ስኬት ብዙ ደረጃዎችን የሚያካትት ሂደት ነው። የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማም ያሰቡትን እና ያቀዱትን እንዴት ማሳካት ይቻላል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ማስቻል ነው። ስለዚህ ምን ማድረግና ማግኘት እፈልጋለሁ የሚለውን ጥያቄ ማሰብ የግድ አስፈላጊ ነው። ሁሉም ሰው ማግኘት የሚፈልገውን መወሰን አለበት።
ያሰብነውን ለማሳካት ያስቀመጥናቸው መርሆች ለስኬታማነት የሚሆኑ መንገዶቻችን ናቸው። ስኬት የምንመራባቸው መርሆች ስብስብ ነው። ለስኬታችን ያስቀመጥናቸው መርሆች ከግባችን እንደሚያደርሱን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። ሰኬታማ ሰዎች ግባቸው ላይ ለመድረስ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፤ ምክንያቱም ስኬት ማለት ያስቀመጣቸው ግቦች ላይ የመድረስ ችሎታ ነው። ስኬት በትልቅ ስራ፣ በአስደሳች ጋብቻ እና ብዙ ገንዘብ ከማከማቸት ብቻ ጋር የሚያያዝ አይደለም፤ ያቀዱትን ማከናወን ወይም ማሳካት መቻልም ነው።
ስኬት በድንገት በአንድ ምሽት አይመጣም። ስኬት በችግር ፊት በመጽናት፣ በመታገስ፣ በእምነት፣ በድፍረት፣ በመሻሻል ውስጥ በሂደት የሚመጣ ለውጥ ነው። በህይወት ላይ ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልገውን በሙሉ ለማድረግ ዝግጁነት ያስፈልጋል። ስኬታማ ለመሆን ከአስተሳሰብ ጀምሮ በርካታ መሰረታዊ ጉዳዮችን ማዳበር የግድ አስፈለጊ ነው። ከእነዚህም ውስጥ አስፈላጊ ነው ያልካቸውን ከዚህ በታች በስፋት አቀርባለሁ።
1. በራስ መተማመን
አንድ ሰው በራሱ ችሎታ ወይም የራሱ በሆነ ውጫዊ እና ውስጣዊ ማንነት ማመን በራስ የመተማመን መገለጫ ነው። ትምህርት፣ ስልጠና፣ አዳዲስ ተሞክሮዎችን መሞከር በራስ መተማመንን እንዲኖር ያደርጋል። በራስ መተማመን የሚጀምረው የራስን በጎም ይሁን መጥፎ ጎኖች በመቀበል ነው።
እራስን ማወቅ በራስ የመተማመን ስሜትን ይፈጥራል። በራስ መተማመን ያላቸው ሰዎች በልበ ሙሉነት ፈተናዎችን
ይጋፈጣሉ። እንዲሁም በክህሎታቸው እና በእውቀታቸው ይተማመናሉ። በምንም አይነት እንቅፋት እና ፈተና አያቆማቸውም በቁርጠኛነት ወደ ፊት ይሄዳሉ።
ለራሳችን ያለንን ግምት ከፍ ማድረግ በራስ መተማመናችን በቀላሉ እንዳይጎዳ ይረዳል። እንደ ገንዘብ ማጣት ያሉ የህይወት ክስተቶች በራስ መተማመናችንን ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በራስ መተማመኑ ከፍ ያለ ሰው በህይወት የሚገጥሙትን ማንኛውም አይነት ፈተና ከመሸሽ ይልቅ መጋፈጥ እና መፍትሔ መስጠት ይችላል። በህይወት የሚገጥሙ ማንኛውንም ፈተናዎች አሸንፈዋለሁ ብሎ ማመን ከፍ ያለ በራስ መተማመንን ያሳያል። ለራስ ያለን አመለካከትን ማስተካከል ለስኬታማና ደስተኛ ህይወት አስፈላጊ ነው። የበታችነት ስሜት አስወግዶ በራስ መተማመን ለመገንባት የሚከተሉት ሃሳቦች ጠቃሚ ናቸው።
