ተወልዶ የልጅነት ዕድሜውን ያጋመሰው በገጠሪቷ አሊባቦር ነው። የዛኔ የአካባቢው በረከት የፈለገውን አላሳጣውም። ከጓዳው ወተት፣ ከጓሮው እሸት እያገኘ ከቀዬው ቦርቋል። ወላጆቹ እሱን ጨምሮ ሌሎች ልጆቻቸውን ማስተማር፣ ቁምነገር ማድረስ ይሻሉ። ሁሉም ቀለም ይቆጥሩ፣ ዕውቀት ይሸምቱ ዘንድ ትምህርት ቤት ለመላክ ሞክረዋል።
አካባቢው በርከት ያሉ ስመ ጥር ወጣቶችን አፍርቷል። በትምህርታቸው የጎበዙ በዕውቀታቸው የላቁ፣ ብርቱዎች የሰፈራቸው ምሳሌ ሆነዋል። ስለእነሱ ሲወራ የሰሙ አንዳንዶች ፈለጋቸውን መከተል አርማቸውን ማንሳት ህልማቸው ነው። በአካባቢው የታላላቆቻቸውን መንገድ ለመያዝ የሚተጉ ተማሪዎች ብዙ ናቸው።
ታዳጊው ደምሴ ዕድሜው ከፍ ሲል ወላጆቹ ትምህርት ቤት ላኩት፤ እነሱም በልጃቸው ስማቸው ቢጠራ፣ ልፋታቸው ቢታይ ይወዳሉ። ደምሴ ይህን ሀሳብ እንደሚሞላ እርግጠኞች ነበሩ። ህጻኑ አንደኛ ክፍል ገብቶ መማር ጀመረ። ከእሱ ጋር እኩዮቹ አብረውት ይውላሉ። ሁሉም ቀያቸውን ለቀው ትምህርት ቤት መሄዳቸው አስድስቷቸዋል። ተምረው ወደቤት ሲገቡ ወላጆች በፍቅር ይቀበሏቸዋል። ነገን አላሚዎቹ ይህን ሲያዩ ልባቸው በተስፋ ይሞላል ።
ደምሴ ትምህርቱን እንደወደደው ዘለቀ። አሁን በየዓመቱ ክፍሎችን እየተሻገረ ነው። አምስተኛ ክፍልን አልፎ ስድስተኛ ሲደርስ ከህልሙ ግማሽ መንገድ ላይ እንደቆመ ገባው። በዚህ ከቀጠለ ተከታዮቹን ዓመታት በድል ይወጣል። የልጅነት አእምሮው አርቆ አሰበ። እሱም እንደመንደሩ ብርቱ ልጆች ህይወትን ታግሎ ሲያሸንፍ ታየው።
ቀጣዩ ዓመት የአዲስ ምዕራፍ መግቢያ ሆነ። ደምሴ ሰባተኛ ክፍል ገብቶ ትምህርቱን ሊጀምር ነው። እንዲህ መሆኑ ለእሱና ለቤተሰቦቹ ታላቅ ተስፋን ያቀብላል። በአዲሱ የትምህርት ዘመን ደምሴና ጓደኞቹ ደብተር ይዘው ከትምህርት መገኘት አለባቸው።
እንዲህ ከመሆኑ በፊት በደምሴ አእምሮ አዲስ ሀሳብ ተከሰተ። ከትምህርቱ ይልቅ መንገድ ያሰበው ልቡ የትምህርቱን ጉዳይ አስረሳው። ጠዋት ማታ በሀሳብ የሚናወዘው ታዳጊ እግሮቹ አዲስ አበባን ናፈቁ። ይሄኔ የትናንትናው ዕቅዱ በሌላ ሀሳብ ተተካ። ከተማ ገብቶ ገንዘብ መቁጠር የፈለገው ደምሴ አዲስ አበባ ዘለቀ። አዲስ አበባና ደምሴ በአካል ተገናኙ። በቆይታ ቀናት ተቆጠሩ። እንዳሰበው በፍጥነት ገንዘብ አልቆጠረም።
ደምሴ ፍላጎቱ ይሞላ ዘንድ ጉልበቱን በስራ አሟሸ። ቀለምና ቡሩሽ ገዝቶ ጫማን ማሳመር መተዳደሪያው ሆነ። ደምሴ ይህ አጋጣሚ ከብዙዎች አግባባው። ደንበኞችን ሲያፈራ የሚያውቃቸው በረከቱ። በቀን የሚያገኘውን እየቆጠረ፣ ራሱን ማሳደር ለመደ።
