ሙያውን የቀሰመው ገና በልጅነቱ ከጣሊያኖች ጋር ሲሰሩ ከነበሩ አያቱና ይህንኑ ስራ ከአያታቸው ከወረሱት አባቱ ነው። ለስራ ጥልቅ ፍቅር የነበረው በመሆኑም ቀን ቀን አባቱ በትርፍ ጊዜ የሚያከናውኑትን የብረታ ብረትና የሻተር ስራን ጨምሮ ሌሎችንም ሥራዎች በመቆጣጠርና በማገዝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በማታው መርሐግብር እስከ መማር ደርሷል።ይኼው የብረታ ብረትና የሻተር ስራ ፍቅር አይሎበት በዚህ ሞያ ያለውን ብቃት ለመፈተሽ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮም ሰርቷል ። ከዚህ ያገኘው ልምድና ያዳበረው ሞያም የራሱን የሻተር መስሪያና ማምረቻ ድርጅት ለመክፈት አስችሎታል።
ለንግድ ቤቶች፣ ለሱቆች፣ ለባንኮችና መጋዘኖች እንደጠንካራ የብረት መዝጊያ ተደርጎ የሚቆጠረውን የሻተር ስራ በራሱ ‹‹ሀ›› ብሎ በመጀመር በቅድሚያ አነስተኛ በመቀጠልም ከፍተኛ ስራዎችን መስራት ችሏል። በሂደት ደግሞ የራሱን የሻተር ብረት ማጠፊያና መቁረጫ ማሽን ከውጪ ሀገር በማስገባት የሻተር ስራውን በስፋትና በብዛት ለመስራት በቅቷል። በዚህም ሞያውንም ከራሱ አልፎ በእርሱ ስር ተቀጥረው ለሚሰሩ ሌሎች ሰዎች አስተላልፏል። ምንም እንኳን የብረት ግብዓት እጥረትና የመስሪያ ቦታ ችግር ቢፈትነውም የነገውን ብሩህ ግዜ በማሰብ አሁንም ከዚሁ ስራ ጋር እየታገለ ይገኛል – አቶ ዮናስ በየነ።
ዮናስ ሻተር ስራና ማምረቻ ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ በየነ ውልደትና እድገቱ እዚሁ አዲስ አበባ ቴዎድሮስ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ቀን አባቱ ከሚሰሩት የመንግሥት ስራቸው ውጪ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሰሩትን ፀጉር ቤት፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሻተር ሥራ በመቆጣጠርና በማገዝ በማታው ክፍለ ጊዜ በካቴድራል ትምህርት ቤት ተምሯል።ትምህርቱን እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ከተከታተለ በኋላ ልቡ ወደ ስራ ስለሸፈተ ሙሉ ትኩረቱን በስራ ላይ ብቻ አደረገ።
ካሉት የስራ ዘርፎች ውስጥ በግዜው ትኩረቱን ይበልጥ የሳበው የብረታብረትና የሻተር ስራ በመሆኑና በተለይ የሻተር ስራን አያቱ ሲሰሩ እንደነበር ስለሚያውቅና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ደግሞ በዚሁ ስራ አባቱን ይረዳ ስለነበር ወደዚሁ ስራ ለመግባት ወሰነ። ምን ያህል የብረታብረት ሙያ እንዳለው ራሱን ለመፈተሽም በቅድሚያ ይህንኑ ስራ በሚያከናውኑ የተለያዩ የግል ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። ከዚሁ ጎን ለጎንም የሻተር ስራውን መስራት ቀጠለ።
በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮ በብረትና በሻተር ስራ እጁን ካፍታታ በኋላ በ2000 ዓ.ም በ10 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል አብነት አካባቢ አነስተኛ ቤት በመከራየት የተካነበትን ስራ በግሉ ጀመረ። በግዜው የሻተር ማጠፊያና መቁረጫ ማሽን ስላልነበረው በእጁ ብረት እያጠፈና እየቀጠቀጠ መስራቱን ተያያዘው። አንዳንዴም ከውጪ ሀገር የሚገባ ያለቀለት ሻተር በመግዛት መግጠም ቀጠለ። ለመጀመሪያ ጊዜም ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ አንድ ሙሉ ፎቅ ሰፊ የሻተር ስራ ሰራ። በሂደት ደግሞ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ በገባ የሻተር ማቴሪያል የሻተር ስራዎችን መስራት ቻለ። በመቀጠል ደግሞ ኦሚዳድ የሚያመርታቸው የሻተር መስሪያ ግብአቶችን በመጠቀም መስራቱን ተያያዘው።
