ወደ ሁለተኛ ዓመት እየተሸጋገረ ያለው የኮቪድ 19 ቫይረስ የሰው ህይወት በመቅጠፍ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይም ተጽዕኖውን በማሳረፍ እያሳደረ ያለው ጉዳት አቅምን የሚፈታተን እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይም በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ዘርፉ ከነበረበት እንቅስቃሴ እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ በዘርፉ ላይ የተሰማሩትንም ተስፋ እያስቆረጠ ይገኛል፡፡ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ጉዳቱ ከፍ ያለ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ሠራተኞችና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ወረርሽኙ አካላዊ መቀራረብ፣ ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴን፣ ህብረትን የሚገድብ ነው፡፡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት የተጣሉትን ማዕቀቦች የሚፈልግ፣በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም እስከ ዛሬ የተለመደው የቱሪዝም እንቅስቃሴ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በጋራ የሚንቀሳቀሱበት በመሆኑ አስጎብኝ ድርጅቶችም በዚህ ቅኝት ውስጥ ነው ሥራቸውን ሲሰሩ የቆዩት፡፡
የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን እየጎዳው ያለው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ብቻ ሣይሆን፣ በሀገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋት ጭምር መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሁለት ያልታሰቡ ክስተቶች ቢያጋጥሙም ከተለመደው አሠራር ወጣ ብሎ ዘርፉን በማንቀሳቀስ በኩልም ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡ እስከ አሁን በተለመደው ወቅትን ጠብቆ መንቀሳቀስና ታሪካዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ቱሪስቱን በተለመደ ሁኔታ ማስተናገድ እንዲሁም በውጪ ቱሪስቶች አተኩሮ መሥራት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያን በደንብ የሚያውቁ፣ በተደጋጋሚ በመምጣት የሚጎበኙ ደንበኛ የሆኑ ቱሪስቶች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እያወቁም እንኳን መጎብኘታቸውን እንደቀጠሉ መረጃዎች ቢያሳዩም ባለው ወቅታዊ ሁኔታና በተለመደው አካሄድ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ቱሪስት ወደ ሀገር በመሳብ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ገቢ ለማግኘት ፈታኝ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ በዘርፉ ላይ የሚገኙትም ይህንኑ ነው ያረጋገጡልን፡፡ችግሩ ግልጽ ቢሆንም በዚሁ ይቀጥላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡በመሆኑም ይህን ሀገራዊ ችግር የተለያዩ አማራጮችን በጋራ በመፈለግ ዘርፉን ማስቀጠልና ተሥፋ ማሣደር ይጠበቃል። የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እንደ አሜሪካን፣ ካናዳ እና ሌሎችም ሀገሮች በከፍተኛ ሙቀት መጠን መጨመር ህይወትን እስከማሳጣት የደረሰ አደጋ ገጥሟቸዋል፡፡ እነዚህ ሀገሮች ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ አየሩን በሙቀት ጊዜ በማቀዝቀዝ፣ በቀዝቃዛ ወቅት ደግሞ በማሞቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ሣያቋርጡ ያከናውናሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ችግር ተቋቁመው በማሣለፍ የተካኑ ቢሆኑም በዚህ ወቅት የገጠማቸው የሙቀት መጠን መጨመር ግን ልምድ ባደረጉት ቴክኖሎጂ እንኳን መቋቋም እንዳልቻሉና ፈተና እንደሆነባቸው ነው ባለሙያዎችን መሠረት ያደረጉ መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ ሀገራቱ በሙቀት ከመጠን በላይ በተቸገሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ለሰው፣ ለእንስሳትና ለዕፅዋት ተስማሚ የሆነ የአየር ፀባይ አለ። በተጨማሪም ለእይታ፣ ለመንፈስና ለጤና ተሥማሚ የሆኑ ደንና ፓርኮች የሚገኙባቸው አካባቢዎች አሏት። እነዚያ በሙቀት መጠን መጨመር የተቸገሩ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ ከሥቃያቸው እፎይ ይላሉ። ኢትዮጵያም በቱሪዝም ኢንዱስትሪው በኩል ይህን በማቅረብ የተዳከመውን እንቅስቃሴ ማነቃቃትና ገቢ በማግኘት ኢኮኖሚያዊ ጫናዋን መቋቋም ትችላለች፡፡
በየክልሎቹ ጥብቅ ደን ያሉባቸውን አካባቢዎች በማስጎብኘት ዘርፉን የማነቃቃት ሰፊ ዕድል አለ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩት እንጦጦ፣ አንድነትና ወዳጅነት ፓርኮችም ከከተማ ርቆ መሄድ ለማይፈልግ ቱሪስት አማራጮች ናቸው፡፡ ለመሆኑ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የተሰማሩት እንዲህ ያለውን የቱሪዝም አማራጭ እንዴት ይመለከቱታል?