ውሎ ሲያድር ወጣቱ ከተማውን በወጉ ለየ። አሁንም ልቡ በሌላ ሀሳብ ተያዘ። ስራውን መለወጥ አሰኘው። ሊስትሮነቱን ትቶ የቀን ስራ ፈለገ፡፤ ያሻውን አላጣም። በቀን ስራ ውሎ የድካሙን እያገኘ ገንዘብ ቋጠረ። ከጫማ ጠራጊነት በተሻለም ገቢው ጨመረ።
የሚውልበት ስራ ድካም አለው። ከሚያገኘው ገንዘብ የቤት ኪራይ፣ የምግብና የሌሎችም ክፍያ አለበት። ይህን ማድረግ ግዴታው ነው። ደምሴ ስራውን ከድካሙ እየመዘነ ከራሱ መከረ። መተዳደሪያዬ ያለው ውሎ ከባድና ፈታኝ መሆኑ ገባው።
አሁንም በሌላ ሀሳብ ቀናትን ቆጠረ። ጉልበቱን ከሚፈትን ላቡን ከሚያፈስበት ሻል የሚል እንጀራን ተመኘ። የምኞቱ መዳረሻ ከአንድ ጥግ አደረሰው። ስራ መቀየር እንዳለበት አመነ።
ደምሴ መቀየር ያለበትን ስራ አላጣውም። የጥበቃ ሙያ ምርጫው ሆነ። ቀን ከሌት እየሰራ በሚያገኘው ገቢ የተሻለ ህይወት እንደሚያገኝ ገባው። በስራው በረታ። ጊዚያትን በዘለቀበት መተዳደሪያ ግዴታውን እየተወጣ ቆየ።
የጥበቃውን ሙያ ጥቂት እንደገፋ ዓይኖቹ ሌላ ስራ አማተሩ። በውሎው አጋጣሚ ከሚያገኛቸው አንዳንዶች ቆሻሻ በማንሳት ኑሮ እንደሚገፉ ያውቃል። ደምሴ እነሱ በሰሩት ልክ የሚከፈላቸው ደመወዝ ዳጎስ ማለቱን ሰምቷል። እሱ ካለበት ስራ እንደሚሻል በገባው ጊዜም ሊገባበት ወሰነ። ውሳኔው አልተደናቀፈም። ጥበቃውን ለቆ የስራ ልብሰ አጠለቀ። ሁሌም ማለዳ ቆሻሻን ከየመንደሩ እያነሳ ከገንዳ መጣል ለመደ። ስራው ፈታኝና ለጤና ጎጂ ነው። ክፍያው ግን አይጎዳም። ደምሴ ከቀድሞው በተሻለ ገቢው ጨመረ። ከእጁ የሚገባው ገንዘብ የልብሱን መቆሸሸ፣ የውሎውን መክፋት አስረሳው። ስራውን አክብሮ እንጀራውን ወዶ በጀመረው ገፋበት። ዘወትር ቆሻሻ ማንሳት ቋሚ መተዳደሪያው ሆነ።
አንዳንዴ ደምሴ ድለላንም ይሞክራል። የድለላ ስራ ከብዙዎች የሚያገናኝ የሚያስተዋውቅ ነው። ፈላጊና ተፈላጊን ሲያገናኝ፣ ተጨማሪ ገንዘብ ያገኛል። ይህ አይነቱን ውሎ ሲሞካክር አንዳንዴ ትዕግስት አልባ ይሆናል። ከሰዎች መግባባት ባጣ ጊዜ ጠብና ድብድብ ይቀናዋል።
ደምሴ ይህ ባህሪው እስከመታሰር አድርሶታል። በጥፋቱ ተከሶ ቀናትን በቆጠረበት የጣቢያ ቆይታ በዋስ ቢፈታም አልፎ አልፎ ብልጭ የሚለው ልማድ እሱንና ሌሎችን ሲፈታተን ቆይቷል። ከስራ ውጭ ከጓደኞቹ ጋር በመጠጥ ቤት ሲዝናና ይህ ባህሪው ለገላጋይ ያስቸግራል።
የአንኮበሩ ወጣት
ትውልድና ዕድገቱ አንኮበር ‹‹ዘንቦ›› ከተባለ ቀበሌ ነው። ለገሰ ይባላል። በልጅነቱ የጀመረው ትምህርት ስኬታማ ነበር። በአካባቢው እስከ ስምንተኛ ክፍል ሳያቋርጥ ተምሯል። አስቀድመው በልጃቸው ተስፋ የጣሉት ወላጆቹ የነገውን መልካም ፍሬ እያሰቡ ተስፋ ሲጥሉበት ቆይተዋል።
