ከ1990ዎቹ ማብቂያ እና ከ2000 ዓ.ም መግቢያ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ የቤት፣ የምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች በአጠቃላይ የሁሉም ነገር ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቆይቷል። ለዚህም ችግር መከሰት በርካታ መንስኤዎች መኖራቸውን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህ መንስኤዎች አንዱ የመንግስት ኢንቨስትመንቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እና ከኢንቨስትመንቶች የሚፈለገውን ያህል ምርትና ምርታማነት ማስገኘት አለመቻላቸው ነው፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ጣሰው ታደሰ እንደሚሉት፤ ከ1997ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል፡፡ በተመሳሳይ ዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱ በዋናነት በመንግስት ኢንቨስትመንት የመጣ ነበር፡፡ መንግስት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶች እና ብዙ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ነበር፡፡ ከነዚህ ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ ዘግይተውም ቢሆን ወደ ስራ ገብተዋል፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ ጭራሽ ወድቀዋል፡፡ አንዳንዶቹ የተወሰነ እጅ ገብተው ቆመው ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እስከዛሬም ዳዴ እያሉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በመንግስት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ ስራ አልገቡም፡፡ አብዛኞቹ የመንግስት ፕሮጀክቶች ውጤታማ አልነበሩም። መንግስት ያስጀመራቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ወደ ስራ አለመግባታቸው በራሱ የራሱን መዘዝ ሲያስከትል ነበር፡፡
የመንግስት ፕሮጀክቶች ውጤታማ ስላልነበሩ በተጠበቀው መጠን ምርት ወደ ኢኮኖሚ ማስገባት አልቻሉም የሚሉት ዶክተር ጣሰው፤ በዚህም ምክንያት በተፈለገው መጠን ገበያን ማረጋጋት አልተቻለም፡፡ በገበያ ውስጥ በጣም ከፍተኛ የምርት ፍላጎት አለ፡፡ በዚያ መጠን የምርት አቅርቦት ደግሞ የለም፡፡
የመንግስት ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ ገንዘብ በቂ ሳይሆን ሲቀር ከሀገር ውስጥ ባንኮች እና ከውጭ ሀገራት ሲበደር ነበር፡፡ እነዚህን ብድሮች በተለይም የሀገር ውስጥ ብድር ለመመለስ ገንዘብ በማተም ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ ሲያደርግ እንደነበር የሚያነሱት ዶክተር ጣሰው፤ ገንዘብ በተለያዩ መንገዶች በመንግስት ወደ ኢኮኖሚ በሰፊው ቢረጭም በሀገሪቱ ውስጥ ተመጣጣኝ የምርትና ምርታማነት እድገት ማስመዝገብ አልተቻለም። በመሆኑም በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ላለው የዋጋ ንረት ዋነኛው ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡
መንግሥት ኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት የተከተለው ይህ አሰራር የዋጋ ንረትን የሚፈጥር እንደነበር የሚያስረዱት ዶክተር ጣሰው፣ በብድር እና ብር በማተም የተነቃቃው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት በምርትና ምርታማነት መጨመር ያልታገዘ መሆኑ ለዋጋ ንረት ዋነኛ ገፊ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በገበያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ አቅርቦት መኖሩ የምርት እድገቱ ደግሞ ተመጣጣኝ አልነበረም፡፡ በብዙ ገንዘብ ጥቂት ምርት እንዲገዛ መሆኑ የመጀመሪያው ምክንያት ነው፡፡
“ላለፉት አስር እና አስራ አምስት አመታት የተከተልነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንድነው ፋይናንስ የተደረገው የሚለውን ማንሳት ይገባል። የመንግሥት መሰረተ ልማት ሰፍቷል፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሰፍተዋል፡፡ የዋጋ ንረቱ አንደኛው ምክንያት ይሄ የኢኮኖሚ ዕድገት የመጣበት መንገድ ነው። በዋናነት ከውጪ፣ ከሀገር ውስጥ የተበደርነው እንዲሁም ብር በማተም የመጣ ነው። ከምግብ ጀምሮ ለሸማች የሚሆኑ ዕቃዎች የማምረት አቅም በደንብ ሳያድግ ፍላጎት ጨምሯል” በማለት ሁኔታውን ያስረዳሉ፡፡
በአንድም በሌላም መንገድ የሀገሪቱ የዋጋ ንረት መንስኤ ልማትን ፋይናንስ ለማድረግ የሚወጣው ገንዘብ እና የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ የፊሲካል ፖሊሲ ናቸው የሚል እምነት እንዳላቸው የሚያነሱት ዶክተር ጣሰው፤ ስለዚህ የተረጋጋ ዋጋ እና አነስተኛ የዋጋ ንረት እንዲኖር ከተፈለገ አዲስ የሚቋቋመው መንግስት ታሳቢ ማድረግ ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ጣሰው ማብራሪያ፤ አነስተኛ የዋጋ ንረት እንዲኖር ከተፈለገ አንደኛው መፍትሄ የተረጋጋ የገንዘብ አቅርቦት ማረጋገጥ ነው፡፡ የገንዘብ አቅርቦቱ በኢኮኖሚው ውስጥ ካለው ምርትና ምርታማነት ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ ሁለቱን በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ማመጣጠን ባይቻል እንኳን በሁለቱ መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩነቱ እየጠበበ እንዲሄድ መደረግ አለበት፡፡
ለዚህም ፊሲካልና ሞኒተሪ ፖሊሲዎችን የማረጋጋት ስራዎች መሰራት አለባቸው። በተለይም ከፖሊሲ አንጻር መሰራት አለበት፡፡ መንግስት ለኢንቨስትመንቶቹ በሚያፈሰው ገንዘብ መጠን ማምረት ወይም የመንግስትን ኢንቨስትመንቶችን በመቀነስ ለግሉ ዘርፍ በማስተላለፍ የግሉ ዘርፍ የማምረት አቅም ሳይጠናከር የዋጋ ንረትን በቁጥጥር ሥር የመዋሉ ነገር እንደማይታሰብ ጠቁመዋል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013