ዓለም በፍጥነት እየተለወጠች ነው። በዓለም ላይ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ እያቀጣጠሉ ካሉ ነገሮች አንዱ ደግሞ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ነው። በከፍተኛ ፍጥነት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እየተካሄደባቸው ካሉት አንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው። ዲጂታል ኢኮኖሚ ቅርጽ እየያዘ መምጣቱን ተከትሎ የተለመደው በሰው እጅ የሚከናወኑ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እየቀነሱ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ቦታ እየለቀቁ ነው። አምራቾች የሚግባቡበት፤ ተገልጋዮች አገልግሎት፣ መረጃና ሸቀጥ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተቀየረ ነው።
ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ኦን ላይን የሚፈልጉትን አገልግሎት እና ሸቀጥ እስከማዘዝ ደርሰዋል። ዋጋቸውን እያነጻጸሩ፣ የፈለጉትን ዕቃና አገልግሎት እየገዙ ነው። ክፍያውን ኦን ላይን በመፈጸም የገዙትን እቃ በአጭር ጊዜ እስከ መረከብ ተደርሷል። ኢትዮጵያ ግን ለዲጂታል ኢኮኖሚ ገና አዲስ ናት። ገና ጅምር ላይ ትገኛለች። “ዲጂታል ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ” በሚል “የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ 2025” ፀድቆ ወደ ስራ የተገባው ባለፈው ዓመት ነው። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የተሰሩ እና በቀጣይ ሊሰሩ በሚገባቸው ስራዎች ዙሪያ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሰሞኑን በአዲስ አበባ መክረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ እንደተናገሩት፤ ስትራቴጂውን መረዳት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጠቀሜታዎችን በአግባቡ ማወቅ እና ማሳወቅ ካልተቻለ ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ 2025ን ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። በመሆኑም የአንድ ዓመት ጉዞ አብዛኛው ስራ ስትራቴጂውን የማሳወቅ፣ ህዝቡ እንዲገነዘብ እና ተቋማት የእቅዳቸው አካል የማድረግ ስራ በስፋት ሲሰራበት ነበር። የአንድ ዓመት ጉዞ በአጠቃላይ ፕሮግራሙን የማስተዋወቅ እና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል።
በተለይም ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ከሌሎች ዘርፎች ጋር የማስተሳሰር ስራዎች ተሰርቷል። ከግብርና ከቱሪዝም ዘርፎች ጋር የማስተሳሰር ሂደቱ አዳጋች የነበረ ቢሆንም በዚህ ረገድ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ ውስጥ በ2025 የሚሰጡ አገልግሎቶች ከወረቀት ንኪኪ ነጻ ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም አብራርተዋል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ትግበራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አብዮት ባዩ እንደተናገሩት፤ የዲጂታል ኢኮኖሚውን እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። የዲጂታል ክፍያ፣ የትራንዛክሽን አዋጅ፣ የስታርት አፕ አዋጅ፣ የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ በማርቀቅና በማፅደቅ በዲጂታል ዘርፍ አዲስ ከባቢያዊ ሁኔታ ተፈጥሯል። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በኢኮኖሚ ዘርፍ ብዙ ለውጦች እየተደረጉ ነው። ለውጡ የሚመራው በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ መሰረት ነው።
ዲጂታል ኢኮኖሚውን እውን ለማድረግ መከናወን አለበት ተብሎ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ ከተቀመጠው አቅጣጫ አንዱ የቴሌኮም ሪፎርሙን ማፋጠን ነው። በኢትዮጵያ ያለው የቴሌኮም ተደራሽነት በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ ከመሰረቱ መቀየር እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል። የቴሌኮም ሪፎርሙ በፍጥነት እየተካሄደ ይገኛል።
