባው ዘግይቶ ነበር:: ያም ሆኖ እስከ አራተኛ ክፍል እንደተማረ ቤተሰቦቹ ባለባቸው የአቅም ውሱንነት ምክንያት ብዙም ሳይገፋ ትምህርቱን ለማቋረጥ ይገደዳል::
ደበበ ገና እሮጦ ሳይጠግብ እራሱን ከቤተብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በማሰብ ሰርቶ የሚኖርበትን አማራጭ ይፈልግ ጀመር:: በአንድ ወቅት ከእርሱ በእድሜ የሚበልጡ የሰፈሩ ልጆች አዲስ አበባ ሄደው ገንዘብ ቋጥረው ሲመጡ አይቶ እርሱም ከትውልድ አካባቢው ርቆ በመሄድ ሰርቶ ለመኖር ልቡ ይከጅላል:: የመስቀል በዓልን ለማክበር የመጡትን የሰፈሮቹን ልጆች ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ይኮበልላል::
አዲስ አበባ እንደደረሰ ጓደኞቹ ጋር ተጠግቶ የቀን ስራ እየሰራ መኖር ይጀምራል:: ጥቂት ገንዘብ በእጁ ላይ ከያዘ በኋላ የሌስትሮ እቃ ገዝቶ እየተዟዟረ ጫማ ይጠርጋል:: ማረፊያውን አውቶቡስ ተራ ሰላሳ ሁለት አካባቢ ያደረገው ታዳጊ ሌስትሮ እየሰራ በቀን ከሃያ እስከ ሰላሳ ብር ለመኝታው እየከፈለና አምባሻ በሻይ እየተመገበ የአዲስ አበባ ህይወትን መለማመዱን ይቀጥላል::
ይሁንና በየጊዜው እየጨመረ በሚሄደው የኑሮ ውድነት ምክንያት ህይወቱን ማሻሻል ያቅተዋል:: በተለይም ክረምት ሲገባ የሌስትሮ ስራ መቀዛቀዙን ተከትሎ ደበበ የእለት ወጪውን መሸፈን እስኪያቅተው ድረስ እንደሚቸገር ይናገራል::
ብልሁ ወጣት ከሁለት ዓመት የስራ ልምዱ ባገኘው ተሞክሮ ክረምት ሲገባ ሌስትሮ ከመስራት ይልቅ ሌላ ስራ መስራት እንደሚያዋጣ ይገነዘባል:: በዚሁ መሰረት በሶስተኛ ዓመት የአዲስ አበባ ቆይታው ልክ ክረምት ሲገባ ሌስትሮ መስራቱን አቁሞ የታክሲ ረዳት ይሆናል:: የምግቡን ችሎ ከሚሰጠው ብር ላይ ለመኝታው እየከፈለ ሁለቱን ወራት ካሳለፈ በኋላ በጋውን ወደ የሌስትሮነት ሙያው ይመለሳል::
ደበበ በበጋ ወቅት ሌስትሮነት መስራት ከታክሲ ረዳትነት እንደሚሻል አጥንቷል:: በሌስትሮ ስራ በቀን እስከ 250 ብር ሊያገኝ ይችላል:: በዚህም ላይ ሲፈልግ እያረፈ የሚሰራበትን እድል ያገኛል:: ክረምት ላይ ግን ከሌስትሮው ስራ የታክሲ ረዳት መሆን እንደሚሻል ያምናል:: እንደ እርሱ አባባል ታክሲ ረዳትነት ብዙ ነጻነት የማይሰጥ፤ ከሰዎች ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ የሚያስገባና ለአደጋም ተጋላጭ የሚያደርግ ነው:: ያም ሆኖ ከጎጃም በረንዳ አዲሱ ገበያ ባለው መስመር ለሁለት ተከታታይ የክረምት ወቅቶች የታክሲ ረዳት ሆኖ በመስራት አስቸጋሪውን የክረምት ወቅት ተሻግሮበታል:: ለእጁ ከምትሰጠው የእለት ገቢ ላይ እያጠራቀመ የአቅሙን ያህል ቤተሰቦቹንም ለመርዳት ሞክሯል:: ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነት ምክንያት የሚያወጣው ወጪ ከገቢው ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ዓይኖቹ ሁልጊዜ የተሻለ ስራ ፍለጋ ማማተራቸውን አልተውም::
ደበበ ዛሬ አስቸጋሪውን የክረምት ወቅት ለመሻገር የታክሲ ረዳት ሆኖ ከመስራት ይልቅ አዋጭነው ባለው ሌላ ስራ ላይ ተሰማርቷል:: ወደ አዲሱ የክረምት ስራው የገባበትን ክስተትም እንዲህ ያስረዳል::