• እራስን ማክበር እና መቀበል
• ከአሉታዊ ውድድሮች ተቆጥቦ ለራስ አድናቆት መስጠት
• ጠቃሚ ትችቶችን ለመቀበል እና ለማስተካከል መሞከር
• ለራስ የሚጠቅመውን መንገድ መወሰን እንደሚችሉ ማመን
• መርዛማ ወይም አሉታዊ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች መራቅ
• መሆን የሚፈልጉትን መሆን እንደሚችሉ ማመን
• የሚፈሩትን ነገር ለመሞከር መወሰን
• ዋጋዎን ማስተዋል ከማይችል ሰው ጋር ጊዜ አለማባከን
• የእራስዎን እውነተኛ ዋጋ ማረጋገጥ
• እራስን መጥላት እና መተቸት ማስወገድ
• በራስ ችሎታ ማመን የሚሉት ይጠቀሳሉ።
2. ውሳኔ መወሰን፣ ቁርጠኝነት እና ጽናት
ውሳኔ የምንፈልገውን ከማንፈልገው የምንለይበት ክህሎት ነው። ውሳኔ መወሰን ማለት ጽኑ ዓላማ መያዝ ማለት ነው። ውሳኔዎች በችግር ፊት እንድንጸና ስለሚያስችሉን ውሳኔ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ውሳኔ ለማድረግ እያንዳዱ አማራጮችን ማሰብ እና አማራጮቹን ማመዛዘን ጠቃሚ ነው። እራሱን ሙሉ በሙሉ የሚያውቅ ሰው የሚጠቅመው ላይ ውሳኔ ለመስጠት አይቸገርም። በህይወት ውስጥ ስንወስን ልናሸንፈው የማንችለው ችግር የለም። ውሳኔዎች ወደ ድርጊት ካልተለወጡ ዋጋ ቢስ ይሆናሉ።
በህይወታችን ማግኘት የምንፈልገውን ወስነን እንዳናደርግ ከሚያደርገን አንዱ ልናጣቸው የምንችላቸው ትንንሽ ጉዳዮች ስለሚያስጨንቀን ነው። አንዳንድ ጊዜ ውሳኔ ለመወሰን እንቸገራለን ይህን ለመቅረፍ ጊዜ ወስዶ እራስን መፈለግ፣ ከዚህ በፊት ምን እንዳሳኩ እና ምን ማድረግ እንደሚችሉ ማሰላሰል በቀላሉ ውሳኔ ለመወሰን ያግዛል። በሌላ በኩል ያሎትን አማራጮች በትክክል መገምገም እና ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማስወገድ ውሳኔ ለማድረግ ጠቃሚ ነው። በህይወትዎ ማንም ላይደግፎት እና ላያግዞት ይችላል፤ ስለዚህ የራስን ውሳኔ ከመወሰን ጀምሮ በሁሉም ነገር እራስን ለመቻል እና ለማብቃት መሞከር የተሻለ ቦታ ያደርሳል።
ቁርጠኝነት፦
ምኞት የሁሉም ታላቅ ስኬት መሪ ነው። ይህ ምኞት ግን ያለ ትግል እና ቁርጠኝነት ለስኬት አይበቃም። ቁርጠኝነት በችግር ፊት እንድንጸና ግባችን ድረስ ያለ ፍርሀት በእምነት ወደ ፊት እንድንጓዝ ያደርገናል። ህይወት አልጋ ባልጋ ስላልሆነ እንቅፋት ሲገጥም ለዓላማው ታማኝ ያልሆነ ሰው ይቆማል፤ ነገር ግን ቁርጠኛ የሆነ ሰው ማንኛውንም አይነት መሰናክሎች ተሻግሮ ይቆማል።
ዓላማን በግልጽ አጥርቶ ማወቅ ለማሳካት አስፈላጊውን ጥረት ለማድረግ ይረዳል። የብዙዎች የዓላማ ቁርጠኛነት ጠንካራ አይደለም ይሁን እንጂ ዓላማ ላይ ለመድረስ ምንም ያህል ጊዜ ቢወስድ ለዓላማዎ ታማኝ እና ቁርጠኛ ከሆኑ እስኪሳካ ድረስ ተስፋ አይቆርጡም። ቁርጠኝነት ተስፋን የሚቀጥል ከውስጣችን የሚመነጭ ማበረታቻ ነው። በተጨማሪም አንድ በጅምር ላይ ያለ ጉዳይ ግቡን ለመመልከት ጥንካሬ ይሰጠናል። በአጠቃላይ ቁርጠኝነት መሰናክልን እየተሻገሩ ወደ ግብ ለመራመድ ይረዳል።