በተሰሩት ስራዎች የተንቀሳቃሽ ስልክ ሽፋን ባለባቸው አካባቢዎች 95 በመቶ ደርሷል። ስለዚህ በተንቀሳቃሽ ስልክ ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችን በሙሉ መስራት ይቻላል። የሞባይል ዳታ ተጠቃሚ ቁጥር 25 ሚሊዮን ደርሷል ይህም ማለት ለ25 ሚሊዮን ህዝብ በኢንተርኔት አገልግሎት ማቅረብ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ፤ ወደ 68 ከተሞች የ4ጂ ኤል ጂ ኢ ተጠቃሚ ናቸው፣ 52 ሚሊዮን ህዝብ ሞባይል አለው። ስለዚህ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ተሟልተዋል። ይህ ተይዞ ወደ ስራ መገባት ይቻላል ማለት ነው። በዚህ ዘርፍ የተደረጉ ሪፎርሞች ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሰረት ከሚጥሉት አንዱ ነው።
ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም ስትጠቀምባቸው የነበሩ ህጎች ለዲጂታል ዓለም የሚሆኑ አይደሉም። ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አስቻይ የሆኑ አዳዲስ ህጎችን ማርቀቅ እና ነባር ህጎችን የማሻሻል ስራም ለዲጂታል ኢኮኖሚ ወሳኝ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ይጠቁማሉ። ስለዚህ ነባር ህጎችን ማሻሻል እና አዳዲስ የህግ ሥርዓቶች መቀረጽ ነበረባቸው። በዚሁ መሰረት በርካታ አዳዲስ ህጎች ወጥተዋል፤ ነባር ህጎች ደግሞ ተሻሽለዋል። ከእነዚህም መካከል የኢ-ትራንዛክሽን አዋጅ አንዱ ነው። ይህ ህግ በዋናነት በወረቀት ወይም በንግግር ሲሰሩ የነበሩ፤ በፊት ተቀባይነት የነበራቸው ነገሮች አሁን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ሲሰሩ እኩል ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያደርግና የህግ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን ነው ያብራሩት።
እንደ አቶ አብዮት ማብራሪያ፤ የተለያዩ አካላት በሰው እጅ የሚሰሯቸው ስራዎችን ወደ ኤሌክትሮኒክስ ዘዴ እንዲቀይሩ የሚያስገድድ ህግም ወጥቷል። በተለይም የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን ደረጃ በደረጃ ወደ ኤሌክትሮኒስ ዘዴ መቀየር እንዳለባቸው የሚያስገድድ አዋጅ ነው። የዚህ አዋጅ ፋይዳው እና ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው።
አንድ ሰው በሳይበር ዓለም በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙት እንደሚችል የሚያብራሩት ዶክተር አብዮት፤ መብቱና ክብሩ ሊነካ እንደሚችል ያብራራሉ። አለፍ ሲልም ጉዳቶች ሊደርሱበት ይችላል። ስለዚህ አስፈላጊው ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል። የግል መብቱ፣ ክብሩ እንዲሁም ከተለያዩ ጉዳቶች ሊጠበቅ ይገባል። ለዚህም የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
የኢኮኖሚ በተለይም የዲጂታል ኢኮኖሚ ዋናው መሪ የግሉ ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ በተለይም በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚናውን መጫወት እንዲችሉ ከባቢውን ምቹ ማድረግ ወሳኝነት አለው። በተለይም በህግ በማስደገፍ ነው ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስፈልገው። የግሉ ዘርፍ ሚናውን እንዲጫወት የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።
እንደ ዶክተር አብዮት ገለጻ፤ አሁን ሁሉም ዘርፋቸውን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችላቸው አንጻራዊ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ምቹ ሁኔታው በፊት ከነበረው አንጻር ሲታይ እንጂ ከሚፈለገው አንጻር ብዙ የሚቀረው ነው። ከዚህ የተሻለ ምቹ ሁኔታ መፈጠር ነበረበት። ከሌሎች ሀገራት አንጻር የተለያዩ ዘርፎች ወደ ዲጂታል ዘርፍ በመቀላቀል ረገድ ወደ ኋላ ቀርተዋል።
የግንዛቤ እና የፋይናንስ እጥረት ዘርፉን እየጎዱ ካሉት መካከል ነው ያሉት ዶክተር አብዮት፤ የዲጂታል ኢኮኖሚ ምንነት እና ለኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ምን እንደሆነ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ ከቴክኖሎጂ ጽንሰ ሃሳብነት ባሻገር ማህበራዊ እድገት መሆኑን እንዲሁም አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ምንነት ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
