ብራ ሆኖ የዋለው የመስከረም አየር ምሽቱን ቀለል ያለው ይመስላል:: በዝናብና ጭቃ የከረመው መሬት ስፍራውን በአረንጓዴ አለምልሞት ይታያል:: ነፋሻማው ቀን በስሱ የሚወርደውን ካፊያ ለማባረር ትግል እየገጠመ ነው:: አንድ አፍታ ሽው የሚለው ንፋስ የመንገዱን አቧራ ከካፊያው ጋር እየጠረገ ቦታ ያስለቅቃል:: አቅም ቢሱ ዝናብ ጫን ያለውን ንፋስ እየተቋቋመው አይደለም::
ብቅ ጥልቅ የሚለው ካፊያ አሁን ሙሉ ለሙሉ በዝናቡ ተሸንፏል :: ስፍራውን በአሸናፊነት የተረከበው ነፋሻማ አየር በሁሉም ዘንድ ይሁንታ ያገኘ ይመስላል:: ሳር ቅጠሉን እያራገበ መልካም ስሜትን ማዳረሰ ይዟል:: አሁን እንደነበረ ተረጋግቶ የቆየው ምሽት እየገፋ ነው:: በጊዜ ወደየቤታቸው የገቡ በርካቶች ለመንገዱ ዝምታ ምክንያት ሆነዋል::
መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም
የሰሚት ጎዳና ጭር ብሏል:: በአካባቢው በየአፍታው ሽው ከሚሉ መኪኖች በቀር የረባ እንቅስቃሴ አይታይም:: ነዋሪዎች ከቆዩበት ጉዳይ በጊዜ ወደቤት ከገቡ ቆይተዋል:: በየመዝናኛው የታደሙ አንዳንዶች የዓመላቸውን አድርሰው ተመልሰዋል:: ቀኑን ሙሉ በመኪኖች አጀብ የሚጨናነቀው ጎዳና ወለል ብሎ እየታየ ነው::
በተለምዶ ሰሚት ሰባ ሁለት ካሬ የሚባለው ሰፈር የአካባቢውን ጭርታ ተጋርቷል:: መንደሩ የመኖሪያ ስፍራ ነው:: በጊዜ የግቢ በሮቻቸውን የዘጉ ነዋሪዎች በየቤታቸው ታድመዋል:: አልፎ በርቀት የሚሰማው የጅቦች ጩኸት ለአፍታ ብቅ እያለ ይጠፋል:: የውሾችና ፣ የእንቁራሪቶች ደማቅ ድምፅ የአካባቢውን ጭርታ እየታገለ ነው::
ከለሊቱ 7 ሰአት ከ45 ሆኗል:: በስፍራው ከተገነቡ ዘመናዊ ፎቅ ቤቶች በአንደኛው ግቢ እንቅልፍ ያላሸነፋቸው ነፍሶች ጨዋታ ላይ ናቸው:: የቤቱን አባወራ ጨምሮ ከፊል ቤተሰቦች እኩለ ሌሊቱ ያስጨነቃቸው አይመስልም:: እየሳቁ ያወራሉ፤እያወሩ ይስቃሉ::
የቤት ሰራተኛዋ እመቤት አሁንም ልክ እንደቀን ውሎዋ በስራ ላይ ነች:: አልፎ አልፎ ሶስተኛ ፎቅ ላይ ሆና በመስታወቱ ወደ ውጭ ትቃኛለች:: እንዲህ ባደረገች ጊዜ የስፍራው ጨለማ መልሶ ይታያታል:: እሷ ግን ከማየት አትቆጠብም:: በስራዋ መሀል ደጅ ደጁን እያስተዋለች መለስ ትላለች::ብቅ፣ መልሳ ደግሞ ጥልቅ፡ በጨለማው በድቅድቁ ይህን ልምድ አዘውትራለች::
እመቤት ጥቂት በስራ ባዝና ወደውጭ ቃኘች:: የለመደችው ድቅድቅ ጨለማ አሁን ብቻውን አይደለም:: ጥቁሩ ገጽታ በድንገት በብርሃን ሲደምቅ ታያት:: ዐይኖቿን አላመነችም:: በትክክል የምታየው ነገር እውነት መሆኑን አውቃለች:: የቤታቸው መኪና ከነበረችበት ቦታ እየተንቀሳቀሰች ነው::
መኪናዋ ሁሌም የምትቆመው ከግቢያቸው ውጭ ከአጥሩ አቅራቢያ ነው:: የቤቱ አባወራ ከቤት እንዳሉ ታውቃለች:: በዚህ ሰአት ማን እንደሚያንቀሳቅሳት አልገባትም:: ጥርጣሬዋ አየለ:: እመቤት ፍጥነቷን ጨምራ በደረጃው ወደላይ ወጣች:: ድምጽዋን አጉልታም ተጣራች::