በሂደትም ድርጅቱ እያደገና የሚሰራቸው ስራዎችም እየሰፉ በመምጣታቸው ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከወንድሙ ጋር 200 ሺ ብር በመበደር ለስራቸው የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎችንና ማሽኖች አሟሉ። ስራውን በመስራትም ቀስ በቀስ ብድራቸውን መክፈል ጀመሩ። በዚህ ሂደት አብነት አካባቢ የነበረው የማምረቻ ቤት በልማት ምክንያት በመፍረሱ ኮካ ኮላ አካባቢ ሌላ ቤት ተከራዩ። ስራው እየሰፋና ሌሎች የብረታብረት ሥራዎችም አብረው ቀጠሉ ።
አስፈላጊ የሻተር ግብአቶችን ከአስመጪዎች በመረከብና የተለያዩ መሳሪያዎችን በመጠቀም ስራውን በዘመናዊ መልኩ ማከናወናቸውን ቀጠሉ። የነበራቸውን ካፒታልና ብድር በመጨመር በ2010 ዓ.ም ስራውን ይበልጥ ሊያቀላጥፍና ሊያዘምን ብሎም ሻተርን በራሳቸው ለማምረት የሚያስችላቸውን ማሽን በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በመግዛት ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ አስገቡ።
የሻተር ስራ ዋነኛ ግብአት የሆነው ብረት በሀገር ውስጥ እንደልብ ባለመገኘቱና አብዛኛውም ከውጪ ሀገር የሚገባ በመሆኑ ማሽኑን ወደ ሀገር ውስጥ ካስገቡ በኋላ በሚፈለገው ልክ ማምረት አልቻሉም። ግብአቱን ወደ ሀር ውስጥ በማስገባት ለመጠቀም የውጪ ምንዛሬ እጥረት መኖርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የብረት ዋጋ መናር ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አወሳሰበባቸው። ይሁንና በትግልም ቢሆን ስራውን ማከናወናቸውን ገፉበት።
በ10 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ስራውን የጀመረው ድርጅቱ በአሁኑ ግዜ ያለውን ማሽነሪ ጨምሮ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ካፒታል አስመዝግቧል። እንደ ገበያው ሁኔታ ከአሥር እስከ ሀያ ለሚሆኑ ሰዎችም የኮንትራት ስራ እድል መፍጠር ችሏል። በዋናነትም ድርጅቱ የሱቆች የብረት ፣ የመጋረጃ እና የተለያዩ የሼድ በር ሻተሮችን ያከናውናል። የስራው ተመን የሚወሰነውም በካሬ ሲሆን ወቅታዊ የብረት ዋጋም ከግምት ውስጥ ይገባል ። በሻተር ስራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ድርጅቶች በመሆናቸው ስራውን ተወዳጅና ተፈላጊ ለማድረግ የራሱን ጥረት ጨምሮ ተወዳድሮ ለማሸነፍ እንደሚሰራ ይናገራል።
ጊዜው ብሩህ ተስፋ የሚታይበት በመሆኑ በቀጣይ ለሻተር ስራና ማምረቻ ድርጅት ስራ ወሳኝ የሆኑ ግብአቶችን በቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ጥቅም ላይ የማዋል እቅድ አለው። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሙሉ የሼድ ግንባታዎችን በስፋት የማከናወን ውጥንም ይዟል ። ለዚህም ከመንግሥት በኩል የፋይናንስ ድጋፍና ስራዎችን ለማከናወን እድል እንዲሰጠው ይፈልጋል። እነዚህንና መሰል ምቹ ሁኔታዎች ካሉም የጀመረውን ስራ በስፋት፣ በብዛትና በጥራት የማከናወን ብሎም ለተጨማሪ ሰዎች የስራ እድል የመፍጠር ራዕይ ሰንቋል። በዚሁ የስራ ዘርፍ ባለሞያዎችንም ጭምር የማፍራት ሃሳብ አለው ።