ለገሰ ስምንተኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ ለቀጣዩ ሂደት ከመንደሩ መራቅ ነበረበት። እስከ አስረኛ ክፍል ያለውን ትምህርት ከተማ ሄዶ መቀጠል ግድ ይለዋል። ይህን የሚያውቁ ወላጆቹ የሀሳቡን ለማድረስ ከጎኑ አልራቁም። የሚስፈልገውን አሟልተው እንዲማርላቸው ከተማ ላኩት።
ለገሰ አንኮበር ገብቶ ከስምንተኛ እስከ አስረኛ ክፍል ያለውን ትምህርት ቀጠለ። እሱን ጨምሮ ወላጆቹ ላሳደሩት ተስፋ መበርታት አለበት። እንደታሰበው አልሆነም። ጠዋት ማታ የሚተጋበት ትምህርት ከአስረኛ ክፍል ተቋጨ። ለገሰ ከትምህርቱ ስራን መረጠ። ከቀለም ይልቅ ብር ማግኘት ገንዘብ መቁጠር ፈለገ። ይህ ፍላጎቱ ውሎ ሳያድር ደብረ ብርሃን አደረሰው።
የገጠሩ ተማሪ አሁን ከተማ ገብቷል። ትናንት ስለትምህርት የሚያስበው ዕቅድ ዛሬ አብሮት አይደለም። ከገጠር ወጥቶ ከተማ የመግባት ሰበቡ የገንዘብ ፍላጎቱ ነው። ገንዘብ ለማግኘት ስራ መያዝ አለበት። የከተማው ውሎ አማራጮችን ሰጠው። ለአቅሙና ለፍላጎቱ የሚበጅ መተዳዳሪያ ፈላለገ ።
የደብረ ብርሃን ቆይታው ያሰበውን አላሳጣውም። በአንድ ሆቴል ተቀጥሮ ከሻይ ማሽን ላይ ስራ ጀመረ። ስራውን አውቆ ባለሙያ ለመሆን አልተቸገረም። ያየ፣ የሰማውን ተቀብሎ ብርቱ ሰራተኛ ሆነ። ሻይ ቡና እየጨመቀ፣ ወተት ማኪያቶ እያዘጋጀ ለሆቴሉ ደንበኞች ማቅረብ ያዘ። በአጭር ጊዜ ያሰበው ተሳካላት። ሻይ ቡናውን የቀመሱ፣ ወተት ማኪያቶውን ያጣጣሙ የእጁን ሙያ ወደዱለት።
አሁን ለገሰ የከተማ ልጅ ሆኗል። ከብዙዎች ተዋውቆ ከበርካቶች ይግባባል። አንዳንዴ የሚስተዋልበት ክፉ ባህርይ ግን ለጠበኝነት እየዳረገው ነው። ለገሰ አንድ ቀን ከአንድ ሰው ተጣለ። የሁለቱ ጠብ ካለመግባባት ያለፈ ነበር። የጠቡን መካረር ያስተዋሉ አንዳንዶች ከመሀል ገብተው ገላገሉ። ለገሰ የግልግሉን አጋጣሚ ተጠቀመበት። ጠበኛውን በግርግር አግኝቶ ጥቃት ፈጸመበት። ገላጋዮች ከጠቡ በኋላ ሁለቱንም ፖሊስ ጣቢያ አደረሱ። ተደብደቢው በደለኛ፣ ለገሰ ጥፋተኛ ተባሉ።
ለገሰ ባደረሰው ድብደባ ለቀናት በፖሊስ ጣቢያ ታሰረ። የጥፋቱን መጠን ያጤነው ፖሊስ ለድርጊቱ አስጠንቅቆ፣ የዋስ መብቱን ጠብቆ ከእስር አሰናበተው። ለገሰ ከጣቢያ እንደወጣ በስራው መቀጠል አላሻውም። ያካበተውን ሙያና ልምድ ይዞ አዲስ አበባ አቀና።
አዲስ አበባና ለገሰ ሲገናኙ በአዲስ ስራና በተለየ ሙያ ሆነ። ለገሰ በቆየበት የሻይ ማሽን ስራ አልዘለቀም። ለቅጥር የሄደበት ሆቴል በገንዘብ ተቀባይነት እንዲሰራ ዕድል ሰጠው። በሆቴል ስራ በቂ ልምድ ያለው ወጣት ስራውን ለመቀበል አልተቸገረም። የትምህርት ስንቁ አግዞት ሙያውን በሀላፊነት ተረከበ።
