የዳቦ ዱቄት አቅርቦቱ ከሸማቾች ማህበራት ከራቀ እና በሌላ የገበያ ስፍራም አንድ ኪሎ ከ50 ብር በላይ መጠራት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል። ይህም በሸማቹ ማህበረሰብ ዘንድም አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል። በአንዳንድ የሸማቾች ማህበራት አማካይነት ብቅ ያለው ዱቄት ሰሞኑን ለወረፋ ምክንያት ሆኖ ታይቷል። ወይዘሮ አጀቡሽ ዘሪሁን ዱቄት ለመግዛት በጨርቆስ ክፍለ ከተማ በወረዳ ስምንት በሚገኘው ቀበሌ 17 ወረፋ ሲጠብቁ ነው ያገኘናቸው። ‹‹ዱቄቱ የመጣው ከርሞ ከርሞ ነው። ወረፋውም የበዛው ለዚሁ ነው።›› ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።
ወይዘሮዋ ቤተሰባቸው በርከት ያለ በመሆኑና የዳቦ ዱቄት ከሌላ ገበያ ለመግዛት አቅም ስለሌላቸው ተቸግረው እንደነበር ይናገራሉ። በአንዳንድ ሱቆች ዱቄቱ ቢኖርም የአንድ ኪሎ ዱቄት ዋጋ ከ50 ብር በላይ በመሆኑ በአቅማቸው ገዝቶ መጠቀሙን አልቻሉም። ሆኖም ግን እንደ አማራጭ ሸገር ዳቦን በመግዛት ይጠቀማሉ። እሱንም በበቂ ሁኔታ እንደማያገኙና በወረፋ እንደሚገላቱም ሳይጠቅሱ አላለፉም። አሁን በሸማቾች የሚሸጠው ዱቄት አንዱ ኪሎ 27 ብር ነው። ቀደም ሲል ሸማቾች ማህበር በድጎማ በስምንት ብር ከሀምሳ መግዛት የሚቻልበት ሁኔታ የለም።
የመንግስት ሠራተኛና ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ፤ በመስሪያ ቤቱ አማካይነት ስኳር፣ ዘይትና ዱቄት የጠቀም እንደነበረ ይጠቅሳል። ሆኖም በሐምሌ ወር መጀመሪያ አንድ ኪሎ ፉርኖ ዱቄት በ38 ብር ሂሳብ ለመግዛት ተመዝገቡ የሚል ማስታወቂያ ቢወጣም ዱቄት አቅራቢዎቹ ከተጠቀሰው ዋጋ በላይ በመጠየቃቸው ሳያቀርቡ መቅረቱን ይናገራል። ይሄ የዋጋ መወደድ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንምይገልጻል። ሌላው ቀርቶ የመንግስት ሰራተኞች እንኳን መግዛትና መጠቀም አይችሉም ይላል።
መንግስት እጥረቱን ለመቅረፍና የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ጥረት ከማድረግ አልተቆጠበም። ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ እስካለፈው ዓመት ድረስ በየዓመቱ በአማካኝ 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባ ቆይቷል። በዘንድሮ ዓመት ደግሞ የመስኖ የቆላ ስንዴ በብዛት እንዲመረት ተደርጓል። ይሄ ግን አቅርቦትና ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ ማጣጣም አልቻለም።
መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እያለማ ያለው ስንዴ ይበረታታል። ችግሩን በዘላቂነት ከመፍታት አንፃር ተስፋ ይጣልበታል። ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ሕብረተሰቡን ማርካትና ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም። በመሆኑም ከያዝነው የሐምሌ ወር ጀምሮ ስንዴ ከውጪ እየተገዛ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ መንግስት ውሳኔ አሳልፎና በቂ በጀት መድቦ እንቅስቃሴ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ዳንኤል ሙለታ እንደተናገሩት፤ መንግስት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከውጪ የሚመጣውን ስንዴ በሀገረ ውስጥ ለመተካት ወደ መስኖ ስንዴ ልማት የገባበት ሁኔታ አለ። ይህም የኢንስቲትዩት አካል በሆነው በወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ተጀምሯል። በዘንድሮ ብቻ የለማው ወደፊት እጥረቱን መቅረፍ እንደሚችል ያመላክታል።
ለማልማት ከታቀደው ውስጥ 172 ሺህ 515 ሄክታሩ በኦሮሚያ ክልል፣13ሺህ 200 የሚጠጋው ደግሞ በአማራ ክልል ሲሆን በአፋር ክልል 1ሺህ 230 ሄክታር፣ በሶማሌ ክልል ጎዴ አካባቢ በሰርቶ ማሳያነት ደግሞ 500 ሄክታር ማሳ ለምቷል። በዘንድሮ በጀት ዓመት በጋ ብቻ ከ187ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በመስኖ ስንዴ ተሸፍኗል። ይሄም በየዓመቱ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገባው 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከ50 በመቶ በላይ መተካት ያስችላል።
በኦሮሚያ ክልል ከበጋ ወደ በልግ ተሸጋግሮ በ209 ሺህ 530 ሄክታር ላይ በበልግ የለማ ስንዴም አለ። ይሄ ከውጪ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሂደቱን ከ70 በመቶ በላይ ያደርሰዋል። በአጠቃላይ በ2013 ዓ.ም በበጋና በልግ የለማውን ማሳ 4ሺህ 526 ሄክታር በማድረስ በስንዴ መስኖ ከዕቅድ በላይ ማስመዝገብ ተችሏል።
ዶክተር ዳንኤል እንዳሳሰቡት ከውጪ የሚመጣውን ስንዴ ለማስቀረት እንዲሁም የዳቦ ዱቄት እጥረትና የዋጋ ውድነቱን ለመቆጣጠር የግል ባለሀብቱ በስፋት ወደ ልማቱ መግባት አለበት። ኢንስቲትዩቱም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የአስተራረስና የዘር አመራረት ዘዴ ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሙያዊ ምክርና እገዛ በማድረግ ያበረታታል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013