የሳይበር ጥቃቶች ለመከላከል የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ወደ ትግበራ መገባቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው የተናገሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ወደዚህ ዘርፍ ስትገባ ምን ሊያጋጥማት ይችላል፣ ሌሎች ሀገራት ምን አጋጠማቸው፣ እንዴት ፈቱት የሚለውን ጥናት ማድረግ፣ ብሄራዊ የሳይበር ደህነት ማዕቀፍ ማዘጋጀት፣ አጠቃላይ የአሰራር ሥርዓቶች እንዲኖሩት የማድረግ እና ፖሊሲዎችን፣ ስታንዳርዶች ከሀገር ጀምሮ በተቋማት የሚሆኑ የአሰራር ስርዓቶችን የመዘርጋት ስራዎች ተሰርተዋል።
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ኤሌክትሮኒክስ መንግስት እና ኢ-ኮመርስ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የዲጂታል አገልግሎት ልማት ክፍል ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ሔኖክ አህመድ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም ከተሰሩት ስራዎች ባሻገር መሰራት ያለባቸው ሌሎች ስራዎችንም ጠቁመዋል። ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የአመራር ለውጥን ይጠይቃል። አመራሩ የዲጂታል አመራር አስተሳሰብ ያለው መሆን አለበት። ስለዚህ የአስተሳሰብ ለውጥ አስፈላጊ ነው። አመራሩ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚፈልገውን አቅም እና ብቃት ካልታጠቀ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን ማሳካት አይቻልም። በመሆኑም ዲጂታል አመራርን የመፍጠር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው።
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የፈጠራ ሰዎችን ይፈልጋል፤ ፈጣሪ መሆን ይጠበቃል። በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውስጥ የሚሰሩ አብዛኞቹ ስራዎች የአዳዲስ ነገሮች ፈጠራ ናቸው ። አዳዲስ የቢዝነስ ሞዴሎችን ይዞ መምጣትን ይጠይቃል፤ ያሉ ሞዴሎችን ማሻሻል የግድ ይላል። በሌላ በኩል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተበራከቱ እንደመሆናቸው አዳዲስ ሞዴሎችን ይዞ መምጣት ያስፈልጋል። ስለዚህ የፈጠራ ሰዎችን ማበረታታት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማቅረብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው።
እንደ አቶ ሔኖክ ማብራሪያ፤ ዲጂታል ማህበረሰብ ባልተፈጠረበት ሁኔታ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማሳካት አይታሰብም። የሰው ባህል መቀየር ያስፈልጋል። ዲጂታል ማህበረሰብ መፍጠር የግድ ነው። ማህበረሰቡ ስለ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያለው ግምት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም አሁንም ብዙ የሚቀረው ነው። ወጣቱ ትውልድ በሌላው ዓለም በተለያዩ መንገዶች የሚያያቸውን ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በሀገራቸው መጠቀም ይፈልጋሉ። ይህንን ፍላጎት መመለስ የሚቻለው ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትኩረት አድርጎ በመስራት ነው።
በዝግጅቱ ላይ የቴሌኮም ሌብራላይዜሽን፣ የመረጃ መረብ ደህንነት፣ የዲጂታል መታወቂያ፣ መሰረተ ልማት፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎ፣ ኢንዱስትሪ፣ የህዋ ሳይንስ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ኢኮሜርስና ሌሎች ጉዳዮች ላይም የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ገለፃ አድርገዋል። በዝግጅቱ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾችና ስራ ፈጣሪዎችን ጨምሮ የ 16 ተቋማት ኃላፊዎች በዘርፉ የተሰሩ ስራዎች አቅርበዋል።
ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን መሆን ተቋማት በትብብር እንዲሰሩና እንዲመክሩ ማስቻልን ታሳቢ ተደርጎ በተዘጋጀው በዚህ ዝግጅት ላይ በዘርፉ ተቋማት በተናጠልና በቅንጅት የሰሯቸው ስራዎች ቀርበዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩትና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊዎች የዘርፉ ስራዎችን የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2013