ለገሰ የአዲስ አበባ ህይወትን ፈጥኖ ለመደ። በሆቴሉ ከሚመጡ ደንበኞችም ተግባባ። የገባበት ሆቴል በሙዚቃ ሲደምቅ ያመሻል። የምሽት ጨዋታን የሚሹ፣ መጨፈር መደነስ የፈለጉ ከሆቴሉ ይታደማሉ። ለገሰ ይህ አጋጣሚ ሌላ ሙያ እንዲለምድ አገዘው። የተዝናኝ ደንበኞችን ማንነት አወቀ። ፍላጎታቸውን እየለየ፣ መደሰቻቸውን መረጠ። ይህ ሙከራው ዲጄ የመሆን ፍላጎቱን አበረታ። ሙከራው ተሳካ። የሙዚቃ ምርጫው ለደንበኞች ጆሮ የሚመች ተፈላጊነቱን የሚያጎላ ሆነ።
ለገሰ በዲጄነት የሚያደምቀው ሆቴል በርካታ ደንበኞች አፈራ። በዋናነት የተረከበው የተቆጣጣሪነት ስራም አስተናጋጆችን ከደንበኞች ለመቃኘት ንቁ አደረገው። ሙዚቃውን እያጫወተ ገቢ ወጭውን ይቃኛል። ሂሳቡን ተቆጣጥሮ የጎደለውን ይሞላል። ይህ ቅልጥፍና ለሆቴሉና ለራሱ ገቢ የተሻለ ሆነ።
ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም
የሐምሌ ወር ገና ከመግባቱ በጨለማ ተውጧል። ከሰኔ የተቀበለውን ዝናብ ከራሱ አዳምሮ ጠዋት ማታ እየዘነበ ነው። ብርድና ዝናቡን ሽሽት በየቦታው የመሸጉ አንዳንዶች ለቅዝቃዜው መፍትሄ ያሉትን ተጠቅመዋል። ወፍራም ልብስና ካፖርት ከሚለብሱት ሌላ በየመዝናኛው መጠጥና ትኩስ ነገር አዘው የሚጋበዙት በርክተዋል።
በዚህ ሰዓት የነለገሰ ሆቴል በእንግዶች ተሞልቷል። ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት ወደ ሆቴሉ የገቡት ደምሴና ጓደኞቹ አንድ ጠረጴዛ ከበው ድራፍት መጠጣት ጀምረዋል። በሚያልቁት መጠጦች ልክ ሌላ የሚታዘዙት አስተናጋጆች ባዶ ብርጭቆ እያነሱ በመጠጥ የተሞላውን ይተካሉ።
በቤቱ መድመቅ የጀመረው ሙዚቃ በለገሰ አጫዋችነት እየተመራ ነው። እንደሙዚቃው ስልት የሚወዛወዙት ደንበኞች የጀመሩትን ጭፈራ ሲጨርሱ ቦታውን ለሌሎች ያስረክባሉ። ሙዚቃው፣ ጭፈራው፣ ጨዋታው ደምቋል። የሐምሌ ዝናብ የጨለማው አጋር እንደሆነ ዘልቋል።
ቀን በስራ ሲደክም የዋለው ደምሴ ዕለቱን ለመዝናናት መርጦ በመጠጥ ቤቱ ተገኝቷል። በማለዳ ሲያነሳ የዋለው ቆሻሻ ያደከመው ይመስላል። ከዚህ ድካሙ ለማረፍ በቦታው የተገኘው አብረውት ካሉት ጋር ከመጠጡ ይደጋግማል። የደምሴ ባልንጀሮች በሙዚቃው እየተወዘወዙ ነው።ሞቅ ያለው ስልት ሲጀምር ደምሴ ተቀላቀለ።
ከነደምሴ ጋር የሚጨፍሩት ጓደኛሞች ከሌላ ወንበር የተነሱ ናቸው። ደምሴንንና ጓደኞቹን አያውቋቸውም። ሞቅ ያለውን ሙዚቃ አጅበው በጋራ ለመጫወት መፈለጋቸው ያስታውቃል። ሁሉም በየራሱ ስልት እየተዝናና ነው። ብርዱ፣ዝናቡ ተረስቷል።
ሙዚቃው አልቆ ጭፈራው እንዳበቃ ከነደምሴ ጋር የጨፈሩት ጓደኛሞች ወደቦታቸው ተመለሱ። ከእነሱ መሀል አንዱ ወንበሩ ዘንድ ከመድረሱ ጠረጴዛው ላይ ካሉት ብርጭቆዎች አንደኛው ከመሬት ወድቆ ተከሰከሰ። ይሄኔ ከሙዚቃው ጋብ ያለው ቤት በሌላ ድንገቴ ድምጽ ተሞላ።