በአስጎብኝነት ሥራ ለሰባት ዓመታት የቆዩትና በ2004 ዓ.ም የተቋቋመው ታላቅ የኢትዮጵያ አስጎብኝ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ናሆም አድማሱ እንዳሉት፤ ጊዜ ወስዶ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ ተፈጥሮን፣ ታሪክና ባህልን በማየት አዕምሮውን ዘና በማድረግ ያሳልፍ የነበረ ቱሪስት ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ከእንቅስቃሴ ተገትቶ ቆይቷል። ረጅም ጊዜ በቤት ውስጥም በመወሰኑ አሁን የሚፈልገው የጊዜ ማሣለፊያ ወይም ምርጫው ተፈጥሮን መጎብኘት ነው፡፡ በመሆኑም ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ቀድሞ ከነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደ አንድ አማራጭ ተይዟል ወይም በዕቅድ ሁለት ውስጥ ተካትቷል፡፡ በዚህ ረገድም በመካከል ላይ ኮቪድ ቀዝቀዝ ማለቱ በተነገረባቸው ጊዜያቶች ለመንቀሳቀስ ተሞክሮ ወረርሽኙ ዳግም በማገርሸቱ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ቱሪስት የሚያመነጩ ከእንቅስቃሴያቸው ተገቱ፡፡በዚህ ምክንያት ዕቅዱን ማሳካት አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ተስፋ ይደረጋል፡፡
ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ፀጋዎች ለመጠቀም በሥራ ላይ ያለውን ጎርጎራ አሁን ባለበት መሸጥ አይቻልም፡፡ ግን በጣም ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ቱሪስቶች በባህርዳር አቋርጠው ጣናንና በአካባቢው የሚገኙ ገዳማትን እንዲሁም ጎርጎራ ላይ የምትገኘውን ደብረሲና ገዳምን ጎብኝተው ለአዳር ወደ ጎንደር መሄድ ሳያስፈልጋቸው ጎርጎራ ላይ አርፈው አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማድረግ ቆይታቸውን ማራዘም የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል የሚል ነው ተስፋው፡፡ እስከዚያው ግን 777 መወጣጫ ደረጃዎች ያሉት የምድር ገነት የተባለለትን የተፈጥሮ ፀጋ ዱራሜ አበርቾ የሚባለው አካባቢ መጠቀም ይቻላል፡፡ ሌላው የተፈጥሮ ፀጋ መገኛ የሆነው ጨበራ ጩርጩራም ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ መሆኑን ይጠቅሳሉ። አሁን ባለው ሁኔታም ከሌሎች አካባቢዎች ዱራሜ አበርቾ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴዎች በመታየት ላይ ናቸው። አዲስ አበባ ላይ በቅርቡ ሥራ የጀመሩት ወዳጅነት፣ አንድነትና እንጦጦ ፓርኮች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጨማሪ ግብአቶች ናቸው፡፡እንዲህ ለቱሪስቱ መስህብ የሆኑ ፓርኮች ቢኖሩም ከጎረቤት ኬንያ እና ከሌሎችም አካባቢዎች አንፃር ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ፓርኮቻቸው ከአረንጓዴ ልማቱ በተጨማሪ በውስጡ የያዟቸው አዕዋፋት፣ የዱር እንስሳትና ሌሎችም መስህቦች ከአንድ ቀን ጉብኝት በላይ ናቸው፡፡ ቱሪስቱን የሚያቆይ ሥራ ተጠቃሚነትን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ በዚህ ልክ መስራት ይጠበቃል፡፡
አቶ ናሆም ዘርፉ ቅድመና ድህረ ኮቪድ ያለውን እንቅስቃሴ፣በአስጎብኝው ኑሮ ላይ ያስደረውን ተጽዕኖ እንዲህ አጫውተውኛል፡፡‹‹የቱሪዝም እንቅስቃሴው እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ስለነበር በዘርፉ ላይ የሚሰራ ብዙ የሰው ኃይል ለመሳብ ችሏል። ተደራጅተው የሚሰሩ ማህበራት ቁጥርም ጨምሯል፡፡ ማህበራችን 40 የሚሆኑ ማህበራትን በሥሩ ለማደራጀት ችሏል፡፡ ከትንሽ ተነስተው ትልቅ ቦታ የደረሱ፣ በልምድ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያላቸው አብዛኞችም ስመጥር የሆነ ድርጅት ያቋቋሙና በባለሙያዎችም የተደራጁ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ወደ ኢንቨስትመንት ያደጉ አሉ›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከተለያየ ሀገር የሚመጣው የቱሪስት ፍሰት ጥሩ የሚባል በመሆኑ አስጎብኝውም ያለፋታ ነበር ሥራውን ሲያከናውን የቆየው፡፡ ሀገርን ከማስተዋወቅ ባለፈ ድርጅት ከፍቶ ሥራውን ከሚያንቀሳቅሰው ግለሰብ ጀምሮ በሥሩ የሚያስተዳድራቸው ሰራተኞች፣ በሰራተኛው ሥር ያለው ቤተሰብ፣እንደሀገር ደግሞ ከሥራ ግብር በሚገኝ የገቢ ሠንሰለት በሀገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት የነበረውን ሚና አስታውሰዋል፡፡
አስጎብኚ ድርጅቶች የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማስተዋወቅ ሚናውን በመወጣት ላይ ካለው ቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት፣ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራና በቅብብሎሽ ይከናወን የነበረው ሥራም ዘርፉ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲኖረው ካደረጉት ተግባራት መካከል ይጠቀሳል፡፡
እንደ ሀገር ካለው ጥቅም ባለፈ በጥናት ተደግፎ በእያንዳንዱ ዘርፍ ላይ የተገኘውን ተጨባጭ ለውጥ ለመናገር ቢያዳግትም በሁሉም አስጎብኚ ድርጅቶች ውስጥ የማይናቅ ለውጦች ታይተዋል፡፡ በባንክ ብድርና በተለያየ መንገድ መኪና በማስመጣት የተጠቀሙ መኖራቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ለውጡ በዘርፉ ውስጥ ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ ያላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ እንደሀገር ሲታይ ደግሞ ሰፊ ጥቅም አስገኝቷል፡፡
አስጎብኝዎች ቱሪስቶችን ከቦታ ወደ ቦታ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ሻይ፣ ቡና፣ ገፀ በረከት፣ የአካባቢያውን ባህላዊና የወግ ዕቃዎች ለሽያጭ በማቅረብ፣ በጀልባ በማስጎብኘትና ቱሪዝሙ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች በማቅረብ እንዲሁም በማስጎብኛ ገቢ ተጠቃሚ የሆነው ማህበረሰብም መንግሥት ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ለሚያደርገው ጥረት አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፡፡
እንዲህ ባለው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኘውና ብዙዎችን ተጠቃሚ ሲያደርግ የነበረው ቱሪዝም ኮቪድ 19 ቫይረስ መከሰት ለዘርፉ እጅግ አስደንጋጭ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከቅድመ ኮቪድ በፊት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን በአየር መንገዱ ለተወሰነ ጊዜ አርፈው ወደሌላ ሀገር የሚሄዱ መንገደኞችን (ስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም) በሚባለው ዘዴ ለመጠቀም እቅድ ነድፈው ገና በጅምር ላይ እንዳሉ ችግሩ መከሰቱ የጀመሩትን አዲስ አሰራር አጨናግፎባቸዋል። የሚተላለፉት (ትራንዚት) የሚያደርጉ መንገደኞች ኢትዮጵያን እንዲያውቁና ደግመው እንዲመጡ ማበረታቻ ለመፍጠር ነበር ዕቅዱ፡፡ ከቅድመ ዕቅድ በፊትም አይስላንድ ሀገር በመሄድ ልምድ ቀስመዋል።ያንን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎቱ ከፍተኛ ነበር፡፡ቱሪስቱን ለመሳብ ሲባል ለሦስት አራት ቀን ቆይታ ሲያደርጉ ከቪዛ ክፍያ ነፃ የሚሆኑበት አቅጣጫም ተቀምጦ ነበር፡፡ የወረርሽኙ መከሰት በጉዞ ላይ የነበሩትን ሁሉ በማስቀረት ትልቅ ኪሣራ ማድረሱን አቶ ናሆም በቁጭት ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ናሆም ማብራሪያ ወረርሽኙ እንደተከሰተም ዘርፉ እንዲያገግም መሰራት ያለባቸው ሥራዎች በምን መልኩ መከናወን እንዳለበት ባለድርሻ አካላት በተለይም ቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጋራ ምክክር አድርገው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በምክክሩም እንደአቅጣጫ የተቀመጠው የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማበረታታት የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መጀመሪያ ላይ ያልተሰራበት ነገር ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ የራሱ ውስንነቶች ይኖሩታል፡፡ ምክንያቱም በሀገር ውስጥ የተለመደው በኃይማኖታዊ ጉዞና ዘመድ ጥየቃ ካልሆነ ለጉብኝት ተብሎ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመጎብኘት ባህል አልዳበረም፡፡
የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የመጎብኘት ፍላጎት ያላቸው ቢኖሩ እንኳን በሀገር ውስጥ ያለውን የቱሪዝም ሀብት ከመጎብኘት ይልቅ ከሀገር ውጭ እንደ ዱባይ ወዳሉ ሀገራት መሄድን ይመርጣሉ፡፡ እነዚህ ፈታኝ የሆኑ ነገሮች ባሉበት ሁኔታም በተደረገው ጥረት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ ግን የበለጠ መሥራት ይጠበቃል፡፡
እንዲህ ያሉ አማራጮችን ቀድሞ ካለማየት የመጣ መሆኑን አቶ ናሆም አልካዱም፡፡ ችግሩ ሲያጋጥም ወዳልተለመደው ለመሄድ በራሱ ተግዳሮት የሚሆነውም ለዚህ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ችግሩን መሠረት አድርጎ በዘርፉ ላይ ለሚገኙት በመንግሥት በኩል መፍትሄ ለመስጠት ያለው ቁርጠኝነትም አናሳ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ። ለዚህም ለአብነት የጠቀሱት ለሥራቸው ከባንክ ተበድረው ለሥራ መኪና ያስመጡ አንዳንድ አስጎብኝ ድርጅቶች የባንክ የብድር ክፍያ ጊዜ እንዲዘገይና መኪናውም ለሌላ አገልግሎት ውሎ ብድሩን ለመመለስ እንዲቻል እንደ ፌዴራል ትራንስፖርት አገልግሎት ባለሥልጣን ያሉና የሚመለከታቸውን አካላት ለመጠየቅ የተደረገው ጥረት ውጤት አላስገኘም፡፡ ችግሩ ቢገባቸውም ደፍረው ለመፍቀድ ፈቃደኝነት አላሳዩም። የባንክ ብድር ለመመለስ ተቸግረው ሕግ ተላልፈው በመኪናቸው የሰሩም ለእሥር የተዳረጉ የድርጅት ባለቤቶች መኖራቸውን በማሣያነት አቅርበዋል፡፡ ግብር መክፈልንም በተመለከተ በየዓመቱ የነበረው ክፍያ ሥራ ከሰሩ በኋላ በሚል ታሳቢ በመንግሥት ሁኔታዎች እንዲመቻች ሀሳብ ቢቀርብም ተግባራዊ አለመሆኑን እንደ ክፍተት አንስተዋል፡፡
አቶ ናሆም ለቱሪዝሙ መዳከም ሌላው እንደክፍተት ያነሱት አብዛኞቹ ኤምባሲዎች ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ የሚያደርጓቸው የጉዞ ክልከላዎች ናቸው። ቱሪስቱ ደህንነቱ ተጠብቆ ሊጎበኛቸው የሚችላቸው ቦታዎች መኖራቸው ተዘንግቶ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ችግሮች እንዳሉ አስመስሎ የሚቀርብበት መንገድ እንዲስተካከል ጥረት ቢደረግም የሚፈለገውን ያህል ባለመሆኑ ጥረቱ ሊጠናከር ይገባል፡፡
በማህበሩ በኩል ስለነበሩ ጥረቶችም እንደገለጹት ከዘርፉ ውስጥ ላለመውጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ከመንቀሳቀስ ጀምሮ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው እሴት ሠንሰለት ውስጥ የነበሩ በአነስተኛ አቅም ሲንቀሳቀሱ የነበሩና በዘርፉ መቀዛቀዝ ገቢ ያጡትን ለዕለት የሚሆን ድጋፍ በማድረግ ጭምር ኃላፊነቱ ተወጥቷል፡፡ በሂደት ግን የማህበሩ አባላትም ዕርዳታ ፈላጊ እንዳይሆኑ ይሰጋሉ፡፡አንዳንዶችም ከዘርፉ በመውጣት ላይ ይገኛሉ። በዘርፉ ላይ የሚገኘው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው ሥራውን በውስጡ በማስገባቱና አማራጭ ሥራዎችን ለማየት እንኳን ፍላጎት የሌለው በመሆኑ ነው።ለዚህም ነው ቱሪዝሙ ሲጎዳ አብሮ የተጎዳው፡፡ በተስፋ ውስጥ የሚገኘው ይህ ዘርፍ ተሥፋው እንደሚለመልም ይጠበቃል፡፡ ግን አማራጮችን ሁሉ ማየት ከእያንዳንዱ ይጠበቃል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013