ወዲያው የቤቱ አባወራ የሆነውን አወቁ:: የግላቸው መኪና ሞተሯ ሞቆ መንቀሳቀስ ጀምራለች:: እየሮጡ ፎቁን ወረዱ::ግቢውን አልፈው ወደመኪናዋ ቀረቡ:: አጠገቧ ሲደርሱ ከውስጥ የተቀመጡ ሰዎች ታዩአቸው:: እጃቸውን እያውለበለቡ እንዲቆሙ አሳሰቡ:: ሰዎቹ በትክክል አይተዋቸዋል:: ሊሰሟቸውም መኪናዋን ሊያቆሙላቸው አልፈቀዱም:: ፍጥነታቸውን ጨምረው ወደፊት ተፈተለኩ::
አባወራው ድንጋጤ ውጧቸዋል:: ቢርበተበቱም የሚያደርጉት አልጠፋቸውም:: የእጅ ስልካቸውን አውጥተው ወደ ጎረቤት ደወሉ:: ጥሪያቸውን የመለሰው ወዳጃቸው ያሉትን ሰምቶ ወደ እሳቸው ፈጠነ:: መኪና ይዟል:: ትንፋሽ እያጠራቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩት:: ሰውዬው አልዘገየም:: ሰዎቹ ወዳቀኑበት አቅጣጫ ፈጠነ::
ጎረቤታሞቹ የመኪናውን መንገድ ተከትለው ሩጫቸውን አፋጠኑ:: ከሰሙት የሞተር ድምጽ ሌላ የታያቸው የለም:: ተስፋ አልቆረጡም:: የመንገዱ ጭርታ ወደፊት ለመክነፍ አገዛቸው:: የጀመሩትን ፍጥነት አልገቱም:: የመኪናው ባለቤት የንብረታቸውን መዘረፍ በቀላሉ አላመኑም:: ጥርሳቸው እየተፋጨ ፣ ሰውነታቸው ይንዘፈዘፋል:: እጃቸውን ደጋግመው ያማታሉ:: ዓይናቸውን ከሰፊው ጥርጊያ ሳይነቅሉ ጎረቤታቸው ወደፊት እንዲፈጥን ይወተውታሉ::
ረጅሙን መንገድ አቋርጠው እስኪጓዙ ከእነሱ የቀደመውን መኪና አልደረሱበትም:: ድምጹን መስማት ጭሱን ማየት አልሆነላቸውም:: ሁለቱም ንዴት ውስጥ ገቡ:: መኪናቸው ከአይናቸው ከራቀች ቆይታለች::ተስፋ አልቆረጡም::
ሰዎቹ ከደረሱበት ጫፍ ወደ ጎሮ አቅጣጫ መክነፍ ቀጠሉ:: አደባባዩ አጠገብ ሲደርሱ መደዳውን ቆመው ገበያ የሚጠብቁ የምሽት ታክሲዎችን አስተዋሉ:: ፍጥነታቸውን አረገቡና ባለ ላዳዎቹን ጠየቁ:: የመኪናዋን አይነትና ቀለም ምልክት አድርገው በመንገዱ ስለማለፏ እንዲነግሯቸው ጠበቁ::
ባለታክሲዎቹ የሰዎቹን ጭንቀትና ሁኔታ ተረድተው ለምላሹ ተጣደፉ:: ከደቂቃዎች በፊት እነሱ ያሉት አይነት መኪና በአስደንጋጭ ፍጥነት እየከነፈ በአጠገባቸው ማለፉን ያለጥርጥር አረጋገጡ:: ጎረቤታሞቹ ሰዎቹ የጠቆሟቸውን አቅጣጫ ተከትለው ዳግመኛ ወደፊት ከነፉ::
እልህ ንዴትና ቁጭት የያዛቸው ፈላጊዎች የመኪና መብራት ባዩ ቁጥር ከኋላ ለመድረስ ይፈጥናሉ:: አጠገቡ ሲቆሙ ያሰቡት እንዳልሆነ ይረዳሉ:: መልሰው ከነፍጥነታቸው እየሮጡ ይፈተለካሉ:: የጨለማው አሳሾች ያለእረፍት እየከነፉ ነው::አሁን ዳግም ወደ ገርጂ አቅጣጫ ታጥፈዋል:: ዓይኖቻቸው ከወዲያ ወዲህ ይቃብዛሉ:: ልቦቻቸው ያለመቋረጥ ይመታሉ:: ያለመታከት ሮጡ::ያለድካም ነዱ::
ባለ ታክሲዎቹ አልዋሹዋቸውም:: ተፈላጊው ቶዮታ ኮሮላ ከፊትና ከኋላ ሰዎችን አጭቆ በርቀት ታያቸው:: አሁን ገርጂ ሮባ ዳቦ ቤት ከተባለ ስፍራ ደርሰዋል:: ዘራፊዎች አልፈዋል የተባለበት ሰአት ቢርቅም በትክክል እያዩዋቸው ነው:: ፍጥነታቸው አልተገታም:: የተባራሪዎችን ጀርባ ተከትለው አጠገባቸው ቀረቡ:: ጊዜ አላጠፉም:: አባራሪዎቹ በአስደንጋጭ ጡሩንምባ እያንቧረቁ ከመኪናው ግንባር ገጥመው መንገዱን ዘጉባቸው ::
መኮንን …
ተወልዶ ደገው አዲስ አበባ ነው:: ገና በማለዳው ቤተሰቦቹ ደብተር አስይዘው ትምህርት ቤት ልከውት ነበር:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በወጉ ተምሯል:: አስረኛ ክፍል ሲደርስ ግን ያሰበው አልተሳካም:: ሲጠብቀው የቆየው ውጤት እንዳልሆን ሆነበት::
መኮንን ሌሎች ዓመታትን ለትምህርት አልሰጠም:: አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ በአካባቢው ከሚገኝ አንድ ሆቴል ዲጄ ሆኖ ተቀጠረ:: የሚያገኘው ገንዘብ እሱን ጨምሮ ቤተሰቦቹን ያግዛል:: የሚሰራበት ሆቴል ምሽቱን በሙዚቃ ደንበኞችን ያዝናናል::ይህ አጋጣሚ ለሙዚቃ አጫዋቹ መኮንን መልካም ሆኖለት ዘልቋል። ስራው ከብዙ ሰዎች አስተዋውቆት ጥሩ ገቢ ያስገኝለታል::
መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት የነመኮንን ሆቴል እንደወትሮው በደንበኞች ሲተራመስ አምሽቷል:: እኩለ ለሊቱ አለፍ እንዳለ የሆቴሉ ገበያ መቀዛቀዝ ያዘ:: በቦታው የቀሩት ጥቂት እንግዶች የያዙትን እየጨለጡ፣ ሂሳባቸውን ከፍለው ወጡ::
በሙዚቃ ሲያጫውት የቆየው መኮንን ፈጠን ብሎ የቤቱን በር ዘጋና ውስጥ ወዳሉት ባልንጀሮቹ ተመለሰ:: ወዲያው ካሉበት ወጣ ብለው ለመዝናናት ፣ለመጠጣት ወሰኑ:: ውሳኔው በስምምነት ጸድቆም በችኮላ ከነበሩበት ተነሱ:: ከመራቃቸው በፊት ግን አንድ ኮሮላ የቤት መኪና ከፊታቸው ቆሞ ሾፌሩ ወዴት ናችሁ? አላቸው::
ሰውዬው ደሳለኝ ይባላል:: የሆቴሉ ደንበኛ ነው:: በመኪናው ሰዎችን ይዟል:: እነመኮንን እንዲገቡ ጋበዛቸው:: አልተግደረደሩም:: ከፊትና ከኋላ ታጭቀው ለመዝናናት ፣ለመጠጣት ወደ ገርጂ አቅጣጫ ከነፉ::
ሴቶቹ …
የመንገዱ ዳርቻ ጭር ማለት ከጀመረ ቆየት ብሏል:: ምሽቱን የመኪና መብራታቸውን ቦግ አድርገው የሚያልፉ አሽከርካሪዎች በየመንገዱ ያለውን እውነት ያውቁታል:: በአጭር ቀሚስና ፣ በራቁት ገጽታ ቆመው ወጪ ወራጁን የሚቃኙ አንዳንድ ሴቶች ባለመኪኖቹን ከመሀል ገብተው ሊያስቆሟቸው ይሞክራሉ:: የምሽት እንጀራቸውን፣ለማግኘት በአስፓልቱ ጠርዝ ከወዲያ ወዲህ ከሚሉት እንስቶች አብዛኞቹ ያሰቡትን አያገኙም:: በብርድና ውርጭ እንደወረዙ ከጠዋቷ ጸሀይ ይገናኛሉ::