‹‹በቀን ሰላሳ ብር እየከፈልኩ ከማድርበት መኝታ ቤት አቅራቢያ ሁልጊዜ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት አካባቢ መኪኖች እሸት በቆሎ ጭነው ይመጣሉ:: አብረውኝ የሚያድሩ የቀን ሰራተኞች በቆሎውን ለማውረድ ሲነሱ እኔም አብሬያቸው እነሳና እሸከማለሁ:: ልክ እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ከሰራሁና ገንዘብ ካገኘሁ በኋላ ወደ ታክሲ ስራዬ እሄዳለሁ:: አንድ ቀን ግን የሆነ ሀሳብ መጣልኝ:: ታክሲ ላይ ከምሰራ ለምን ቀን ቀን በቆሎ እየቀቀልኩ አልሸጥም? የሚል ሀሳብ ተመላለሰብኝ:: ነግጄ አላውቅም፤ ግን ከበቆሎ ነጋዴዎች ጋር ስለምግባባ ከእነርሱ እየገዛሁ ብሸጥ እንደሚያወጣኝ አስቤ ወደ ስራው ለመግባት ወሰንኩኝ::
በቆሎ እየቀቀሉ ለመሸጥ የሚያስፈልጉ እቃዎችን ዝርዝር ካወጣሁ በኋላ ምን ያህል ገንዘብ ሊያስፈልገኝ እንደሚችል ሂሳብ ሰራሁኝ:: እጄ ላይ ባለችው ብር ላይ ተጨማሪ ከሌሎች ጓደኞቼ ተበድሬ መጀመሪያ አንድ ትልቅ ብረት ድስት እና ከሰል ማንደጃ በ1750 ብር ገዛሁ:: ከዚያም አንድ ቁምጣ/ማዳበሪያ በቆሎ በ800 ብር እና አንድ ቁምጣ ከሰል 180 ብር ገዝቼ ቄራ ወደ ጎፋ ማዞሪያው አካባቢ ሰው በሚበዛበት ስፍራ ቁጭ ብዬ መቀቀል ጀመርኩ::
ልምዱ ስላልነበረኝ በመጀመሪያው ቀን ከሰል ለማያያዝና በቆሎውን ላስቲክ ውስጥ አስገብቼ በእንፋሎት እንዲበስል የማድረጉ ስራ አስቸግሮኝ ነበር:: ነገር ግን በሰዎች እርዳታ ተወጣሁት:: እናም በቆሎው ሲበስል በሰባት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሂሳብ የተገዛውን አንድ ራስ በቆሎ ሁለት ቦታ እየሰበርኩ አምስት አምስት ብር መሸጥ ጀመርኩኝ:: ይሄ የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት ነው:: እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ስሸጥ አምሽቼ የቀቀልኩትን በቆሎ ሳልጨርስ ቀረሁ:: ያም ሆኖ ከታክሲ ረዳትነት ከማገኘው የእለት ገቢ የተሻለ አገኘሁ›› ይላል ደበበ:: አሁን ግን አንዱን ራስ በቆሎ ሁለት ቦታ ሰብሬ ሰባት ብር ነው የምሸጠው::
ደበበ በቀን የሚቀቅለው ውስን በቆሎ ቢሆንም ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ብር ጥቅም እንደሚያገኝ ይናገራል:: ዘንድሮን ጨምሮ ሁለት ክረምቶችን በቆሎ በመሸጥ አሳልፏል:: በሁለቱ ክረምቶች ከታክሲ ረዳትነት የተሻለ የእለት ገቢም አግኝቷል:: ገቢውን ለማሳደግ ቦታ እየቀያየረ ሰርቷል:: ቦታውን እንዲቀይር የሚያደርገው የገቢው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ አካባቢ የሚገኙ ደንብ አስከባሪዎች የጎዳና ላይ ንግድ ህገወጥ ስራ ነው በሚል ስራውን ስለሚያስተጓጉሉት እንደሆነም ይገልጻል::
እሸት በቆሎ እየቀቀለ መሸጥ የጀመረው ቄራ አካባቢ ነበር:: ከዚያም አራት ኪሎ ጆሊ ባር አካባቢ ይመጣል:: በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ስድስት ኪሎ የካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል በር አጠገብ እየሰራ ይገኛል:: ደበበ አሁን አንዷን እራስ በቆሎ በስምንት ብር ሂሳብ እየተረከበ ሁለት ቦታ ሰብሮ ሰባት ሰባት ብር ይሸጠዋል:: ስራውን እንደጨረሰ የከሰል ማንደጃውንና ብረት ድስቱን እዚያው ስድስት ኪሎ ከአንድ ሰው ቤት አስቀምጦ ወደ መርካቶ ማደሪያው ሰፈር ይሄዳል:: ጠዋት ጠዋት እንደተለመደው እሸት በቆሎውንና ከሰሉን ይዞ እየመጣ ወደ ስራው ይገባል::
