ትውልድና እድገታቸው ይርጋለም ከተማ ቢሆንም በቤተሰባቸው የሥራ ዝውውር ምክንያት ወደ ሀዋሳ ከተማ በመሄድ ከስድስተኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በሀዋሳ ተከታትለዋል። ትጉ ተማሪ ቢሆኑም በወቅቱ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ሊያስገባቸው የሚያስችል ውጤት ሳያመጡ ቀርተው ወደ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በማቅናት የመምህርነት ሙያን ተቀላቅለዋል።
መነሻቸውን በመምህርነት ሙያ ላይ አድርገው በግል ጥረታቸው ኑሯቸውን ማሻሻል የቻሉት አቶ ያሬድ ገብረሚካኤል የእለቱ የስኬት እንግዳችን ናቸው። በትርፍ ጊዜያቸው መቀመጥ የማይወዱት አቶ ያሬድ ከመምህርነት ሥራቸው በተጨማሪ ተፈጥሮ ባደለቻቸው ችሎታ ተጠቅመው የተለያዩ የእንጨት ሥራዎችን በመስራት ትርፍ ጊዜያቸውን ትርጉም ባለው ተግባር ላይ በማሳለፍ ለዛሬ ደረጃ በቅተዋል።
ልክ እንደዛሬው የእንጨት ማሽን ባልነበረበት በዚያን ወቅት መላጊያ ተጠቅመው ለግላቸው አልጋና የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን መስራት የጀመሩት አቶ ያሬድ፤ ችሎታቸውና ጥረታቸው በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጎልቶ ለመታየት ዕድል አገኙ። እያገለገሉ ካሉበት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ አለታ ወንዶ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ። በትምህርት ቤቱም ከመደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ የተለያዩ ትምህርታዊ የሆኑ ማስታወቂያዎችንና በማዕከሉ የአርት ሥራዎችን በመሥራት ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል። በወቅቱም የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በማዘጋጀት ኤግዚቢሽን ማሳየት ችለዋል።
ከመምህርነት ሙያቸው ጎን ለጎን በውስጣቸው ያለውን የሥዕል ጥበብና የእንጨት ሥራ አጠናክረው የቀጠሉት አቶ ያሬድ፤ በተለይም ወደ እንጨት ሥራው በማድላት ማሽን ገዝተው በስፋት ማምረት ጀመሩ። ከእንጨት ሥራው በተጨማሪም ወደ ኮንስትራክሽን መለስ በማለት ፈቃድ አውጥተው ከአለታ ወንዶ ጀምረው በአካባቢው ባሉ የገጠር ከተሞች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መስራት ችለዋል።
የመምህርነትን ሙያን አጥብቀው ይወዱት እንደነበር የሚናገሩት አቶ ያሬድ፤ በተጓዳኝ የሚሰሯቸው የተለያዩ ሥራዎች ከመምህርነት ሙያ ገፍተው ያስወጧቸው ስለመሆኑ ያነሳሉ። ለዚህም የመምህርነት ሙያ ሰፋ ያለ ትርፍ ጊዜ የነበረው በመሆኑ በተጓዳኝ የሚሰሯቸው ሥራዎች ጊዜያቸውን እንደተሻማባቸውና አጥብቀው የሚወዱትን ሙያ ኢኮኖሚያቸውን ፈርጣማ ወደሚያደርገው የግል ሥራ ተሰማሩ። በዚህ ጊዜ መደበኛ በሆነ አካሄድ ሕጉን ተከትለው መልቀቂያ በመጠየቅ በ2004 ዓ.ም ከሚወዱት የመምህርነት ሙያ በክብር ተሰናበቱ። ከዛ ጊዜ ጀምረውም ሙሉ ጊዜያቸውን ለጠየቃቸውና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እያፈረጠመ ላለው የግል ሥራቸው አዋሉ፡፡
በወቅቱ የጀመሩትን የኮንስትራክሽን ሥራ በማስቀጠልም ከአለታ ወንዶ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ተሳትፈዋል። ቀጥለውም ከሞጆ ጅቡቲ በሚሰራው የመንገድ ሥራ ላይም ከቻይናውያን ጋር ኮንትራት ወስደው ሙያዊ አሻራቸውን አሳርፈዋል። ዘርፈ ብዙ የሙያ ባለቤት የሆኑት አቶ ያሬድ የኮንስትራክሽን ዘርፉን የተቀላቀሉት በልምድ ሲሆን፤ የእንጨት ሥራውንም ቢሆን ተማሪ እያሉ በክረምት ወቅት እንጨት ቤት ተቀጥረው መስራት በመቻላቸው ያገኙት እውቀት ነው። የሥዕል ሥራውም እንዲሁ በተማሪ ቤት ቆይታቸው ባካበቱት ልምድ አግኝተዋል።