ኤልሳና ሶፍያ ‹‹ቢዝነስ ›› ለሚሉት ስራቸው እንደወትሮው ከአስፓልቱ ጠርዝ ተገኝተዋል:: ወጪ ወራጁን ለመማረክ፣በአላፊ አግዳሚው ለመታየት የማይሆኑት የማያሳዩት ትዕይንት የለም:: እነሱም እንደሌሎች እግራቸውን እያነሱ፣ እጃቸውን እያውለበለቡ ፈላጊዎቻቸውን ይፈልጋሉ::
ምሽቱ እየገፋ ሰአቱ መጨመር ሲይዝ ሴቶቹ ስለገበያቸው ተስፋ ቆረጡ:: ዕለቱ ለእነሱ ቀና አልሆነም:: እንዲህ በሆነ ጊዜ አብዝተው መቆማቸውን፣ ሰው መናፈቃቸውን ይተዋሉ:: ድካማቸውን ለመርሳት፣ ችግራቸውን ለመዘንጋትም ብርጭቆ እያነሱ ዘና ማለት ይወዳሉ::
ቆይታቸውን ከመጠጥ ቤት አጠናቀው ወደ ማረፊያቸው ለመሄድ አማራጮች ፈለጉ:: ባለ ላዳዎቹ ደንበኞቻቸው በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ካሰቡት ሲያደርሷቸው ቆይተዋል::ዛሬም እንዲህ ከማድረግ የዘለለ ዕድል የላቸውም::
ከአንድ ቦታ ጎራ ማለት የፈለጉት ሴቶች ምርጫቸው በአካባቢው ያለ ሆቴል ሆነ:: አሁን በብርድ የተኮማተረው ገላቸው በመጠጥ ሞቅ ማለት አለበት:: ኪሳቸውን ዳበሱ:: ላሳቡት ቆይታ የሚሆናቸው በቂ ገንዘብ ይዘዋል:: ተያይዘው ወደሆቴሉ ሲገቡ ብዙ ወንበሮች ክፍት ነበሩ:: ሴቶቹ በሙዚቃ እየተወዛወዙ ፣ የሚጠጡትን አዘዙ::
ሴቶቹ ሆቴሉን ብቻ ሳይሆን ቤቱን በሀላፊነት የሚመራውን ወጣት ጭምር ያውቁታል:: ጥሩ መግባባትና ሰላምታ አላቸው:: ገበያ ባገኙና ባጡ ጊዜ ጎራ በሚሉበት ሆቴል ክፉና በጎ ቀናትን አሳልፈዋል:: አሁን ሴቶቹ ከምሽቱ ብርድና ድካም አገግመዋል:: ከመጠጡ ሲደጋግሙ ሙቀትና እፎይታ ተሰምቷቸዋል::
ከጠረጴዛቸው አለፍ ብለው የተቀመጡ ወንዶች ከቤቱ ሀላፊ ጋር በቅርበት ያወራሉ:: ለሴቶቹ መጠጥ ሂሳብ ከፍለዋል:: እነሱን ጨምሮ ሌሎች ሂሳባቸውን ዘግተው ለመሄድ ተነሱ:: ሁለቱ ሴቶችም በተመሳሳይ ከነበሩበት ተነስተው ለመሄድ ተዘጋጁ::
በር ላይ ቆመው ጥቂት እንዳማተሩ መኪና ከያዘው ሰው ጋር ተያዩ:: ቀደም ሲል አብሯቸው ካመሹት ወንዶች አንደኛው ነው:: ፡ሰውዬው ወደ እነሱ እያየ ወዴት ናችሁ ? አላቸው:: ሴቶቹ ቀልጠፍ ብለው ወደ መብራት ሀይል መሆናቸውን ተናገሩ:: ‹‹ልሸኛችሁ ›› አለና በሩን ከፈተላቸው::
ሁለቱ ሴቶች ከሁለቱ ወንዶች ጋር ከኋላ ተቀመጡ:: ቦታው ተጨናነቀ:: ከሁለቱ ሴቶች አንደኛዋ ከአንደኛው እግር ላይ ተቀመጠች:: ከአቅሟ በላይ የጫነችው መኪና ሌሎችንም ጨማምራ ለመንቀሳቀስ ተዘጋጀች::
ደረጀ…
ደረጀ ደምበል ትውልድና ዕድገቱ በአዲስ አበባ ነው::እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል:: ደረጀ እነ ደሳለኝን የተቀላቀለው ከታላቅ ወንድሙ ሆቴል ጉዳዩን ጨርሶ እንደወጣ ነበር:: ደረጀ የነደሳለኝን ማንነት አሳምሮ ያውቃል:: እነሱ በተለያየ ጊዜና ቦታ ያሻቸውን መኪና እየሰረቁ እንደሚሰወሩ ጠፍቶት አያውቅም::