ክረምቱ ዘላቂ ቢሆንና እሸት በቆሎም ገበያ ላይ ቢኖር ህይወቱን ሊለውጥበት የሚያስችለው ስራ እንደሆነ ይናገራል:: ግን የበቆሎ ንግዱ ከሁለትና ሶስት ወራት የማይዘል በመሆኑ የመስከረም ወር እንዳበቃ ወደ ሌሎች ስራዎቹ ይመለሳል:: ምክንያቱም በጋውን ለሌስትሮና ለታክሲ ረዳትነት ስራ ክረምቱን ለበቆሎ ንግድ አድርጎታል::
ደበበ ወደፊት መንጃ ፈቃድ አውጥቶ በሾፌርነት የመስራት ህልም ስላለው የክረምቱ የበቆሎ ገበያ ሲቀዛቀዝ በመጪዎቹ የበጋ ወራት ወደ ታክሲ ረዳትነት ስራው የመመለስ እቅድ እንዳለው ይናገራል:: የገንዘብ አቅሙን ቢያሳድግ ደግሞ ሱቅ ተከራይቶ አልባሳትን የመሸጥ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል::
ገንዘብ ለማግኘት እና እራስን አሸንፎ ለመኖር ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚናገረው ወጣቱ፣ ጠንክሮ በመስራት ከችግር ለመላቀቅ እየተጋ መሆኑን ያስረዳል:: ደበበ ዛሬ እራሱን ችሎ እየኖረ ነው:: ያን ያህል አይሁን እንጂ ከሚያገኛት ጥቂት ገንዘብ አንዳንዴ ለቤተሰቦቹም ይልካል::
አንዳንዴም ዓመት በዓል ሲሆን እቃ እየገዛ ይጠይቃቸዋል:: አልፎ አልፎም የሥራ ወቅት ሲሆን ቤተሰቦቹን እየሄደ አዝመራ በመሰብሰብ ያግዛቸዋል:: አሁን ባለበት ሁኔታ ትምህርቱን መማር አለመቻሉ ያንገበግዋል:: ቀን በቀን ካልሰራ መኖር ስለማይችል ስለ ጉሮሮው እንጂ ስለ ትምህርቱ የሚያስብበት ሁኔታ እንዳልተመቻቸለት ይገልጻል::
አብዛኛዎቹ አብሯ ደግ ጓደኞቹ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ወደ ደቡብ አፍሪካ መሰደዳቸውን የሚናገረው ደበበ፣ አንዳንዶቹ ህይወታቸውን እንዳጡና አንዳንዶቹም ተንገላተው እንደተመለሱ ይጠቅሳል::
ደበበ ከመሃል ከተማ ራቅ ብሎ ቤት ተከራይቶ የመኖር አቅም ላይ እንደደረሰ ቢናገርም ከአስር ሰዓት ጀምሮ መርካቶ ተገኝቶ የሸክም ስራ ለመስራት ስለማያመቸው እዚያው መርካቶ በቀን ሰላሳ ብር የመኝታ እየከፈለ ለማደር ተገዷል::
ከሀገሩ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን ጎዳና ላይ አድሮ እንደማያውቅና ለምኖ እንደማያውቅም የሚናገረው ወጣቱ ሌላው ቀርቶ አቅም ያላቸውን የራሱን ዘመዶች እንኳ እንዲረዱት ጠይቋቸው እንደማያውቅ ይገልጻል፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ እራሱን የማኖር ሃላፊነት እንደተጣለበት የሚናገረው ደበበ ከሀገር ቤት ጀምሮ ዶሮ እያረባ እንቁላል በመሸጥ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈ መሆኑን ይገልጻል:: ይህ የልጅነት ትጋቱ ለዛሬ ጥንካሬው እገዛ እንዳደረገለት ይናገራል:: እንደ ወቅቱ ሁኔታ ስራውን እያቀያየረ ህይወቱን የሚመራው ወጣት ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደረስ በመመኘት እንሰናበታለን:: ሳምንት ሌላ ባለታሪክ ይዘን እስክንመጣ ቸር እንሰንብት::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013