‹‹እድገታችን በተግባር እየታየና ሰርተን ማደግ የምንችል ወጣቶች ነን›› የሚለው አቶ ዮናስ፤ ከዚህ አኳያ በመንግሥት በኩል እገዛ ቢደረግላቸው መልካም መሆኑን ይጠቅሳል። ለቤት ኪራይ በየወሩ 25 ሺ ብር ወጪ ያደርጋል። ይሄ ደግሞ ሰርቶ ለእድገት ሳይሆን ሰርቶ ለቤት ኪራይ ነው ። በመሆኑም በኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ የማምረቻ ሼድ እንዲሰጣቸው ይጠይቃል። የተለያዩ የፋይናንስ ድጋፍ ቢደረጉላቸው ስራውን በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰሩት ይናገራል። ለስራቸው ጥሬ እቃ እንደልብ በሀገር ውስጥ ባለመኖሩ ከውጪ ለማስመጣት እንዲችሉ መንግሥት በውጪ ምንዛሬ በኩል ያለውን ችግር ሊፈታ እንደሚገባም ይጠቁማል። ሆኖም ግን በአሁኑ ግዜ በአንፃራዊነት ጥሩ መሻሻሎች እንዳሉና ከውጪ ሀገር ግብዓቶችን ማስመጫ ዶላር እንደተፈቀደም ይጠቅሳል።
በግል ጥረት ጠንክሮ መስራት ውጤታማ ቢያደርግም ከመንግሥት ሼድ ወስደው ከሚያመርቱ ጋር መወዳደር ከባድ ነው። ከዚህ አኳያ ውድድሩን ፍትሃዊ ለማድረግና ሁሉም በዚህ የስራ ዘርፍ ላይ ያለ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን እድሉን ላላገኙ የፋይናነስ ድጋፍና የሼድ አቅርቦት ሊመቻች ይገባል። ሁሉንም ነገር ከመንግሥት ብቻ መጠበቁ ተገቢ ባለመሆኑ ድርጅቱ የራሱን ጥረት በማድረግ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርግም ይጠቁማሉ።
ሰው ራሱን የሚለካበት የተለያየ ሚዛን እንዳለ ሆኖ የብረታብረትና የሻተር ስራ እስካሁን ባለው ሂደት ውጤታማ መሆኑን የሚገልፀው አቶ ዮናስ የዚህ ውጤት አንዱ ማሳያ ስራውን ከራሱ አልፎ በስሩ በቀጠራቸው በሰለጠኑ ባለሙያዎች ማከናወን መቻሉ እንደሆነ ይናገራል። የራሱን ህይወት በዚሁ ስራ አሸንፎ ለሌሎችም ጭምር መትረፍ መቻሉ የውጤቱ ሌላኛው ማሳያ መሆኑንም ይናገራል። በሌላ በኩል ደግሞ ትናንት በእጅ እየቀጠቀጠ ይሰራ የነበረውን ሻተር ዛሬ ላይ በማሽን መስራት መቻሉም ትልቅ መሻሻል እንደሆነም ይጠቅሳል።
በከተማዋ ቀደም ሲል ከውጪ ሀገር የሚገቡ ሻተሮች በአብዛኛው ጥቅም ላይ ይውሉ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ግዜ በርካታ የሻተር አምራች ድርጅቶች መፈጠራቸውና ከነዚሁ ድርጅቶች ውስጥ እርሱ አንዱ መሆኑ በራሱ ትልቅ ሥኬት እንደሆነም ያምናል። ከዚሁ የስራ ዘርፍ ጋር በተያያዘ ቻይና ሀገር ድረስ በመሄድ ልምድና እውቀት ቀስሞ መምጣቱ ስራውን በተሻለ ደረጃ ለማከናወን እንዳስቻለውና ይህም ሌላ ውጤት መሆኑን ይገልፃል። ከዚህ በዘለለ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ድርጅቱ ትርፋማ መሆኑንም ይመሰክራል።
ለሌሎችም በዚሁ የስራ ዘርፍ ገብተው መስራት ለሚፈልጉ ወጣቶች በቅድሚያ ስራን ሳይንቁ ከትንሹ ጀምሮ መስራት እንዳለባቸው ይመክራል። ራሳቸውን ከአልባሌ ሱስ አርቀው በስራቸው ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባቸውም ያሳስባል። ትልቅ ውጤት ላይ ለመድረስ ጠንካራና ታታሪ መሆን እንዳለባቸውና ስራቸውንም ሌት ተቀን ማከናወን እንደሚገባቸው ይናገራል። የሻተር ስራ የአእምሮና የጉልበት ስራን የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያ ጤንነታቸውን ከጠበቁ በስራቸው ውጤታማ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው ሲል ይገልጻል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013