በመምህርነት ሙያ ውስጥ በነበሩበት ወቅት በትምህርት ዘርፍ መሰማራት ምኞታቸው ነበር ። ይህንኑ ዕውን ለማድረግ ሲሉ ከቻይናውያን ጋር የነበራቸውን የኮንስትራክሽን ሥራ ገታ አድርገው ከአዲስ አበባ ወደ አለታ ወንዶ ተመለሱ። አለታ ወንዶ ተመልሰው ትምህርት ቤት ለመክፈት ሲነሱ በቅድሚያ ልምድ መቅሰም ፈለጉ። በመሆኑም ሌላ ቦታ ላይ ኮሌጅ ከፍቶ እየሰራ ካለ አንድ ሰው ውክልና በመውሰድ እርሳቸው ደግሞ አለታ ወንዶ ላይ ሥራውን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ልምድ ማካበት የቻሉት አቶ ያሬድ፤ ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ጊዜው ሆነና የራሳቸውን ኮሌጅ ለመክፈት ፈቃድ አውጥተው ዘርፉን መቀላቀል ቻሉ።
ታድያ ፈቃዱን ለማግኘት ማስተማሪያ ቦታን ጨምሮ ማሟላት የሚገባቸው በርካታ ነገሮችን አሟልተው ወደ ትምህርት ዘርፍ መግባት የግድ ብሏቸዋል። ይህን ለማሟላት በጥቂቱም ቢሆን መፈተናቸውን ያነሱት አቶ ያሬድ፤ ‹‹ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ ጠይቁ ይሰጣችኋል፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል›› በሚለው በታላቁ መጽሐፍ ታምነውና በጽናት ተግተው በመሥራታቸው የሚፈልጉትን ሁሉ እንዳገኙ ይናገራሉ።
በዚህ ጊዜ ታድያ የስኬታማነት መንገዳቸው ተጀምሯልና ቀና የሆኑ ሰዎች አጋጥመዋቸው ለትምህርት ሥራው ምቹና አስተማማኝ የሆነ ቦታን አግኝተው መግዛት ቻሉ። በወቅቱ ለቦታው የተጠየቀው ገንዘብ ምንም እንኳን ከአቅማቸው በላይ የነበረ ቢሆንም በእርሳቸው ድፍረት ላይ ፈጣሪ ተጨምሮበት ማግኘት እንደቻሉ ይጠቅሳሉ ። በተለይም ሥራ ላይ ድፍረት አስፈላጊ እንደሆነና እርሳቸውም ለሚሰሩት ሥራ በሙሉ በወኔና በድፍረት የሚነሱ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡
ቦታውን አጽድተው ለሚፈልጉት የትምህርት ሥራ ካመቻቹ በኋላ ፈቃዱን ማግኘት ቻሉ። ፈቃድ ካገኙ በኋላ በከተማዋ ዙሪያ ተዘዋውረው የማስታወቂያ ሥራውን በሚገባ ሰሩ። ከዚህ በኋላ በቂ ተማሪዎችን ማግኘት በመቻላቸው በቀጥታ በቢዝነስ ላይ የሚሰራውን ኤክሶደስ ኮሌጅን ዕውን በማድረግ ዕውቅና ባገኙበት አምስት የትምህርት ዘርፎች ማለትም በአይሲቲ፣ በአካውንቲንግ፣ በማኔጅመንት፣ በሴክሬቴሪያል ሳይንስና በማርኬቲንግ ለማስተማር የኮሌጅ ሥራቸው ተጀመረ።
‹‹ሁልጊዜም ወደ ተሻለ ከፍታ ላይ መውጣት አለብኝ ›› ብለው የሚያስቡት አቶ ያሬድ የኮሌጁን መጠሪያ ኤክሶደስ ማለታቸው ምንጊዜም ቢሆን መሻገርን፣ መውጣትንና የተሻለ ነገርን ለማምጣት የሚተጉ በመሆናቸው እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ሰዎች በትጋታቸው ልክ የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ እንዲሁም ለተቸገሩ ሰዎች መድረስ ከቻሉ መውጣት መሻገር ችለዋል። ነገር ግን ሰዎች ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ማናቸውም ነገሮች በራሳቸው ጥረት ማሟላት ሳይችሉ የሌሎችን እጅ ካዩ ይሄ ድህነት ነው ብለው ያምናሉ። ስለዚህ እንዲህ ካለ ድህነት እራስን ለማውጣት ያለዕረፍት መስራት ተገቢ እንደሆነና እርሳቸውም በሕይወታቸው የተገበሩት ይህንኑ ስለመሆኑ በኩራት ይጠቅሳሉ ። የኤክሶደስ ጥሬ ትርጉምም ይሄው መሆኑን ይናገራሉ።
ታድያ በአሁን ወቅት የመውጣት የመሻገር ትርጓሜ ባለው ኤክሶደስ ኮሌጅ ውስጥ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ ተማሪዎች አሉ። ኮሌጁም በአምስቱም የትምህርት ዝግጅት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩትን እነዚህን ተማሪዎች በቀጣይ ነሐሴ መጨረሻ አልያም መስከረም ላይ ለማስመረቅ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡
አቶ ያሬድ በኮሌጁ በቂ ተማሪ መዝግበው መምህራን ቀጥረው ሥራው በሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሶ መስመር ውስጥ ሲገባ ሌላ አዲስ ነገር ማሰብ ጀመሩ። ሁልጊዜም አዳዲስ ነገሮችን በማሰብ ወደ ውጤት ለመሸጋገር በሚያደረጉት ጥረት ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህም አንድ እርምጃ ወደ ፊት ሄዱ። የኮሌጁ ዙሪያ ገባ ቆሻሻ የሚጣልበትና ሽንት የሚሸናበት አካባቢ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በየጊዜው ቦታውን በማጽዳት አካባቢውን ማስዋብ ጀመሩ፡፡