ምሽቱን የያዙት መኪና የተሰረቀ ስለመሆኑ አልጠረጠረም::ሁሌም እንዳሻቸው በሚቀያይሩት መኪና ብዙ ነገር እንደሚፈጽሙ ያውቃል:: ሌሎች በኮሮላው የታጨቁት ሰዎች ምንነትም አልጠፋውም:: ያም ሆኖ ሊቀላቀላቸው ሲፈቅድ አልዘገየም:: ሴቶቹን በእግሮቹ ላይ አስቀምጦ ፣ባለው ቦታ ተጣቦ ለመሄድ ደስተኛ ነበር::
በመኪናዋ ተደራርበው ጉዞ ሲጀምሩ ሾፌሩ የመኪናውን ቁልፍ አስረከበው መንጃ ፈቃድ ያለው እሱ ብቻ በመሆኑ የሹፍርና መንበሩን ተረከበ:: አካባቢውን ለቀው ወደ ገርጂ አቅጣጫ ሲከንፉ ሰአቱ እኩለ ለሊቱ ገፍቶ ነበር::
አባራሪዎቹ…
አባራሪዎቹ ከኋላ ደርሰው ሁሉን አረጋገጡ:: በመኪናው አራት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ተጨናንቀው ተቀምጠዋል:: ጋቢናው ሁለት ሰዎችን አጋርቷል:: ሰድስቱ ሰዎች ድንገት ከሁለቱ ወንዶች ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጡ:: አባራሪዎቹ መኪናውን ዘግተው መቆማቸውን ያየው ደሳለኝ በድንጋጤ ክው አለ:: አስከትሎም ‹‹ተበላን.. ተበላን›› እያለ መጮህ ያዘ:: አባባሉ የገባቸውም ያልገባቸውም ድንጋጤውን ተጋሩት::
ሁለቱ አባራሪዎቹ ከመኪናው እንደወረዱ ወደጋቢናው አመሩ:: ወዲያው ከመሪው ላይ የተቀመጠውን አሽከርካሪ አነቁት:: ሾፌሩ ለምላሹ አልዘገየም:: እጃቸውን አስለቅቆ መታገል ያዘ:: አልቻላቸውም:: ይህን ሲያውቅ እንደምንም ታግሎ አመለጣቸው:: ይህኔ እሱን ያዩ ሌሎች ወንዶች ከጀርባቸው እየሮጡ ተከተሏቸው:: ደሳለኝና ሁለቱ ሴቶች በድንጋጤ እንደተዋጡ ከሰዎቹ እጅ ገቡ::
የፖሊስ ምርመራ..
ከፖሊስ ጣቢያው ደርሰው ጉዳያቸውን አቤት ካሉ ተበዳዮች መረጃ ያገኘው ፖሊስ ሶስቱን ሰዎች አቅርቦ ምርመራውን ጀመረ:: በመኪናው ከነበሩት ስድስት ሰዎች መካከል ሶስቱ ማምለጣቸው ተረጋግጧል:: መርማሪው ምክትል ሳጂን አዳም አስፋው የተጠርጣሪዎችን ቃል በወንጀል የመዝገብ ቁጥር 354/12 ላይ በአግባቡ መዘገበ:: ምርመራውን ሲጨርስ ሶስቱ ሰዎች ክስ ይመሰረትባቸው ዘንድ ዶሴውን ለዓቃቤ ህግ አስተላለፈ::
ውሳኔ…
ታህሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሶስቱ ተከሳሾች ላይ የመጨረሻ ብይን ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል:: ከፖሊስ መዝገብና ከዓቃቤህግ ክስ በቂ መረጃ የደረሰው ፍርድ ቤት መኪናውን የሰረቀው ተከሳሽ ደሳለኝ ውቤ ጥፋተኛ ስለመሆኑ አረጋግጧል:: በዕለቱ በሰጠው ብይንም ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲወስን፣ ሁለቱን ሴቶችም በነጻ አሰናብቷል፡፡
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013