ጽናት
መተው ወይም መልቀቅ አለመፈለግ ጽናትን ይገልጻል። በችግር ውስጥም ቢሆን የጽናት ሀይል ከፍተኛ ነው። ህይወት በትግል የተሞላ ነው ስለዚህ ስኬትን ማግኘት የሚቻለው በጽናት ብቻ ነው። ስኬት ከብዙ ሙከራ በኋላ ዓላማ ላይ በመጽናት የሚገኝ ውጤት ነው።የዓለም ታላላቅ ውጤቶች በጽናት የተገኙ ናቸው። የጥረትን ውጤት ለማየት ጽናት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ዓላማን፣ ህልምን እና ራዕይን እውን ለማድረግ የጽናት ኃይል የማይተካ ሚና አለው። ጽናት በተፈጥሮ ያለ በጠንካራ የራስ ፍቃድ የሚዳብር እንጂ በትምህርት ወይም በስልጠና የሚካኑት ክህሎት አይደለም።
ጽናት የስኬት አካል ነው። ለስኬት ቀላል የሚባል መንገድ የለም እንዳለውም ጽናት የስኬት ምንጭ እና ምሶሶ ነው። መውደቅ ማለት አበቃለት ማለት ሳይሆን ለማሸነፍ መጀመር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን መውደቅ የሚጀምረው ችግር ገጠመኝ ብሎ ላለመጽናት ማፈግፈግ ሲጀመር ነው። ጽናት በስኬት መንገድ ላይ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለማሸነፍ የሚረዳ እሴት ነው።
በዓላማ እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚያስችሉ መንገዶች፦
• ለመውደቅ አለመፍራት
• በየቀኑ እራስን ማሻሻል
• ግብን በአእምሮ መያዝ
• የደረሱበትን ማወቂያ ግልጽ መለኪያ ማስቀመጥ
• በየቀኑ ከነበሩበት አንድ እርምጃ ወደፊት ለመራመድ መሞከር ስኬታማ ሰዎች በዓላማቸው እና በራዕያቸው አጥብቀው ያምናሉ በህልማቸው ላይ በቀላሉ ተስፋ ሳይቆርጡ ይጸናሉ።
3. ችግሮችን የመፍታት ችሎታ ማዳበር
ሰዎች ለማሳካት የሚፈልጉት ማንኛውም ጉዳዮች እንዳይሳኩ የሚያደርጉ ማንኛውም ሁኔታ ችግር ነው። ይህን ችግር ለማስወገድ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ ችግር መፍታት ተብሎ ይጠራል። መረጃን እና እውቀትን በማቀናጀት መጠቀም የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ይረዳል። ችግሩ እንዴት እንደሚፈታ ለማወቅ የችግር አፈታት ክህሎት ማዳበር ወሳኝ ነጥብ ነው።
የተከሰተውን ችግር የምንረዳበት መንገድ እና የምንሰጠው ምላሽ ከውድቀት አድኖ አዳዲስ ነገሮችን እንድናይ ይረዳናል። አንድን ችግር ለመፍታት አማራጭ መፍትሄዎችን ማመንጨት እና የተሰጠውን መፍትሄ ተግባራዊ ማድረግ ችግሩን ለመፍታት ይረዳል። በተጨማሪም በጥልቀት ማሰብ እና መመርመር ችግሩ ምን እንደሆነ ለመለየት ይረዳል ይሁን እንጂ ችግሩን ትልቅ አድርጎ መቁጠር መፍትሄውን ከመሞከር ሊያግዶት ይችላል።
ዮርዳኖስ አየነው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2013