አጋጣሚዎችን ወደ ዕድል መቀየር የሚችሉት አቶ ያሬድ አካባቢውን ውብ በማድረጋቸው አዲስ ሀሳብ ወደ አዕምሯቸው መጣ። ጸአዳ በሆነው አካባቢ የነበረውን ወንዝ መሰረት በማድረግም ቦታውን ላቢያጆ ወይም ምቹ የመኪና ማጠቢያ ቦታ ገንብተው ሥራ መፍጠር ቻሉ፡፡ ዕረፍት የለሹ አቶ ያሬድ፤ መኪና ሊያሳጥቡ የሚመጡ ደንበኞችን ታሳቢ በማድረግም ተጨማሪ የሥራ ፈጠራ ማሰናሰን ቀጠሉ።
አሰናስነውም አልቀሩም መኪና የሚያሳጥቡ ደንበኞች መኪናቸው እስኪታጠብ ድረስ አረፍ የሚሉበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻቹ፡፡ በዚህም ደንበኞች አረፍ በሚሉበት ቦታ አበቦችን ተክለው ከማስዋብ በተጨማሪ ሻይ ቡና መጠቀም እንዲችሉ በማጥናት የጀበና ቡና ሥራ ጀመሩ። አንዱ ሥራ ሌላ ሥራ እየወለደ መጣና ከጀበና ቡና ባለፈም ምግብ ቢዘጋጅ የተሻለ እንደሆነ ደንበኞች ያቀረቡትን ሀሳብ መሰረት በማድረግ መኪና ማጠቢያ ቦታ ላይ ምግብና ሻይ እንዲሁም የጀበና ቡና መቅረብ ጀመረ። በዚህም ለሌሎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ተጨማሪ ገቢ ማመንጨት ቀጠሉ።
አንድን ነገር ተመርኩዘው ሌሎች አዳዲስ ሥራዎችን መፍጠር የሚቀናቸው አቶ ያሬድ፤ መንግሥት በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተነሳሽነት ገበታ ለአገር ፕሮጀክቶች በተለያዩ አካባቢዎች ዕውን መሆን ሲጀምሩ እርሳቸውም ‹‹ገበታ ለአለታ ወንዶ›› የሚል ፕሮጀክትን ዕውን ማድረግ ተመኙ። ምኞታቸውንም ተግባራዊ ለማድረግ መነሻ ይሁነኝ በማለት ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው እንጦጦ እና አንድነት ፓርክን ጎብኙ። በጎበኙት ነገር ተደስተውና መስራት እንደሚቻል አምነው አለታ ወንዶ ላይ ለሰርግ፣ ለልደትና ለተለያዩ ፕሮግራሞች መገልገያ የሚሆን በ11 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውን ያቤጽ መናፈሻ በሶስት ሚሊዮን ብር መግዛት ችለዋል።
አካባቢው በተፈጥሮ የታደለና ለመናፈሻ ምቹ መሆኑ ጭምር አግዟቸው ያቤጽ መናፈሻን በማቋቋም ወደ ሥራ ገብተዋል። ቦታውን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የተለያዩ ግንባታዎችንም አከናውነዋል። በኤክሶደስ ኮሌጅ በመምህርነት እያገለገሉ ያሉ አምስት መምህራንን ጨምሮ በያቤጽ መናፈሻና በመኪና ማጠብ ሥራ እንዲሁም በቀን ሥራ ቀጥረው ከሚያሰሯቸው ጋር አጠቃላይ 50 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡
አቶ ያሬድ አሁን ለደረሱበት የኑሮ ደረጃ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው ዝቅ ብለው መስራታቸው መሆኑን አንስተዋል። ለዚህም ሥራ ሳይንቁ መስራትንና አዳዲስ ሀሳቦችን መከተል ጠቃሚ ቢሆንም ስኬት የሚገኘው ግን ከፈጣሪ እንደሆነ ያላቸውን ዕምነት ይገልጻሉ ። የሰዎች ጥረት ግን ወሳኝ መሆኑን ያምናሉ። በቀጣይም ያቤጽ መናፈሻን ከአለታ ወንዶ ባለፈ በክልሉ ተጠቃሽ መሆን የሚችል መናፈሻ የማድረግ ዕቅድ አላቸው። ይህን ዕቅዳቸውንም ዕውን ለማድረግ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የዋና ገንዳ እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑና ነገሮችን ለማሟላት እንዲሁም የእንግዳ ማረፊያ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ይህም ከተማዋ የቱሪስት መስህብ የምትሆንበት አጋጣሚ የሚያሰፋ ስለመሆኑ ዕምነታቸው ነው። እኛም እቅዳቸው እንዲሳካ በመመኘት በዚሁ አበቃን።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2013