አስተናጋጁ
በድንገት የብርጭቆውን መሰበር የተመለከተው አስተናጋጅ ድምጹን ተከትሎ ወደ እንግዶቹ አመራ። ሰዎቹ ከመቀመጫቸው ተነስተው በመውጣት ላይ ነበሩ። አስተናጋጁ ከኋላ ተከትሎ እንዲቆሙ ተጣራ። መስማት የፈለጉ አይመስልም። ወዲያው ድምጹን ከፍ አድርጎ የተሰበረውን ብርጭቆ እንዲከፍሉት ጠየቀ። ከመካከላቸው አንዱ በአስተናጋጁ ጥያቄ በሸቀ። ከወንበሩ ሲጠጋ ብርጭቆውን የሰበረው ወጣት ነበር።
አስተናጋጁ ደግሞ ጥያቄ አቀረበ። እንግዳው በንዴት እየጋለ አውቆ ያለማድረጉን ተናገረ። አስተናጋጁ ሊሰማው አልፈለገም። የተሰበረውን ብርጭቆ መክፈል እንዳለበት አሳሰበ። ይሄኔ እንግዳው በንዴት አልከፍልም ሲል አንባረቀ። ከአስተናጋጁ ጋር ተናነቁ። ይህን ያዩ ሌሎች ለቤቱ አለቃ ፈጥነው አሳወቁ።
አለቃው ለገሰ እሳት እንደለበሰ መሀላቸው ተገኘ። እንግዳው የተሰበረውን መክፈል እንዳለበት ነገረው። ይህን የሰማው ደምሴ የለገሰን ሀሳብ ደገፈ። ወደ ደንበኛው ሄዶም እንዲከፍል አስጠነቀቀ። ለገሰ፣ ደምሴና አስተናጋጁ ደንበኛውን ይዘው ግዴታውን ጠየቁት። ጩኸት ግርግር ተነሳ። ብርጭቆ ተወረወረ። እንግዳው ራሱን ለማዳን አንድ ጠርሙስ ወረወረ። ከቤቱ አለቃ ከለገሰ ላይ አረፈ። ደምሴ የድራፍት ብርጭቆ አንስቶ ወረወረ። ብርጭቆው ከእንግዳው ግንባር አርፎ ከመሬት ተከሰከሰ።
ወጣቱ ደንበኛ ከሆቴሉ በራፍ ከመውደቁ ለገሰና ደምሴ ከኋላው ደርሰው በድብደባ አጣደፉት። የነደምሴ ጓደኞች ተጨመሩ። ከመሀል የገቡ ገላጋዮች አልቻሉም። ደብዳቢዎቹ ሲበቃቸው ጥለውት ሄዱ። የተዘረረው ደንበኛ ከወደቀበት አልተነሳም።
የፖሊስ ምርመራ
መረጃ የደረሰው ፖሊስ ምሽቱን ከስፍራው ሲደርሰ ተደብዳቢው ወጣት እንደወደቀ ነበር ። ጠጋ ብሎ ትንፋሹን አዳመጠ። ወጣቱ አይተነፍስም። በጥንቃቄ አካሉን ዳሰሰ። እንደበረዶ ቀዝቅዟል። ፖሊስ ባገኘው ተጠርጣሪዎችን ፈለገ። አላጣቸውም። መርማሪ ፖሊስ ዋና ሳጂን ግዛው አዳነ የተጠረጣሪዎችን ቃል ተቀበለ። ሁሉም ድርጊቱን እንደፈጸሙ አመኑ።
ውሳኔ
ነሐሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም በችሎቱ የተሠየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተባብረው የሰው ህይወት ባጠፉት ሶስት ግለሰቦች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ግለሰቦቹ በፈጸሙት ወንጀል ጥፋተኝነታቸውን አረጋግጦ በሰጠው ብይንም እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጡ ሲል ወስኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013